Print this page
Sunday, 06 May 2012 15:00

በሱፐር ሂሮዎች ቡድን የተሰራው “አቬንጀርስ” በገቢ ተሳክቶለታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ታዋቂ የአሜሪካ የኮሚክ መፅሃፍት ጀብደኛ ገፀባህርያትን ባሰባሰበ ቡድን የተሰራው “ዘ አቬንጀርስ” እንደተጠበቀው በገቢ ስኬታማ እየሆነ መምጣቱን ዘ ሆሊውድ ሪፖርተርስ አስታወቀ፡፡ ፊልሙ ለእይታ በበቃ ሁለት ሳምንት ውስጥ በቀረበባቸው 39 አገራት በአጠቃላይ 208 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገባት ችሏል፡፡ ፊልሙ በሰሜን አሜሪካ ዛሬና ነገ ለመጀመርያ ጊዜ ለተመልካች የሚቀርብ ሲሆን የቦክስ ኦፊስ የገበያ ትንተና እንደሚገልፀው “ዘ አቬንጀርስ” እና ተከታታይ የፊልም ስራዎች በመላው ዓለም እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኙ ተገምቷል፡፡

በማርቭል ስቱዲዮ የተሰራው “ዘ አቬንጀርስ” 220 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ፊልሙን ዲያሬክት ያደረገው ጄስ ዌይደን ነው፡፡ በፊልሙ ላይ ቡድን ከመሰረቱት ታዋቂ ጀብደኛ ገፀባህርያት መካከል በቀዳሚነት የ”ካፒቴን አሜሪካ” ፊልም ተዋናይ ክሪስ ኢቫንስ፤ የ”አይረንማን” ሮበርት ዳውኒንግ ጁኒዬር፤ የ”ቶር” ክሪስ ሄስሞስ፤ የ”ሃልክ” ማርክ ሩፋሎ፤ የ”ሃውካይ” ዠረሚ ራነር እንዲሁም የ “ዘ ብላክ ዊዶው” ስካርሌት ጆሃንሰን ተሳትፈዋል፡፡ በተጨማሪም ሳሙኤል ጃክሰን፣ ጅዌኔትዝ ፓልትሮው እና ቶም ሂድልስተንም በፊልሙ ላይ የሰሩ ሌሎች ዝነኛ ተዋናዮች ናቸው፡፡ማርቭል ስቱዲዮስ “ዘ አቬንጀርስ”ን ለመስራት ስድስት አመት የፈጀበት ሲሆን ከዚህ ቀደም ኩባንያው የሰራቸውን የሱፐር ሂሮ ፊልሞች በማዋሃድ በ”ዘ አቬንጀርስ” ያስመዘገበው ስኬት ተከታታይ ፊልሞችን ለመስራት አነሳስቶታል ተብሏል፡፡ ማርቭል ስቱዲዮ በሚያሳትማቸው የኮሚክ መፅሃፍት ላይ የተሰሩትና የ”አቬንጀርስ”ን ስድስት ዋና ዋና ገፀባህርያት የሚተውኑት ጀብደኞች በተናጠል በተሰሩባቸው ፊልሞች በዓለም ዙርያ ከ2.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገብተዋል፡፡ እነዚህ ጀብደኛ ገፀባህርያትን በቡድን የያዘ ራሱን የቻለ ኮሚክ መፅሃፍ በስቱዲዮው የተዘጋጀ ሲሆን “ዘ አቬንጀርስ” በሚል በመጀመርያ ክፍል የተሰራው ፊልም ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በኮሚክ መፅሃፍት ላይ የተሰሩ ፊልሞች የ2012 አጋማሽ ገበያን ይቆጣጠራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይ በ”ዘ አቬንጀርስ” እና በ”ዘ ዳርክ ናይት ራይዝስ” መካከል ከፍተኛ ፉክክር እንደሚፈጠር ተገምቷል፡፡ “ቦክስ ኦፊስ ባይ ነምበርስ” በድረገፁ እንዳመለከተው፤ በኮሚክ መፅሃፍት ውስጥ ያሉ ገፀባህርያትን በመጠቀም የተሰሩ ፊልሞች ከ5 ቢ. 345 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝተዋል፡፡

 

 

Read 3458 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 15:02