Saturday, 02 June 2018 11:59

መኖር ደስ ይላል!

Written by  ተሾመ ገ/ሥላሴ
Rate this item
(6 votes)


    “ብዙዎች ደሴቶቻቸውን ፍለጋ ላይ ናቸው”

በቅድሚያ ስለ ራሴ  ልንገርህ። አለመኖርን አላውቀውም፤ ላውቀውም አልጓጓም። በመኖር ቤተ-መቅደስ ውስጥ ነኝ። መኖርን እቀድሳለሁ። መኖርን አሞካሻለሁ። እንዳንተው ስለ መኖር አዜማለሁ።በነገሥታት የአትክልት መናፈሻ ውስጥ አይደለሁም። ባለጸጋና ሰቀላዬን በቃፊር የማስጠብቅ አይደለሁም። ሠፈሬ ከመኳንንትና መሳፍንት የተጣጋም አይደለም። የከበሩ ማዕድናትንና እሴቴን የማከማችበት ጥብቅ ሳጥን የለኝም። ምክንያቱም የማከማቸው የለኝምና። በሌለሁበት ቦታና ጊዜ ስለመዘከር አላልምም። በአዕላፍት ትውስታ ውስጥ የምነሳም አይደለሁም። ክፉ ታሪክ የለኝም- በጎም። ብዙ የዓለም ጀግኖች፤ ከመቃብር በፊትና በኋላ ስማቸው በሌሉበት ጊዜና ቦታ ሲወደስ ሰምቼ አውቃለሁ። በየዕለቱ አዳዲስ ስመ ገናናዎች ይወለዳሉ። የቀደሙትም የነበረ ገናናነታቸውን ለማጽናት ሲሉ የሥቃይ ግብግብ ገጥመው እንደዋዛ ሲያልፉም እንዲሁ።
ወዳጄ ሆይ!
ከሞት በኋላ ለዝክሬ የሚሆን ዘላለማዊ ሐውልት ለማቆም አልደክምም። ሐሳቡ ራሱ ያደክማል አይደል? ይልቁኑ እርሱን በማሰብ የምትባክነውን ጊዜ መኖርን ባዜምባት እመርጣለሁ።

መኖርን ‘የሚረግሙ በመኖራቸው የሚበሳጩ’ የሚመስሉ ወዳጆቼን ቃል በየዕለቱ አዳምጣለሁ። “ፍለጋ ያደክማል ለመኖር መታተር ያታክታል!” ይሉኛል። የዕለት እንጀራቸውን በድካምና በመዛል ያገኛሉ። ግና ማዕዳቸውን ሲቆርሱ ፊታቸው ተፈትቶ አላየሁም። “እኛን መፍጠሩ ስህተት ነበር!” እያሉ ጣታቸውን ሽቅብ ይቀስራሉ።ታዲያኮ ማልደው ይነሳሉ። ያንኑ የዕለት እንጀራቸውን ሊያገኙ ይፈተለካሉ።
“መኖርን ቀድሳችሁት ታውቃላችሁ ወይ?” ስል ጠይቄያቸዋለሁ።
“ በፍጹም!” ብለውኛል፤ ነገር ግን በምላሹ እርግጠኞች እንዳልነበሩ አይነ-ውኃቸው ራሱ ያሳብቅ ነበር። የዕለት እንጀራቸውን ቆፍረው የሚያወጡበት ጉድጓድ ጥልቅ  ቢሆንም ሁሌም መኖርን ሳይቀድሱ ውለውና አድረው እንደማያውቁ ታዝቤያለሁ። የሚኖሩበትን ሌላ ቀንና ሌላ ሌሊት ለመድገም ሲሉ ማልዶ ከመነሳት በላይ ቅዳሴ ምናለ?
ወዳጄ ሆይ ታዲያ አንተ ከወዴት ነህ?
ጀግና ብትሆን ቦቅቧቃ፤ አዋቂ ብትሆን ቂል፤ ብታልም ባታልም፤ ብታሸንፍ ድል ብትሆን፤ ቢሳካልህ ባይሳካልህ፤ ብትታመም ወይ ጤና ብትሆን፤ ብታዝን ብትደሰት፤ ክቡር ብትሆን ወይ ተርታ፤ አለቃ ብትሆን  ምንዝር፤ ዝና ቢኖርህ ባይኖርህ፤ ዘመደ ብዙ ብትሆን ዘመደ-አልቦ… ያው የመኖር ዘማሪ ነህ።
ምኩራብ፣ መስጂድና ደጀ-ሠላም አጥር ሥር ተንጋልሎ በእንተ-ፈጣሪ ተመጽወቱኝ የሚል በደዌ የተመታ ሥቁይ አይተህ “ከዚህስ ሞት ይሻለዋል!” ስትል ሞትን መርጠህለት ይሆናል። እርሱ ግን አንተ የመረጥክለት ሞት ምርጫው አይደለም። ያማ ባይሆን ቆሞ ባላየኸው ነበር።ምርጫው መኖር ነው። መኖር! መኖር! መኖር!
ለመኖር ሲል የሚያቀነቅነው ዜማ ለጆሮ ባይሰልጥም፤ ለሕልውናው ሲል የሚዘርፈው ቅኔ አንጀትን ቢንጥም፣ ካንተ ቀድሞ የማለዳዋን ጀንበር የሚያየው ይህ ሰው ነው። ነገ ለዚህ ሰው ብርቁ ናት በምንም የማትለካ! አንተ በሰው ልብ ውስጥ ውሎ ስለማደር ታልም ይሆናል። ሕልምህ ከነገ ወዲያ ስላሉት ብዙ ቀናት፣ወራትና ዓመታት ይሆን ይሆናል። እርሱ ግን እያንዳንዷን ቀን በስስት ይኖርባታል። ነገ ይዞት የሚመጣውን ብሩህ ቀን ለማየት ይጓጓል። ታዲያ ለዚህ ፍጡር ሞትን የምትመኝለት ከቶ አንተ ማነህ?
ይህ ሰው ዝና የለውም። ቢሞት እንኳ አስከሬኑን የሚያነሱት የማዘጋጃ ቤት ሰዎች ይሆኑ ይሆናል። መቃብሩን በስሙ ለይቶ የሚያሳይም አይኖርም።ማን ያውቃል ስም እንኳ የለውም ይሆናል። ይህ ሁሉ ለእርሱ ምንም አይደለም። ይህ ሰው መኖርን ይፈልጋል። እዚህ ሰው ዘንድ ስላለመኖር ታነሳበትና ወየውልህ!
በሕይወት መካከል ስለ ሞት ከሚያዜም በላይ ክፉ የለም።

መኖርህን የምትኩልባቸውንና የምታጌጥባቸውን አያሌ ቀለማት ስታማርጥና ስትቀላቅል ኖረሐል። መኖርህ ትርጉም ያገኝ ዘንድ ታንኳህን እየቀዘፍክ ደሴትህን ፍለጋ ውቅያኖስ አካልለህም ታውቃለህ። መኖርን የምትኩልበትን የራስህን ቀለም አግኝተህ ይሆናል። ካገኘኸው እሰየሁ እንኳን ደስ ያለህ! በእርግጥ ፍለጋው አድካሚ ነው፤ ቢሆንም ያው የመኖር አካል ነው። የውቅያኖሱን ወዠብ ጥሰህ መቅዘፊያና ታንኳህን ከነፋሱ ፍጥነትና አቅጣጫ ጋር አስማምተህ እየነጎድክ መዳረሻዬ ነው ካልከው ሥፍራ ደርሰህ ይሆናል። ከደረስክ እሰየሁ! ከመድረስ ይልቅ ፍለጋ የሚያስደስትህ ሰው ከሆንክም እሰይ እንኳንም ፍለጋህን አገኘኸው!
ቀለም ፈላጊ!
ሺህ ጊዜ ብትመርጥ ቀለምህን ላታገኘው ትችል ይሆናል። ወይ ቀለሙን ታገኝና አጊያጌጡ ይጠፋብህ ይሆናል። ይሔኔ መላ ነገርህን በቀለማት አዥጎርጉረህ በመጪና  ሒያጁ ዘንድ እንደ እንግዳ ፍጡር ትታይ ይሆናል። ብዙዎች “አጊያጌጡን ሳትችልበት እንዴት ኖርኩ ትላለህ?” እያሉ ተሳልቀውብሃል። ወዳጄ! ውሸታሞች በላቸው። ይሄ እንዲህ ማለት ለብቻው መኖር የሚመስላቸው ግራ የገባቸው ሰዎች ንግግር ነው።
ቀለማቱን ስትመርጥ እየኖርክ ነው። ከፍለጋ በላይ ኑሮ ምናለ? ሳታገኘው ቀርተህም ከሆነ ያው እየኖርክ እንጂ እየሞትክ አይደለህም። ነገረ-ዓለምህ የቀለማት ኅብር መሆኑ ብዙዎችን ያስቃቸው ይሆናል። አንተ ግን ዜማ ስልቱ ይለያይ እንጂ ያው የመኖር ዘማሪ ነህ።
ባሕረኛ ሆይ! ወዠቡ በርትቶ ታንኳህ ልትናጥ ትችላለች። እፎይ አረፍኩ ስትል በየርቀቱ ያንተ ካልሆኑ ብዙ ደሴቶች ጋር ተገናኝተህ ይሆናል። ምናልባትም እስክታረጅ ድረስ ፍለጋው አያበቃ ይሆናል። ደሴቱን የሚፈልግ ሰው እርጅና አይገድበውም። መፈለግ ሁሌም ትኩስ ነው። አንተም እየኖርክ ነው።

“መኖር ከመኖር ይበልጣል ይበላለጣል።” ሲሉ ሰምተሃል? እኔ ብዙ ጊዜ ሰምቻለሁ። “የዚህ ሞያ ባለቤት በመሆኔ ከሌላው ከየትኛውም ባለሞያ ይልቅ ኑሮን እየኖርኩት ነው።የሕይወት ተልዕኮዬና የተፈጠርኩለት ተሰጥኦ ይሔኛው ስለሆነ ከኔ በላይ ኗሪ ላሳር።” የሚሉ ሰዎች አልገጠሙህም? እኔ በየቀኑ እሰማቸዋለሁ። በተለይ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ነን በሚሉቱ አይብስ?
ከሰው የተለየ የሰላ ዓይን እንዳላቸው ይነግሩናል። ፍጥረትን የመተርጎምና ቅኔ የማድረግ ኃይል የእነርሱ ብቻ እንደሆነ ያትታሉ። ከክህሎታቸው ቆርሰው ጧፍ ሆነው እየነደዱ ብርሃን እንደሰጡን ይደሰኩራሉ። አንዳንዶቹማ እነርሱ ባይኖሩ ምድር ትርጉም እንደማይኖራት እስከመናገር ይደፍራሉ። እንዲህ ካሉት አያሌዎች መካከል የበለጠ መኖር የሚሉትን የኖረ አንድ ስንኳ የለም። የበለጠ መኖር ማለትስ ምንድነው?
ጸሐፊ ወረቀቱን ቢሞላ፤ ሰዓሊም ሸራ ቢያቀልም፤ ተዋናዩ መድረኩን ቢንቧችበት፤ ጠራቢ ምስል ቢያቆም፤ አዝማሪውም ቢዘምር…ከነዚህ መካከል ብዙዎቹ ገና ቀለሞቻቸውንና ደሴቶቻቸውን ፍለጋ ላይ ያሉ ናቸው። ጥበብን እየኖሯት ያሉ ጠቢባን ነን ያሉ ብቻ አይደሉም። እንዲያውም መላው ዘረ-ሰብ ጥበብን እየኖራት ያለ አይመስልህም?
ዜማህን ሰው ስላልሰማው እንጂ አንተ‘ኮ ጥሩ አዝማሪ ነህ። ብልጥና ተሸሎክላኪ ስላይደለህ እንጂ ጥሩ ገጣሚ ነህ። ሰው አክባሪ ሆነህ እንጂ ትልቅ ባለቅኔ ነህ። ያማ ባይሆን እንዴት መኖር ትችል ነበር? ለሌሊቱ መንጋት፤ ለቀኑ መምሸት፤ ለፍሬው ማሸት፤ ለያዘህ ፍቅር፤… የምትሰጠው የራስህ ትርጉም ቅኔ ማለት ጥበብ ማለት እርሱ ነው። እናም ለመኖር ከመትጋት የላቀ ቅኔ ከወዴት ይመጣል?
አንተ ጠቢብ ነህ። ከሰቀላም ሆንክ ከዛኒጋባ፤ ባለሰረገላም ሆንክ እግረኛ፤ መጽዋችም ሆንክ ተመጽዋች፤…ሁሌም ታዜማለህ። የመኖርን ዜማ ማልደህ ተነስተህ ታዜማለህ፤ ለነገ ይሁን ለከርሞ መኖር። መኖር ደስ ይላል!!
(ከላይ የቀረበው ጽሁፍ በአዲስ አድማስ ድረ-ገጽ ላይ April 12,2012  የወጣ ነው፡፡

Read 3375 times