Sunday, 17 June 2018 00:00

“ጠ/ሚሩ ስልጣናቸውን ለድርድር አቅርበው ነው ያስፈቱኝ”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(22 votes)

በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የ“አርበኞች ግንቦት 7” ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ስልጣናቸውን ለድርድር አቅርበው፣ ከእስር እንዳስፈቷቸው ሰሞኑን ተናገሩ፡፡
ከ4 ዓመታት እስር በኋላ ባለፈው ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም ከማረሚያ ቤት የተለቀቁት የሞት ፍርደኛው አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፤ ከቢቢሲ “ሃርድ ቶክ” አዘጋጇ ዘይናብ በደዊ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አንዳርጋቸው ፅጌን ልቀቁ፤ አለበለዚያ እኔ ስልጣኔን እለቃለሁ” በማለት፤ ሥልጣናቸውን ለድርድር አቅርበው፣ ከእስር እንዳስፈቷቸው አስረድተዋል፡፡
ከእስር ከተፈቱ በኋላም ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ለቢቢሲ የገለፁት አቶ አንዳርጋቸው፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኔን ለማስፈታት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ተገንዝቤያለሁ” ብለዋል፡፡
ዶ/ር አብይ በኔ ከእስር የመፈታት ጉዳይ፣ ከድርጅታቸው አመራሮች ተቃውሞ  እንደገጠማቸው ተረድቻለሁ ያሉት አቶ አንዳርጋቸው፤ በመጨረሻም  “የማትፈቱት ከሆነ ስልጣኔን እለቃለሁ” ማለታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደነገሯቸው ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየወሰዷቸው ያሉ የፖለቲካ ማሻሻያዎች፤ የሚበረታቱና ሊደገፉ የሚገባቸው ናቸው ብለዋል - አቶ አንዳርጋቸው ከቢቢሲ “ሃርድ ቶክ” ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ።

Read 11160 times