Print this page
Sunday, 03 June 2018 00:00

አባይ ኢትዮጵያውያንና ግብፃውያን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ይድረስ ለሁለቱም አገራት  መሪዎች፡-
ግብፅና ኢትዮጵያ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት አላቸው፤ ከሰማኒያ በመቶ በላይ ከኢትዮጵያ የሚፈልቀው ጥቁር አባይ፣ ከነጭ አባይ ጋር ተጨምሮ፣ ለግብፃውያን የህልውናቸው መሰረት ነው፡፡ የጥንትም ይሁን ዘመናዊ የግብፅ መሪዎች፤ ይህንን የግብፃውያን የህልውና  መሰረት መጠቀምና ማስቀጠል የሚፈልጉት በኢትዮጵያውያን ኋላ ቀርነት፣ ደካማነትና ኪሳራ ላይ ብቻ ሆኖ መዝለቁ፣ የሁለቱን ሃገሮች ግንኙነት እስከ ዛሬ አሉታዊ አድርጎታል፡፡ ይህ በዲፕሎማሲ ቋንቋ፣ በተሸናፊነት መንፈስ፣ በኢትዮጵያ መሪዎችና ፖለቲከኞች የሚሸፋፈን ቢሆንም፣ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ልቦና ሁሉ እንደ ሰማዩ ፀሃይና ጨረቃ፣ በግልፅ ለዘመናት ለተያዘ ቅሬታና የቁጭት ስሜት ምክንያት ነው፡፡
ቀደም ብሎ ግብፃውያን መሪዎች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ፣ ጥንታዊውን የሁለቱን ሃገሮች የሃይማኖት ግንኙነት ይጠቀሙ ነበር፤ ውጤታማም ነበሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የቀጠሉት የሃገራችንን የውስጥ ጉዳይና ቅራኔ፣ ኋላ ቀርነታችንን በመጠቀም፣ እሳቶቻችንን በመቆስቆስ፣ በማንደድና ቤንዚን በመጨመር ሲሆን ውጤታማ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግብፃውያን ዘመን የፈጠረላቸውን፣ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ግድ የሌለውን ዓለምና በተለይ የአረብ ሃገሮችን አጋርነት ተጠቅመው፣ የሃገራችንን የመልማት፣ የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀም መብቷን ሙሉ ለሙሉ አፍነው ቆይተዋል፡፡
እስካሁን በዚህ አጠቃላይ አውድ የቀጠለው የአገራቱ ግንኙነት፣ ትላንትም ዛሬም፣ ለወደፊቱም ለሁለቱም አይጠቅምም፡፡ በተለይ ለግብፃውያን ደግሞ የበለጠ አይበጅም፡፡ ዛሬ ሁኔታዎች እያዘገሙም ቢሆን መቀየራቸውን መታዘብ ይቻላል፣ ወደፊትም መቀየራቸውም ግዴታ ነው፡፡ አዝጋሚው ሂደትና በተለይ የግብፅ መሪዎች ፍላጎት ግን ሁለቱንም እየጎዳ መቀጠሉን፣ ወደፊት ደግሞ የበለጠ ጉዳትና ኪሳራ እንደሚሆን መረዳት ተገቢ ነው፡፡
የሁለቱ ሃገሮች አጀንዳ ዛሬ ለሃይል ምንጭ ብቻ ነው ተብሎ እየተገነባ ካለው፣ ከህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና ከውሃ ክፍፍል በላይ፣ በወቅቱ የውሃ ሃብቱን የመጠቀም፣ በተለይ በኢትዮጵያ በተፈጥሮ ላይ ያለው ጥገኝነት በወቅቱ የቀነሰ ህዝብና ኢኮኖሚ ዕውን የማድረግ፣ ተፈጥሮን የመጠበቅና ግብፃውያን መሪዎች በኢትዮጵያውያን ስሜት ላይ የፈጠሩትን ቁስል የሚያሽር ግንኙነት፣ እውነተኛ ትብብርና ዕርቅ መሆን ይኖርባቸው ነበር፡፡ በሁለቱም ሃገሮች መሪዎች እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች፣ ውይይቶችና ስምምነቶች የጋራ ሆነው፣ በዚህ መሰረት ላይ ካልተፈፀሙ፣ ለሁለቱም ህዝቦች ችግርን የሚያራዝሙ፣ ከላይ የተጠቀሰውን የኢትዮጵያውያን ስሜት የሚያስቀጥሉ ብቻ ይሆናሉ፡፡ አለባብሰው ቢያርሱ ደግሞ ነገ በአረሙ መመለስ አይቀርም፡፡ እርሻውን በሁለቱ ሃገሮች በእየተራ እንመልከተው፡፡
አባይ፣ የህዳሴው
ግድብና የኢትዮጵያ መሪዎች
የኢትዮጵያ መሪዎች የወቅቱን ትኩሳትና ግርግር ብቻ ከማብረድ በላይ፣ ታሪካዊውንና ወቅታዊውን የግብፅ መሪዎችን ፍላጎቶችና ችግሮቻቸውን፣ ለሁለቱም ሃገር ህዝቦች ያተረፉትንና ወደፊት የሚያተርፉትን ችግር፣ የቀጠለውን የኢትዮጵያውያንን እውነተኛ ስሜት፤ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ለእራሳቸው ለግብፃውያን ሁሉ ለማስገንዘብ  መስራት ይገባቸው ነበር፡፡ ለሁሉም ስለሚጠቅም፡፡
የዛሬውን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ የአባይ ውሃን በኢትዮጵያ ለልማት ለመጠቀም ዕቅዱ የተዘጋጀው በንጉሱ ዘመን ቢያንስ ከዛሬ ሃምሳ ዓመታት በፊት በአሜሪካኖች ድጋፍ ነበር፡፡ የአሜሪካኖች የድጋፍ ጅምር ለግብፅ የርዕዮተ ዓለም አሰላለፍ የተመዘዘ ቢጫ ካርድ ብቻ ስለነበር፣ ግብፅ አሰላለፏን ስታስተካክል፣ ለዓመታት የተደረገው ጥናት፣ በሁለት ቀናት ተቋርጦ፣ ዕቅዱ ከግማሽ መቶ አመታት በላይ አቧራ ሲጠጣ ቆይቷል፡፡
ከምስራቁ ወደ ምዕራቡ ዞረው ለጊዜው የተሳካላቸው የግብፅ መሪዎች፣ ኢትዮጵያ በእራሷ አቅም ልትሰራ የምትችለውን ልማት ለመከላከል የመረጡት ስልት፣ በሃገሪቱ ችግሮች ስንጥር በማስገባት ማዳከምን ነበር፡፡ ጀብሃን፣ ሻዕቢያን፣ ወያኔንና ሌሎችንም መሳርያና ችግሮቻችንን ብቻ ከላይ (መሰረታዊ መንስኤዎቻቸውን ሳይሆን) ማስታጠቃቸውን፣ ዛሬም የአኩራፊዎቻችን አለኝታና መጠጊያ ሆነው መዝለቃቸው ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ለሶማሊያ አሸባሪዎች፣ለወራሪው ሻዕቢያ መሳርያ አቅራቢም ነበሩ፤ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ከዚህ ጋር ግብፅ፣ ኢትዮጵያ ዓባይን ለሚመለከቱ ማንኛውም ዕቅዶች፣ ከየትኛውም ሃገር የገንዘብ ተቋም ብድር፣ እርዳታና የቴክኒክ ድጋፍ እንዳታገኝ ሳታመነታ በመስራቷና ስለተሳካላት ጭምር፣ ዛሬ የሃገራችን መሪዎች ግፉን አሜን ብለው ሊቀበሉት ችለዋል፡፡
በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ በረጅም የእርስ በእርስ ጦርነት፣ በችጋርና በመከራ ውስጥ እየተንፏቀቀች፤ በድርቅና በርሃብ የሰው ህይወት እየጠፋ፣ ለስድሳ ዓመታት ስትዘልቅ፣ የተገነጠሉትን ትተን፣ የህዝብ ቁጥሯ ዛሬ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሆኗል፡፡ ከሃምሳ ዓመታት በፊት ሃያ አምስት ወይም ሰላሳ ሚሊዮን ስለነበር የህዝብ ቁጥሯ በአራት እጥፍ ሲያድግ፣ እንደ ጥንቱ ሙሉ ለሙሉ የተፈጥሮ ጥገኛ እንደሆነ ነው፡፡ ቀደም ብሎ የተሻለ ውጤታማ የሆነውን የአባይ ውሃ በተወሰነ መጠን የማልማት ዕድል ቢኖራት፣ሃገሪቱ የጦርነት አውድማ ባትሆን፣ትምህርት ቢስፋፋና እድገት ብታስመዘግብ ኖሮ፣ዛሬ ሃገሪቱ የተመጠነ የህዝብ ቁጥር፣በተወሰነ መልኩ ከተፈጥሮ ጥገኝነት የተላቀቀ ኢኮኖሚና ህዝብና ሌሎች የተፈጥሮና የውሃ ሃብቶቿን ለመጠቀም የሚያስችል አቅም ይኖራት እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ ዛሬ ለግብፅም ለኢትዮጵያም የተሻለ ይሆን ነበር፡፡
ባለቤቶች ራሳችን ብንሆንም፣ በግብፅ መሪዎች የሚደገፈው ኋላ ቀር ጉዞ ግን ሌሎችን ጨምሮ የተፈጥሮ ሃብት የሆነውን አባይ ውሃ በመጠኑ ቀንሶታል፡፡ የተፈጥሮ ሃብቶች (ውሃን ጨምሮ) ለሃገራችን ያላቸውን አስፈላጊነት ደግሞ ከነበረው በአራት እጥፍ ጨምሮታል ማለት ይቻላል፡፡
የግብፅ መሪዎችን አፍራሽና አፋኝ ፍላጎት ለመቋቋምና መብታችንን መጠቀም ለመጀመር ደግሞ ዘገየን፤ ዋጋ አስከፈለን እንጅ እስከ መጨረሻው ሊገታን አልቻለም፡፡ የህዳሴውን ግድብ ጥርሳችንን ነክሰን ጀምረነዋል፤  ወደፊትም እንቀጥላለን፤ የቆመ መራመዱ ስለማይቀር፣ መቀጠሉ ግዴታ ይሆናል፤ በተለያየ ዓይነትና መጠን፡፡ የኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ ሃብታቸውና በአባይ ውሃ የመጠቀም መብት፤ ወቅቱንና ጊዜውን፣ መልኩን፣ ወርዱንና ስፋቱን የሚወስኑት፤ ዓለም አቀፍ ህጎችና ስምምነቶች፣ እንዲሁም  የእራሳችን ሃገር ውስጣዊ አቅም ናቸው፡፡
ከነዚህ ሁሉ በታች ግን በኢትዮጵያ ያለውና ወደፊት የሚኖረው የተፈጥሮ ሃብቶች፣ የውሃ ሃብቱ ተጨባጭና ወቅታዊ አስፈላጊነት፣ ከታችኛው ተፋሰስ ሃገሮች በተለይ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ያሉን ታሪካዊና ወቅታዊ ግንኙነቶች፣ ታሪካዊ ቁርሾዎችና ጠባሳዎች ድርሻ አይኖራቸውም ማለት አይቻልም፡፡ ይህንን ለግብፅ መሪዎች በግልፅ ቋንቋ ማስረዳት ተገቢ ነበር፡፡ በተለያዩ ስልቶች ለሃገራችን ጉዞ ዕንቅፋት መሆናቸውን ማቆም፣ እርም ማለት እንደሚገባቸው ዛሬ ሳይሆን በፊትም ሊነገራቸው ይገባ ነበር፡፡ ከህዳሴው ግድብ ግንባታ በፊትም፣ በኋላም፣ ሁልጊዜ እስካልታረሙ ድረስ፣ የመሰረት ድንጋዩ ሲጣልም ቢሆን አብዩ መልዕከት መሆን ነበረበት፡፡
ይቻላል ተብሎ የተጀመረው የህዳሴው ግድብ መሰረት ሲጣል፣ ሃገራችን ሃብቷን ለምን ሳትጠቀም እንደዘገየች፣ ዛሬም እንዴት እንደምትገነባው ተገልፆ፣ ከታሪካችን የወደፊቱን ማመላከት ለሁሉም ጠቃሚ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን የመልማትና የመጠቀም መብታቸውን በግብፅ ታፍነው ለዘመናት ከዘለቁ በኋላ ይህንን አፈና ለመቀልበስ የተጀመረውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የአፈናውን አንዳንድ ስልቶች ከተቀበለ፣ የተሸናፊነት ስሜት ላይ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥና ከዚያ በኋላ ማስቀጠል ስህተት ነው፡፡ ለወደፊቱም አቅም አይሆንም፡፡
የግብፅ መሪዎችን ግፍ አሜን ብላ የተቀበለችው ሃገር፣ የአባይን ውሃ መጠን በጣሳ የሚቀንስ ዕቅድን ይዛ የብድር፣የእርዳታና የቴክኒክ ድጋፎች ለማግኘት ሙከራ የምታደርግ አይመስልም፡፡ ባይገኝም ግን ችግሩን ለማስገንዘብ ሙከራው መደረግ፣ አጀንዳውን ሁልጊዜ ወቅታዊ ማድረግ ነበረብን፡፡ ይህን ትተን ለሃይል ማመንጫ ብቻ ብለን፣ የያዝነውን ዕቅድ የሚደግፍ ሃገርና ተቋም ዓለም ላይ ሲጠፋ እኛ የት እንዳለን፣ዓለም ምን እንደሆነች፣ የግብፅ መሪዎችንና ፍላጎቶቻቸውን ልናጠይቅበት፣ልንረዳበትና የጋራ አቋም ልንይዝበት ይገባ ነበር - ከታሪካዊ ጅምር ጋር፡፡
በውጭ ሃገር ስራ ተቋራጭ፣ በከፍተኛ ብድር ላይ የተደገፈና በእርዳታ በሚደጎም  አጠቃላይ ኢኮኖሚ የሚገነባን አንድ ፕሮጀከት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር፤ “መሀንዲሶችም፣ ግንበኞችም፣ የፋይናንስ ምንጮችም እኛው  ነን” ብለው በኩራት መናገራቸው፣ ተገቢ ሳይሆን ከፍተኛ ስህተትም ነበር፤ ይህ የተጫነብንን ግፍ፣ በፈቃዳችን እንደመረጥነው ምርጫና ችሎታችን የሚያስገነዝብ ንግግር ዛሬም ድረስ ይደጋገማል፡፡ አስተሳሰቡ ሲቀጥል መንግስት ለስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ይውላል በማለት ለዓለም ገበያ ያቀረበውን የቦንድ ብድር የተበደረው ገንዘቡ ለምን እንደሚውል (ዛሬ ቢባክንም) ከመግለፅ በተጨማሪ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ በጭራሽ እንደማይውል አበክሮ፣ ደጋግሞ፣ በመግለፅ ምሎ ተገዝቶ ነበር፡፡ በፍርሃት፣ በራስ ስሜት ብቻ መሸነፋችንን፤ ግፍን አሜን ብሎ መቀበላችንን ያረጋግጣል፡፡ ከዚህ ስሜት መውጣት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
በመንግስት ብቻ ተገድቦም አልቀረም፤ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ስለ ህዳሴው ግድብ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ቀርበው ሲናገሩ፣ ታሪክን አንስተው የገለፁትም ተመሳሳይ ነበር፤ ቆቅ ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ የሆነ፡፡ ዲያቆን ዳንኤል፤ “የአክሱም ህንፃን ስናቆም፣ ላሊበላን ስናንፅ የአለም ባንክ፣ አይ.ኤም.ኤፍ ነበሩ?” ሲሉ ራሳቸው ጠይቀው “አልነበሩም፤” ብለው ራሳቸው መልሰዋል፤- ዲያቆን ዳንኤል፡፡ በአወንታ እራሱን ለሚነቀንቀው ጋዜጠኛ “የህዳሴውን ግድብ ለመገንባትም ዛሬ እነዚህ ተቋማት ግዴታ አይደሉም፣ አያስፈልጉንም፣ በእራሳችን አቅም መገንባት እንችላለን፤” ሲሉ በስሜት ተናግረዋል፤ ከስሜት ጋር ደግሞ ስህተቶች አሉ፡፡
ዓለም ላይ ስመ ገናና የነበረውን አክሱም፣ የመን ድረስ ተሻግሮ አስተዳድሯል፣ ህንድ ድረስ የንግድ ግንኙነት ነበረው፣ ለግብፅ ክርስቲኖች ጭምር አለኝታ ነበር፤ የምንለውን ሃገርና ህዝብ ሃውልት ሲያቆም፣ ግብፃውያን ንቀውት፣ በአለም ሃገሮች አይን አይሞላም፣ ብቻውን ነበር ማለት ከፍተኛ ስህተት ነው፡፡ መነሻቸው ከመካከለኛው ምስራቅ የሆኑት፣ በእየጊዜው ከምንጫቸውና ከሌሎች ሃገራት ጋር ግንኙነቶች የነበራቸው ክርስትናችንና ንጉሱ ላሊበላ፣ ቤተ-መቅደስ ሲገነቡ፣ ብቻቸውን ነበሩ ማለት አለማገናዘብ ብቻ ነው፡፡
ዛሬ እኛ አሽቆልቁለን ዓለምና ተቋማት ተራምደው፣ እነዚህ ሁሉ አያስፈልጉንም ማለት ሞክራ ያልቻለችውን ጦጣ የሚያስታውስ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ በግብፅ መሪዎች ፍላጎት ጫማ ስር ወድቀን በሌሎች ሃገሮች፣ በአለም ባንክ፣ በአይ.ኤም.ኤፍ አይን መሙላት አለመቻላችንን በተለይ ከአክሱም ስልጣኔ ጋር ማነፃፀር ነው ተገቢም፤ የሚጠቅመንም፡፡
በዘመናቸው ያላስፈለጋቸውን አባይ፤ አክሱማውያን ለግብፅ ወንድሞቻቸው ብቻ ቢተውት ትክክል ነበሩ፤ አባይን ተቀባይነታቸውን፣ ጥቅማቸውንና ፍላጎቶቻቸውን ለማረጋገጥ የተጠቀሙበት ግን ውሃውን መቀነስ ፣ማቀብ (መገደብ) ስለሚችሉ ነበር። ዛሬ የውሃ ሃብቱ እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም ለዘመናት ሳንጠቀምበት የሰው ህይወት እየጠፋ፣ በችጋርና በመከራ ውስጥ ቆይተናል፡፡ ይህንን ታሪክ ለመቀየር እንደምንችል፣እንደጀመርነው ከዚህ በኋላ መቀጠል ይቻላል፡፡ ለህዝቡ ሞራል ተብሎ ከተገለፀም መቅደም የነበረበት ችግሩ ነው፡፡ ለህዝቡ ሞራል፣ መነሳሳትና እርብርብም ምክንያቱ እነዚህ የውሸትና የማስመሰል ንግግሮች አይደሉም - ከላይ የተገለፀው የዘመናት ቁጭቱ እንጅ፡፡  በሃገራችን መሪዎች የተሸናፊነት አቋም ምክንያት የግብፅ መሪዎች፣ አንድ ጊዜ ሰው፣ አንድ ጊዜ አፈር እየሆኑ እንዲቀጥሉ የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል ማለት ይቻላል፤ እንመልከተው፡፡
ናይል፣ የህዳሴው ግድብና የግብፅ መሪዎች
ከግብፃውያኑ መሪዎች ዛሬ ደግሞ የሚጠበቀው፤ የትላንቱን ስህተት ሁሉ የሚያራግፍ፣ አፍራሽ ተልዕኮቻቸውን ሁሉ ማቆም ብቻ ሳይሆን በእውነተኛ ስሜትና ቁርጠኝነት፣ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሃብታችንን የመጠቀም፣ የማልማት መብቶቻችንን በማክበርና በማረጋገጥ የታሪካዊውን ግንኙነት መስመር በወቅቱ ማስተካከል ነበር፡፡ ግብፃውያን መሪዎች የዛሬውን የኢትዮጵያ መሪዎች ፖለቲካና ዲፕሎማሲ ትተው፣ ዘላለማዊውን ከላይ የተገለጠውን፣ የፀሃፊውን ጨምሮ የዜጎችን ስሜት መረዳት አለባቸው፤ ፖለቲከኞችም ከዚህ የተለየ ስሜት ይኖራቸዋል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡
ግብፅና መሪዎቿ በቅርቡም በሃገራችን የተከሰተውን ችግር ለማራገብ ሞክረዋል፤ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ በቅኝ ግዛት ውል ለመሞገትና ንቀታቸውን ለመቀጠል ሞክረዋል፡፡ ቀደም ብለን እንደገለፅነው፤ ኢትዮጵያ በአዝጋሚ ሂደትም ቢሆን መቆም ጀምራለች፤ ተመስገን ነው፤ ግብፅና መሪዎቿ ያራገቡት ችግር ዛሬ አዲስ ተስፋን አምጥቷል፤ዶ/ር አብይ አህመድን የመሰለ መሪ። ምንም ቢሆን ግን ነገን በኢትዮጵያ በተሻለ ተስፋ መጠበቅ ግዴታ ስለሆነ፣ አቋምን በወቅቱ ማስተካከል የግብፅና መሪዎቿ ወቅታዊ ግዴታ ነበር፡፡  
ከኢትዮጵያ መሪዎች የተሸናፊነት ስሜትና ፈራ - ተባ ብለው በያዙት የዲፕሎማሲ አቋም ምክንያት የህዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለና በኢትዮጵያ ህዝብ እርብርብ ግንባታው ከቀጠለ በኋላም የግብፅ መሪዎች አቋም የተለያየ መልክ ነበረው፤ በመጨረሻ የነበረው ሊቀጥልበት ቢችልም፡፡
የመሰረት ድንጋዩ በተጣለ ማግስት የግብፅ መሪ የነበሩት ሁስኒ ሙባረክ ያቀኑት ወደ ምስኪኗ ኢትዮጵያ ሳይሆን ወደ ጣልያን ነበር፤ በንቀታቸው ምክንያት። ግድቡን የሚገነባው ሳሊኒ የጣልያን ስራ ተቋራጭ ስለሆነ፣ በጣልያን መንግስት በኩል እንደተለመደው እንቅፋት ለመሆን የተደረገ ሙከራ ነው፡፡ የጣልያን መንግስት፤ “ሳሊኒ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆነ ተቋም ስለሆነ ጣልቃ መግባት አንችልም፤” በማለት ሙከራውን አልተቀበለውም፡፡ ሙከራው ወደ ሳሊኒ አልቀጠለም ወይም ቀድሞ አልተሞከረም ብሎ የሚያስብ ገልቱ የለም፤ ስለዚህ ጣልያናዊው ሳሊኒ ግን ከሃገራችን ጎን ቆሞ መቀጠሉን ለማድነቅ እንገደዳለን፡፡
እኔ በግሌ የስራ ተቋራጩን አቋምና ወቅታዊ ስሜት ለመከታተል ሞክሬያለሁ፤ በአይናቸው ከማንሞላው የመገናኛ ብዙኋን፤ ሳሊኒ የህዳሴውን ግድብ የሚገነባበት ክፍያ (ከምስኪኗ ኢትዮጵያ) በወቅቱ እየደረሰው እንደሆነና ለወደፊትም ስጋትና ጥርጣሬ እንዳለው ተጠይቆ፣ በመገናኛ ብዙሃን አንብቤያለሁ፡፡ በሳሊኒ አመራሮች የተሰጠው መልስ አንጀቴን አርሶታል፡፡ ጣልያንንም ሳሊኒንም እጅ እንደነሳሁ አለሁ፡፡ ሁስኒ ሙባረክን የተኩት የሙስሊም ወንድማማቾች ሙርሲ፤ከዚህም በላይ የግብፃውያንን ህልውና ለማስጠበቅ እዘምታለሁ፣ የጦር መሪዎቻቸውን ሰብስበው፣ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ታዝበን ነበር፡፡ በተለያዩ የውስጥ ቀውሶች በቀጠለችው ግብፅ፤ ከሙርሲ በኋላ ወደ ስልጣን ከመጡት አልሲስ፣ መጀመርያ ላይ የለውጥ አዝማሚያ ታይቶ ነበር። አል.ሲ.ስ የኢትዮጵያውያንን የመልማት ፍላጎት እንረዳለን፣ እንደግፋለን ብለው፤ ከመሪዎች አልፎ የሁለቱ ሃገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ተጀምሮ ነበር፡፡ በሊብያ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ በግብፅ በኩል ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ ከመተባበርም አልፈው መሪው፣ በአውሮፕላን ማረፍያ ተገኝተው፣ አቀባበል አድርገውላቸው ነበር፡፡ ለሁለቱ ሃገሮች የሚበጀው ተመሳሳይ ግንኙነት፣ መተባበርና መከባበር ስለሆነ፣ ተስፋን ያጫረ ጅምር ቢሆንም የቀጠለና የጎለበተ ግን አልነበረም፡፡
በሁለቱ ሃገሮች ከዚህ በኋላ የቀጠለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፤ ውይይትና ድርድሩ ሁሉ በትክክለኛው መሰረት ላይ ያልቆመ፣ በጥርጣሬና ባለመተማመን ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሱዳን የነበራትን አቋም ያስተካከለችበት፣ የግብፅ መሪዎች ግን ዛሬ የኤሌክትሪክ ሃይል ብቻ አመንጭተን የምንለቅበት ነው የምንለውን ግድብ እንኳ በሙሉ ልባቸው ለመቀበል ተቸግረዋል፡፡ እስከ ዛሬ የባከነው ጊዜ፣ ኢትዮጵያውያን ጥቂት መብቶቻችንን ለመጠቀም ሳንችል የቆየንበትን ታሪክ አልተረዱትም፡፡ አንድ ጊዜ ዝቅ ስላደረጉን የወደፊቱን ተገቢ ፍላጎቶቻችንን ከወዲሁ አልገመቱትም፡፡ ስለዚህ በዚህ የምንቀጥል ከሆነ መጨረሻው ለማንም የማይጠቅም፣ በተለይ ግብፃውያንን ዋጋ የሚያስከፍል ብቻ ይሆናል፡፡ ትላንትን ወደ ኋላ ማስታወስና ዛሬን መመልከት፣የወደፊቱን መዘዝ ለመተንበይ ያስችላል፡፡
አባይ ኢትዮጵያውያንና ግብፃውያን - እንደ መደምደሚያ
የግብፅ መሪዎች ኢትዮጵያን እንደ ጥንቱ አፍነው መቀጠል አይችሉም፤ ቢችሉም ግን አይጠቅማቸውም። ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት በነበርንበት ጉዞ ብንቀጥል፣ ከሃምሳ ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር አራት መቶ ሚሊዮን ይሆናል፤ እንደነበረው የተፈጥሮ ብቻ ጥገኛ ሆኖ ማለት ነው። በዚህ ወቅት ግድቡንና መስኖውን ትተን፣ ህዝቡ  ከብቶቹን ይዞ ወደ ተራሮቻችን ይወጣል፤ የውሃ ቅሉን ይዞ ወደ አባይና ገባሮቹ ይወርዳል፤ ግዴታው ነው፡፡ የሰው ዱካና የከብት ኮቴ ተፈጥሮን፣ዕፅዋትንና ውሃን ምን እንደሚያደርጉ መመልከት ይቻላል፤ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ብቻ፡፡ ያኔ ለሁላችንም አጀንዳ ላይኖር ይችላል፤ የበለጠ የምትጎዳው ሃገር ደግሞ ግብፅና ግብፃውያን ይሆናሉ፡፡
ከዚህ በመለስ የግብፅ መሪዎች በዚሁ ቀጥለው፣ ሃገራችን የጀመረችውን በተለያዩ መንገዶች የተፈጥሮ ሃብቷን  የመጠቀም መብቷን እያረጋገጠች ስትቀጥል አቅማችን ያድጋል፡፡ ያልነበረን ወንድማማችነትና ትብብር ድንገት ማምጣት ስለማይቻል፣ግብፃውያን እንደ አክሱም ዘመን፣ በወንድማማች ህዝቦች መካከል በሚኖር የትብብር መንፈስ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የመስራት ዕድላቸው እየጠበበ ይሄዳል፡፡ በዚህ ወቅት በመካከላችን የሚኖረው ዓለም አቀፉ ህግና ስምምነት ብቻ ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታም ግብፃውያን አያተርፉም፤ ስለዚህ ያዙኝ ልቀቁኝ አማራጭ ሆኖ ሊታያቸው ይችላል፡፡
በንጉሳችን የተመራውን ጉንዴትና ጉራን አናነሳውም፡፡ የሩቅ ታሪክም ቢሆን ሃገራችን ግን በዘመነ መሳፍንት ተከፋፍላ ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ሃገሪቱን በቀላሉ አንድ አድርገው ቢነሱም፣ መጨረሻቸው እንደ ዘመነ መሳፍንት ወቅት ነበር፡፡ ንጉሱ በመቅደላ ተወስነው፤ በትግራይ በዝብዝ ካሳ፣ በሸዋ አፄ ምኒልክ፣ በላስታ ዋግሹም ጎበዜ ነግሰው ነበር፡፡ እንግሊዝ በአፄ ቴዎድሮስ የተያዙ ዜጎቿን ለማስፈታት ዕቅድ ስትነድፍ፣ የተያዘ አንድ ግንዛቤ ነበር፡፡ እንግሊዞች ለኢትዮጵያ ቅርብ ከሆኑት ቅኝ ግዛቶቻቸው፣  ግብፅና ሱዳን ጦር ለማዝመት ሃሳብ ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ምን ቢከፋፍሉ፣ ከእነዚህ ሃገሮች የሚሰነዘር ጥቃት አንድ ላይ እንደሚያቆማቸው ስለተረዱ፣ ከህንድ ነበር ጦር ያዘመቱት፡፡ ሶማሊያና ዛይድ ባሬ እስካፍንጫቸው ታጥቀው፣ ኤርትራና ሻዕብያ በራሷ በግብፅ እስፖንሰርነትም በቅርቡ አይተውታል፡፡ ዛሬ ደግሞ ሁኔታዎች፣በኢትዮጵያ ተቀይረዋል፣ የተፈጠረ አቅም፣ የተያዘ ግንዛቤና ስምምነት አለ፤ ይቀጥላል፡፡

Read 2085 times
Administrator

Latest from Administrator