Sunday, 03 June 2018 00:00

ጠ/ሚኒስትሩ በሰ.አሜሪካ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ እንዳይገኙ ተወሠነ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  ከአንድ ወር በኋላ በሰሜን አሜሪካ ዳላስ ቴክሳስ፣ ለ35ኛ ጊዜ በሚካሄደው በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለመገኘት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም ተባለ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሣምንት በፊት ለስፖርት ፌስቲቫል አዘጋጁ ፌዴሬሽን፤ “በፕሮግራማችሁ ላይ ከኢትዮጵያውያን ጋር ልገናኝ” የሚል ደብዳቤ መፃፋቸው የታወቀ ሲሆን ፌዴሬሽኑም ይገኙ አይገኙ የሚለውን የወሠነው በአባላቱ ድምፅ ነው ተብሏል፡፡
14 የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት “ዶ/ር አብይ መገኘት የለባቸውም” የሚል ድምፅ ሲሠጡ፣ “11 ደግሞ ይገኙ” ብለዋል፡፡ 8 ድምፀ ተአቅቦ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
ፌዴሬሽኑ በድረ ገፁ በሠጠው መግለጫ፤ “አብዛኛው አመራር አይገኙ የሚል ውሣኔ ያሣለፉት እንዳይገኙ ከመፈለግ ሣይሆን ጥያቄው የቀረበበት ጊዜ አጭር በመሆኑ፣ ሁኔታዎች አገናዝቦ ለመወሰን አመቺ ባለመሆኑ ነው” ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ በቀጣይ በሚደረገው ተመሣሣይ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ የመገኘት እድል እንዲሰጣቸው መመቻቸቱንና ጥያቄያቸው ለቀጣይ መሸጋገሩንም ፌደሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ በሠሜን አሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚሰባሰቡበት የስፖርት መድረክ ላይ ልገኝ ብለው የጠየቁ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ ናቸው ያለው ፌዴሬሽኑ፤ ይህን ጥያቄያቸውንም በከፍተኛ ሁኔታ እናከብራለን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት እያደረጉ ያለውን ጥረት እናበረታታለን ብሏል፡፡
በሐምሌ ወር በዳላስ- ቴክሳስ በሚካሄደው የኢትዮጵያና ትውልደ ኢትዮጵያኑ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ዶ/ር አብይ ይገኙ አይገኙ የሚለው ጉዳይ የፌደሬሽኑን አባላትና በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሲያወያይ መሠንበቱ ታውቋል፡፡

Read 5496 times