Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Sunday, 06 May 2012 14:49

ሐረር ቢራ በሄንከን እጅ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከአዲስ አበባ በ526 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሐረር ከተማ፣ ሐኪም ጋራ ሥር ተቋቁሞ ለዓመታት ምርቶቹን ለተጠቃሚዎቹ ሲያቀርብ የቆየው የሐረር ቢራ ፋብሪካ ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ውድድር አሸንፎ የጥራት ተሸላሚ ሆኗል፡፡ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ፋብሪካው ከበደሌ ቢራ ፋብሪካ ጋር ወደ ሔንከን የግል ይዞታነት የተዛወረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በማስፋፊያ ሥራዎችና በአዲስ ፋብሪካ ግንባታ ሥራ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡

ፋብሪካው የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀሙን፣ የአመራረት ሒደቱን፣ የሠራተኛ ደህንነት አያያዙን፣ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤውን ሰሞኑን ለጋዜጠኞች አስጐብኝቷል፡፡ በዚህ የጉብኝት ፕሮግራም ሳይ የሔንከን ቢራ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚ/ር ጆሃን ዶየር ፋብሪካው ሊያከናውናቸው ስላቀዳቸው ጉዳዮች ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ፋብሪካው የአዳዲስ መሣሪያዎች ተከላ እየተከናወነለት እንደሆነ የተናገሩት ሚ/ር ጆሃን፤ ከ350-400 ሚሊዬን ብር በሚደርስ ወጪ የፋብሪካ ማስፋፊያ ሥራ እያከናወነ መሆኑንና ይህም የፋብሪካውን ዓመታዊ የምርት አቅም ከ90 ማሊዬን ጠርሙስ ወደ 120 ሚሊዬን ጠርሙስ ለማሳደግ እንደሚያስችለው ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው ወደ ግል ይዞታ ከተዛወረ በኋላ ያሳየውን መሻሻል፣ የፋብሪካ ማስፋፊያ ሥራዎቹን፣ የሠራተኛ አያያዙንና የዘንድሮ የጥራት ሽልማቱን አስመልክቶ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ ከሐረር ቢራ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከአቶ ጁነዲን ባሻ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ፋብሪካው ወደ ግል ይዞታነት የተዛወረው ባለፈው ነሐሴ ወር መሆኑ ይታወሳል፡፡ ከዚያ ወዲህ የፋብሪካው የማምረት አቅምና ትርፋማነት ላይ የታየው ለውጥ ምንድነው?

ፋብሪካችን ወደ ሔንከን ከመዛወሩ በፊትም በመንግስት እጅ እያለ ትርፋማ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ሰማንያ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ትርፍ አግኝተናል፡፡ ሆኖም አሁን ወደ ግል ከተዛወረ በኋላ ከፍተኛ የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ መሣሪያዎችን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመተካት፣ የምርት ጭማሪ ለማድረግ ስለተፈለገ ከ350-400 ሚሊዬን የሚደርስ ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የአዳዲስ መሣሪያዎች ግዥ ከመጪው ክረምት ወር ጀምሮ ተካሂዶ እስከመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ሥራው ይጀመራል፡፡ ይህም የፋብሪካውን የማምረት አቅም ከዘጠና ሚሊዮን ጠርሙስ ወደ 120 ሚሊዮን ያሣድጋል፡፡ በሩብ አመቱ ከአምናው በላይ 37%፣ ከዕቅዳችን በላይ ደግሞ 105% ሠርተናል፡፡ ይህ ከፍተኛ ለውጥ ነው፡፡

ፋብሪካችሁ በማስፋፋት ስራው ላይ ቀደም ሲል ሲያካሂድ የነበረው ጥናት ነበር፡፡ ከምን ደረሰ?

ቀደም ባሉት ዓመታት በፋብሪካ ማስፋፊያ ሥራዎች ላይ በመሀል አገር ቢራ ፋብሪካን ማቋቋምን ጨምሮ ጥናት አድርገን ጨርሠን በመንግስትም ተፈቅዶልን ነበር፡፡ ፋብሪካው ወደ ግል ይዞታነት ሲዛወር ገዥዎቹ ጥናቱን ወስደው በማሣደግ፤ ፋብሪካውን የበለጠ ወደ አዲስ አበባ እንዲጠጋ አድርገው ሠሩት፡፡ እናም አሁን አዲስ አበባ ላይ 2.3 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ የቢራ ፋብሪካ ለማቋቋም ታቅዶ ቦታውን በመረከብ ሒደት ላይ እንገኛለን፡፡

የቆርቆሮ ቢራ ማምረትና ቢራ ወደ ውጪ ለመላክ ምን ታቅዷል?

በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ የቢራ ገበያ በጣም እያደገ በመሆኑ ይህንን ፍላጐት ለማሟላት የሚያስችል ምርት በጥራትና በብዛት በማሳደግ ለማምረት ነው ዋነኛው እቅዳችን፡፡ ሆኖም ግን ቢራዎችን ወደ ውጪ የመላኩና የቆርቆሮ ቢራን የማምረቱ ጉዳይ በዕቅዳችን ውስጥ ተካቷል፡፡

ፋብሪካው ወደ ግል ይዞታነት በመዛወሩ ከሥራ የሚፈናቀሉ ሠራተኞች አሉ? በሠራተኛው ላይስ ይሄ ስጋት አለ?

ሔንከን በዓለም ላይ ከ170 በላይ ፋብሪካዎች ያሉት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ከሰባ አምስት ሺህ በላይ ሠራተኞችም አሉት፡፡ ዋናው መ/ቤት የሚገኘው አምስተርዳም ነው፡፡ እንግዲህ ሐረር ቢራንና በደሌ ቢራ ፋብሪካን የገዛው ይኸው ድርጅት ነው፡፡ በእርግጥ ድርጅቱ ወደግል ይዞታነት ተዛወረ ሲባል ሠራተኛ ጭንቀት ሊኖረው እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ይህ ለፕራይቬታይዜሽን ያለን አመለካከት ነው፡፡ ዋነኛው ጉዳይ ግን ድርጅቱን የገዛው ኩባንያ አቅም ነው፡፡ በእርግጥ የድርጅቱ ውስጣዊ ይዞታ፣ አቅሙ፣ ትርፋማነቱ ሥራው ላይ ወሣኝነት ይኖረዋል፡፡ ግሩፑ የገዛው ድርጅት የከሰረ ቢሆን ኖሮ ሠራተኛውን ለመቀነስ ይጣደፍ ነበር፡፡ ይህ ግን ሐረር ቢራን አያሰጋውም፡፡ እናም ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሠራተኛን ከሥራ ለማፈናቀል የሚያስችል ሥጋት በዚህ ፋብሪካ ላይ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ እንደውም ለሚገነባው አዲስ የቢራ ፋብሪካ ሠራተኞችን የመቅጠርና የሥራ ዕድልን የመፍጠር ሂደቱ ይጨምራል ብዬ ነው የማስበው፡፡

ምርቱ የሔንከን ስያሜ ይዞ ነው ለገበያ የሚቀርበው ወይስ ባለበት ይቀጥላል?

በስያሜው ላይ ለውጥ አይደረግም፡፡ በራሱ ስያሜ ነው የሚቀጥለው፡፡ የኢትዮጵያን ባህል ታሪክ ኢትዮጵያዊ ከተሞችን መያዝ እኮ በራሱ ትርጉም አለው፡፡ ከዛ አንፃር ሐረር፣ በደሌ የሚሉትን ሥያሜዎች እንፈልጋቸዋለን፡፡ በእርግጥ የሄንከን የንግድ ምልክት በዓለም ላይ ትልቅ ቦታ ያለው ቢሆንም የራሱን ስያሜ ይዞ የመቀጠሉ ጉዳይ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

ጥራት ላይ ምን የተለየ ነገር እየሠራችሁ ነው?

ጥራት ለብቻው እራሱን ችሎ ቀይ ወይም ነጭ ተብሎ የሚገለፅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጥራት በሰዎች በመሣሪያ፣ በጥሬ ዕቃ፣ በሲስተም ላይ የሚሠራ ጉዳይ ነው፡፡ ድንገት የሚፈጠርም ጉዳይ አይደለም፡፡ ከጥሬ ዕቃ፣ ከውሃና ከገብስ ጀምሮ አምስተርዳም እየተላከ የሚመረመርበት አሠራር አለን፡፡ በጥራት ላይ ምንም ድርድር የለንም፡፡ ከፍተኛ ሥራ እየሠራን ያለነውም ጥራት ላይ ነው፡፡

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የጥራት ውድድር አሸናፊ ሆናችኋል? እንዴት ነበር ውድድሩ?

ፋብሪካችን ከዚህ በፊትም በ2003 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው የጥራት ውድድር አሸናፊ ሆኗል፡፡ በወቅቱ በጥራት ውድድሩ አሸናፊ ከነበሩት ሶስት ፋብሪካዎች አንዱ ሐረር ቢራ ነበር፡፡ ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ የጥራት ሽልማቱ አሸናፊ ሆነናል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ በተከታታይ ለሁለት ጊዜያት የጥራት ሽልማት አሸናፊ የሆነ ፋብሪካ ነው፡፡

የውድድሩ መስፈርት ምን ነበር?

ወደ ሰባት የሚጠጉ መስፈርቶች ነበሩት፡፡ ከእነዚህ መካከል ድርጅቱ ስትራቴጂክ ፕላን አለው ወይ፣ ደንበኛን ያማከለ ሥራ ይሠራል ወይ፣ የሠራተኛ ደህንነት አጠባበቁ ምን ያህል ነው፣ ገቢው በትክክል አድጓል ወይ፣ በገበያ ውስጥ ተወዳድሮ የመዝለቁ ጉዳይ ምን ያህል ነው በአካባቢ ጥበቃ ላይ ምን እየሠራ ነው፡፡ በመሣሪያዎች ንፅህና፣ በኬሚካል አጠቃቀም ላይ እንዴት እየሠራ ነው የሚሉ ጉዳዮች ሁሉ በመስፈርቱ ይካተታሉ፡፡ አወዳዳሪው አካል እነዚህን ነገሮች ሁሉ ካየና ከመረመረ በኋላ ከሌሎች ጋር በማወዳደር ውጤቱን ያሳውቃል፡፡

ሽልማት የአንድ ጊዜ ልፋት አይደለም፡፡ የአመታት የድካምና የሥራ ውጤት ነው፡፡ እኛ ከሞላነውና ከላክነው መጠይቆች ውጪ አወዳዳሪው አካል ቴክኒካል ኮሚቴ አቋቁሞ ድርጅቱን በአካል በማየት የሚያደርገው ምርመራ ሁሉ አለ፡፡ ይህንን ሁሉ ምርመራ አልፈን ነው ለሽልማት የበቃነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድርጅታችን በISO በምግብ ሴፍቲና በአካባቢ ጥበቃ ሰርቲፋይድ የሆነ ድርጅት ነው፡፡

የሔንከን ወደ አገራችን መምጣትና በቢራ ማምረት ዘንድ ውስጥ መግባት በአጠቃላይ በአገሪቱ የቢራ ገበያ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል ብለው ያስባሉ?

ዋናው የውድድር ጉዳይ ነው፡፡ ውድድር ሲመጣ ለደንበኛም፣ ለመንግስትም፣ ለጥራትም ያለው ፉክክር እያደገ ይመጣል፡፡ የሚተከሉት መሣሪያዎች ምነነት፣ ገበያው ውስጥ መከተል የሚገባው ስትራቴጂ፣ የሚቀጠረው የሰው ሃይል ሁሉ በደንብ እንዲታሰብበት ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ በምርት ጥራት ላይ የሚኖረው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

ስለዚህም በጥራትና በመጠን ከፍተኛ የሆነ ደንበኛው የሚፈልገው አይነት ምርት በገበያው ውስጥ እንደልቡ ለማግኘት ያስችለዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

 

 

 

Read 2324 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 14:55