Saturday, 23 June 2018 11:48

ዕድል ያሟልጫል!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

“--ለዚህ ነው መጀመሪያ የቤት ሥራችሁን ሥሩ የምልህ፡፡ ደግሞ እመነኝ፣ በዚህ ዘመን ጀግና የሚባለው በፍቅር የሚያሸንፍ ብቻ ነው፡፡ እናንተም መሸናነፍ ካለባችሁ መሳሪያችሁ ፍቅር ብቻ ይሁን፡፡ ቃል የምገባልህ…ያኔ፣ ወደ ጥንቱ ታላቅነታችሁ ትመለሳላችሁ፡፡--”
    
   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ እኔ ነኝ፣ እኔ ምስኪኑ አበሻ ነኝ፡፡
አንድዬ፡— ዛሬ ስታንኳኳ እንኳን ተለወጥክብኝ ልበል…
ምስኪን አበሻ፡— እንዴት አንድዬ?..ያው እንደ በፊቱ ነው እኮ ያንኳኳሁት፡፡
አንድዬ፡— በፊት ጊዜ ስታንኳኳ በር ልትገለብጥ የምትፈልግ ይመስል ነበር፡፡ ዛሬ ግን በጣም ለስለስ ብለህ ነው፤ ከፈለገ ይስማ፣ ካልፈለገ የራሱ ጉዳይ ብለህ ነው እንዴ?
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ…ኸረ ተው እንደ እሱ አትበል!
አንድዬ፡— እናንተ እኮ ትንሽ ተንፈስ ባላችሁ ጊዜ፣ ስትጸልዩ እንኳን ከፈለገ ይስማ ብላችሁ ስለሆነ እኮ ነው … እሺ እሱን ተወውና ዛሬ ደግሞ ምን እግር ጣለህ? መቼም ለአቤቱታ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— እንደው ለምን ብቅ ብዬ አላመሰግነውም ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— ብቅ ብለህ!  ጥሩ አነጋገር ነው፡፡ ግን ለምኑ ነው የምታመሰግነኝ!
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ፣ አሁን እንዲህ ይባላል! ስንት ነገር እየተካሄደ እያለ ለምኑ ይባላል!…እንደው ፊቴ ከሌላው ጊዜ ይልቅ ፈካ ማለቱን እንኳን አላስተዋልክም?
አንድዬ፡— አስተውያለሁ…ደግሞም አሁንም እያስተዋልኩ ነው፡፡ ብዙዎቻችሁ ሰሞኑን ትንሽ ዘና ያላችሁ ትመስላላችሁ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— ምን ትንሽ ብቻ!…እስከ ጥግ ነው ዘና ያልነው፡፡ የእኔንማ አልነግርህም፡፡ ብቻ ብረር፣ ብረር እያለኝ ነው፡፡
አንድዬ፡— ከስንት ዘመን በኋላ የተስፋ ቃላት ከአንደበትህ ሲወጡ በመስማቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ግን ደግሞ ብረር ብረር ከሚልህ ነገር…እስቲ ተረጋጋ፡፡ ክንፍ አውጥተህ መብረርህ ይቅርና ይልቁንስ ፈጠን፣ ፈጠን እያልክ መራመድና ሮጥ፣ ሮጥ ማለት ከቻልክ ለጊዜው ይበቃል፡፡
ምስኪን አበሻ፡— እሱስ እውነትክን ነው፡፡ ግን መብረር መመኘቴ ምን ችግር አለው?
አንድዬ፡— ምንም፣ ምንም ችግር የለውም። ግን መብረር ከመመኘትህ በፊት እስቲ መጀመሪያ በስነስርአቱ መራመድና አለፍ ሲልም ሮጥ፣ ሮጥ ማለትን ልመድ ለማለት ነው፡፡ እስከ ዛሬ እኮ ቀጥ ብለህ የተራመድክ እየመሰለህ እንጂ፣ እዚህና እዛ ስትረግጥ ነበር፣ አሁንም ገና ነህ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— እሱስ ልክ ነህ፡፡ አንድዬ ግን አትታዘበኝና…በዚህ ነገር ውስጥ አለህበት ይባላል፡፡
አንድዬ፡— ምን አልከኝ?…እስቲ ድገመው…
ምስኪን አበሻ፡— አይ…ምን መሰለህ፣ ሰሞኑን እየሆኑ ባሉ ነገሮች ሁሉ፣ የአንተ እጅ አለበት እየተባለ ነው የሚወራው፡፡
አንድዬ፡— እንደዚህ ሆነ! ሲቸግራችሁ፣ ማጣፊያው ሲያጥራችሁ “ምን አድርገንህ ነው እንዲህ የምታሰቃየን! ምን በድለንህ ነው!” ትላላችሁ፡፡ አሁን ደግሞ ትንሽ ዘና ያላችሁ ስትመስሉ፣ “አለህበት ይባላል” ትሉኝ ጀመር!
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ የአነገጋር ስህተት ነው። ምን መሰለህ፣ ሰሞኑን እንደው ዘና ብለን  የመጣልንን ስለምንናገር አምልጦኝ ነው እንጂ…
አንድዬ፡— እኮ ችግሩ ይኸው ነው እኮ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— ምኑ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡— የመጣላችሁን መናገሩ… አየህ የመጣልህን የምትናገር ከሆነ አስበህ፣ አመዛዝነህ እየተናገርክ አይደለም፡፡
ምስኪን አበሻ፡— ማለቴ አንድዬ… ቀደም ሲል እየተሳቀቅን እናወራ የነበረውን፣ አሁን ሳንገላመጥ በአደባባይ ማውራት ስለጀመርን ነው ማለት ፈልጌ ነው፡፡
አንድዬ፡— ይሁን፣ ግን አሁንም ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ እንደ ልብ መናገር ማለት እውነት መናገር ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ መልካሙን ጅምር እንዳታበላሹት ብዬ ነው፡፡
ምስኪን አበሻ፡— እሱማ ገና ምኑ ተይዞ አንድዬ፣ ገና ምኑ ተይዞ፡፡
አንድዬ፡— ዝም ብዬ ከፊሎቻችሁን ስታዘባችሁ፣ ሁሉ ነገር ያለቀ የደቀቀ እየመሰላችሁ ነው፡፡ ተስፋ ጥሩ ነው፣ ግን በብልህነት ካልያዛችሁት አጉል ይሆናል፡፡
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ፣ ግን እንደው አንተን መጨቅጨቅ ትንሽ መቀነሳችን ጥሩ አይደለም  ትላለህ?
አንድዬ፡— በጣም ጥሩ እንጂ! እኔም የምፈልገው ይሄንኑ ነው፡፡ ዘላለም አቤቱታ አቅራቢ ከምትሆኑ በራሳችሁ ጉዳይ የራሳችሁን መፍትሄ መፈለግ ስትጀምሩ በማየቴ ደስ ይለኛል፡፡
ምስኪን አበሻ፡— እንደው አንዳንድ ምክር ጣል፣ ጣል ብታደርግብን፡፡
አንድዬ፡— የእኔ ምክር ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ ራሳችሁ ራሳችሁን እየመከራችሁ፣ በጎደለ እየሞላችሁ፣ በተጣመመ እያቃናችሁ፣ በተሰነጠቀ እየጠገናችሁ መሄዱ ነው፡፡ ምክር ጠያቂና ምክር ተቀባይ እየሆናችሁ እስከ መቼ!
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ ምንም ቢሆን አንተ ሁሉም ነገራችን ላይ አለህበት አይደል እንዴ!
አንድዬ፡— ጎሽ፣ አሁን እንኳን “አለህበት ይባላል” አለማለትህ ጥሩ ነው፡፡
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ አንተም እንደ እኛ ቂም ትይዛለሀ እንዴ!…
አንድዬ፡— አጋባችሁብኝ መሰለኝ፡፡ ለነገሩማ የፈለገውን ቂመኛ ብሆን፣ እናንተን አልስተካከልም፡፡
ምስኪን አበሻ፡— እሱ ላይ እውነት ብለሀል፡፡ ግን እኮ አሁን ይቅር እየተባባልን ነው፡፡ ቂም መያያዝ አጫረሰን እንጂ የትም አላደረሰንም፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እናስወግድው እየተባባልን ነው፡፡
አንድዬ፡— ጥሩ ነው፣ ግን በወሬና በመፈክር ብቻ የሚጠፋ ነገር የለም፡፡ ዋናው ልባችሁ ውስጥ ያለውን የእሾህ ጫካ መመንጠር ነው፡፡
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ ግን እኮ፣ ብናወራውም አያስችልም…
አንድዬ፡— ምኑ ነው የማያስችለው?
ምስኪን አበሻ፡— ቂምን እንዲህ አውጥቶ መጣል ይከብዳል፡፡ አይደለም በትልልቅ ደረጃ፣ መንገድ ላይ በስህተት ገፋ ያደረገን የማናውቀው ሰው ላይ ቂም የምንይዝ ነን፡፡ አንድዬ ግን ከሌላው ለይተህ እንዲህ ቂመኞች ያደረግኸን ምን ብንበድልህ ነው!
አንድዬ፡— ይኸው…ይኸዋ ጀመረህ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— ይቅርታ አንድዬ፣ አፍ እላፊ ነው።
አንድዬ፡— ስማኝ፣ አሁን እናንተ ቀጥ ያለ ዳገት እንደሚወጣ መኪና ናችሁ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— አልገባኝም…
አንድዬ፡— ማለት ቀጥ ያለ ዳገት የሚወጣ መኪና ጉዞው ቀላል አይሆንለትም፡፡ በየመሀሉ አቅም እያነሰው ይሁን በሌላ ምክንያት ሊቆም ይችላል። ታዲያ በሚቆምበት ጊዜ ወደ ኋላ እንዳይንሸራተት ካልደተረገ ወዴት እንደሚሄድ አልነግርህም፡፡
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ፣ የእኛ መኪና ግን ከእንግዲህ የትም ቦታ አይቆምም፡፡
አንድዬ፡— እርግጠኛ ነህ?
ምስኪን አበሻ፡— በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡
አንድዬ፡— ሁሉም እንደ አንተ እርግጠኛ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ግን እኮ ሰው ሲደክመው ቆም እንደሚል ሁሉ መኪና ወይ ሞተር ከልክ በላይ ሲሞቅ፣ ለማቀዝቀዝ ቆም ታደርጉ የለም እንዴ?
ምስኪን አበሻ፡— በእኔ ይሁንብህ አንድዬ! ይሄኛው መኪና አይደለም ሊቆም፣ ለሴኮንድ እንኳን ፍጥነቱን አይቀንስም፡፡
አንድዬ፡— ለሰከንድ እንኳን ፍጥነቱን አለመቀነሱ ጥሩ መሆኑ ነው?
ምስኪን አበሻ፡— ታዲያስ አንድዬ…ታዲያስ!
አንድዬ፡— ግን እኮ እንደ መንገዱ ሁኔታ፣ እንደ አየር ሁኔታ፣ መኪናው ውስጥ እንደቀረው ነዳጅ መጠን…በየጊዜው ፍጥነት መስተካከል የለበትም ትላለህ?
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ፡ ይህኛው የተለየ ነው፤ ምንም ነገር አያቆመውም፡፡
አንድዬ፡— ይሁንላችኋ፣ ሌላ ምን እላለሁ…
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ አልሰማህም እንዴ!
አንድዬ፡— ምኑን?
ምስኪን አበሻ፡— ዓለም ሁሉ በእኛ እየተደነቀ ነው እኮ፤ ምን ልበልህ፣ ከኒው ዮርክ እስከ ቶከዮ የእኛ ነገር ጉድ እየተባለ ነው፡፡
አንድዬ፡— ለምን?
ምስኪን አበሻ፡— አንድዬ፣ ሆነ ብለህ ነው አይደል ለምን ያልከኝ! አሁን የምለውን ሳታውቅ ቀርተህ ነው…
አንድዬ፡— ማለቴ ሌሎቹ ምን አግብቷቸው ነው ብዬ ነዋ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— እንዲህ አይነት ነገር ታይቶ አይታወቅማ! አንድዬ፣ ምን አለ በለኝ ትንሽ ቆይቶ ሁሉም በሰልፍ ነው የሚመጡት፡፡
አንድዬ፡— ምን እናገኛለን ብለው?
ምስኪን አበሻ፡— የእኛን ወዳጅነት ፈልገው ነዋ!
አንድዬ፡— ምኞትህ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ግን እኮ ወዳጅ ሲመጣ ዝም ብሎ አይመጣም..
ምስኪን አበሻ፡— ማለት፣ አንድዬ…
አንድዬ፡— ማለትማ ማንኛውም ወዳጅ ሲመጣ እኮ የአንተን ጥቅም ሳይሆን የራሱን ጥቅም አይቶ ነው። ብወዳጃቸው የእኔ ጥቅም ምንድነው ብሎ ነው፡፡ ደስ ስላላችሁት፣ ከእናንተ ፍቅር ስለያዘው አይደለም፡፡
ምስኪን አበሻ፡— እሱስ ልክ ነው…ግን አንድዬ አሁን ያለንበት ሁኔታ ከበፊቱ የተሻለ ነው አትልም!
አንድዬ፡— በጣም እንጂ! የተሻለ ማለቱ ብቻ አይገልጸውም፡፡ እውነቱን ለመናገር፤ እኔ ራሴ ዓይኔ ነው ወይስ የማየው ነገር ሁሉ እዛች አገር ላይ እየተደረገ ነው እያልኩ ነው፡፡ ግን ደግሞ ስጋትም አለኝ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— ለምን አንድዬ?
አንድዬ፡— አንዳንድ የምሰማቸውና የማያቸው ነገሮች ያሳስቡኛል፡፡ በነገራችን ላይ የእናንተ ጥሩ መሆን፣ የእናንተ ከችግር መላቀቅ፣ የእናንተ በአንድ ልብ ማሰብ፣ በአንድ አንደበት መናገር፣ እናንተን ደስ የሚላችሁን ያህል ደስ የማይላቸው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— የት ይደርሳሉ አንድዬ…
አንድዬ፡— ይሄ እንኳ ብስለት ያለው አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ስለ ውጪ ወዳጅ ከማሰባችሁ በፊት የቤት ሥራችሁን ጨርሱ፡፡ መጀመሪያ የራሳችሁን ሽንቁር ድፈኑ፡፡ በቡራ ከረዩና በመናናቅ ሳይሆን በእውቀትና በመከባበር ተወያዩ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— ልክ ብለሀል፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— ስማኝ፣ ይቺ አገር እንደ ዘንድሮ አይነት መልካም እድል ገጥሟት አያውቅም፡፡ እውነቴን ነው የምልህ፣ ይህ በመቶ ዓመት አንዴ እንኳን የሚመጣ እድል አይደለም፡፡ እድል ደግሞ ያሟልጫል፡፡ አሟልጮ እንዳያመልጣችሁ፡፡ ለዚህ ነው መጀመሪያ የቤት ሥራችሁን ሥሩ የምልህ፡፡ ደግሞ እመነኝ፣ በዚህ ዘመን ጀግና የሚባለው በፍቅር የሚያሸንፍ ብቻ ነው፡፡ እናንተም መሸናነፍ ካለባችሁ መሳሪያችሁ ፍቅር ብቻ ይሁን፡፡ ቃል የምገባልህ…ያኔ፣ ወደ ጥንቱ ታላቅነታችሁ ትመለሳላችሁ፡፡ ጨርሻለሁ፣ በሰላም ግባ፡፡
ምስኪን አበሻ፡— አመሰግናለሁ አንድዬ፣ መጥቼ አልጣህ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 7617 times