Saturday, 16 June 2018 13:17

ጆሴፍ ካቢላ ለ3ኛ የስልጣን ዘመን እንደማይወዳደሩ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ህገ-መንግስቱን ጥሰው በስልጣን ላይ የመቆየት ዕቅድ እንዳላቸው በስፋት ሲነገርላቸው የቆዩት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ፤ በቀጣዩ አመት ታህሳስ ወር በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ለ3ኛ የስልጣን ዘመን እንደማይወዳደሩ በይፋ መነገሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ህገ-መንግስት አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት ተከታታይ የስልጣን ዘመናት በላይ በመንበሩ ላይ እንዳይቆይ እንደሚከለክል የጠቆመው ዘገባው፤ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላም ህጉን በማክበር በምርጫው እንደማይወዳደሩና ስልጣናቸውን በምርጫ ለሚያሸንፈው ተወዳዳሪ በሰላማዊ መንገድ እንደሚያስረክቡ ባለፈው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቡርኖ ሺባላ ማስታወቃቸውን አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2001 የአባታቸውን ቦታ ተክተው ስልጣን የያዙት ጆሴፍ ካቢላ፤ በመጪው ታህሳስ ወር ላይ በሚከናወነው የአገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የመወዳደር ዕቅድ እንዳላቸው በስፋት ሲነገርና ብዙዎችም ይህንን ዕቅድ ሲተቹና ጉዳዩ በአገሪቱ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል በሚል ስጋታቸውን ሲገልጹ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢላ እንደማይወዳደሩ በይፋ ያስታወቁትም ይህን ስጋት ለመቅረፍ በማሰብ ሳይሆን አይቀርም መባሉን አስረድቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም በህዝበ ውሳኔ ለተጨማሪ 14 አመታት በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚስችላቸውን የህገ-መንግስት ማሻሻያ አስጸድቀዋል በሚል ከተቃዋሚዎችና ከአለማቀፍ ተንታኞች ውግዘት ሲወርድባቸውና በስልጣን ጥመኝነት ሲታሙ የከረሙት የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፤ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ በ2020 ስልጣን እንደሚለቁ መግለጻቸው  ይታወሳል፡፡
በ2020 የስልጣን ዘመናቸውን የሚያጠናቅቁት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፣ በቅርቡ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ የህዝብ ድጋፍ አግኝቶ በህግነት በጸደቀው ማሻሻያ፣ ለተጨማሪ ሁለት የስልጣን ዘመናት ወይም 14 አመታት በመንበራቸው ላይ እንደሚቆዩ ብዙዎች በእርግጠኝነት ሲናገሩ ቢቆዩም፣ ፕሬዚዳንቱ ግን በስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት እንደሌላቸውና በቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ እንደማይወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡

Read 1308 times