Sunday, 17 June 2018 00:00

ብሔራዊ ቴአትርና ብሔራዊ የባህል ማዕከል አዳዲስ ዳይሬክተር አገኙ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

ረ/ፕ ነብዩ ባዬ ለብሔራዊ ቴአትር አቶ ተስፋዬ ሽመልስ ለብሔራዊ ባህል ማዕከል ተሹመዋል
                 
    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል አዳዲስ ዳይሬክተሮችን አገኘ፡፡ በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ዲን በመሆን ለረጅም ጊዜ ሲያገለግሉ የነበሩት ረዳት ፕ/ር ነብዩ ባዬ ለብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተርነት እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርን ለረጅም ዓመታት የመሩት አቶ ተስፋዬ ሽመልስ ለብሔራዊ ባህል ማዕከልነት ዳይሬክተርነት ተሹመዋል፡፡
ሹመቱ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደምብ ቁጥር 2574/2003 አንቀፅ 7(1) መሰረት የተካሄደና የሹመቱ ደብዳቤ በኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ የፀደቀ መሆኑም ታውቋል፡፡
ረዳት ፕ/ር ነብዩ ባዬ በሹመቱ ምን እንደተሰማቸው ተጠይቀው ሲመልሱ “ቴአትር የጀመርኩት በ12 ዓመቴ ነው፡፡ ህይወቴ ከሙያው ጋር የተቆራኘ ነው” ካሉ በኋላ፣ በየትኛውም ዓለም ያለ የቴአትር ባለሙያ የመጨረሻ ግቡ የአገሩን ብሔራዊ ቴአትር ማገልገል ነው እኔም የአገሬን ብሔራዊ ቴአትር እንዳገለግል በመመረጤ ደስታና ክብር ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡  
“አቶ ተስፋዬ ሽመልስ በበኩላቸው የተሾምኩበት ቦታ እንደ ባለሙያ ትልቅ ቦታ ነው” ያሉ ሲሆን በስራ ቆይታዬ በሌሎች አለማት ያየኋቸውን የባህል ማዕከላት አገሬ ላይ እውን ለማድረግ እሰራለሁ ብለዋል፡፡
አክለውም ቦታው የአንድን አገር ባህል ለማሳደግ ታሪካችንን ለማጉላት እና ያሉንን ጠንካራና የጋራ እሴቶች ለማጉላት ብዙ የሚያሰራ በመሆኑ በቦታው ላይ በመሾሜ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡

Read 7111 times