Print this page
Sunday, 17 June 2018 00:00

አሮጌ ውሻን አዲስ ዘዴ ማስተማር አይቻልም፤ የቆቅም ለማዳ የለውም

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ አሮጌ ውሻ፤ ከጌታው ጋር የመጨረሻ የመለያያ ውይይት ያደርጋሉ፡፡
ጌታው - እንግዲህ ውሻ ሆይ! በህይወታችን በጣም ረዥም መንገድ ተጉዘናል፡፡ አያሌ ውጣ ውረዶችንም አልፈናል፡፡ የእናንተ የውሾች ሞቅ ያለው ኑሮ የጉልበታችሁ ዘመን ላይ ያለው፤ ወርቃማ ጊዜ ነው፡፡ ሰውም እንደ እንስሳ ወርቃማ ጊዜ አለው፡፡
ውሻው - አዎን ጌታዬ! ለማንም ቢሆን ጉልበት የሚሰማው ዕድሜ፣ ጥበብ የሚሰማው ዕድሜና አዳዲስ ዘዴ ለመፍጠር ህዋሳቱ የነቁበት የተሐድሶ ወቅቱ ነው!
ጌታው - አዎን፡፡ ውሻ ልዩ ልዩ ለሰው ጠቃሚ ባህሪያት አሉት፡፡
ውሻ - አዎን ቤት ይጠብቃል፡፡
ጌታው - ታማኝ ነው፡፡
ውሻ - የጌታውን ወዳጅና ጠላት ይለያል፡፡
ጌታው - ባለቤቱ እንቅልፋም ቢሆን እንኳ እሱ ንቁ ነው፡፡
ውሻ - ብቻ ምንም ውለታ ይዋል፤ ምንም፤ በመጨረሻ ጌታው የበቃው ዕለት ያባርረዋል፡፡
ጌታው - ሁሉም ጌታ፤ እንደዚያ ላያደርግ ይችላል፡፡
ውሻ - አይመስለኝም፡፡ የጌታ ሁሉ ጠባይ፣ ደረጃው ይለያያል እንጂ ያው ነው!
ጌታው - ይልቅ ሌላ ስለ ውሻ መልካም ጠባይ ያላነሳነው ካለ አስታውሰኝ!
ውሻ - እ … አንድ በጣም ትልቅ ፋይዳ፣ ከውሻ ባህሪ ውስጥ ተጠቃሽ፣ አስታዋሽነቱ ነው፡፡ የሠራውን ያስታውሳል፡፡ የተሰራበትንም ያስታውሳል፡፡ ስለዚህ ውሻ ከሰው ይልቅ ሙሉ ነው!!
ይህ የመጨረሻው አባባል ህሊናውን እየጠቀጠቀው፣ ጌታዬው ውሻውን አሰናበተው!
ከዓመታት በኋላ እንድ ሌባ በፖሊስ ተይዞ፣ ወደ ጌትየው ቤት መጣ፡፡ ጌትየው የዚያን ሌባ መምጣት ጨርሶ አያስታውስም፡፡ ትዝ ያለው ነገር ውሻው በማስታወስ ጉዳይ እንደማይታማ የነገረው የመጨረሻ ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ፈልጉልኝ አለ፡፡ በእግር በፈረስ ያስፈልገው ጀመር፡፡ በመካያው ተገኘ ውሻው!! ውሻው ዝርዝሩን አወቀው፡፡
ሌባው - “የዛን ሌሊት ይሄ ውሻ ባይኖር፣ ጌትዬውን ገድዬ፣ ቤቱን ዘርፌ ልሄድ ነበር ዕቅዴ! ዕድሜ ለዚህ ያረጀ ውሻ ፈርቼ ሄድኩ! አንተን ሰውዬውን ሳይሆን የውሻህን ግርማ ሞገስ ነበር የፈራሁት!!” አለ፡፡
ጌትዬውም፤
“ለካ ከመጮህም፣ ከመናከስም በላይ ግርማ ሞገስ የበለጠ ልምድ ነው!” ብሎ፤ “ውሻዬን ግርማ ሞገሱን አክብሬ ማስቀመጥ አለብኝ!” ብሎ ወሰነ!!
*   *   *
ሰራተኛ መቅጠርና ማባረር (hire and fire) በካፒታሊስት ስርዓት እጅግ የተለመደ ክስተት ነው! መታሰብ ያለበት ግን የሥራ ልምድ ጥያቄ ነው! የለመደውና ሥራውን የሚያውቀው ለቅቆ መሄዱ፤ አዲሱ፣ ጉልበተኛው ሰራተኛ አዲስ ደም ይዞ ወደ ሥርዓቱ ሲገባ (New blood - injection እንዲሉ)፤ የቆየውን የነባሩን ልምድ ስለሚያጣ ስራው ጎዶሎነት የማያጣው አይሆንም፡፡ ትልቁ ቁምነገር አዲሱን አስለማጅ ማስፈለጉን ልብ ማለትና የሂያጁን ልምድ መቅሰሚያ ዘዴ ማስፈለጉን ማስተዋል ላይ ነው፡፡ አገር የተገነባችውና ለዘመናት የቢሮ ሥርዓት ሀዲዷን ጠብቃ እስከ ዛሬ የዘለቀችው አበው ጠዋት ባሰመሩት መስመር ላይ እየተጓዘች፣ እንከንና ግድፈቷን እያረመች ነው፡፡ ነገም ተረካቢው ትውልድ ኃላፊነቱን በወጉ እያስተናገደ ከመራመድ ሌላ ብዙ አማራጭ የለውም! የዚህ ታላቅ አደራ ተረካቢ ደግሞ ወጣቱ ትውልድ ነው፡፡ ሳይቸኩል፣ በፍቅር በተስፋና በጉጉት፣ እያሰበ ለውጥን ማሰብ፣ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ መፍታትት የፈርጀ ብዙ ችግር አገር ተረካቢ መሆኑን አውቆ በልክ በልኩ፣ በቅጥ በቅጡ፣ ጥሬውን ማብሰል፣ ብስሉን በፍትሃዊ መንገድ ማከፋፈልና መምራት ይጠበቅበታል፡፡ መደማመጥ፣ መወያየት፣ አንጋፋን ማክበር፣ ከባለሙያ መማር፣ በሥነ ምግባር መታነፅ ዋና ዋና ተግባራት ናቸው፡፡
አገር መውደድ ከዘፈን፣ ከግጥም፣ ከስሜታዊነትና ከትኩሳት ባሻገር፤ የጠለቀና የመጠቀ ደርዝ መጨበጥን እንደሚጠብቅ እናስተውል፡፡ አገርን ማገልገል ቀናነትንና ብስለትን፣ ሀቀኝነትንና ከቤተሰብ እስከ ህብረተሰብ ያሉትን እርከኖች ጠንቅቆ የማወቅን ፅናት ይጠይቃል፡፡ የሚከተለውን ግጥም ልብ እንበል፡-
            እሳት ያልገባው ልብ
            ሚሚዬን ጠየኳት፡-
            “ሁል ጊዜ አረንጓዴ፣ ለምለም ፍቅር አለ
            ትወጃለሽ ሚሚ፣ ይህን የመሰለ?”
            ሚሚዬ እንዲህ አለች
            ሳስቃ መለሰች፡-
            “የምን እኝኝ ነው፣ ዕድሜ ልክ ካንድ ሰው
            ቋሚ ፍቅር ይቅር፣ ለብ ለብ እናርገው!”
            ፍቅሯ ለብ ለብ
            ትምህርቷ ለብ ለብ
            ዕውቀቷ ለብል
            ነገር - ዓለሟ ግልብ፤
            እንዴት ይበስል ይሆን
            እሳት ያልገባው ልብ!?
                                                            (ነ.መ.)
ኢትዮያ እሳት የገባው ልብ ያለው፣ አዲስ ኃይል ያስፈልጋታል፡፡ የዕውቀት ኃይል ወሳኝ ረሀቧ ነው፡፡ ጤና የጧት ማታ ህመሟ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉልበቷ እንደ አዲስ መፈተሽ ያለበት ነው፡፡ ፍትሐዊ ውስጠ ነገሯ፤ መመርመር ያሻዋል፡፡ ሁሉም እሳት የገባው ልብ ይኖራቸው ዘንድ ግድ ይላል፡፡ አንድ ነገር ግን ዛሬን ከትላንቱ ጥያቄ ይለየዋል፡፡ ሰጪና ተሰጪ የለም፡፡ ሁሉም ድርሻዬ ምንድን ነው ብሎ የሚገነባው ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና ፍትሐዊ ሥርዓት መሆን አለበት፡፡ መጠንጠኛው የሀገር ፍቅር መሆን አለበት፡፡  
ደራሲ ዘውዴ ረታ፤ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት” በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለፁት፤
“ለኢትዮጵያ ኃላፊነትን ለሚቀበለው መሪ፣ በኢትዮጵያዊነት ግዳጄ ለማገልገል የምቀርበውም፤ ለሀገራችን ዕድገት፣ ለህዝባችን ደህንነት የሚጥር፣ የሚያስብና የሚሰራ ሆኖ ሳገኘው ነው እንጂ፤ በውርስ ንጉሥ፣ በዘሩ መስፍን ነው ብዬ አይደለም፡፡ የለፈው ታሪኬ በትክክል እንዳሳየው፤ ልጅ እያሱ አጉል ጠባያቸውን አሻሽለው ኢትዮጵያን ከነክብሯ በሰላም እንዲመሯት ብዙ ደክሜ ሳይሆንልኝ ሲቀር፤ ለለውጡ ከሸዋ መኳንንት ጋር የተሰለፍኩት፤ ኢትዮጵያን የምወድ፣ ለኢትዮጵያ የቆምኩ በመሆኔ ብቻ ነው፡፡ ዛሬም እኔና ጓደኞቼ የምንመካውም ሆነ የምንኮራው በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ስለሆነ፤ ኢትዮጵያንና ህዝቧን በቅንነት ከማገልገል ሌላ የሚያረካን ነገር አይኖርም” የሚል የሀገር መሪ ለኢትዮጵያ መድሕን ይሆናል፡፡ ያም ሆኖ ህብረተ ሱታፌን የሚያምን ህዝብ ሲኖር ነው! ሕብረተ ሱታፌን የሚቀበል የለውጥ አራማጅ ሲኖር ነው!
ይህን ዓይነት አስተሳሰብ የማይጥማቸው በርካታ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ወደፊት የሚራመድን ሁሉ የኋሊት የሚጎትቱ፣ በየሥርዓተ ለውጡ ይከሰታሉ፡፡ ፈረንጆች “You can’t teach an old dog a new trick” የሚሉት ወደው አይደለም፡፡ አሮጌ ውሻን አዲስ ዘዴ ማስተማር አዳጋች ነው እንደማለት ነው፡፡ አንድም ደግሞ ምንም ዓይነት ስልጠና ብንሰጥ፣ ምንም ዓይነት የመግራት ችሎታ ቢኖረን፣ ከባህሪ የተጣባን ነገር ማስወገድና ማልመድ ከባድ ነው፡፡ የቆቅ ለማዳ የለውም የሚለው ተረት ቢውጠነጠን፤ ብዙ ገፀ ባህሪያትን እንድንመረምር ያግዘናል፡፡ ህብረተሰባችን፣ ቡድኖች፣ ፓርቲዎችና ማህበራት ውስጣቸው ተከፋፍቶ ሲታይ፣ የቤት ጣጣ እንዳለባቸው እንገነዘባለን! ቆም ብለን እናስብ! ቆም ብለን እንምከር! የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬውኑ ልናያት እንጣር!

Read 6929 times
Administrator

Latest from Administrator