Sunday, 17 June 2018 00:00

“የሰላምን አስፈላጊነት ከኢሮብ ህዝብ በላይ የሚያውቅ ያለም”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

· “ኢሮብ ከሥርዓቱ ያልተጠቀመ ማህበረሰብ ነው”
 · የትግራይ ጠቅላይ ግዛት አካልና ህዝቡ ኢትዮጵያዊ ነው
 · በኤርትራውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አለን
 · ህዝብ የኖረበት ቦታ፣ ከደሙና ህልውናው የተቆራኘ ነው
 · ማህበረሰቡ ከኢህአፓ ጋር ተያይዞ ብዙ ይነሳ ነበር


   ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1990 ዓ.ም ከድንበር ጉዳይ ጋር በተያያዘ በ100ሺዎች የሚገመት ህይወት የጠፋበት አስከፊ ጦርነት ማድረጋቸው ሳያንስ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ስምምነት በአልጀርስ መፈራረማቸውን ተከትሎ 20 ዓመታት በሁለቱም አገራት ላይ ውጥረት ሰፍኖ፣ ጦርነትም ሰላምም በሌለበት ድባብ ውስጥ መዝለቃቸው ይታወቃል፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን አዲስ ነገር ተከሰተ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፤ ለሰላምና ለወንድማማችነት ሲባል የአልጀርሱን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበለው መወሰኑን አስታወቀ፡፡ ውሳኔውን ተከትሎም በባድመ ድንበርና አካባቢው ላይ የሚገኘው የኢሮብ ማህበረሰብ፣ ውሳኔውን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል፡፡ የአልጀርሱን ስምምነት መተግበር፤ “በአገርም ሆነ በማህበረሰቡ ህልውና ላይ አደጋን የጋረጠ ነው” ይላሉ ውሳኔውን የሚቃወሙ - የኢሮብ ነዋሪዎች፡፡
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የማህበረሰቡ ተወላጅ ምሁራን፣ ባለሀብቶችና ግለሰቦችም ነገ ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ ውሳኔውን በመቃወም በመዲናዋ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ከሆኑት ከአቶ ፀሐይዬ አለማ ካህሳይ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አደርጋለች፡፡

    እስኪ ራሰዎትን በደንብ ያስተዋውቁን …
ትውልድና እድገቴ በምስራቅ ትግራይ፣ በኢሮብ ልዩ ወረዳ፣ መሀል ኢሮብ አሊቴና አካባቢ ነው፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም ያጠናቀቅኩት በትውልድ ቦታዬ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ወደ አዲግራት ነው የሄድኩት፡፡ ከአዲግራት አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ከዚያም ለትምህርት ወደ ውጭ ሄጄ ነበር፡፡
እስቲ ስለ ማህበረሰቡ አኗኗር፣ ባህል፣ ታሪክ እንዲሁም ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ስላለው መስተጋብር ያጫውቱኝ …
እዛ አካባቢ ያለው የኢሮብ ማህበረሰብ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተከባብሮና ተሳስቦ የሚኖር ነው፡፡ የራሱን ማንነት የገነባና በኢትዮጵያ ህገ መንግስት እውቅና ያለው ብሄረሰብ ነው። ቁጥሩ ላለፉት 20 ዓመታት 30 ሺህ እየተባለ ነው የቆየው፡፡ አንዳንዴ እንደውም የህዝቡ ቁጥር እንዴት አይጨምርም የሚባል ጥያቄ ይነሳል፤ ግን 30 ሺህ ላይ ነው የቆመው፡፡ እንደኔ ማህበረሰቡ ትኩረት ተሰጥቶት በአግባቡ ባለመቆጠሩ እንጂ ከዚያም በላይ ይሆናል። ባህሉን በተመለከተ ከላይ ከትግሬዎች፣ ከታች ደግሞ ከሙስሊሞች እንዲሁም ከኤርትራዊያን ጋርም የሚወራረስ ባህል አለው፡፡ ሆኖም የራሱን ኢሮብኛ ቋንቋ የሚናገር ሲሆን የዘር ግንዱ ከሙስሊሞችም ሰናአፌ ከሚገኙ ኤርትራዊያንም ከላይ ደግሞ ከአዲግራትና ከዛላንበሳ ህዝቦች ጋር የተዋለደ ነው፡፡ ቋንቋው ከአፋር ሳሆ ጋር ይቀራረባል፡፡ ህዝቡ እውነትን አክባሪ ነው፡፡ ነገሮችን እያመዛዘነ፣ የወደፊቱን አርቆ እያስተዋለ፣ የቆየ ሢሆን በአጠቃላይ ብልህ ማህበረሰብ ነው፡፡
ብዙ ሰው ኢሮብን ማወቅ የጀመረው ከአልጀርሱ ስምምነት በኋላ ይመስለኛል፡፡ ከዚያ በፊት ብዙም ሲነሳ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ተሳስቻለሁ?
 ይሄ ለእኔ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ብዙ አይነገርለትም፤ አልተነገረለትም፡፡ እንዲነገርለትም አይፈለግም፤ በተለይ በዚህ ስርዓት፡፡ እንደውም የኢሮብ ማንነት በ60ዎቹ የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ በተለይ ከኢህአፓ ጋር ተያይዞ ብዙ ይነሳ ነበር፡፡ በተሳትፎውም ደረጃ በተለይ ኢህአፓ ውስጥ ከፍተኛ ነበር፡፡ በአመራር ደረጃ እንኳን ብዙ የኢሮብ ልጆች ነበሩ፡፡ አሲምባ ራሱ የኢህአፓ ዋና ማዕከል ከነበሩት ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ አሲምባ ኢሮብ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ እንግዲህ በዛን ወቅት የኢህአፓ ዋና ማዕከላት ከነበሩት ውስጥ አሲምባ፣ ሰንገዳ፣ ኢንጋልና ካልሃሳይ የተባሉት ዋና የኢህአፓ የጦር ካምፖች ነበሩ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የህውሓት ታጋዮችም ወራአትሌና አይጋ በሚባል ስፍራ ላይ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር፡፡ ይህ አካባቢ እንደውም ዴሞክራሲን ቀድሞ የተለማመደና ተግባራዊ ያደረገ አካባቢ ነው፡፡
እንዴት? እስኪ ያብራሩት …
በዛን ወቅት የህውሓት ታጋዮች ይመጣሉ፤ አላማቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡ ኢህአፓዎችም ይመጣሉ፤ አላማቸውን በግልፅ ያስተዋውቃሉ፡፡ ይህን ተራ በተራ እንሰማለን፡፡ በገበያ፣ በቀብርና በተለያዩ ህዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች እየመጡ፣ አላማቸውን ሲያስተዋውቁ፣ ህዝቡ ያለ ተፅዕኖ ይሰማል። የሚፈልገውን ሃሳብ ይወስዳል፣ የማይፈልገውን ይተዋል፡፡ ለምሳሌ በወቅቱ የኢሮብ ትልልቅ ሰዎች “ኢህአፓዎች ሃይማኖት የላቸውም፤ እግዚአብሔርን አያውቁም” እያሉ ሲወቅሷቸውና ሲጠሏቸው ልጅም ብሆን አስታውሳለሁ፡፡ ኢሮቦች ከኢህአፓ የሚጠሉት እምነት የለውም በሚል ብቻ ነው፡፡ በወቅቱ ስለ ማርክሲዝም ሌኒንዝም እንዲሁም ስለ ሌሎች ርዕዮተ ዓለማት ብዙ ማወቅና መገንዘብ ችለናል፡፡ ስለ አብዮት በዘፈንም በግጥምም፣ ከዚህኛውም ከዚያኛውም ወገን ስንሰማ ነው ያደግነው፡፡ በአጠቃላይ የ60ዎቹ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፓርቲዎች፤ ኢሮብን እንደ ስደተኛ ካምፕ ተጠቅመውባታል፡፡ ህዝብ ሁሉንም ተቀብሏል። በተለይ ኢህአፓን በደንብ ተቀብሏል፡፡ ህውሃትንም የሚቀበሉ ነበሩ፡፡ ሌላው አገር በቀል የግጭት አፈታትን በራሱ ያዳበረና የተገበረ ማህበረሰብም ነው፡፡ ለምሳሌ ህውሓትና ኢህአፓዎች እንዳይጣሉ፣ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን ይጠቀም ነበር፡፡ የኢህአፓ አባሎች ኢሮብ ወይም አንድ ቤት ውስጥ ካሉና ህውሓቶች ድንገት ሲመጡ ካዩ፣ ኢህአፓዎችን ቀስ አድርገው፣ በጓሮ በር አስወጥተው፣ በመሸኘት፣ ግጭትና ተኩስ እንዳይከፍቱ ያደርጉ ነበር፡፡
ከካቶሊክ ሚሲዮናዊያን መግባት ጋር በተያያዘ፣ በአገራችን ዘመናዊ ትምህርት በመጀመር ኢሮብ ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው?
በጣም ጥሩ! በኢሮብ ዘመናዊ ትምህርት የተጀመረው በ1835 ዓ.ም እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ አሊቴና ያለው ቤተ መፃሕፍት በጣም ጥንታዊ ነው፡፡ የሙዚቃ መሳሪያዎችም ነበሩት፣ የጥንት ስነ ፅሁፎችም ያሉበት አካባቢ ነው፡፡ አንድን ትምህርት ዘመናዊ የሚያደርገውን ጂኦግራፊ፣ ቋንቋ፣ ታሪክ ይማሩ ነበረ፡፡ ቋንቋ የውጭም የአገር ውስጥም ተምረው እንደነበር ይነገራል፡፡ ለምሳሌ ላቲን ይማሩ ነበር፡፡ አማርኛ በደንብ ይማሩና ይናገራሉ፡፡ እንግሊዝኛም እንዲሁ፡፡ የግዕዝም የሂሳብም ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ስኮላርሺፕ አግኝተው ወደ ውጭ የሄዱት ከዚያ ት/ቤት ነው፡፡
ቀደም ሲል “በዚህ ስርዓት ስለ ኢሮብ ብዙ አይነገርም፤ እንዲነገርም አይፈለግም” … ያሉኝ ለምንድን ነው?
ባለፉት 20 ዓመታት በተነሳው የድንበር ጦርነት አካባቢው በጣም ጉዳት የደረሰበት ነው፡፡ ብዙ ጦር የሰፈረበት፣ ለብዙ መፈናቀል የተዳረገና ከኢሮብ ወጥቶ ዛላንበሳ አዲግራትና በየበረሃው ለመኖር የተገደደ ማህበረሰብ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ህልውናው አደጋ ላይ ወድቆ ትኩረት ስለተነፈገው አይነሳም፡፡ መሰረተ ልማት አልተስፋፋለትም፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ ልዩ ወረዳነቱ፣ አስፓልት እንኳን የለውም፡፡ መንግስት ባወጣው ስትራቴጂ፤ ወረዳዎችን ከዋና ዋና ከተሞች ጋር የማገናኘት አሰራር አለው፡፡ ይህ ማህበረሰብ ግን ምንም አይነት ጠቀሜታ ከስርዓቱ ከስርዓቱ አላገኘም፡፡ መንገድ ከሌለ መሰረተ ልማት ከሌለ፣ ወደዚያ የሚሄድ ኢንቨስትመንት ቱሪዝምና መሰል ነገር አይኖርም፡፡ መሰረተ ልማት አልተስፋፋም ማለት ደግሞ አካባቢው እንዲነሳ አይፈለግም ማለት ነው፡፡ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ የመጠጥ ውሃ የለም፤ ውሃ ከታች ቀድቶ ለመመለስ ቀጥ ያለ ዳገት፣ 40 እና 45 ደቂቃ መውጣት ግድ የሚልበት አካባቢ ነው፡፡
ታዲያ ማህበረሰቡ የሚያስታውሰው ከሌለ፣ ራሱን በራሱ ለማስተዋወቅ መጣር የለበትም? የአካባቢው ተወላጅ ባለሀብቶችስ አካባቢያቸውን አይጎበኙም? አያስተዋውቁም? ማለት ነው?
እንደነገርኩሽ፤ ህዝቡ በትግል፣ ራስን በማሸነፍ ሩጫ የተጠመደ ነው፡፡ ተምሮ ለመለወጥ፣ በንግድ ለማደግ … ብቻ ራስን የማዳን ስራ ላይ የተጠመደ ማህበረሰብ ነው፡፡ ጉዳዩ የህልውና (የሰርቫይቫል) ነው፡፡ ኑሮውን ለማሸነፍ ከመጣር አልፎ ራሱን ፕሮሞት ማድረግና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ለማድረግ አቅሙ የተገደበ ነው፡፡ እንዳልኩሽ የመሰረተ ልማቱ ነገር ባለመሟላቱ፣ ኢንቨስት የማድረጉ ነገር ብዙ ትኩረት አይስብም፡፡ ተወላጅ ባለሀብቶችም ፀጥታው አስተማማኝ ባልሆነ አካባቢ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ብቻ ብዙ ጭንቅና ችግር የተሸከመ ማህበረሰብ ነው። ከስርዓቱ ምንም ያልተጠቀመ ማህበረሰብ (አካባቢ) ነው፡፡
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ፣ የአልጀርሱ ስምምነትን በተመለከተ ያስተላለፈው ውሳኔን በተመለከተ ምን ይላሉ?
ይሄ ከባድና የማልስማማበት ውሳኔ ነው፡፡ አንደኛ፤ ባድመን አሳልፈን ከሰጠን በኋላ ኤርትራ ሰላም ትሰጠናለች ወይ? የሚለው ጥያቄ፤ የምንጊዜም ጥያቄ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ አንድን አገር ቆርሶ መስጠት፣ ከሉአላዊነት አኳያስ እንዴት ነው የሚታየው፡፡ በነገራችን ላይ ኤርትራ የ“ዱርዬ” የ“ወመኔ” ስራ ሰርታ ነው የወረረችን፤ ከእነ ቅጣቷ መሬታችንን ለራሳችን ማድረግ ሲገባን፣ ለወረረን አገር መሬት መስጠት፣ ከስጋዬ ተቆርሶ እንደተሰጠ ነው የምቆጥረው፡፡ በጣም ያምማል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የመላው ኢትዮጵያዊ አጥንት ተከስክሷል፤ ደም ፈስሳል፡፡ 70 ሺህና ከዚያ በላይ ወገን ገብረናል፡፡ የእነዚህ አርበኞች ውለታስ ይሄ ነው? እኔ በበኩሌ ታሪካዊ ክህደት ነው የምለው፡፡ በዚያ ወረራ 152 የኢሮብ ሰዎች ታፍነው ወደ ኤርትራ ከሄዱ በኋላ የገቡበት አይታወቅም፡፡
የአልጀርሱ ስምምነት ቢተገበር ትልቁ አደጋ የሚሉት ምንድነው?
የኢሮብ ህዝብ በተለያዩ ችግሮች የተበታተነና የተመናመነ ህዝብ ነው፡፡ ውሳኔው ደግሞ ህዝቡን ለሁለት ይከፍለዋል፡፡ ግማሽ ኤርትራ፣ ግማሽ ኢትዮጵያ፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው …  እንደ ኢሮብ ህዝቡን ለሁለት ከፍሎ፣ የመነጣጠልና ጭራሽ ኢሮብን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት የተቃጣ ነው፡፡ በዘመነ መሳፍንት፣ በደርግም ጊዜ፣ በኃይለ ሥላሴ ጊዜም ሆነ በፌዴሬሽን ጊዜ ኤርትራ ነበረች፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን፣ ታሪክ ሲሄድና ሲመጣ፣ የኢሮብ ምድር የኤርትራ ሆኖ አያውቅም፡፡ የትግራይ ጠቅላይ ግዛት፣ አካልና ህዝቡም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ኤርትራ የኢትዮጵያ በነበረችበት ጊዜ ኢሮብ የትግራይ አካል ሆኖ ነው የኖረው፡፡ የኢሮብ ህዝብ የህልውና ጉዳይ በአሁኑ ወቅት ምርጫ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ ለምርጫም የሚቀርብ አይደለም። ኢሮብ ኢትዮጵያ ነው፤ ህዝቡም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የምርጫ ጉዳይ ቢሆን እኮ ህዝቡ ወደ ኤርትራ ቢሄድ የተሻለ ጥቅም ሊያገኝ ይችላል፡፡
ከምን አንፃር ነው ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው?
ከባህር ወደብም በይው ከግብይትና መሰል ጉዳዮች አንፃር ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፤ ግን ህዝቡ አገሩን ማንነቱን ማጣት የማይፈልግ በመሆኑ፣ የኢሮብ ጉዳይ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የሰላምን አስፈላጊነት ካነሳን፣ መሬቱን የሰጠነው ሰላም ለማስፈን ነው የሚለው ምክንያት አይዋጥልኝም፡፡ የሰላምን አስፈላጊነት ከኢሮብ ህዝብ በላይ የሚያውቅ አለ ብዬ አላምንም፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ከጦርነቱ በፊት በፍፁም ፍቅር፣ በፍፁም መከባበርና ሰላም የኖረ ህዝብ ነው፡፡ እኛም ኢሮቦች፤ በኤርትራዊያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለን ህዝብ ነን፡፡ እኛም እንዲሁ እንወዳቸዋለን፡፡
አንድ ነገር ልንገርሽ በኤርትራ እዛ ማዶ አንድ ኤርትራዊ ሲሞት፣ የኢሮብ ህዝብ ወዲህ ማዶ ትልቅ ተራራ ላይ ነጭ ለብሶ ይቆማል፡፡ ነጭ የሚለብሰው ለባለለቅሶው ጎልቶ እንዲታይ ነው፡፡ እናም የቀብር ሥርዓቱ እስኪፈፀም ይቆማል፡፡ ሲያልቅ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ይሄ ማለት ቀብር ላይ ተገኝቷል፤ ቀብሯል ማለት ነው፤ መሻገርና መሄድ አይችልማ፡፡ እነሱም ይህንን ያደርጋሉ፤ እስኪ ምን ያህል የምናሳዝን፣ ሁለት ህዝቦች እንደሆንን ተመልከቺ …
ምንም እንኳን ወራሪዋ ኤርትራ ብትሆንም በመጨረሻ መሬቱ ግን የተወሰነው ለኤርትራ ነው ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም የተፈራረመው ይሄንኑ ነው፤ አይደለም እንዴ?
ባድመን ለመስጠት አይደለም የተስማሙት፤ አለም በሚፈርደው እንስማማለን ነው ያሉት፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ አገር ተስማሙ ሲባል አልስማማም አይባልም፡፡
እና በእርስዎ አመለካከት ምን ተወስኖ ነው ኢትዮጵያ የተስማማችው ይላሉ?
ዓለም ይሄን የመሰለ አስቀያሚ ፍርድ ይወሰናል ብለው ላያስቡ ይችላሉ፡፡
እንዴት አይገምቱም? ጂኢፖለቲክሱን ያውቁታል … ሁኔታውን ያውቁታል … የጦርነቱን መጀመሪያና መጨረሻ ያውቁታል … ሌላው ቀርቶ ዓለም ምን ሊወስን እንደሚችል መገመታቸው አይቀርም…?
ለማንኛውም እኔ እያልኩ ያልኩት “እናደራድራችሁ” ሲሏቸው፤ “እሺ አደራድሩን” አሉ። “እንደምትደራደሩ እና በውሳኔው እንደምትስማሙ ፈርሙ” ተባሉ፡፡ ይሄ ውጤት እንደሚመጣ ቀድመው ላያውቁ ይችላሉ ነው ያልኩት፡፡ በኋላ ውሳኔው ተወሰነ፡፡ ውሳኔው ከተወሰነ በኋላ የኢትዮጵያ መልስ ምን ነበር፡፡ ውሳኔውን በመርህ ደረጃ እንቀበለዋለን ግን ብዙ ችግር አለው፤ አምስት የመፍትሄ ሀሳብ እንሰጣለን፤ በዛ መሰረት ይፈፀም ተባለ፡፡
አምስቱ የመፍትሄ ሀሳቦች ምንድናቸው?
ከአምስቱ አንዱን ነው የማውቀው፡፡ አንዱ ምን መሰለሽ … ውሳኔውን መሬት ላይ አውርደን እንየው ተባለ፤ ምክንያቱም ውሳኔው ቤቶችን ሳይቀር ለሁለት የከፈለ፣ አንድን ህዝብ ለሁለት የከፈለ፤ ነገር ግን ጠረጴዛ ላይ ብቻ የተወሰነ ነው፤ ስለዚህ መሬት ላይ ይውረድ ተባለ፡፡ መሆን ያለበትም ይሄ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ አገር የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነ ትልቅ አገር ነው፡፡ አልደራደርም አልስማማም ሊል አይችልም። ውሳኔው መሬት ላይ ሲወርድ ግን የሚመጣው ህዝቡ ጋ ነው፡፡
ህዝቡ ደግሞ የትኛው ድንጋይ የኢትዮጵያ፣ የትኛው ዛፍ የኤርትራ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የአሁኑን ውሳኔ ራሳቸው ኤርትራዊያኑ አይቀበሉትም። ድንበሩ ከአይጋ እንደሆነ፣ ድንበሩ ከእንዳልጌዳ በታች በኩል እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ዕድሉ ቢሰጠው ህዝቡ ራሱ በሰላም የሚጨርሰው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ውሳኔውን እንቃወማለን! ችግሩ አሁን በወሰኑትም፣ በፊት በፈረሙትም የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን በፊት ተፈርሟል ተብሎ፣ አሁን በእጃችን ያለን ነገር አሳልፎ መስጠት ስህተት ነው፡፡ በነገራችን ላይ አሁን የኢሮብ ህዝብን ለሁለት የከፈለው ውሳኔ፣ የተባበሩት መንግስታት በማይኖሪቲ ራይት ስር ያለውን ድንጋጌ በእጅጉ የሚፃረር ነው፡፡ አንድ ህዝብ ለሁለት አይከፈልም፡፡
በነገራችን ላይ በአንድ ወቅት አንድ አገር የነበሩ፣ ለሁለት ሲከፈሉ አንድ የባህር በር ሲጠቀሙ ከነበረ ሁለቱም የባህር በሩን የመጠቀም መብት አላቸው የሚል ይመስለኛል … ዓለም አቀፍ ህጉ?
ትክክል ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን ይሄን የባህር በር የመጠቀም መብት አላት፡፡ ለምን መብታችንን አልተጠቀምንም ብዬ ራሴን ስጠይቅ፣ መልሱን ማግኘት ይከብደኛል፡፡ ግራ ይገባኛል፡፡ ሌላው ኢሮብን ትንሽ መሬት ነው፣ ቢሄድና ሰላም ቢመጣ ምንም አይደለም ብሎ የሚያስብ መንግስትም ሆነ ግለሰብ ካለ ስህተት ነው፤ የትንንሽ መሬት ድምር ውጤት ነው፤ አገር የሚባለው፡፡ ህዝብ ደግሞ “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ” እያለ መገፋት የለበትም፤ “መሬቱ ይሂድ፤ አንተ ና” አይባልም፡፡ ህዝቡ የኖረበት ቦታ ከደሙና ከህልውናው ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም የኢሮብ ህዝብ በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ቅሬታውን ገልጿል፡፡ እናንተም አዲስ አበባ የምትኖሩ የአካባቢው ተወላጆች፤ ነገ በመዲናዋ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አቅዳችኋል። ተቃውሞው ውጤት ያመጣል ብላችሁ ታስባላችሁ?
የማይቀበለስ ውሳኔ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ሰው ነው ውሳኔውን የሚወስነው፡፡ አንድ እውነታ ደግሞ የትኛውንም ውሳኔ ሊቀለብስ ይገባል፡፡ እኛም በዚህ እምነታችን ቅሬታችንን ለማሰማት አንቦዝንም፡፡ ኢሮቦች ብቻቸውን ሰልፍ ስለወጡ ግን የሚቀለበስ አይደለም፤ የመላው ኢትዮጵያ የቤት ሥራ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፤ ምክንያቱም የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትና ሚዲያ ያለበት አገር ነው፡፡ ይህ ሆኖ እያለ ህዝብን ማዕከል ያላደረገ ውሳኔ አዎንታዊ ሰላም አያመጣም፡፡ ይሄ ሌላ ቦታ፣ ሌላ ቦንብ የሚቀብር ውሳኔ ነው፡፡ ስለዚህ በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ውሳኔው የፍትህና እኩልነትን የተላበሰ መሆን አለበት፡፡

Read 4085 times