Sunday, 10 June 2018 00:00

“ከግንቦት 7” እስከ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት (የወጣቱ ፖለቲከኛ የእስር ማስታወሻ)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 · ዶ/ር ዐቢይ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት አደንቃለሁ
  · የማረምያ ቤት ሰዎች፣ እየተደረገ ያለው ለውጥ የገባቸው አይመስለኝም

     ፍቅረማርያም አስማማው ይባላል፡፡ የ31 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ወደ ፖለቲካው ዓለም ከገባ አምስት አመት እንዳስቆጠረ ይናገራል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ከ“ሠማያዊ” ፓርቲ የጀመረው የፖለቲካ ተሣትፎው፤ እስከ “አርበኞች ግንቦት 7” ፍለጋ አድርሶታል፡፡ የማታ ማታም ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ክስ ሊመሰረትበት ችሏል፡፡ ወጣቱ፤ ከፓርቲ የፖለቲካ ተሣትፎው እስከ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ክስና እስር ድረስ ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አውግቶታል። በምርመራ ወቅት የገጠመውን ሥቃይም ይገልጻል። እንዴት ወደ
ፖለቲካ ህይወት እንደገባ በመግለፅ ፍቅረማርያም እንዲህ ታሪኩን ይጀምራል፡-


   ከ2005 ዓ.ም በፊት ምንም አይነት የፖለቲካ ተሣትፎ አልነበረኝም፡፡ በኋላ ግን የማያቸውና የምሰማቸው ነገሮች፣ ውስጤን ወደ ፖለቲካው ይገፋፉኝ ጀመር፡፡ ዳር ላይ ቆሞ፣ “ፖለቲከኞች ብቁ አይደሉም፤ አይረቡም” እያሉ መተቸት ተገቢ አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ እምነት በመነሣትም፣ እስቲ ፓርቲዎች ውስጥ በመሣተፍ፣ ሁኔታውን ልየው ብዬ በመወሰን፣ ወደ ፓርቲ ፖለቲካ ገባሁ፡፡ በወቅቱ ጠንካራ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ ተብለው የሚታመኑት ፓርቲዎች፡- አንድነት፣ ሠማያዊና መኢአድ ነበሩ፡፡ እኔም ሁሉንም ካጠናሁ በኋላ ሠማያዊ የተሻለ ሆኖ ስላገኘሁት ፓርቲውን ተቀላቀልኩኝ፡፡ ወጣቶችም ስለሆኑ ተግባብቶ ለመስራት ጠቃሚ ነው በሚል ነበር የመረጥኩት፡፡
በሽብር የተፈረጀውን “ግንቦት 7” ለመቀላቀል ጉዞ ጀምረህ ነበር---?
ሠማያዊ ፓርቲ ውስጥ ሆኜ ብዙ ነገሮች እመለከት ነበር፡፡ እነዚህ በግልፅ የሚታዩ፣ ለሠላማዊ ትግል አመቺ ያልሆኑ ሁኔታዎችን እንዴት ነው መቋቋም የሚቻለው፣ የሚለው በውስጤ ይፈጠርብኝ ነበር። በሠላማዊ መንገድ ስንታገል እስር፣ ድብደባና ወከባ ይፈጸማል፡፡ ስርአቱ ይሄን የሚፈፅመው በምርጫ ሣይሆን በደምና በአጥንት የተገነባ መሆኑን ተረዳው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በምርጫ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ እውነተኛ ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል ስረዳ፣ አሁን በስርአቱ ቁንጮ ላይ የተቀመጡ ሰዎች፣ ወጣቶች ሆነው ያደረጉትን ነገር ማድረግ እችላለሁ በሚል፣ “ግንቦት 7”ን ኤርትራ ሄጄ ለመቀላቀል ወሠንኩ፡፡ እነሡ በግንቦት 20 ውስጥ ተደብቀው፣ ሌላ ሰው ግን እነሱ ያደረጉትን ማድረግ እንደማይችል ነበር የሚያስቡት፤ ስለዚህ በዚህች ሃገር ላይ የምፈልገውን ለውጥ ለማግኘት፣ እኔ በመረጥኩት መንገድ መታገል አለብኝ ብዬ ነው ያመንኩት፡፡ እኔ እንኳን ነፃነቱን ባላገኝ፣ልጆቼ የልጅ ልጆቼ፣ ይህ ጭቆና እንዳይጫንባቸው ማድረግ ይገባኛል በሚል ቁርጠኝነት ነው፣ ከዚህ ውሣኔ ላይ የደረስኩት፡፡ የትጥቅ ትግሉ የመጨረሻው አማራጭ በመሆኑ፣ ወስኜ ወደዚያው ጉዞ ጀመርኩ፡፡  
ለእኔ “ግንቦት 7” አሸባሪ የተባለበት ሂደት አሣማኝ አልነበረም፡፡ ድርጅቱ ለኔ የነፃነት ታጋይ ነው፡፡ በዚህ መነሻ ነው የመጨረሻው የመታገያ አማራጭ ያደረግሁት፡፡ በውስጡ የተሠባሠቡት ሰዎች ኢትዮጵያ…ኢትዮጵያ የሚሉ እንጂ አንድም ቀን በኢትዮጵያ ላይ ሞትን ደግሠው አያውቁም፡፡
እንዴት ነበር ወደ ኤርትራ ጉዞ የጀመራችሁት?
ከዚህ ከአዲስ አበባ ነው የተነሣነው፣ በየብስ ትራንስፖርት ባህርዳር …. ጎንደር እያልን እስከተያዝንበት ማይካድራ ድረስ 6 ቀን ነበር የፈጀብን። ጉዟችን በህዝብ ትራንስፖርት ነበር፡፡ ትልቅ ጥንቃቄ ይጠይቅ ስለነበር ነው፣6 ቀን የፈጀብን፡፡ በኋላ ትግራይ ውስጥ የምትገኘው ማይካድራ ስንደርስ፣ በደህንነቶች ተያዝን።
ኤርትራ ለመድረስ ምን ያህል ይቀራችሁ ነበር?
ብዙ አይደለም፡፡ እርግጥ ከማይካድራ እስከ ኤርትራ ልንሄድ የነበረው በእግራችን ነው፡፡ እኛን ለማሻገር የተስማማው ልጅ፣ ቢበዛ የአንድ ሠዓት የእግር መንገድ ርቀት ቢቀረን ነው ብሎን ነበር። እንግዲህ ደህንነቶች የያዙንም የእግር ጉዞውን ለመጀመር በተሰናዳንበት አጋጣሚ ነው፡፡ በወቅቱ ልንያዝ እንደምንችል በመገመታችን፣ ተይዘን ከተከሰስን ሌሎች እንደሚሉት፣ “ወደ ሱዳን ወይም ወደ ሌላ ሃገር ስደት ልንወጣ ነው አንልም፤ በግልፅ “ግንቦት 7”ን ልንቀላቀል ነው እንላለን” ብለን ተነጋግረን ነበር፡፡ ከኔ ጋር በወቅቱ ኢየሩሣሌም ተስፋው፣ ብርሃኑ ተ/ያሬድ እና አሸጋጋሪያችን ልጅ ነበረ፡፡ የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል ተስማምተን ስለነበር፣ ደህንነቶቹ ይዘውን፤ “የት ልትሄዱ ነው?” ሲሉን፤ ኤርትራ አልናቸው፤ “ምን ልታደርጉ?” አሉን፤ “ግንቦት 7ን ልንቀላቀል” አልናቸው፡፡
ከዚያስ ---?
ከተያዝን በኋላ አንድ ሁለት ቀን ሁመራ አካባቢ የሚገኝ የደህንነት ቢሮ አቆዩን፤ ጎንደር ሁለት ቀን አደርን፡፡ ከዚያ አዲስ አበባ አምጥተው፣ ማዕከላዊ አስገቡን፡፡ በወቅቱ እኛ አምነንላቸው ስለነበር፣ ድብደባና ግብግብ አልገጠመንም፡፡ በምርመራ ወቅትም፣ በግልጽ “ግንቦት 7ን ልንቀላቀል ነው” ስላልናቸው፣ ብዙ ጫና አላደረጉብንም፡፡
ፍ/ቤትስ የነበረው ሂደት ምን ይመስላል?
ለፍ/ቤቱም ድርጊቱን መፈፀማችንን አምነናል። “ያው ወጣቶች ነን፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ሠዎች፤ ግፍ ይፈፅማል ያሉትን ስርአት ለማስወገድ የወሠዱትን አማራጭ ነው እኛም የወሠድነው፡፡ እኛም ለሃገራችን፣ ለወገናችንና ለራሣችን የምንፈልገውን ዲሞክራሲያዊ ስርአትና ፍትህ ለማምጣት ስንዘምት ነው የተያዝነው” የሚል ቃል ነው ለፍ/ቤት ያስረዳነው፡፡ ሌላው ሠላማዊ የተባለው አማራጭ፣ የውሸት ስለሆነ፣ የወሠድነው አማራጭ ትክክል ነው ብለን ተናገርን፡፡
ፍ/ቤቱ ክሳችሁን ተከላከሉ ሲለንም፣ የቀድሞ ታጋዮችንና እነ ጀነራል ሣሞራ የኑስን፣ እነ አቶ አባይ ፀሃዬን፣ እነ አቦይ ስብሃትን ነበር በምስክርነት የጠራነው። በሃገሪቱ ያለው ስርአት ያለበትን ደረጃ ከዲሞክራሲና ከፍትህ አንፃር እንዲያስረዱም ምሁራንን አዘጋጅተን ነበር፡፡ ፍ/ቤቱ ለምስክሮቻችን መጥሪያ ከላከልን በኋላ ማረሚያ ቤቱ መጥሪያውን ወሠደብንና እንዳንከላከል ተደርገን ተፈረደብን፡፡ እኔ አራት አመት፣ ብርሃኑ ተ/ያሬድ አምስት አመት፣ ኢየሩሳሌም ተስፋው ደግሞ አራት አመት ከአምስት ወር እንዲሁም ወደ ኤርትራ ሊያሻግረን የነበረው ደሴ አራት አመት ከአምስት ወር ነው የተፈረደብን፡፡
በማረሚያ ቤት ቆይታህ ምን ታዘብክ?
እኔ በማረሚያ ቤት ስቆይ የተረዳሁት፣ ወደ ኤርትራ ተሻግሬ፣ “ግንቦት 7”ን ለመቀላቀል የወሠንኩት ውሣኔ ትክክል እንደነበር ነው፡፡ በፊት ማረሚያ ቤት ሲባል፣ አጥፊዎች ከስህተታቸው ታርመው፣ መልካም ዜጋ ሆነው የሚወጡበት ይመስለኝ ነበር፡፡ ግን በኋላ ማረሚያ ቤቶቻችን የስነ-ምግባር ቦታ አለመሆናቸውን ተረዳሁ፡፡ ሰዎች ይዘረፋሉ፣ ይደበደባሉ፣ ኢ-ሠብአዊ ድርጊት ይፈፀምባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ አስተማሪ ሳይሆን ሰዎችን ወዳልሆነ መንገድ የሚመራ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ለምሣሌ አንድ ጊዜ ግቢ ውስጥ ረብሻ ተነስቶ፣ “ረብሻውን አስነስታችኋል” ተብለን፣ በካቴና አስረውን፣ መሬት ላይ አስተኝተው፣ ሲደበድቡን ነበር የዋሉት፡፡ በዚህ ድብደባ አንድ ልጅ እዚያው ነው ደም የተፋው፡፡ ህክምና ባለማግኘቱም ከ12 ቀናት ቆይታ በኋላ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡ በማረሚያ ቤት ሙስና ህጋዊ ነው የሚመስለው፡፡ ገንዘብ ያለው ጥሩ ሁኔታ ሊገጥመው ይችላል፡፡ በዚያ ላይ “እኛ ይሄን ስርአት ያቆምነው እንዳንተ ነጭ ጤፍ እየበላን አይደለም” በሚል  የስነ ልቦና ጉዳት ይደርስብን ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ ሥርአቱን የበለጠ እንዲጠላ የሚያደርግ ነው። ለፍትህና ለዲሞክራሲ መስፈን የወደቁ ጓዶቻቸውን ረስተው፣ ጭቆናን ነው ለኛ የተረፉት፡፡ ይሄ ያሣዝናል። አሁን እነዚህ ሰዎች ከስህተታቸው ተምረው፣ በሃገሪቱ እየተጀመረ ያለውን የለውጥ ተስፋ ሊደግፉ ይገባል፡፡ መለወጥ አለባቸው፡፡ ህዝቦቿ የሚዋደዱባት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ የሠፈነባት፣ ሁሉም ዜጋ እኩል የሆነባትን ሃገር መገንባት እንድንችል እድል ሊሠጡን ይገባል። የዚህ ለውጥ አጋዥ መሆን ያለባቸውም ለራሣቸው ሲሉ ነው፡፡
በቂሊንጦ ቃጠሎ ከተከሰሱት ውስጥ አንዱ ነበርክ። በእርግጥ በቂሊንጦ ቃጠሎ ተሣትፈሃል?
የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከመቃጠሉ ሁለት ሣምንት በፊት፣ እኔ ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ተልኬ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ግን የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደሮች፤ እኔን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎችን “እስረኛ ታሳምፃላችሁ” በሚል ከሌሎች እስረኞች ለብቻ ነጥለው፣ ዞን 4 የሚባል ቦታ አስረውን ነበር፡፡ በእዚህ ቦታ እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ ዮናታን ተስፋዬ ነበሩ፡፡ በኋላ እኔ ወደ ዝዋይ ተላኩ፡፡ እዚያ ደግሞ እነ ጀነራል አሣምነው ፅጌ የታሠሩበት ልዩ ጥበቃ የሚባል ቦታ ነው የገባሁት፡፡ ዝዋይ ሆኜ ነው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተቃጠለው፡፡ በወቅቱ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የነበረው እስረኛ በእጅጉ የሚበደል በመሆኑ በየጊዜው ያማርር ነበር፡፡ ቃጠሎ ከደረሠ በኋላ በተለያዩ መድረኮች መንግስትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ነገሮች ሲነገሩ፣ መንግስትን ከተጠያቂነት ለማዳን ሁላችንንም ከያለንበት ሠብስበው ነው ክስ ያዘጋጁልን። ለምሣሌ ዶ/ር ፍቅሩ  ማሩ፤ ከቃጠሎ አንድ ቀን በፊት ሣንባቸውን ታመው ሆስፒታል ገብተው ነበር፡፡ ግቢ ውስጥ በስኳር ህመም ስለሚታወቁ፣ ክሡ ሲዘጋጅ፣ “ቸኮሌት ሆን ብለው በልተው ስኳራቸው ሲነሣባቸው ነው ሆስፒታል የገቡት” ብለው ነበር፡፡ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል ነው - ክሣቸው፡፡ ዶክተሩ ግን፣ ሆስፒታል የገቡት በሣንባ ህመም ነበር፡፡
የናንተስ ክስ  ምን ነበር?
ያው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን አቃጥለው፣ በር ላይ በሚጠብቋቸው 60 አውቶቡሶች ተሳፍረው፣ “ግንቦት 7”ን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ፣ ሌሎች ደግሞ በሞያሌ አድርገው አልሸባብን ለመቀላቀል አስበው ነበር በሚል ነው የተከሰሰነው፡፡ 60 አውቶቡስ ይሄን ኦፕሬሽን ለማሣካት እንደተዘጋጀ፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ገንዘብ ለዚህ እንዳወጡ፣ እኛም እንደተደራጀን ተደርጎ ነው ክሡ የቀረበው፡፡ በተጨማሪም የማረሚያ ቤት ሃላፊዎችንና ውስጥ ያሉ በተለምዶ “አስጠጪዎች” የሚባሉ ከማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ጋር ቅርበት ያላቸው ታሣሪዎችን ገድለን ለመውጣት እንዳቀድን ጭምር ነው ክሡ፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ አስጠጪ ከሚባሉት በአደጋው የሞተው አንድ ሠው ነው፡፡ ሌሎቹ በተለያየ ሽብር ክስ የነበረባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ይሄ አሳዛኝ ነበር። የኔ ክስ አንዱ፣ “እኛ ዝዋይን ለማቃጠል ተዘጋጅተናል፤ እናንተ ቂሊንጦን አቃጥሉ” የሚል ደብዳቤ ፅፈሃል የሚል ነበር፡፡ “ይሄ ሲሆን ደግሞ መጀመሪያ አቅደህ ነው ወደ ዝዋይ የሄድከው” የሚል ነገር ነው ያመጡት። የቀረቡብኝ ምስክሮችም፤ “በብዛት ከአማራ ልጆች ጋር ተሰብስቦ ይቆማል፣ መፅሐፍ ያነባል፣ የይስማዕከ ወርቁን ዴርቶጋዳ--” በማለት ነው የመሰከሩት፡፡
በምርመራ ወቅት ምን የተለየ ነገር አጋጠመህ?
በአዲስ አበባ በቆመው የቀይ ሽብር ሠማዕታት መታሠቢያ ሃውልት ላይ “አይደገምም” ተብሎ የተፃፈውን በኛ ላይ ደግመውታል፡፡ የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብት ኮሚሽንም ምርመራ አድርጎ፤ በደሎች መፈፀማቸውን ለፍ/ቤት አቅርቧል፡፡ ከአካላዊ ጥቃቱ ባለፈ ባልዋልንበት ባላደረግነው ነገር፣ ክሡ እጃችን ላይ ሲደርስ፣ የተቃጠለ ሬሣ ፎቶ ስናይ ስነልቦናችን መንፈሣችንን በእጅጉ ነው የተጎዳው፡፡ ጉዳቱ እንዲህ ነው ተብሎ የሚገለፅ አልነበረም፡፡ የብዙ ሰው አዕምሮ ስለተጎዳ ነበር ፍ/ቤት ውስጥ እንደዚያ አይነት ንትርክና እሠጣ ገባ የነበረው፡፡ ከአካላዊ ጉዳቱም በላይ ነው የመንፈስ ጉዳቱ፡፡
ሌሎች ደግሞ በዚህ ተጠርጥራችኋል ተብሎ ጥቅምት 4 ቀን 2009 ዓ.ም ወደ ሸዋ ሮቢት ነው የተላኩት፡፡ በወቅቱ የገባሁ ቀን ማታ አሠቃቂ የስቃይ ጩኸት እሠማ ነበር፡፡ በኋላ እኔንም ወደ ምርመራ ወሠዱኝ፡፡ “ሰው ገድለሃል” አሉኝ፡፡ “ይሄን አላደረግሁም” አልኳቸው…በቃ ገልብጠው አስረው ደበደቡን፡፡ ይሄ አልበቃ ሲላቸው፣ የአንድ እግሬ አውራ ጣት በትንሹ መሬት እንዲነካ አድርገው፣ ሌላውን እግሬን ወደ ጎን ወጥረው፣ ሁለት እጆቼን ወደ ላይ ወጥረው አስረው ሲደበድቡኝ ነበር፡፡ ይሄ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ደብድበውኝ ሲደክማቸው አውርደው አሣረፉኝ፡፡ በኋላ አንድ መርማሪ፣ “ፍቅረ ማሪያም ሞኝ አትሁን፤ ይሄ ከላይ የመጣ ስለሆነ የሚሉህን እሺ ብለህ ተቀበል!” አለኝ፡፡ “ይሄ እኔ የማላምንበት ነው” አልኩ፡፡ ግን በቃ የሆነ ነገር መዝገብ ላይ ጽፈው፣ በማናይበት ሁኔታ፣ እያስፈራሩ ያስፈርሙን ነበር። የሆነውን ነገር ያለ አማራጭ ነው የተቀበልኩት፡፡ እጄ ከአልጋ ጋር ታስሮ ነበር የማድረው፣ ሽንት ቤት፣ ሻወር  ቅንጦት ነበር፡፡ እጆቼ በካቴና ነበር ታስሮ ውሎ የሚያድረው። ለሁለት አጋጥመውም ያስሩናል፡፡ ሽንት ቤት ስንጠቀም፣ አንዱ ቆሞ ነበር የሚያስጠቅመው። በቃ በደንብ ነው ያጠቁን፡፡ እኔ ስለዚህ ነገር ሣወራ በእጅጉ አዝናለሁ፡፡
ክሣችሁ በመጨረሻ እንዴት ተቋረጠ?
የቃጠሎው ክስ የተቋረጠው፣ የውሸት ክስ እንደሆነና እንደማያዋጣቸው ስላወቁ ነው፡፡ በምርመራ ወቅት በሚገርም ሁኔታ “ማንን ገድልሃል” ሲባል ተጠያቂ፣ እከሌን ሲል  “አይ እሡ በህይወት አለ” ይባል ነበር… ይደርስብን ከነበረው ድብደባ ለመዳን፣ በቃ ስሙን የማላውቀውን ሰው ነው የገደልኩ እንድንል ይደረግ ነበር፡፡ ለአስራ አንድ ሰው ሞት ተጠያቂ ነህ ተብሎ የነበረ ልጅ፤ በኋላ ሁለት ሰዎች በህይወት ስለተገኙ ተብሎ፣ ሁለቱ ሰዎች ተቀንሠውለታል፡፡ ይሄን ይመስል ነበር ጉዳያችን፡፡ በዚህ ምርመራ በደረሠብን ድብደባ፣ አብዛኞቹ በእጅጉ ተጎድተው መሄድ፣ መቀመጥ፣ መራመድ አቅቷቸው ነበር፡፡ ለመናገር የሚከብዱ አሠቃቂ በደሎች ናቸው የተፈፀሙብን፡፡ ብልቱ የተኮላሸ፣ እግሩ ከጥቅም ውጪ የሆነ ሁሉ አለ፡፡
አሁን በአገሪቱ ላይ እየታየ ስላለው የለውጥ ነፋስ ምን ትላለህ?
እርግጥ እኛ ከእስር ወጥተናል፤ ግን ዛሬም አብረውን የተከሠሱ ሠዎች ከእስር አልወጡም። ሌሎችም መፈታት ያለባቸው አሉ፡፡ በተረፈ ዶ/ር አብይ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የትግል ውጤት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ የትግል ጥያቄ ተከትለው እየሄዱ ነው ያሉት፡፡
አሁንም ግን በፊት የነበረው የኢህአዴግ ጉልበተኛነት በማረሚያ ቤት አለ፡፡  እውነቱን ለመናገር፣ የማረሚያ ቤት ሰዎች ሃገሪቱ ለይ እየተደረገ ያለው ለውጥ የገባቸው አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር አብይ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄን ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት አደንቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንደ ሃጢያት በሚታይበት ሃገር ላይ እሣቸው ይሄን ሃሣብ አጉልተው መምጣታቸው ጥሩ ነው፡፡ አሁን የሚታየው ነገር ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ፈጣሪ ከረዳን የተሻለ ነገር ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

Read 4231 times