Sunday, 10 June 2018 00:00

በ400 ሚ. ብር የተገነባው ሀይሌ፣ ሪዞርት አርባ ምንጭ ሥራ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 የሆቴልና ሪዞርቶቹን ቁጥር በ6 ዓመት ውስጥ 20 ለማድረስ አቅዷል
                
   በአርባ ምንጭ የተገነባው 400 ሚ. ብር የወጣበት ኃይሌ ሪዞርት አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ግንባታው አንድ ዓመት ከሰባት ወር የፈጀ ሲሆን ሁሉም ስራው ተሰርቶ የተጠናቀቀው በአገር ውስጥ ባለሙያዎች መሆኑን ሻለቃ አትሌት ኃይሉ ገ/ሥላሴና የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርቶች የሆስፒታሊቲ ግሩፕ ዳይሬክተር አቶ መልካሙ መኮንን ከትላንት በስቲያ በዓለም ሲኒማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ኃይሌ በቀጣይ 6 ዓመታት ውስጥ የሆቴሎቹን ቁጥር 20 ለማድረስ ማቀዱንም ገልጿል፡፡
ሆቴሉ በአርባ ምንጭ በጣም የሚያምር እይታ ላይ የተሰራና በ42 ሸህ ስኩየር ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን ለከተማዋ የመጀመሪያ ሪዞርት መሆኑ ታውቋል፡፡ ባለ አራት ኮከብ ሪዞርቱ 110 ደረጃቸውን የጠበቁ የመኝታ ክፍሎች፣ አራት የተለያየ መጠን ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች፣ አራት የምግብ አዳራሾች፣ እንግዶችና የአካባቢው ህዝብ ጤናውን የሚጠብቅበት ጂምናዚየም፣ የመዋኛ ገንዳ፣ የህፃናት መጫወቻ፣ መለስተኛ ኳስ ሜዳ፣ አባያና ጫሞንና የእግዜር ድልድይን ጨምሮ የአካባቢውን ልዩ ተፈጥሮ መመልከቻ ማማ፣ ስፓ እንዲሁም ለባንክ፣ ለስጦታ እቃ መሸጫ፣ ለቢሮና መሰል አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችና በቂ የመኪና ማቆሚያን አካትቶ የተገነባ መሆኑን ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ  አስታውቋል፡፡
ሪዞርቱ በሙሉ አቅሙ ስራ መጀመሩን የገለፀው ኃይሌ፣ ለ300 ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠሩንና ከሰራተኞቹ 95 በመቶ ያህሉ የአካባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውን ጠቁሞ፣ ይህም የኃይሌ አለም ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ጠቅላላ ሰራተኞችን ቁጥር ወደ 2300 ከፍ እንዳደረገው በዕለቱ ተናግሯል፡፡
የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርቶችን ለየት የሚያደርጋቸው ልክ እንደነ ሂልተን ሸራተንና ማሪዎት ቼይን አገር በቀል ሆቴልና ሪዞርት በመሆኑ ነው ያለው ኃይሌ፤ በቀጣዮቹ 6 ዓመታት የሆቴልና ሪዞርቶቹን ቁጥር 20 ለማድረስ መታቀዱን ገልፆ በአዲስ አበባ የባለ 5 ኮከብ ሆቴል ግንባታ መጀመሩን፣ በኮንሶ  በደብረብርሃንና ሶዶ ሆቴልና ሪዞርቶችን ለመገንባት ቦታ ወስዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግሯል፡፡
ኃይሌ አለም ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ግሩፕ በ1992 ዓ.ም በ50 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በግብርና (በቡና ማር)፣ በትምህርት፣ በሪል እስቴት፣ በማዕድንና በተለይም በሆቴሉ ዘርፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡

Read 4147 times