Sunday, 03 June 2018 00:00

ህገወጥ በሚል ቤት ለፈረሰባቸው መፍትሄ እንዲሠጣቸው የጠ/ሚ ፅ/ቤት አስተዳደሩን አሣሠበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)


           ሠኞ ከንቲባው ቅሬታ አቅራቢዎችን ያነጋግራሉ በከተማዋ በሁለት አመት ውስጥ 36 ሺህ ህገወጥ ቤቶች ፈርሠዋል

     በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ሃና ማርያም አካባቢ ከሁለት አመት በፊት “ህገ ወጥ ናችሁ” በሚል ቤት ለፈረሠባቸው ነዋሪዎች የአዲስ አበባ አስተዳደር መፍትሄ እንዲሠጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አሣሠበ፡፡
በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 እና ወረዳ 11 ውስጥ በሚገኙ ቀርሳ ኮንቶማ፣ ማንጎ በሚባሉ አካባቢዎች ቤታቸው በሃይል የፈረሠባቸው ዜጎች፤ ላለፈው አንድ አመት ተኩል ለአስተዳደሩ አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ቢቆዩም ምላሽ ባለማግኘታቸው፣ በሠላማዊ ሠልፍና በደብዳቤ ከሠሞኑ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ሃላፊ ወ/ሮ ደሚቱ ሃምቢ፤ የቅሬታ አቅራቢዎቹን ተወካዮች ከትናንት በስቲያ በፅ/ቤታቸው ያጋገሩ ሲሆን እስካሁን መፍትሄ ሳያገኙ መንገላታታቸው ተገቢ አለመሆኑንና አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመው፤ ለዚህም ከንቲባው ከነገ በስቲያ ሠኞ ግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ.ም አቤቱታ አቅራቢዎቹን ሰብስበው እንዲያነጋግሩ ቀጠሮ ማስያዛቸውን እንደነገሯቸው ተወካዮቹ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር ከሁለት አመት በፊት በከተማዋ የሚገኙ 36 ሺህ ህገ ወጥ ቤቶችን ማፍረሡን በመግለፅ፤ ለዚህ ሁሉ መፍትሄ መስጠት ይከብደናል የሚል ምላሽ ሰጥቷቸው እንደነበር ተወካይዋ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ሐና ማርያም አካባቢ ቀርሣ፣ ማንጎ በተባሉ አካባቢዎች ቤታቸው የፈረሠው ከሁለት ዓመት በፊት መሆኑን፤ በፍራሹ ላይም በድጋሚ የማዳበሪያና የላስቲክ ቤቶችን ሰርተው ይኖሩ እንደነበር የሚናገሩት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከሠሞኑ የፕላስቲክ ቤታቸው መፍረሡን ተከትሎ፣ ለጎዳና መዳረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

Read 7163 times