Print this page
Sunday, 10 June 2018 00:00

ጥሩ፡ ሁለተኛ

Written by  ከቃል፡ ኪዳን
Rate this item
(14 votes)

በክረምቱ ዝናብና ቅዝቃዜ ተሸንፎ፤ጋቢ ተከናንቦና ሶፋ ላይ ተኝቶ ፊልም የሚመለከተዉን ጎረምሳ ከደቂቃዎች በፊት ለሙቀት ብሎ የጠጣውን ሻይ መጠጫ ብርጭቆ ከጎኑ ካለች ጠረጴዛ ላይ ተኮፍሶ ተቀምጦ እይታዉን በከፊል ጋርዶታል፡፡ ጎረምሳው ክረምቱ ከፈጠረበት ስንፍና የተነሳ የሻይ ብርጭቆውን ጠጋ ለማድረግ እንኳን ሳይሞክር ከግርዶሽ የተረፈው ስክሪን ላይ አፍጥጦ በሚያየው ፊልም እንደ ሞኝ ብቻውን ይሥቃል፡፡ ድንገት ስልኩ ጠራ፡፡ እሱም እህቱን ተጣራ፡-
‹‹ቤቲ!...ቤቲ!››
‹‹አቤት!›› እህቱ ከምትንጎዳጎድበት ክፍል ወጥታ እየተጣደፈች፣ እሱ ወዳለበት ሳሎን ገባች፡፡ ‹‹ምንድነዉ የሚያስጮህህ እንደዚህ?›› በመሰላቸት ጠየቀችው፡፡
‹‹አንዴ በናትሽ ስልኬን አቀብዪኝ?›› ከክንብንቡ ሳይወጣ በዓይኑ ተለማመጣት፡፡ ልምምጡ ለውጥ እንዳላመጣ ሲረዳ ትንሽ ፈገግታ ለገሳት፡፡ እያጉረመረመች ሄዳ፣ ከቲቪው ማስቀመጫ አጠገብ ካለ ማከፋፈያ ላይ ቻርጅ ላይ የተሰካውን ስልክ ነቅላ አምጥታ፣ ፊት ለፊቱ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጣለት ሄደች።
‹‹ቆይ በዚህ ምሽት ወዴት ልትሄጂ ነው--- እንዲህ ?›› እንዳልሰማችው ጥላው ወደመጣችበት ስትመለስ ግግሩን በእንጥልጥል ተወው፡፡ ከክንብንቡ ላለመውጣት ሲል ጠርቶ ያበቃው ስልኩ እንደገና እስኪጠራ ድረስ አድብቶ ጠበቀ፡፡ ስልኩ ድጋሚ ሲጠራ እንደ ምንም ብሎ አነሳውና ተመለከተው - ደነገጠ፡፡ ከተኛበት ተፈናጥሮ እስኪነሳ ድረስ ደነገጠ፡፡ ጋቢው ከገላው ላይ እንደ ፈንጠጣ እስኪረግፍ ድረስ ደነገጠ፡፡ ገላው የክረምቱን ቅዝቃዜ ድል እስኪነሳና ሰውነቱ ላብ እስኪያመነጭ ድረስ ደነገጠ፡፡ ማህሌት ነበረች፡፡ ቆፈን አቆራምቷቸው የነበሩት ጣቶቹን ላብ እስኪያመነጩ ጭብጥ ዘርጋ ፣ ጭብጥ ዘርጋ አድርጎ ሲያበቃ ስልኩን እንደ አላዲን ፋኖስ በጣቱ ፈትጎ አነሳው፡፡
‹‹አሉ! አቤልሻ›› ከዛኛው ጥግ ደስተኛ የመሰለችና የምሥራች ለመናገር የተዘጋጀች የመሰለች ሴት ድምጽ ተሰማ፡፡
‹‹ሄሎ! እንዴት ነሽ?...ዛሬ እንዴት አስታወስሺኝ?›› ምን ማለት እንዳለበት እርግጠኛ መሆን አልቻለም፡፡ ፍጹም ግራ ተጋባ፡፡ ግራ በመጋባቱ መልሶ ግራ ተጋባ፡፡ ቆይ እንደዛ ስልክ ስቀጠቅጥላት የነበረዉ ምን ላወራት ነበር ታድያ? ሲል አሰበ፡፡
‹‹ስልኬ እኮ ተሠብሮ በምን ልደዉልልህ፡፡ ይኸዉ ዛሬ አዲስ ስልክ ገዝቼ ነዉ የማዋራህ!…..ታድያ እንዴት ነህልኝ አንተ? ሥራ እንዴት ነው?›› ውላቸው የማይጨበጥ ርዕሶችን አከታትላ የወሬውን አቅጣጫ ለመቀየር ሞከረች፡፡
‹‹ሥራ አሪፍ ነዉ፡፡ አንቺስ ህይወት እንዴት ይዞሻል?››
ስልኳ የተሠበረው ከሁለት ሳምንት በፊት ሲሆን ከእሱ ጋር መደዋወል ካቆመችና ስልኩን ማንሳት ካቆመች ወደ ሦስት ወር ይጠጋል፡፡ ሃቁ እንደዛ እንዳልሆነ የሁለቱም ልብ ያውቃል፡፡ ብቻ አሳማኝ የሚመስል ምክንያት ካለ ሃቁ እዚህ ጋ ምን ያደርጋል? ከስንት ጊዜ በኋላ ያውም እራሷ ደውላ ምን አከራከረኝ ብሎ እሱም ወደቀየረችው የወሬ አቅጣጫ ሄደላት፡፡
‹‹ይኸው ያላንተ ህይወት አልሆንልሽ  አለኝ!›› ስታወራ ትጮሀለች፡፡ ጩኸቷ ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ ዓይኗን በጨው አጥባ የመደወል እፍረቷን ለመደበቅ ሳታስበው ከአንደበቷ የምታወጣው ነው፡፡
‹‹እና ክረምቱ እንዴት ይዞሻል?›› ምን አስቦ እንደዛ ብሎ እንደጠየቃት ግራ ገባው፡፡ ምናልባት ክረምት ስለሆነ ይሆናል፡፡ ወይ ደግሞ ክረምቱ ብቸኝነት ፈጥሮባት ይሆናል ብሎ አስቦ ይሆናል - ልክ እንደሱ ካደረጋት፡፡ የክረምት ቀዝቃዛ አየርና አረንጓዴ ገጽታ የፍቅር ስሜት ይፈጥርበት ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉ ጠፍቶ ብርድ፣ብርድ ብቻ ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ ከሥራ ሲመለስ ወይ በእረፍት ቀኑ ሶፋ ላይ በጋቢ ተጠቅልሎ ተኝቶ ኮሜዲ ፊልሞችን ይመለከታል፡፡
‹‹ርዕሱን መለወጥህ ነዉ?››
‹‹ኧረ አይደለም!›› ይበልጥ ግራ ተጋባ፡፡ እንዴት ዛሬ አስታውሳው እንደደወለች ሲጠይቃት ርዕሱን የቀየረችው እሷ ነበርች፡፡ ደግሞ እንኳን ርዕሱን እሱን እራሱ በሌላ የለወጠችዉ እራሷ ናት፡፡ ታድያ ደርሶ ወቃሽ የመሆን አንጀት ከየት አገኘች?
አንድ ቀን ከእንቅልፉ ሲነቃ ደኅንቷን ሊጠይቅ ደወለ- ስልክ አታነሳም፡፡ ተኝታ ይሆናል ብሎ አሰበ። ከዛም መነሳት አለባት ብሎ በገመተው ሰዓታ ደወለ- አሁንም አታነሳም፡፡ ከዛ ደኅንነቷን የሚጠይቅ መልዕክት ጽፎ ስልኳ ላይ ሰደደላት፡፡ መልዕክቱ አለመድረሱን ስልኩ ‹ፔንዲንግ› በሚል ማስታወቂያ አረዳው፡፡ መልሶ ሲደውል ስልኳ ተዘግቷል፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲደውል አደረ፡፡ ስልኳ ዝግ ሆነበት፡፡ ተመሳሳይ ሦስት ቀን ሙሉ እንደዚያ ሆነ፡፡ ያለችበት ድረስ ሄዶ ፈለጋት፡፡ ደህና እንደሆነች ግን እንደሌለች በቤተሰቦቿ ተነገረው። የሚያውቃቸው ጓደኞቿ ጋር ደወለ፡፡ ለሷ ያላቸውን ጓደኝነት ለማሳየት ሲሉ ምንም እንደማያውቁና ሰሞኑን እንዳላገኟት እየማሉ ነገሩት፡፡ ሰብአዊነት ተሰምቷቸው እና ለእሱ አዝነዉ ደግሞ ካሁን በኋላ እንዳይጨነቅና እራሱን እንዲጠብቅ አሳሰቡት፡፡
በሳምንቱ የተዘጋዉ ስልኳ ተከፈተ፡፡ ግን ሲደውልላት አይነሳም፡፡ መሽቶ እስኪነጋ ደጋግሞ ደወለ፡፡ በመጨረሻም ትዕግስቱ ፍሬ አፍርቶ ስልኩ ተነሳ፡፡ እየተስገበገበ፤
‹‹ሄሎ›› አለ
‹‹ሄሎ›› አለው አንድ ወንድ ስልኩን አንስቶ በጎርናና ድምጽ፡፡ ፍሬ ከመልካም ዛፍ ላይ የተገኘ ፍሬ አልነበረም፡፡
‹‹ሄሎ ኧ…..›› ማህሌትን አቅርብልኝ ሊለው አስቦ ስሟ ጠፋበት፡፡ ለግማሽ ደቂቃ ያህል ካሰበ በኋላ ስሟን ሲያስታውስ፤
‹‹ኧ…ማህሌትን ፈልጌ ነበር፡፡ የማህሌት ስልክ አይደለም?›› አለ የሞት ሞቱን፡፡
‹‹የለችም!›› ብሎት ስልኩን ዘጋው ባለጎርናና ድምጹ ሰውዬ፡፡
ከዚህ የስልክ ምልልስ በኋላ አቤል በጭንቀት ታመመ፡፡ ህመሙ ሲበረታና ሥራዉ ላይ ክፍተት እየፈጠረ ሲመጣ የገረጣ ፊቱን እና የደከመ አካሉን ይዞ የዓመት እረፍት እንዲወጣ አለቃው አዘዘው፡፡ እሱም ምን እንደሆነ የሚጠይቀው በመብዛቱና በመሰላቸቱ እቤቱ ሆኖ ብቻዉን ለመጨነቅናለማልቀስ ይችል ዘንድ እረፍት ሞልቶ ወጣ፡፡
የመጀመርያ የእረፍት ቀኑን ስለሷ በማሰብና በማልቀስ በአግባቡ አሳለፈው፡፡ ሌሊት እንኳን በህልሙ የጎረምሳው ጎርናና ድምጽ ድሮ የሚፈራቸው፣ ጆሮ ይቆርጣሉ የሚባሉት ሽማግሌ አናጺ ጎረቤቱን ስጋ ለብሶ ሲያቃዠዉ አደረ፡፡ በነጋታዉ ጨጓራውን ታመመ። እህቱ ‹ወይ ፍቅር እያለ ሰዉ ያወራል…› እያለች እየዘፈነችና እየሣቀች ደግፋ ሃኪም ጋር ወሰደችው፡፡ ሃኪሙ ጨጓራው አሲድ እየረጨ እንደሆነ በመንገር፣ አሲዱን ያቆመዋል ወይ ያለዝበዋል ብሎ ያሰበውን መድኃኒት አዘዘለት፡፡ ‹አትጨነቅ› የሚል ትእዛዝ ይሁን ምክር ውሉ ያለየ ሀሳብም ሰጠው፡፡
በሀኪሙ ምክርም ባይሆን በቀን ብዛት ነገሩን እየተቀበለውና  ቀልቡን እየገዛ መጣ፡፡ በል፣ በል ሲለው ግን ባታነሳለትም አልፎ፣ አልፎ ይደውልላታል። አላነሳ እያለችው ደጋግሞ ከደወለላት ደግሞ እሷ ስልኳን ትዘጋዋለች፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ግን ስልኳ ጭራሹኑ ተዘጋ፡፡ ምናልባት ባለ ጎርናና ድምጹ ሰዉዬ እኔ እንዳልደውልላት ቁጥር አስቀይሯት ይሆናል ሲል አሰበና፣ እሱም መደወሉን እርግፍ አድርጎ ተወዉ፡፡
‹‹ለማንኛዉም ስልኬ ሲከፈት አስቀድሜ ልደዉልልህ ብዬ ነዉ የደወልኩልህ!›› አላመናትም ግን ደስ አለው፡፡ ዋናው መደወሏ እንጂ ለምን የአገሩን ሰዉ በሙሉ አዳርሳ ስትጨርስ አትደዉልለትም፡፡
‹‹የምር?›› አላት ድንገት፡፡ ተቆጣች፡፡
‹‹ያንተ እኮ ችግር ይሄ ነዉ፡፡ ለምንድነዉ ግን የማታምነኝ? ለማንኛዉም እቤት ስገባ እደዉልልህ እና እናወራለን›› ቻዎ እንኳን ሳትለዉ ስልኩን ዘጋች፡፡
ስልኩ ከተዘጋ በኋላ ወደ ላይ ተወርውሮ፣ ጭቃ ላይ በቁሙ ተሰክቶ ወዴትም መውደቅ እንዳልቻለ የቁማር ሳንቲም ግራ ተጋባ፡፡ ምን ሊሰማዉ እንደሚገባ ሊያዉቅ አልቻለም፡፡ ቤቲ ትንጎዳጎድበት ከነበረዉ ክፍል ወጥታ እሱ ወዳለበት ሳሎን ገባች፡፡ አገባቧ ወደ ውጪ ለመዉጣት እንደሆነ ያሳብቅባታል፡፡ አገባቧ ባያስታዉቅ እንኳን አለባበሷ ያስታዉቃል፡፡ መቼም ሰዉ ከጓዳ ወደ ሳሎን ለመግባት ብሎ እንዲህ አይለብስም፡፡
‹‹ምን ሆንክ ደግሞ? እንዲህ ለመሆን ነዉ እንዴ ስልኬን አቀብዪኝ ያልከኝ?...ይኸዉልህ ምስኪን ወንድሜ፤ በሰላም ለመኖር ከፈለክ እኔን አትዘዘኝ፡፡እግዚአብሔር ታናናሾች በመላላክ ተሰላችተዉ እንባቸዉን ሲያፈሱ ይመለከትና…››
‹‹ማህሌት ደወለች!›› አቋረጣት፡፡
‹‹ምን? ምናባቷ  ፈልጋ ነዉ የደወለችዉ?›› መጥታ አጠገቡ ቁጭ አለችና እጆቹን ጨብጣ ያዘቻቸዉ፡፡ ማህሌትን እንደዛ በማለቷ ሊናደድና ሊናገራት የነበረዉ ልጅ፣ የእህቱ እጆች ሲይዙት፤
‹‹አላውቅም›› አለ ለስለስ ብሎ፡፡ ጭለማና ክረምት - ምንም ነገር ግልጽ ሊሆንለት አልቻለም። እጆቹን ከእህቱ አስለቅቆ አንገቱን ደፍቶ፣ እራሱን በእጆቹ እስኪይዝ ድረስ አዘነ፡፡ ከሁሉም አስበልጣ የምትወደው ወንድሟ ማዘኑን ስታይ እህቱ ልቧ ተነካ፡፡
‹‹ይኸውልህ ወንድሜ!...አይ ኖው ማሂን በጣም ትወዳታለህ፡፡ ግን ያሳለፍከውን ጊዜ አትርሳ። ላደረገችህ ነገር ምንም አይነት ‹ኤክስኪዩዝ› ብታቀርብልህ እንዳትቀበላት›› አቤል እህቱ የምትለዉ ነገር ሃቅ እንዳለበት ቢያዉቅም፣ ሊቀበላት ግን አልፈለገም፡፡ ሃቅ ከማህሌት ይበልጣል እንዴ?
‹‹ግን ቢያንስ ምክንያቷ ምን እንደሆነ እንኳን መስማት አለብኝ!››
‹‹ምክንያቷንም አልነገረችህም እንዴ?...ቆይ ታድያ ምን ብላ ነዉ የደወለችልህ?›› ቤቲ ሀዘኗን ትታ ወደማሽሟጠጥ ገባች፡፡
‹‹ስልኳ ተሰብሮ እንደነበርና ዛሬ አዲስ ስልክ እንደያዘች ለመጀመርያ እኔ ጋ እንደደወለችልኝ ነገረችኝ!››
ቤቲ ከት ብላ ሣቀችና፤‹‹እና አመንካት ሞኙ ወንድሜ?......እኔ እንዳንተ አይነት ሞኝ አይቼ አላዉቅም፡፡ ምን አይነት ሰዉ ነህ ግን?›› አለችዉ፣ ከተቀመጠችበት ተነስታ ቁልቁል እያየችዉ፡፡
‹‹አመንኳት አልሁሽ እንዴ? ብቻ በኋላ እደውልልሀለው ብላኛለች፡፡ የዛኔ ምን እንደምትልኝ እሰማለሁ፡፡››
‹‹ለምን እኔ ምን ልትልህ እንደምትችል አልነግርህም?...›› ድምጿን ሙዝዝ አድርጋ፤ ‹‹አቤልዬ የኔ ሞኝ፤ እኔ ባንተ ፍቅር ዓይኔ ታውሮ ስልክ ስትደውልልኝ ቁጥርህ ዓይታየኝም ነበር። ጆሮዎቼም ባንተ ‹የእወድሻለሁ› ጋጋታ ደንቁረዉ ስልኬ ሲጠራ አይሰማኝም ነበር፡፡ ደግሞ ማየትና መስማት ስላልቻልሁኝ፣ ያ ድምጹ ጎርናናዉ ሰዉዬ አንተን መስሎኝ ከእሱ ጋር ሦስት ወር ሙሉ በፍቅር አሳለፍሁ። ከዛ በኋላ ባንተ እንባና ለቅሶ ማየትና መስማት ስለቻልኩሁ ይኸዉ ተመልሼ መጣሁልህ!፡፡ አቤሎ የኔ ፍቅር! የኔ ሞኝ›› ነዉ የምትልህ፡፡›› አለችዉ፡፡
‹‹ቆይ ምክንያቷን መስማት የለብኝም እንዴ? እንዴት የአንድን ሰዉ ምክንያት ሳትሰሚ ልትፈርጂበት ትችያለሽ? ጭንቅላትሽ አይሠራም?››
‹‹ያንተ ጭንቅላት ነው እንጂ የማይሠራው!  ቆይ ደግሞ ከመች ጀምሮ ነው የሰዉ ምክንያት መስማት የጀመርከው? እኔ እንኳን ድንገት ታክሲ አጥቼ አምሽቼ ከመጣሁ ዝም ብለህ ትጮኻለህ እንጂ ለምን አምሽቼ እንደመጣሁ ምክንያቴን ጠይቀህ ታውቃለህ?›› ጮኸችበት፡፡
‹‹ቆይ እሺ በዚህ ምሽት ወዴት ልትሄጂ ነዉ እንዲህ የለባበሺዉ?››
‹‹ማህሌት ጋ!›› ወደ በሩ መንገድ ጀመረች፡፡
‹‹እሺ ቆይ እራትስ ምንድን ነው የምንበላው?›› ተነስቶ ተከተላት፡፡ ዞረችና አጠገቡ ደርሳ በስንዝር እርቀት ቆመች፡፡ ከዛም ጣቷን ቀስራ ልቡን እየጠነቆለች፤
‹‹ስማ ወንድ ሁን እስኪ! እኔ ብዙ እህቶች አሉኝ ወንድም ነው የምፈልገው፡፡ ቁጭ ብለህ በረሃብ ሆድህ እየጮኸ፣ የእሷን ስልክ ከምትጠብቅ የሆነ ነገር ሥራና ብላ!››
‹‹ቤቲ አልገባሽም እኮ! እኔ…››
‹‹አንተ ነህ ያልገባህ›› አለችው ጣቷን ከደረቱ ላይ አንስታ፣ ጭንቅላቱን እየነቆረችው፤ ‹‹ማህሌት ካንተ የተሻለ ሰው አግኝታ ነው የሄደችው፡፡ ትታህና ፍጹም እረስታህ ነበር፡፡ ይህን አምነህ ልትቀበል ይገባል። ወንድሜ ስልክህን እንኳን አንስታህ ‹አግብቻለዉ አግባ› የማለት ሀዘኔታ እንኳን አልነበራትም፡፡ ያሰበችው አልሳካ ሲላት ደግሞ እያለቀሰ ወደሚጠብቃት ደነዙ ወንድሜ ተመለሰች፡፡ አንተ ጥሩ ሁለተኛዋ ነህ፡፡……ስታስበው ባለ ጎርናናዉ ድምጹ ሰዉዬ፣ እሷ እንደምትፈልገው ቢሆንላት ኖሮ ተመልሳ ወደ አንተ ትመጣ ነበር? ልንገርህ? አትመጣም - ይህን ወደድክም ጠላህም አምነህ ተቀበል፡፡ ወንድሜ ተመልሶ የመጣን ሁሉ እንኳን ደህና መጣህ እያልክ መቀበል የለብህም!››
‹‹ኧረ ባክሽ እንደዛ አይደለም…›› ሊያቋርጣት ሞከረ፡፡ በዓይኗ እንዳያቋርጣት ተቆጣቺዉ፡-
‹‹አቤሎ አመንክም አላመንክም አንተ ለሷ ሙሉ ሰው  አይደለህም፡፡ እሷ ብቻ የሚሰማት የሆነ የሚጎድልህ ነገር አለ፡፡ በርግጥ እኔም ብሆን ጭንቅላት የሚጎድልህ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ሙሉ እንደሆንክ የምታስበዋ እስክትመጣ አርፈህ ሶፋህ ላይ ተኝተህ ፊልምህን ተመለከት፡፡ ማህሌት ተመልሳ እንደመጣች ተመልሳ መብረሯ አይቀርም፡፡ አንተ ማረፊያዋ እንጂ መድረሻዋ አይደለህም! ስለዚህ የእህትነቴን የምትሰማኝ ከሆነ ትቅርብህ፡፡ ካለበለዚያ እራስህን ደግፈህ ወደ ሃኪም ቤት መሄዱንም ተለማመድ›› ፊቱን በስሱ በጥፊ መታችውና እየተውረገረገች በቆመበት ጥላው በሩን ከፍታ ወጣች፡፡
‹‹ቆይ ወዴት ነው የምትሄጂዉ?›› ወጥታ በሩን ዘጋች፡፡ በእሱም በእሷም ላይ ያለ አድሎ ዘጋች፡፡ ለውጡ እሱ ፊቱ ላይ እስዋ ደግሞ ጀርባዋ ላይ መዘጋቱ ብቻ ነዉ፡፡
‹‹እሺ በቃ በርገር ይዘሽልኝ ነኝ፡፡ ‹ኤክስትራ ቺዝ› ይኑረዉ እሺ፡፡ደግሞ አምሽተሽ ነይ አሉሽ!›› ተስፋ በመቁረጥ ወደ ሶፋዉ ተመለሰ፡፡
‹‹እኔ ምንም ምግብ ይዤልህ አልመጣም፡፡ ካገኘሁ ጭንቅላት ገዝቼልህ እመጣለሁ! ‹ኤክስትራ ፕሮሰሰር› ያለዉ፡፡ይልቅ ስልክህ ላይ ከማፍጠጥና ሌላ ችግር ከመጠበቅ ተነስተህ እራትህን ሠርተህ ብላ፡፡›› የቤቲ ድምጽ እንደ አስማተኛ የተዘጋውን በር አልፎ ገብቶ ተናገረው፡፡
አቤሎ የእህቱ ንግግር ሃቅ እንዳለው ቢሰማውም ማመን አልፈለገም፡፡ ሃቅ ምንድነው? ሃቅ ደስታን የማይሰጥ ከሆነ ምን ይሠራል? ወደ ሶፋው ተመልሶ ሄዶ የሻይ ብርጭቆውን ወደ ጎን አስጠጋና ስልኩን አስቀመጠ፡፡ ከዛም እንደ ቅድሙ ጋቢውን  ተከናንቦ ተኛና አንዴ ቲቪውን አንዴ ስልኩን እያፈራረቀ ማየት ጀመረ፡፡ ስልኩን ለማየት ዓይኑን ከቴሌቭዢኑ በሚያነሳባቸው ክፍልፋይ ሰከንዶችና የሚያመልጡት የፊልሙ ትእይንቶች ድምር፣ ቅድም በሻይ ብርጭቆ ተጋርዶ የማያየቸው ከነበሩት ጉራጅ ትእይንቶች ድምር ጋር እኩል ሆኑ፡፡

Read 3829 times