Saturday, 23 June 2018 11:57

ብህትውናና ዘመናዊነት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)

 ክፍል - 2 የብህትውና ጉዞ ወደ ጥንታዊቷ አክሱም
          
   በክፍል-1 ፅሁፌ ብህትውና፤ ፍልስፍናዊና ሃይማኖታዊ የሥነ ምግባር አስተምህሮ እንደሆነና ይሄም አስተምህሮ ላቅ ወዳሉ እሳቤዎችና መንፈሳዊ ከፍታዎች የሚያደርስ መንገድ ነው ተብሎ ስለሚታመን፣ በጥንቱና በመካከለኛው ዘመን ላይ በስፋት ጥቅም ላይ እንደዋለ ተመልክተናል። ከዚህም በተጨማሪ፣ ብህትውና ከጥንታዊ ግሪክ ፍልስፍናዎች ተነስቶ በአሌክሳንደሪያ አድርጎ፣ ወደ ክርስትና ሃይማኖት ውስጥ እንደገባም ተመልክተናል፡፡ በዛሬው ፅሁፌ ደግሞ ግሪክ ላይ የተነሳው የብህትውና አስተምህሮ ማሳረፊያውን ኢትዮጵያ ላይ እንዳደረገ እንመለከታለን፡፡
በክርስትና ውስጥ ያሉት የመጀመሪያዎቹ 500 ዓመታት፣ በሦስት ዘመናት ይከፈላሉ - ዘመነ ሐዋርያት (1ኛው ክ/ዘ)፣ ዘመነ ሊቃውንት (2ኛውና 3ኛው ክ/ዘ) እና ዘመነ መነኮሳት (4ኛውና 5ኛው ክ/ዘ) በመባል። በሦስቱም ዘመናት ላይ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል፡፡ በዘመነ ሐዋርያት ጊዜ እየሩሳሌምን ለመጎብኘት በሄደው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፣ በዘመነ ሊቃውንት ጊዜ በአባ ሰላማ (ፍሪሚናጦስ) እንዲሁም፣ በዘመነ መነኮሳት ጊዜ በዘጠኙ ቅዱሳን አማካኝነት፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ሦስቱ ክስተቶች በጥንታዊ የአክሱም ማህበረሰብ ላይ ያሳረፉት ተፅዕኖ የተለያየ ነው፡፡ በዘመነ መነኮሳት ጊዜ የተነሳው ክርስትና ከቀደሙት ሁለቱ የክርስትና ዘመናት ውስጥ ለየት የሚያደርገው ብህትውናን ማህበራዊ ንቅናቄ አድርጎ መነሳቱ ነው፡፡
በመሆኑም፣ ከእነዚህ ሦስት የክርስትና ዘመናት ውስጥ፣ በኢትዮጵያ ተስተካካይ የሌለውና አሁን ድረስ ዘላቂ የሆነ የማንነትና የባህል አሻራውን በስፋት የምናገኘው፣ በሦስተኛው ዘመን ላይ በዘጠኙ ቅዱሳን አማካኝነት ወደ ሀገራችን የገባው የብህትውና ክርስትና ነው፡፡ ስለ አገባቡ ከማየታችን በፊት ግን ከዘመነ ሊቃውንት ወደ ዘመነ መነኮሳት የተደረገው ሽግግር፣ የብዙ ተመራማሪዎችን ቀልብ የሳበ ስለሆነ እሱ ላይ ትንሽ ነገር ልበል፡፡
በታላቁ የሮማን ኢምፓየር ውስጥ እስከ 4ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ድረስ ለክርስትና ሃይማኖት ምንም ዓይነት ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ እውቅና ስላልተሰጠው፣ እነዚህ ዘመናት ለክርስትያኖች ከባዱን የመከራ ዘመናት ያሳለፉበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በንጉስ ኔሮ እና በንጉስ ዲዮቅሊጥያኖስ ዘመን በርካታ ክርስትያኖች (ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ) በሰማዕትነት የተሰውበት ዘመን ነው፡፡ እናም በእነዚህ ዘመናት ውስጥ ‹‹ከፍተኛው ክርስትና›› የሚገኘው ‹‹በሰማዕትነት›› ነበር፡፡
ቀዳማዊ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ (306—337) በሮም ሲነግስ ግን ለሮማን ክርስትያኖች አዲስ ዘመን ወጣላቸው፡፡ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ (የእየሱስን መስቀል ያስገኘችው የቅድስት እሌኒ ልጅ ነው) በ313 ዓ.ም ክርስትና የሮማን ኢምፓየር ኦፊሴላዊ ሃይማኖት መሆኑን አወጀ፡፡ በዚህም ክርስትያኖች ከተደበቁበት ወጥተው እምነታቸውን በአደባባይ ማንፀባረቅ ጀመሩ። አብያተ ክርስትያናትም በብዛት መሰራት ጀመሩ፡፡
ክርስትና የመንግስት ሃይማኖት መሆኑን ተከትሎ ግን አንድ ችግር አብሮ መጣ፡፡ እሱም ‹‹ከፍተኛውን ክርስትና›› ማግኘት የማይቻል ሆነ፡፡ ክርስትያኖች በሚሳደዱበት ዘመን ላይ ‹‹ከፍተኛውን መንፈሳዊነት›› አንገታቸውን ለሰይፍ በመስጠት ‹‹ከሰማዕትነት›› ያገኙ ነበር፡፡ በንጉስ ቆስጠንጢኖስ ዘመን ግን ይህ ‹‹ሰማዕትነት›› ቀረ፡፡ ሰማዕትነቱ ሲቀር ‹‹ከፍተኛውን ክርስትናም›› ማግኘት አልተቻለም፡፡ ‹‹በዚህ ወቅት ነበር ክርስትያኖች የሰማዕትነቱን ዘመን መናፈቅ የጀመሩት›› ትላለች፤ ኤሊዛቤት ካስቴሊ “Martyrdom and Memory” በተባለው ስራዋ ውስጥ፡፡
በዚህ ወቅት ነበር ‹‹ከፍተኛውን ክርስትና›› ለማግኘት ብህትውናን እንደ ብቸኛ አማራጭ ማየት የተጀመረው፡፡ ሰማዕትነቱም ከውጭ ወደ ውስጥ ሆነ — በራስ ፍቃድ አካልን ማሰቃየትና ከዓለም መነጠል። በዚህ ወቅት ነበር ‹‹ፍፁም መሆን ከፈለክ፣ ሁሉ ነገርህን ትተህ ተከተለኝ›› የሚለው የማቴዎስ ወንጌል ከሁሉም የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ ጎልቶ መውጣት የጀመረው፡፡ በሦስቱ የግብፅ የበርሃ አባቶች (አባ እንጦስ፣ አባ መቃርስ እና አባ ጳኩሜስ) በ4ኛው ክ/ዘ የተጀመረው ይህ የብህትውና ህይወት በሁለት ምክንያቶች በፍጥነት ወደ ማህበራዊ ንቅናቄነት ማደግ ችሏል፡፡
የመጀመሪያው፣ ቀድሞውንም ከዋናው ማህበረሰብ የተነጠሉ የተለያዩ ክርስትያናዊ ማህበረሰቦች በታናሹ እስያ መኖራቸው ነው፡፡ በእነዚህ ‹‹ንጥል ማህበረሰቦች›› ውስጥ የተአቅቦ ህይወት የሚወደስ ሲሆን፣ ምናኔንም እንደ መጨረሻ ግብ ያስቡት ነበር፡፡ በመሆኑም ‹‹በንጥል ማህበረሰቦች›› ያለውን ህይወት፣ ለዋናውና ለመጨረሻው የብህትውና ህይወት እንደ መዘጋጃ (apprenticeship) ይቆጥሩት ነበር፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፣ የሥነ ፅሁፍ ሚና ነው። በተለይም በእስክንድርያው ፓትሪያርክ በአቡነ አትናቲዎስ የተዘጋጀው የአባ እንጦስን የብህትውናና የተጋድሎ ህይወትን የሚተርከው (The Life of St. Anthony) መፅሐፍ በብዛት ወደ እነዚህ ‹‹ንጥል ማህበረሰቦች›› መሰራጨቱ፣ ብህትውና በቀላሉ ማህበራዊ ንቅናቄ ሆኖ እንዲወጣ አስችሎታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ አቡነ አትናቲዎስ ብህትውና ላይ የፃፏቸው ሥራዎች በኋላ ላይ ለመጡት እንደ ቅዱስ ባሲል፣ ቅዱስ ጄሮምና ቅዱስ ኦገስቲን ላሉት የቤተ ክርስትያን ሊቃውንትም ብህትውናን በስነ መለኮት ውስጥ ምሁራዊ ተዋስዖ እንዲሰጡት አድርጓቸዋል፡፡
ምንም እንኳ ክርስትና በታላቁ የሮም ግዛት ውስጥ መንግስታዊ ሃይማኖት መሆኑ ለክርስትያኖች ታላቅ እፎይታን ያጎናፀፈ ቢሆንም፣ ይሄ እፎይታ ግን የቆየው ለ138 ዓመታት ብቻ ነበር፡፡ በክርስቶስ ሰዋዊና መለኮታዊ የባህሪ ውህደት ላይ የምዕራቡና የምስራቁ ክርስትና ለዘመናት ሲወዛገቡ ኖረዋል፡፡ ይሄንን ውዝግብ የመጨረሻ እልባት ለመስጠትም በ451 ዓ.ም ኬልቄዶን ላይ አጠቃላይ ጉባዔ ቢጠራም፣ ስምምነት ግን ሊመጣ አልቻለም፡፡ ጉባዔውም አንዱ አካል ሌላውን በማውገዝ ተጠናቀቀ፤ ካቶሊክና ኦርቶዶክስ ሆኖ መለያየትም ብቸኛው መፍትሄ ሆነ፡፡
ይሄንን ክፍፍል ተከትሎም ለኦርቶዶክሳውያን ሌላ የመከራ ዘመን መምጣት የጀመረውም ካቶሊካዊት ቤ/ክ በሮም ንጉስ መደገፏ ነበር፡፡ ኦርቶዶክሳውያን መነኮሳት ለመንፈሳዊ ከፍታ ብለው ከዓለም ተነጥለው በብህትውና ቢኖሩም፣ ተነጥሎ መኖርም የማይቻልበት ዘመን ሆነባቸው፡፡ እናም ወደ መካከለኛው ምስራቅ ስደትን መረጡ፡፡ ግብፅ፣ ሶሪያና ኢትዮጵያም ዋነኛ መዳረሻዎች ሆኑ፡፡ ከእነዚህ ተሳዳጅ መነኮሳት ውስጥ ዘጠኙ አክሱምን መረጡ፡፡
ስለ ዘጠኙ ቅዱሳን መነኮሳት አመጣጥና በኢትዮጵያ የነበራቸውን ሃይማኖታዊ ተጋድሎ በስፋት የፃፈው ፕ/ር ስርግው ሐብለ ስላሴ ነው - Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270 በሚለው የዶክትሬት ማሟያ መፅሐፉ ውስጥ፡፡ ስርግው እንደፃፈው ከሆነ፣ ዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከተከታዮቻቸው ካህናት፣ ዲያቆናትና የተለያዩ መፃህፍት ጋር ስለነበር፣ ሁኔታው ቀስ እያለ አክሱም ላይ አዲስ ዓይነት የሥነ ፅሁፍ ባህል እንዲወለድ ምክንያት ሆኗል፡፡ አክሱም ለክርስትና አዲስ ባትሆንም ከብህትውና አስተሳሰብ ጋር የተዋወቀችው ግን በዚህ ወቅት ነበር፡፡
ዘጠኙ ቅዱሳን በ466 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ፣ በወቅቱ አክሱም ላይ የነገሰው ንጉስ ዳግማዊ አፄ እለ አሚዳ (460-472) (የአፄ ካሌብ አያት) ነበር። ንጉሱም መነኮሳቱን ሞቅ ባለ አቀባበል የተቀበላቸው ሲሆን መነኮሳቱ ከህዝቡ ጋር እንዲተዋወቁም ከፍተኛ እገዛ ያደርግላቸው ነበር፡፡ መነኮሳቱ ከአክሱማውያን ባህል ጋር እየተለማመዱና የግዕዝ ቋንቋንም እያጠኑ ለ12 ዓመታት በአክሱም ቆዩ፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር መፅሐፍ ቅዱስን ወደ ግዕዝ መተርጎም የጀመሩት፡፡
‹‹የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ›› በሚለው መፅሐፋቸው ውስጥ መሪራስ አማን በላይ  እንደፃፉት ደግሞ፣ ዳግማዊ አፄ እለ አሚዳ ከመነኮሳቱ ጋር እጅግ ከመዋደዳቸው የተነሳ የብህትውናው ትምህርት በንጉሱ ላይ እጅግ ሰርፆባቸው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ነበር ንጉሱ በ472 ዓ.ም ሥልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለቀው ሊመንኑ የቻሉት፡፡ ገና ከመምጣቱ የአክሱም ቤተ መንግስት በክብር የገባው ብህትውና ያመነኮሰው ግን አፄ እለ አሚዳን ብቻ ሳይሆን የልጅ ልጆቻቸውንም - አፄ ካሌብን፣ አፄ ገብረ መስቀልንና አፄ እለ ገበዝንም - ጭምር ነው እንጂ፡፡
ልክ አፄ እለ አሚዳ ከስልጣን ሲለቁ በምትካቸውም፣ ልጃቸው አፄ ታዜና ወደ ሥልጣነ መንበሩ መጡ፡፡ ፕ/ር ስርግው እንደሚነግሩን ከሆነ ደግሞ አብዛኛዎቹ መነኮሳት፣ በአፄ ታዜና ወደ ሥልጣን መምጣት ደስተኞች አልነበሩም፡፡ አፄ ታዜናም መነኮሳቱ የፖለቲካ ፍላጎት ማሳየታቸውን ባይወዱትም፣ እሳቸውም ግን እንደ አባታቸው ለመነኮሳቱ ድጋፍ ያደርጉላቸው ነበር።
አክሱማውያን ለዘመናት የተለያዩ አማልክቶችን ሲያመልኩ የነበረ በመሆኑ፣ የመነኮሳቱ የወንጌል አገልግሎት ከህዝቡ ተቃውሞ ሊገጥመውና መስዋዕትነትም ሊያስከፍላቸው እንደሚችል የታመነ ነው፡፡ ይሄንን ስጋት ታሳቢ በማድረግ ነበር በንጉሱ ልዩ ጥበቃ መነኮሳቱ ለወንጌል አገልግሎት ብዙ ህዝብ የሰፈረባቸውን አካባቢዎች ለመድረስ፣ የአዱሊሱን የንግድ መስመር ተከትለው ግራና ቀኝ የተሰማሩት፡፡
ክርስትና በሁለቱም ዘመናት (በዘመነ ሊቃውንትም ሆነ በዘመነ መነኮሳት) በታላቁ ሮም እና በአክሱም ውስጥ የተስፋፋበት መንገድ በጣም የተለያየና ተቃራኒ ነው፡፡ የሮማው - በብዙ መስዋዕትነትና በጣም በረጅም ጊዜ ከታች ወደ ላይ (ከህዝቡ ወደ ቤተ መንግስቱ) የተስፋፋ ሲሆን፤ አክሱም ላይ ግን በተቃራኒው ነው - ያለ ምንም መስዋዕትነትና በጣም በአጭር ጊዜ ከላይ ወደ ታች፡፡
እንግዲህ እዚህ ጋ ነው ዋናው ጥያቄ የሚመጣው። አክሱም ላይ የብህትውና አስተሳሰብ ወደ ህዝቡ ከመግባቱ በፊት ወደ ቤተ መንግስት መግባቱና ከፖለቲካ ጋር መጋባቱ ምን ዓይነት አንድምታዎች ይኖሩታል? የአስተሳሰቡስ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? የሚሉት ጥያቄዎች እጅግ አጓጊና ወሳኝ ናቸው፡፡
ብህትውና ገና ከመነሻው አክሱም ላይ ከፖለቲካ ጋር ጋብቻ መፈፀሙ፣ ማህበረሰቡ ላይ ሁለት ዓይነት ዘላቂ አሻራዎችን እንዲያስቀምጥ አድርጎታል። የመጀመሪያው፣ አስተሳሰቡ በጣም በፍጥነት እንዲስፋፋና የህዝቡ ባህል ሆኖ እንዲወጣ ማድረጉ ነው፡፡ የዚህ ማሳያው ደግሞ የዜማው ሊቅ የቅዱስ ያሬድ መነሳት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር›› ለመፍጠር ‹‹የብሄራዊ ሀገር ግንባታ›› ፕሮጀክት ይዞ መነሳቱ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከ1400 ዓመታት በኋላ ከአብዮቱ ‹‹የብሄር ብሔረሰብ ሀገራዊ ፕሮጀክት›› ጋር በተቃርኖ የቆመ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ተቃርኖ ነው በአብዮቱ ጊዜ የአማራ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የዘውግ ፖለቲካ እንዲፈለፈል ያደረገው፡፡ በክፍል-3 እና 4 መጣጥፎቼ ላይ እነዚህን ሁለት አሻራዎች እንመለከታለን፡፡
(ጸሃፊው፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› መፅሐፍ ደራሲ ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 1994 times