Sunday, 03 June 2018 00:00

ፖለቲካችን ወደ አዲስ ምዕራፍ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

- “ኢትዮጵያ እንዲህ ይቅር ባይ መሪ ያስፈልጋታል” - ፖለቲከኛ አብርሃ ደስታ
- “የኢትዮጵያ ትንሣኤ መቅረብ ምልክት ነው” - ጋዜጠኛ ነቢዩ ሲራክ
- “ይህቺ ሃገር ሊያልፍላት ይሆን እንዴ?” - ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሃይሉ


   ከእስር የተፈቱት የአርበኞች ግንቦት 7 ዋና ፀሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተገናኝተው መወያየታቸው ብዙዎችን ያስደሰተ ሲሆን የአውሮፖ ህብረትና የእንግሊዝ መንግስት የሚበረታታ እርምጃ ነው፤ እንደግፈዋለን ብለዋል፡፡
ማክሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2010. ዓ.ም ከ4 ዓመት እስር በኋላ በይቅርታ ተፈትተው  ቤተሠቦቻቸውን የተቀላቀሉት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፤ በብሔራዊ ቤተ መንግስት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
በውይይታቸውም የተለያዩ ፖለቲካዊና ሃገራዊ ጉዳዮች መነሣታቸውን በጥቅሉ የገለፁት አቶ አንዳርጋቸውም የተወያዩባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በብሄራዊ ቤተ መንግስት የተነሱትና በጠ/ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ድረገፅ የወጣው ፎቶ ግራፍ በማህበራዊ ሚዲያዎች ከተሠራጨ በኋላ በርካቶች የተሠማቸው ደስታ ገልፀዋል፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩና የመብት አራማጁ ስዩም ተሾመ በፌስ ቡክ ላይ ባሰፈረው አስተያየት፤ የቂም በቀልና የመጠፋፋት፣ የጥላቻ ዘመን እያበቃ ለመሆኑ የሁለቱ መገናኘት አመላካች ነው ብሏል፡፡ “አሁን የማየው ነገር ፍፁም የተለየ ነው፤ በቂም-በቀል አስተምህሮ የዛገው አዕምሮዬ በዶ/ር አብይ ይቅር ባይነትና አክብሮት ግራ ተጋብቷል፡፡ በእርግጥ መሆን ያለበት እንደሆነ፣ ሊደረግ የሚገባው ነገር እንደተደረገም አውቃለሁ” ብሏል-መምህሩ፡፡
የኢሣት ቴሌቪዥንና ሬድዮ ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ አበበ ገላው በበኩሉ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ አዲስ የፖለቲካ ቀለም እየፈጠሩ ነው፤ ታሪክ እየሠሩ ነው”  ሲል አድናቆቱን ገልጿል፡፡ የአረና ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር መምህር አብርሃ ደስታ “የጥላቻና የመናቆር የፖለቲካ ባህላችንን የሚያስቀይር ተግባር ማየት ለውጥ ነው፤ በጣም ትልቅ ለውጥ። ኢትዮጵያ እንዲህ ይቅር ባይ መሪ ያስፈልጋታል፤ እናመሠግናለን” ብሏል… በሠጠው አስተያየት፡፡
በሚያቀርባቸው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ወጎች የሚታወቀው ዘውዳለም ታደሠ በበኩሉ፤ “ጊዜው የይቅርታ ነው ብለን እናስባለን፤ ሁለት ጦር የተማዘዙ አካላት ይቅር ተባብለው ስናይ እናደንቃለን፤ ከብሽሽቅ ፖለቲካ ወጥቶ የይቅርታና እርቅ መንፈስ ማበራከት ይገባል” ሲልም ድጋፉን ሰጥቷል፡፡
ታዋቂው ገጣሚና ፀሃፊ በእውቀቱ ስዩም “በዶ/ር አብይ እና በግብረ አበሮቹ መሪነት እየተነቃቃ ያለው የእርቅና ሆደ ሠፊነት ባህል አስደናቂ ነው” ብሏል፡፡ ወጣቱ ፖለቲከኛ ሃብታሙ አያሌው በበኩሉ፤ እርምጃው የዶክተር አብይ የለውጥ ፍላጎት ጉልህ ማሣያ ነው፤ ግማሽ መንገድ ሲመጡ ግማሽ መንገድ መሄድ የለውጥ ፈላጊዎች ግዴታ ነው ብዬ አምናለሁ” ብሏል፡፡
የመብት ተቆርቋሪና ጋዜጠኛ ሃብታሙ ምናለ በሰጠው አስተያየት፤ ጨለምተኛ መሆን የሚገባን ሰአት አይደለም፤ አይናችንንም ከፍተን ማየት፣ የመጣውንም ልንቀበለው ይገባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ፤ ኢህአዴግን በህዝብ ከመበላት ታድጓል፡፡ ሃገሪቷም ጥሩና መምራት የሚችል እልፍ ሠው እንዳላት አስመስክሯል” ብሏል፡፡
“የኢትዮጵያ ትንሣኤ መቅረብ ምልክት፣ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ መፍታትና ሃሣብን አለመፍራት ነው” ያለው ነዋሪነቱን ሣወዲ አረቢያ ያደረገው ጋዜጠኛ ነቢዩ ሲራክ በበኩሉ፤ “ሃገሬ ትንሣኤዋ ይቀርብ ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይና ጓዶቻቸው እየሰሩ ያለውን፣ ታላቅ ችግሮችን የመፍታት ዘዴ አለማድነቅ አይቻልም፤ ለዚህም እርምጃቸው ታላቅ አክብሮት አለኝ” ብሏል፡፡
ሰሞኑን የተከሠሠበት የሽብር ክስ የተቋረጠለት የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ስራ አስኪያጅና የፖለቲካ ተንታኙ፤ ጃዋር መሃመድ በበኩሉ፤ “ይህን በማየቴ ደስተኛ ነን፡፡ ይህ ለውጥ ህጋዊና ይፋዊ በሆነ መንገድ ጠንካራ መሠረት እንዲይዝ፣ ከመሣርያ ሃይል አገዛዝ ወደ ህግ የበላይነት የሚደረገው ለውጥ መቀላጠፍ አለበት” ብሏል፡፡
በሽብርተኝነት የተፈረጀው የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣  የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን መፈታት ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የትጥቅ ትግልን አማራጭ ያደረገው ድርጅታቸው፣ የአቅጣጫ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል ብለዋል፡፡
“ይህቺ ሃገር ሊያልፍላት ይሆን እንዴ?” በሚል ጥያቄ አስተያየቱን የጀመረው ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ፤ “ማሠር መፍትሄ ነው ብሎ የሚያስብ መንግስት በኖረበት ሃገር ውስጥ መፍታት መፍትሄ ነው” የሚል ሲመጣ ተስፋ አለማድረግ ይከብዳል” ብሏል፡፡ አክሎም፤ የመከራ፣ የመገደል፣ የመታሠር፣ የመሠደድ ዘመን ሊያልፍላት ይሆን?” ያ የመጠላላት፣ የቂም በቀል ዘመን ሊያልፍላት ይሆን? ሲል ይጠይቃል-ጦማሪ በፍቃዱ፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም በበኩላቸው፤ የአብይና የአቶ ለማን እንቅስቃሴ ልንደግፍ ይገባል፣ ሃገሪቷን ማዳን የሚቻለው እነሡን መደገፍ ስንችል ነው፤ አስተሳሰባችንን በማቃናት ሁለቱን የእግዚአብሔር ስጦታዎች እንደግፋቸው” ብለዋል፡፡
በዶ/ር አብይ የሚመራው መንግስት፣ አቶ እንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞችን መፍታቱን ያደነቁት የአውሮፓ ህብረትና የእንግሊዝ መንግስት፤ እርምጃው ለሃገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት በጎ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡
እስረኞችን ከመፍታት ጎን ለጎንም የፀረ ሽብር ህጉን የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት እና ነፃ ተቋማት ጉዳይ እንዲፈተሹና ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ጠይቀዋል፡፡
ስጋት አንዣቦበት የነበረው ወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች በመወሠዳቸው ምክንያትና ከሃገር ውጪ ከሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በመጀመሩ ውይይትም በበጎ እንደሚታይ የአውሮፖ ህብረት አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ እና የእንግሊዟ አቻቸው ቴሬሣ ሜይ በስልክ ባደረጉት ውይይት በአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው እንግሊዝ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፀረ ሙስና እና በስራ ፈጠራ በመሣሠሉት ላይ እርዳታዋን እንደምታስቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ትናንት ጠዋት እንግሊዝ ለንደን ሲደርሡ ባለቤታቸው፣ ልጆቻቸው እና በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው እንደተቀበላቸው ታውቋል፡፡

Read 10304 times