Saturday, 23 June 2018 12:16

“አልቃሽና ዘፋኝ” ከተውኔት ይዘት አንፃር

Written by  በኃይሌ ሲሳይ ገበየሁ
Rate this item
(8 votes)


    ርዕስ ፦ አልቃሽና ዘፋኝ
 ደራሲ ፦ ፍሰሐ በላይ ይማም
የጊዜ ቆይታው ፦ የሙሉ ጊዜ ተዉኔት
ተውኔቱ የተጻፈበት ዘመን ፦ 1978 ዓ.ም
ዘውግ ፦ ኮሜዲ
በዚህ ተውኔት ውስጥ በገሃዱ ዓለም ፍጡራን አካልና አምሳል ተለክተዉ፣ የተቀረፁ ሰባት ገጸ ባህሪያት ሲሆኑ በስም የሚጠሩ ግን  ወደ መድረክ የማይመጡት ደግሞ ከአምስት በላይ ናቸዉ፡፡ ተውኔቱ የሚከወነዉ በአንድ ትልቅ ከተማ፣ ሶስት ሰዎች በደባልነት ተከራይተዉ በሚኖሩበት ቤት ውስጥ ነው። ተውኔቱ የሚፈጸምበት ዘመን፣ ቅድመ የኢትዮጵያ አብዮት ሲሆን የተጻፈዉ ደግሞ በዝርዕውና በግጥም ነዉ፡፡ የመቼት ገለጻ ያለው፣ በዘልማድ ተውኔታዊ መዋቅር የተዋቀረ፣ ባለ አንድ ገቢርና ባለ ሶስት ትዕይንት ተውኔት ሲሆን ትዕይንት አንድ- አርብ ጧት፣ ትዕይንት ሁለት- አርብ ከሰዓት በኋላ፣ ትዕይንት ሶስት- በማግስቱ ቅዳሜ ጧት የሚከወን፣ ባጠቃላይ 519 ቃለ ተውኔትና 45 የገጽ ብዛት ያለው ተውኔት ነው፡፡
ፈንታሁን እንግዳ እንደሚለዉ፤ የትዕይንት ለውጥ አብዛኛውን ጊዜ የሚከወነው፣ አንድ ምሉዕነት ወዳለዉ የድርጊት ሽግግር ሲደረግ ነዉ፡፡ አብዛኛዉን ጊዜ በትዕይንት ለውጥ ምክንያት የቦታና የጊዜ ለዉጥ አይኖርም፡፡ ገቢርን በትዕይንት በመከፋፈል ረገድ የፈረንሳይና የእንግሊዝ ሃያስያን፣ የተለያየ ንድፈ-ሃሳባዊ አቀራረብ አላቸው፡፡ በፈረንሳይ የተውኔት ሃያሲያን ዘንድ የትዕይንት ለውጥ ተደረገ ተብሎ የሚታመነዉ ገጸ ባህሪያቱ በተዉኔቱ ታሪክ ዉስጥ መጥተዉ ሲጨመሩ ወይም ከተውኔቱ ታሪክ ሲቀነሱ ነዉ፡፡ በእንግሊዝ ሃያሲያንና ጸሀፌ ተውኔቶች ባንጻሩ፣ የገጸ ባህሪያት መውጣትና መግባት የትዕይንት መለዋወጥንና እንዲሁም መተዋወቅን አያመለክትም፡፡ ለእነዚህ ወገኖች የትዕይንት ለውጥ ተደረገ የሚባለው ወይም አንድ በመከወን ላይ ያለው ተውኔታዊ ድርጊት  አልቆ መድረኩ በጸዳ ጊዜ ነዉ፡፡ ከዚህ አኳያ አልቃሽና ዘፋኝን ስንመረምር፣ ትዕይንቶቹ፣ በእንግሊዝ የትዕይንት አከፋፈል የተከፈለ ነው፡፡ አከፋፈሉም የሰመረ ነው፡፡ ምክንያቱም ከትዕይንት ወደ ትዕይንት ሲሸጋገር በሚገባ ተንሰናስኖና ተዋህዶ ነው፡፡ በዚህ ተውኔት ውስጥ የቦታ ለውጥ ባይኖርም፣ በመቼ ጊዜ እና በምን ማህበራዊ እውነት ውስጥ እንደተከናወነ ለተደራሲያን ግልጽ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ተውኔቱ ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድርጊቱ የሚፈፀመው አስጋርጅው፣ ማሩና ሽማግሌው በደባልነት ተከራይተው በሚኖሩበት  ቤት ውስጥ ነው።
በዚህ ተውኔት ውስጥ ያሉት ሶስቱም ትዕይንቶች የየራሳቸው ቁርጥራጭ ተውኔታዊ ድርጊያ አላቸው። እያንዳንዱ ትዕይንት ለውጡን መሰረት ያደረገው በጊዜ ላይ ነው፡፡ ለምሣሌ በመጀመሪያው ትዕይንት ውስጥ ያለው ተውኔታዊ ድርጊያ መከወኛ ቦታው አስጋርጅው፣ ማሩና ሽማግሌው በደባልነት ከሚኖሩበት የክራይ ቤት ውስጥ ሲሆን ጊዜውም አርብ ጧት ነው፡፡ በተውኔቱ መግቢያ ላይ ያለው “የታሪኩ አመዳደብ” የተውኔቱን ጊዜ ይጠቁመናል። በዚህ ትእይንት እያንዳንዱ የተውኔት ተሳታፊ ገጸ ባህሪያት ተዋውቀው እናገኛቸዋለን፡፡ የተውኔቱ ርእሰ ጉዳይም ምን እንደሆነ በቃለ ተዉኔት ይጠቅሳል፡፡ ትዕይንት ሁለት የሚከናወነው እዛው ትዕይንት አንድ በተከናወነበት ቦታ ላይ ነው፡፡ ተውኔታዊ ድርጊያው ስንመለከት በትዕይንት አንድ ፍንጭ ተሰጥቶበት የነበረው ሃሳቡ ተብራርቶና ግልጽ ሆኖ የቀርበበት ነው። ትዕይንት ሦስት የተውኔቱ የመጨረሻ ትዕይንት ሲሆን ለውጥ የተደረገበት በጊዜ ላይ ብቻ ነው፡፡ ትእይንት አንድና ሁለት ከተፈጸመ ከአንድ ቀን በኋላ በማግስቱ ቅዳሜ ጧት ነው፡፡ ተውኔታዊ ድርጊቱ የሚከናወነው አስጋርጅዉና ማሩ ፍላጎታቸውን ለመሙላት ሲያደርጉ የነበረው ውጣ ዉረድ (ጥረት) ፍጻሜ ሲያገኝ ያሳየናል። በትዕይንቶች መሀከል ያለው ለውጥ፣ ባጠቃላይ መሰረት ያደረገው ጊዜ ላይ ብቻ በመሆኑ የትዕይንት አከፍፈል ቀመርን  መሰረት ያደረገ ነው፡፡
የትዕይንቶች እርስ በእርስ ግንኙነት ስናይ፣ በሦስቱም ትዕይንቶች መሀከል የጠበቀ ቁርኝትና የሰመረ ውህደት አለ፡፡ ሦስቱም ትዕይንቶች፣ ገጸ ባህሪያቱ፣ ፍላጎታቸዉን ለመሙላት በሚያደርጉት በተጫረ ግጭት ላይ መሰረት በማድረግ፣ እርስ በእርሳቸው እየተወሳሰቡና እየተቆላለፉ፣ በመጨረሻ ወደ አንድ መቋጫ ላይ በሚደርስ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያደርሰናል። ትዕይንቶቹም እርስ በርሳቸው ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ትዕይንት ውስጥ የምናገኛቸው ንዑስ ግጭቶች ፣ ሴራዎች ፣ ጭብጦች ዋናውን  ሴራና ጭብጡን የሚያዳብሩ ናቸው፡፡
አልቃሽና ዘፋኝ ተውኔት- ከኮሜዲ ዘውግ አንጻር
አልቃሽና ዘፋኝን ከማየታችን በፊት ስለ ኮሜዲ ተዉኔት ንድፈ-ሃሳብ ቅኝት እናድርግ፡፡ ኮሜዲ ተውኔት በገጸ ባህሪያት ሁናቴዎችና በቃለ ተዉኔቶች በኩል ያለን አለመመሳሰል፣ በንፅፅር እያሳየ፣ ሳቅን በተደራሲያን ልቦና የማጫር ሃይል አለው፡፡ ይሁንና ኮሜዲ ተዉኔት ካለፋቸው ደረጃዎች ብዛት፣ ከቅርጾቹ ዓይነትና ወቅታዊነት አኳያ ለበርካታ የቴአትር ምሁራን ትርጓሜው አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለዚህም ነው ምሁራኑ የኮሜዲን ተውኔት ትርጓሜ ለመስጠት ከትራጄዲ የተውኔት ዘውግ አኳያ እየተመለከቱ ትንታኔ እንዲሰጡ የተገደዱት፡፡ ይሁንና የቅርጾቹ መበራከት፣ ከታሪካዊ ዳራው ርዝማኔ፣ ከይዘቱ ወቅታዊነትና ክልላዊነት ውጭ ኮሜዲ በውስጡ የሚይዘው የሳቅ መንፈስ በትርጓሜው አስቸጋሪ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ይህ የሳቅ መንፈስ ከሰው ሰው ስለሚለይ ነው፡፡ በአንድ የኮሜዲ ተውኔት ውስጥ ያለው የሳቅ መንፈስ፣ ለሁለት የተለያዩ ተደራሲዎች ብናቀርበውም፣ አንደኛውን አስቆ፣ ሌላኛውን ላያስቀው ይችላል። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሳይቀር የሳቅ መንፈስ የተለያየ ነው፡፡ ለምሣሌ በተለያየ ባህል ውስጥ ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች በአንድ በኮሜዲ ተውኔት ውስጥ ያለ የሳቅ መንፈስ፣ አንደኛውን ክፍል አስቆ፣ ሌላኛውን የማህበረሰብ ክፍል ላያስቅ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ተደራሲያኑ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል የተውጣጡ መሆናቸው ነው፡፡ በማህበረሰባቸው ወግና ልማድ እስረኛ ስለሆኑ፣ አንደኛውን የማህበረሰብ ክፍል ያሳቀው የሳቅ መንፈስ ምናልባት ለሌላኛው የማህበረሰብ ክፍል ነውር  ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡ ሳቅ ስሜት ነው፡፡ ሊያስቅ የሚችልን ነገር ተመልክተን ወይም ሰምተን የምናመነጨው የደስታ ስሜት መግለጫ ነው፡፡ የሰብአዊ ፍጡር ስሜት ደግሞ ከግለሰብ ግለሰብ በእጅጉ ይለያያል፡፡ ሳቅም  ከግለሰብ ግለሰብ እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛውን ሰው ሊያስቅ የሚችል ክስተት ቢኖርም ማለት ነው፡፡
እንደ ስነልቦና ባለሙያዎቹም መላምት ከሆነ ግን ለመሳቃችን ወይም ለመደሰታችን  አዕምሮ  ነፃ መሆንና መዳበሩ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ይላሉ፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ኮሜዲ ካለፈባቸው የጊዜ ርዝማኔ፣ ከይዘቱ ወቅታዊነትና ክልላዊነት፣ ከቅርጾቹ መበራከት፣ እንዲሁም በውስጡ ከሚይዘው የሳቅ መንፈስ፣ ከሰው ሰው መለያየት ሳቢያ፣ ትርጓሜው አስቸጋሪ ነው ብለናል፡፡ ለዚህም ይመስላል ምሁራን ይህ ነው የሚል ትርጓሜ ከመስጠትና ምንነቱን በጉልህ ከማሳየት ይልቅ ኮሜዲ ወይም የሚያስቅ ማለት ነው በማለት ድፍን ያለ ትርጓሜ የሚሰጡት። እዚህ ላይ የሚያስቅ የምንለው ታድያ ምንድነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ እንደ አብዛኞቹ የስነ ልቦና ምሁራን እምነት፤ ሳቅ የሚፈጠረው ከቅራኔ እንደሆነ ይታመናል። እንዲያዉም ከጥንታዊው ፈላስፋ ከአርስቶትል እስካሁን ድረስ፣ ሳቅ የሚፈጥር ቅራኔ በምን መካከል እንደሆነ የየራሳቸውን አስተያየት ወይም አመለካከት ያቀርባሉ እንጂ በትክክለኛው ይህ ነው ብሎ የአንዱን ፈላስፋ ሀሳብ መቀበሉ ትክክል አይመስለኝም። ለምሳሌ አርስቶትል፣ ቅራኔው በቆንጆና በአስቀያሚ መካከል ያለው ነው ሲል፣ ሄግል ደግሞ በትክክለኛው የህይወት ክስተትና በኪነ ውበታዊው እሳቤ መሀከል ባለው ቅራኔ ነው ይላል፡፡ የሌሎቹንም ፈላስፎች እሳቤ ይዘረዝራል፡፡ የሆነዉ ሆኖ ኮሜዲ ተውኔት የተደራሲያንን መንፈስ ሳያስጨንቅ በደስታ እየሞላ የሚጓዝ ነው፡፡ በኮሜዲ ተውኔት ተደራሲያን መድረኩን የሚመለከቱት መንፈሳቸውን ሳያስጨንቁ በፈገግታ ነው፡፡ በኮሜዲ ተውኔት ውስጥ የማይገቡና ሊፈቱ የማይችሉ ጥያቄዎች የሉም፡፡ ኮሜዲ ተውኔት አብዛኛውን ጊዜ የሚያተኩረው፣ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ባለ ልምድ፣ ወግ፣ ባህል፣ እንዲሁም እሴቶች ላይ ነው። እነዚህ ዘላለማዊ ወይም ቋሚ አይደሉም። ኮሜዲ ተውኔት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ባሉ ሁኔታዎች ላይ ያተኩራል፡፡ በእለት ተእለት ኑሯቸው ውስጥ የሚታዩ ህጸጾችን አስቂኝ በሆነ መልኩ የሚያሳይ፣ አሳይቶም የሚያስተምር የተውኔቱ አይነት ነው፡፡
እንዲያዉም የሥነ ልቦና ባለሙያዎች፤ ሳቅ ከጀርባው ነጻ የሆነ ስሜትን የመፍጠር ሃይል አለው ይላሉ፡፡ ኮሜዲ ደግሞ በእውነታዉ ዓለም የሚገኘውን ይህን የተለየ የመገናኛ መስመር የምናገኝበት ዘዴ ነው፡፡ ሳቅና ፈገግታ ለማጫርም አስቂኝና አስደሳች ገለጻዎችን ይጠቀማል። በተውኔቱ ውስጥ በንግግር፣ በድርጊት፣ የገጸ ባህሪያቱን አለመስማማት የሚገልፁ ነገሮችን ይጠቀማል፡፡ ገጸ ባህሪያቱ እርስ በእርስ፣ ከራሳቸው ወይም ከልማድ፣ ከተፈጥሮ ሕግ እንዲሁም ከማህበረሰብ ጋር በሚያደርጉት ንግግር፣ ድርጊት፣ የጸባይ አለመስማማት ሳቅን ይፈጥራል፡፡ ከላይ በተደጋጋሚ እንደተገለፀው፤ ተቀዳሚ ተግባሩ እያሳቀ ማስተማር ስለሆነ፣ ያንን ሳቅ ለመፍጠር የተለያዩ ዘዴዎችንና ብልሃቶችን መጠቀም መቻል አለበት። የገፀ ባህሪያት አጠቃላይ ሰብእና፣ አካሄድ፣ አበላል፣ አነጋገር አለባበስ፣ ድርጊት.. ከተለመደው ውጪ መሆንና ለየት ማለት ለኮሜዲ ተውኔት የሳቅ ምንጭ በመሆን ያገለግላል፡፡ በድርጊት፣ በንግግር በአጠቃላይ በአስተሳሰብ የማይመጣጠኑ ተቃራኒ ገጸ ባህሪያትን በተውኔቱ ውስጥ በመቅረጽ ሳቅን ማጫር ይቻላል። ደበበ ሰይፉ፤ ኮሜዲ ተውኔት ውስጥ ውስብስብ የሆነ ዳኝነት የለም፡፡ ሁሉም እንደ የሰራው እና እንደ የበደሉ ዳኝነት ያገኛል፡፡ ገጸ ባህሪያቱ ሊወጡበት ወደ ማይችሉት የህይወት ስንክሳር ሲገቡ አይስተዋሉም፡፡ ይህ የተውኔት ዘውግ የአንድን ግለሰብና የማህበረሰብን የህይወት ግንኙነት ማንጸባረቅ ይችላል፡፡ ግለሰቡ ማህበረሰቡን ሴቶች ወይንም ማህበረሰቡ ግለሰቡን ሲተች ማሳየት ይችላል፡፡ ሁልጊዜም ለታሪኩ መነሻ የሚያደርገው፣ ማህበረሰቡንና በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኝውን ነገር ነው፡፡ በአጠቃላይ ኮሜዲ በሰዎች ልጆች መሀከል በሚገኙ ህጸጾች ዙሪያ በማተኮር ማህበረሰቡ በህጸጽ እየተዝናና እራሱን ዞሮ እንዲመለከትና ለችግሮቹ መፍትሄ ማፈላለግ እንዲችል ለመጠቆም አመች የሆነ የተውኔት ዘውግ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር አልቃሽና ዘፋኝ ተውኔትን ስንመለከት ከርዕሱ ጀምሮ የሚያስደምም ወይም ፈገግታን የሚያጭር ሲሆን ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦችን በመያዙ ነዉ ‹ሰርግና ሞት አንድ ነዉ› እዲሉ አልቃሽና ዘፋኝ የተጣመሩበት ነዉ። ከላይ ዕደተመለከት ነዉ ሳቅን ከሚፈጥርልን አንዱ ቅራኔ ወይም ተቃርኖ ነው በመሆኑም ይህንኑ ሀሳብ የሚጋራ ምርጥ ኮሜዲ ተውኔት ነው፡፡ በእርግጥ እንደተገለጸው አልቃሽና ዘፋኝ ተውኔትም ቢሆን ሁሉንም ተደራሲ ያስቃል ወይ የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሱ  ከላይ እደተጠቀሰዉ አንዱን ሲያስቀው ሌላውን ደግሞ ላያስቀው ይችላል ፡፡ አልቃሽና ዘፋኝ  ግን አብዛኛውን ተደራሲ የማሳቅ ሃይል ያለዉ ተውኔት ነው፡፡ በተለይ የገጸ ባህሪያቱ የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚጠቀሙት ቃለ ተውኔት ድርጊታቸው ሳቅን ከመፍጠር አልፎ ከገፅ ባህሪያቱ ጋር እያወራን እስከሚመስል ድረስ ቀልብን የመግዛትና ስሜትን ቆንጥጦ የመያዙ ጉልበት አለዉ፡፡ በርግጥ የአልቃሽና ዘፋኝ ተውኔት ከድርጊት ይልቅ ቃለ ተውኔቱ የበዛ ቢመስልም ቅሉ ከታሪኩ ጋር አብሮ እየተሳሰረ ስለሆነ ይበልጥ እየጋለ የሚሄድ ነው። የማሩና የአስጋርጅው  ፍላጎት የተለያዩ  መሆኑና የአደኛዉ ደስታ ለሌላኛዉ ሀዘን በመሆኑ አስቂኝነቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ያንዱ ፍላጎት ሲሳካ የሌላው ሲጎድል የሚያደርጉት ነገር የሚያወሩት ቃለ ተዉኔት ሳቅ ያጭራል፡፡
ለምሣሌ አንዱ ሳይሳካለት በሀዘን ውስጥ እየኖረ እንዴት ሳቅን ተፈጠረ የሚል ጥያቄ ሊያጭር ይችላል፡፡ ለገጸ ባህሪያቱ የሚያሳዝን ሆኖ ለተደራሲ ግን የሚያስቅ ቃለ ተውኔት የሚጠቀሙ ከሆነ በተጋነነ ድርጊት የተሞላ እንቅስቃሴ ከሆነ በተደራሲ ላይ ሳቅ መፍጠሩ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ነው ትራጄዲና ኮሜዲ ተደጋጋፊነት አላቸው የሚባለው፡፡ ማሩ ሰርጉ ተሳክቶለት አለመስራቱ ለሱ ሀዘን ተደራሲዉ ግን የሚናገረው ቃለ ተውኔት ከሚያደርገው ድርጊት ጋር ሳቅን ይፈጥራል፡፡ -  ይቀጥላል

Read 2272 times