Sunday, 17 June 2018 00:00

የሀያ አምስት ብር ዋጋው ስንት ነው!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)


    ኢድ ሙባረክ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የእራት ሰዓት ነው፡፡ ምግቡ ቀርቧል፡፡ ባል ነካ፣ ነካ እያደረገ ይጎርሳል፡፡ ሚስት ሰረቅ አድርጋ ታየዋለች፡፡
እሷ፡— አትበላም እንዴ!
እሱ፡— እየበላሁ ነው፡፡
እሷ፡— ምን እየበላሀ ነው…ወይ በደንብ ጉረስ፣ ወይ ተወው! ምግቡን ቀልቡን አታሳጣው እንጂ!
እሱ፡— አሁን ይሄ ምግብ ምን ቀልብ አለው!
እሷ፡— ደግሞ ምን ሆነ ልትል ነው! እ…ከዚህ በላይ ምን ይሁንልህ?!
እሱ፡— ምናለ እንደው ቢያንስ፣ ቢያንስ ለጣእም እንኳን ትንሽ ቲማቲም ጣል ብታደርጊበት! ለዚህ የአምስት ኮከብ ሆቴል ሼፍ ማምጣት አለብኝ!?
እሷ፡— ቲማቲም!  ቲማቲም ጣል ይደረግልህ! በኪሎ ሀያ አምስት ብር የገባ ቲማቲም ሹሮ ላይ ጣል ይደረግልህ!
እሱ፡— ሙያው ያላቸው እኮ ሹሮውን ዶሮ የሚያስንቅ ነው የሚያደርጉት፡፡
እሷ፡— አንተ ግን ይሄ ሰሞን ምግብ በቀረበ ቁጥር አራስ ልጅ ይመስል የምትነጫነጨው ምን ይሁን ነው! ትበላለህ ብላ፣ ካልፈለግህም የራስሀ ጉዳይ፡፡
እሱ፡— የራስህ ጉዳይ መባባል ደረጃ ደረስን!
እሷ፡— አዎ ደረስን፣ እና፣ ምን ይሁን! ምግብም ምኑም ላይ ዋጋውን ያስጨመረችው እሷ ናት አሉህ እንዴ! ለእኔ ስትል ለምን አራት ኪሎ ሄደህ ሰልፍ አትወጣም፡፡ የሌለውን ከየት አምጥቼ ልሥራልህ፤ነው ወይስ ገጠር ሀያ ጋሻ የቲማቲም እርሻ አላት አሉህ!
እሱ፡— መናገር ቀላል ነው፣ በገንፎሽና በመኮሮኒሽ መሀል ልዩነት… (እስካሁን ድረስ እኮ “አንቺ የምትሠሪውን መኮሮኒ ጣልያኖች ራሳቸው አይሠሩትም፣” ሲል ነው የከረመው፡፡)
እሷ፡— ነው አንዴ! አክስቴ፣ አጎቴ ምናምኔ አንቺ የምትሠሪው ምግብ አምሯቸዋል እያልክ ስታግተለትላቸው አልነበር እንዴ የከረምከው! አሁን ድንገት ገልቱ ሆንኩብህ!
እሱ፡— እሱማ ያኔ ነው… ገልቱነትሽ…
እሷ፡— ምን! ጭራሽ ገልቱ አልከኝና አረፍከው!
እሱ፡— አንቺን ለማለት አይደለም …እኔ ያልኩት በዘዴ ብታብቃቂው…
እሷ፡— ዘዴ! በዘዴ ላብቃቃው! ገልቱ ከሆንኩ በየትኛው እውቀቴ ነው የማብቃቃው፡፡
እሱ፡— አንቺ ደግሞ ነገር አታክርሪ…
የምር አያሳዝንም!…የምንናቆርበት ነገር ያነሰን ይመስል፣ ቋጥኝ የሚያካክሉ ቃላት የምንወራወርባቸው ጉዳዮች ያነሱን ይመስል… የሰሞኑ የኑክሌር ሀይል ያለው የኑሮ መወደድ ደግሞ ሌላ አይነት የቤት ውስጥ ጦር ግንባር ከፍቶብናል፡፡ እንደዛ ባይሆን ኖሮ ማሬ፣ ወለላዬ ምናምን እያለ ማድነቂያ ቃላት ሲያጥረው የከረመ ሰው፤ አጋሩን ጭራሽ “ገልቱ” ባላለ ነበር፡፡
እና የምለው… እውነትስ ይሄን ያሀል የምርት እጥረት ገጥሞን ነው እንዴ! እውነትስ ይሄን ያህል የአገሩ አፈር ሁሉ አጠፋሪስ እንኳን አላበቅል ብሎ ነው እንዴ!
የአፈር ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ…
እንቁራሪቱ መሬቱን ጫር፣ ጫር ያደርግና ትንሽ አፈር ቃም ያደርጋል፡፡ አንዲት አተኩራ ስታየው የነበረች ወፍ፡-
“ለምንድነው እንዲህ የከሳኸው?” ትለዋለች፡፡ እንቁራሪቱም… 
“የከሳሁት ሁልጊዜ ስለሚርበኝ ነው” ይላታል፡፡
“ግን አፈሩን ብቻ አይደል እንዴ የምትመገበው! ለምን እስኪበቃህ አትቅመውም?” ትለዋለች፡፡ እንቁራሪቱም ምን ቢል ጥሩ ነው፤ “ምክንያቱም ከእለታት አንድ ቀን አፈርም ሊያልቅ ይችላል” አለ አሉ፡፡
“ስማ…ቲማቲም ስጠኝ!”
“ስንት ኪሎ?” (ስንት ኪሎ! ሰውየው ምን ነካው! ስንት ኪሎ የሚለው፣ በኪሎና በፈረሱላ ሊሸጥልኝ ነው እንዴ!)
“አንድ ኪሎ”
“ሀያ አምስት ብር”
“ይቅርታ አንድ ኪሎ ነው እኮ ያልኩህ…”
“ሀያ አምስት!” ብሎ ይቆጣል፡፡ ቀና ብሎ አያያችሁም እኮ!  ልክ አቁማዳ ይዛችሁ “ተዘከሩኝ!” ምናምን ያላችሁ ነው የሚያስመስለው፡፡ ትእቢት አይሉት፣ የገበያ ስትራቴጂ አይሉት፣ “ምድረ ቺስታ ምን ያደርቀኛል!” አይነት መጠየፍ አይሉት!… ገንዘብ ይዛችሁ ሄዳችሁለት እንኳን… አለ አይደል… “እነሱን ፊት ለፊት በማየት ለሚደርስብህ ጦስ ሁሉ ተጠያቂው አንተ ራስህ ነህ” የተባለ ይመስል ጀርባ አዙሮ ሲያናግራችሁ በእርግጥም ያበሳጫል፡፡ ደግሞ እኮ ብሩ ሲጠፋ የወጪ መብዛት፡፡ ለነገሩማ ሁሉ ነገር ሲጠም፣ ኪስ ሲሳሳ ጺም እንኳን በቀን ሁለት ጊዜ ያድጋል፡፡ ጢሙ ጫካ የመሰለ ሰው ከበዛባችሁ የእነማርክስ ውቃቤ ሰፈሮበት ሳይሆን ምላጭ በመጥፋቱ ሊሆን ይችላል፡፡
እኔ የምለው…… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አሁን፣ አሁን ‘የአንዳንድ’… (ይቅርታ) ‘የብዙ’ ነጋዴዎች ባህሪይ ይገርማል፡፡ እኛ በየዓመቱ ሐምሌ ምናምን በመጣ ቁጥር ነጋዴዎቹ… “ያልሠራሁትን ግብር ጫኑብኝ፣” “በመንፈቅ የማላገኘውን የቀን ገቢ ብለው ገመቱብኝ” ምናምን አያሉ ሲበሳጩ ስናዝንላቸው ኖረን የለም እንዴ! “እዚህ አገር ነግዶ መብላት እንኳን ላይቻል ነው!” እያልን አብረን አምተን የለ እንዴ!
እና… እኛ ለእነሱ እንደምናዝነው ለእኛስ የማያዝኑትሳ! “እነሱም ማውጣት የሚገባቸውን ያውጡ፣ እኔም ማትረፍ የሚገባኝን ያህል ብቻ ላትርፍ” ማለት ማንን ገደለ! ስሙኝማ…የእኛን ሞራል እርዳታ ማጣት ቀላል አይደለም፡፡ “እንኳን እኔ፣ ዘር ማንዘሬ ከፍሎ የማይጨርሰው ግብር ጫኑብኝ” ሲባል… “ምናለ ሠርተው ልጆቻቸውን ቢያሳድጉበት!” የምንለው ሲቀር አሪፍ አይሆንም፡፡ እንደውም እኛ የዛኛው ወገን ደጋፊ ልንሆን እንችላለን፡፡ “ይቺ ምን አላት! ኸረ ደህና አድርገው የዚህን እጥፍ ግብር በጣሉበት!” ምናምን አይነት እርግማን ሊዳዳን ይችላል፡፡ በቀጥታም ተነገረ፣ በሆድም ተባለ…የሀዝብ እርግማን ደግሞ ጥሩ አይደለም፡፡ እንደውም እኮ ለ‘አፍ እላፊ’ በቀረበ አነጋገር… የዛኛው ዘመን የጣት አሻራ አይነት የነበሩትን  “አቆርቋዥ…” “አሻጥረኛ…” “ስግብግብ…” ምናምን የሚባሉት የዛኛው ዘመን ቃላት በስማቸው ፊት ልንጨምር እንችላለን፡፡
እኔ የምለው… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የማይሆን ነገር፣ የማይሆን ቦታ ላይ የምንናገር ሰዎች ቁጥራችን “በነጥብ ምናምን ፐርሰንት” ያደገ አይመስላችሁም! አለ አይደል…አንዳንድ ጊዜ ፈንገጥ ማለት እንደመሰልጠን፣ ‘እንደልብ መናገር’ ደግሞ ዘመናዊነት የሚመስለን አለን፡፡
“ባለቤትሽ ደህና ነው?”
“አዎ፣ ደህና ነው፡፡”
“ማለቴ፣ እንዴት ናችሁ?”
“እንዴት ናችሁ ማለት…”
“ማለቴ፣ መሀላችሁ ሰላም ነው?”
“በጣም፣ ግን ለምን ጠየቅኸኝ?”
“አይ መጠጥ እንዲቀንስ ብትነግሪው…” (ኸረ ረጋ!) ሚስት፤ ሰው መሀል እንዲህ ያለ ነገር ቢነግራት የሚሰማትን አስቡት!
ስሙኝማ… የምር ግን…ለምሳሌ ሰርግ ላይ “የመቃብር እጮኛዬ ጠብቂኝ እመጣለሁ” ብሎ የሚዘፍን ከተፋ ዘፋኝ ይታያችሁማ! “አዳልጦት ነው…” አይባል፣ “አደናቅፎት ነው…” አይባል ነገር፡፡ የሙዚቃ ባንዱን ፈልጎ ያመጣው ባልየው ከሆነ፣ ትዳሩ እዛው ባይፈርስ እንኳን እሷዬዋ ሊሰማት የሚችለውን አስቡት! ወይ ደግሞ ሙት ዓመት ሄዶ ቀበቶው እስኪጠበው ድረስ ከበላ በኋላ “ከዓመት ዓመት ያድርሰን…” የሚለውን አስቡት፡፡ ይሄ ነገር አንድ ጊዜ በእርግጥም ሆኗል፡፡ ልጆቹ ግን ሆነ ብለው ያደረጉት ሳይሆን እንደዛ የሚባል መስሏቸው ነው፡፡ “እንኳን ማርያም ማረችሽ!” ለማለት ሄዶ… “አንቺ ማሺን ይመስል ዝም ብለሽ በአናት በአናቱ ትፈለፍያለሽ እንዴ!” የሚለውን አስቡት፡፡ ምን (በአርትኦት የወጣ ቃል) አገባው! ደግሞስ ካልጠፋ ቃል “ትፈለፍያለሽ…” ምናምን ብሎ አማርኛ ምን ማለት ነው!
እናማ…ጎማውም፣ ፊኛውም፣ ምናምኑም ‘ጧ’ ባለ ቁጥር መደንበራችን አንሶ…ኪሎ ቲማቲም “ሃያ አምስት ብር…” አንድ እንቁላል “ስድስት ብር…” አንድ ቀሺም ሻማ “ዘጠኝ ብር” እያላችሁ ‘ጧ’ በሌለበት አታስደንግጡና!
የሀያ አምስት ብር ዋጋው ስንት ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2661 times