Sunday, 03 June 2018 00:00

የፀረ ሽብር አዋጁ እየተሻሻለ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

- ተቃዋሚዎች ስድስት አንቀፆች እንዲሠረዙ ጠይቀዋል
 - ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ የመድረክ አመራሮችን ሊያነጋግሩ ነው


    ለበርካታ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እስር ምክንያት የሆነው የፀረ ሽብር አዋጅ እንደሚሻሻል መንግስት ያስታወቀ ሲሆን ተቃዋሚዎች ስድስት አንቀፆች ከአዋጁ ላይ ሙሉ ለሙሉ እንዲሠረዙ ጠይቀዋል፡፡
የፀረ ሽብር አዋጁ ማሻሻያ በህግ ባለሙያዎች እየተሠራ መሆኑን የገለፀው መንግስት፤ ሊካተቱ የሚችሉ አዳዲስ አንቀፆችም ይኖራሉ ተብሏል። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም አምስት አንቀፆች እንዲጨመሩ፣ ስድስት ነባር አንቀፆች እንዲሠረዙና አራት አንቀፆች ማሻሻያ እንዲደረግባቸው የጠየቁ ሲሆን ኢህአዴግም በአብዛኛው መስማማቱ ታውቋል፡፡
ይሠረዛሉ ተብለው ከሚጠበቁት አንቀፆች መካከል አንቀፅ 14 ላይ የተደነገገው “ተጠርጣሪዎች አሻራ በግዳጅ መስጠት” የሚለውን ጨምሮ የግለሠቦችን ስልክና ማናቸውንም የግንኙነት አውታር የመጥለፍ ስልጣን ለደህንነት ሃይሉ የሚሠጠው አንቀፅ ይገኝበታል፡፡
 በፀረ ሽብር አዋጁ ይሻሻላሉ ተብለው ከሚጠበቁት አንቀፆች መካከልም የቅጣት አወሣሠን ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ባደረጉት ድርድር ላይ በአዋጁ ከእድሜ ልክ እስከ ሞት የተደነገገው የቅጣት ደረጃ ተሻሽሎ፣ “አንድ በእስር የሚፈረድበት ሰው ከ10 ዓመት በማይበልጥ እስራት ብቻ እንዲቀጣ” የሚለው ሃሣብ ጎልቶ መውጣቱ ታውቋል፡፡
በአዋጁ ይጨመራሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል ደግሞ በተቃዋሚዎች የቀረበውና በሽብር ተጠርጥሮ ኋላ ላይ ነፃ የተባለ ሰው፣ የሞራል ካሣ ሊከፈለው ይገባል የሚለው ይገኝበታል። በተጨማሪ የሃይል ምርመራ የሚፈፅሙ መርማሪዎች በህግ የሚጠየቁበት አግባብ በአዋጁ ይካተታል ተብሎም ይጠበቃል፤ ብለዋል - ምንጮች፡፡
በሌላ በኩል፤ መንግስታቸው ከሃገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ተቃዋሚዎች ጋር ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ ቀደም ብሎ ከተጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ራሱን አግልሎ የቆየውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አመራሮችን ለማነጋገር መወሠናቸውን የመድረክ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ አስታውቀዋል፡፡
ቀደም ሲል ወደተቋረጠው የድርድር መድረክ እንዲመለስ ከገዥው ፓርቲ ጥያቄ የቀረበለት ሠማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ “ድርድሩ በገለልተኛ አደራዳሪ እስካልተመራ ድረስ አልመለስም” የሚል ምላሽ በደብዳቤ መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 7103 times