Saturday, 23 June 2018 12:17

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - በሥነ ልቦና ሳይንስ መነጽር

Written by  ወንድወሰን ተሾመ (አልፋ የምርምርና የምክር አገልግሎት ማዕከል)
Rate this item
(1 Vote)

 የምንኖርበት አካባቢ በልጆች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ፣ በተለይም በዘለቄታው ህይወታችን እስከ አዋቂነት ዕድሜ ድረስ የሚታዩ በርካታ ጥቅሞችና ጉዳቶች ይኖሩታል፡፡ ይህ ደግሞ የሚወሰነው፣ ልጅ ወይም ልጅቷ ባደጉበት አካባቢ ነው፡፡ ለምሳሌ ሳይንቲስቶች በዘመናችን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰሩ ጥናቶችን መሰረት አድርገው ሲናገሩ፤ አረንጓዴና ለም አካባቢ፣ ምንጮችና ፏፏቴዎች በታደሉ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች፤ የአእምሮ መረጋጋት፣ ከዚያም በተጨማሪ የፈጠራ አቅም (ሃሳብ አመንጪነትን፣ የተለየ ምልከታ) ይጎናፀፋሉ፡፡ በዚህ አይነት አካባቢ የሚያድጉ ልጆች፣ በአንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ፣ በሚገባ ማሰብና መመራመርም ይችላሉ፡፡ በሕይወታቸው ደስተኛም ናቸው፡፡
በተለይ ለደስታቸው አንጎላቸው (ሴሬብራል ኮርቴክስ) ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮች አሉ፡፡ በተጨማሪም እንቅልፋቸውም የተስተካከለና ሁሌ እረፍት ያላቸው ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ጋር ብዙ የሚገናኝ የማይመስል ሌላ ነገርም አላቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ለሰዎች መራራት፣ በሌሎች ሰዎች ጫማ ቆመው ራሳቸውን እንዲሁም ሁኔታዎችን የማየት ችሎታ አላቸው፡፡ ጥናቶቹ ውስን ቢሆኑም የዚህ ዓይነቶቹን የሕይወት መልኮች ያንፀባርቃሉ፡፡ ይሁንና እነዚህን ሥነ ልቡናዊ ጥቅሞች በሚገባ ካልተንከባከብናቸው፣ በህይወት በሂደት ውስጥ ሊናዱ ይችላሉ፡፡
ወደ ማህበረሰቡ ስንመጣ፣ ደግ ማህበረሰብ ውስጥ ያደጉ፣ ይቅር የሚል፣ ቶሎ የሚግባባ፣ ተጣልቶ የሚታረቅ፣ ነገሮችን ቀለል አድርጎ በሚያይ ማህበረሰብ ውስጥ ያደጉ ልጆች፣ ከሌሎች ጋር የሚኖራቸው የተግባቦት ክህሎት የላቀ ነው፡፡ ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዴት መኖር እንደሚቻል እያወቁ ይሄዳሉ፡፡ ነገሮችን አያከርሩም፡፡ የበቀል ስሜት፣ “ቆይ” በሚል ቁርሾ፣ ነገሮችን ለሌላ ቀን ማሳደር አይችሉም፡፡ ክፋትን ጧትና ማታ አያሰላስሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ አካባቢ ጧት መራራ ጥል ተጣልተው፣ ከሰዓት አብረው ምሳ ሲበሉ የምናገኛቸው ማህበረሰቦች አሉ፡፡
በዚያ መሰል ማህበረሰብ ውስጥ የሚያሳልፉት ጊዜ፣ በተለይ በልጅነት ዕድሜ፣ እስከ አስራ አምስት ዓመት ባለው ዕድሜ ሲሆን፣ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል፡፡
ምናልባት የዶክተር ዐቢይ አህመድ አስተዳደግና አሁን እያሳዩት ያለው ባህርይ፣ የዚህ ዓይነት ማህበረሰብ ያለበት እንደሆነ መረጃው ስላለኝ፣ የዚያ ማህበረሰብ ነፀብራቅ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ስለ ሌሎች ሰዎች ማሰብ፣ በሰዎች እግር ሆኖ የሰዎችን ጭንቀትና እሮሮን መጋራት፣ ግራ መጋባትን መገንዘብ ከተወለዱበት አካባቢ ጋር ተያያዥነት ያለው ይመስለኛል፡፡
በሌላ በኩል፤ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በተለያዩ ተቋማት በቆዩባቸው ጊዜያት፣ በፖለቲካውና በተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች ሲያልፉ፣ እነዚያን ከስር የያዟቸውን ክህሎቶች አዳብረው፣ ሌሎች የሚሰማቸውን ስሜቶች ተካፍለው፣ የሰዎችን ሕመም ተሸክመው የኖሩ ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም ራሳቸውን እያዘጋጁ፣ ዕድልና ቀን ሲጠብቁ እንደቆዩ እገምታለሁ፡፡ ለአሁኑ ታሪካዊ አገር የመምራት ሃላፊነት፡፡  
እናትና ማኅበራዊነት
ጠቅላይ ሚኒስትራችን በበዐለ ሲመታቸው ላይ ሲናገሩ፤ እናታቸው ከሰባት ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ፣ እዚህ የመሪነት ቦታ ላይ እንደሚደርሱ በትንቢት መልክ እንደጠቆሟቸው መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ በልጆች ሥነ ልቡና ላይ የምንናገረው ቃል ትልቅ ድርሻ አለው። ንግግሮች ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ በስነ ልቡና ሳይንስ፣ ቃል ሰብዕናን ይፈጥራል፤ሰብዕናን ያፈርሳል ተብሎ ይታመናል፡፡ በተለይ በልጅነት የምንናገራቸው ቃላት፣ በልጆቹ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና አለው። በጎ መልዕክቶች፣ ገንቢ ሀሳቦች፣ የማበረታቻ ቃላት ስንናገር፣ ልጆቹ ውስጥ ጥንካሬን የሚፈጥር ሲሆን ለተነገረው  ዓላማ  ዝግጅት ለማድረግም ያነሳሳል፡፡
በተለይ የቅርብ ሰው የሚናገራቸው ቃል፣ በልጆች ላይ ለጥቅምም ለጉዳትም ወሳኝነት አለው። ይሁንና ለአንድ መንገደኛና የራሳቸው ቤተሰብ ለሚናገራቸው ነገር የሚሰጡት ግምት ተመጣጣኝና እኩል አይደለም። ለአንድ ልጅ እናቱ፤ “ልጄ ትልቅ ሰው ትሆናለህ!” ብትለውና አንድ መንገደኛ ያንኑ ቃል ቢለው፣ የሚሰማው ስሜትና የሚፈጥርበት ትርጉም የተለያየ ነው፡፡ ከልቡ አምኖ የሚቀበለው  የእናቱን ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የቅርብ ቤተሰቡ ሀሳብና ቃል፣ በበለጠ ሁኔታ በህይወቱ ላይ ቦታ ይኖረዋል፡፡ የዶክተር ዐቢይ እናት፤ በልጃቸው ላይ መልካም ቃል ዘርተዋል፤ ይህ ቃል ህይወት አለው፡፡  ያኔ የተናገሩት ነገር፣ ዛሬ በልጃቸው ህይወት ላይ እንደታየ መገንዘብ  ይቻላል፡፡
ሌላው የተለያየ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ልማድና አስተሳሰብ ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ ማደግ፣ የተለያዩ ሰዎችን አስተሳሰብና አመለካከት እንዲሁም አኗኗር የመገንዘብ ዕድል ይሰጣል፡፡ ከዚህም ባሻገር ልዩነት ባለበት በየትኛውም ቦታ፣ እንዴት ተቻችሎ በጥበብና በብልሃት መኖር እንደሚቻል የመለማመድ አቅም የማግኘት፣ በዚያም የመጠቀም ትልቅ ተሞክሮ  ያስገኛል፡፡
ለምሳሌ በተለያዩ ሀገራት፣ የተለያዩ ማህበረሰቦች ከሚኖሩበት አካባቢ የሚወጡ ሰዎች፣ ወደተለያዩ ዓለማት እንኳ ቢሄዱ፣ በነዚያ በሚሄዱባቸው ቦታዎች ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር በቀላሉ ተግባብቶና ተቻችሎ የመኖር ክህሎት ይኖራቸዋል፡፡ ይህ ክህሎት ያላቸው ሰዎች ወደ ሀገር መሪነት በሚመጡበት ጊዜ ደግሞ ሰዎች ተቻችለው መኖር እንደሚችሉ፣ አንዱ ለሌላው ፍቅርን ሰጥቶ፣ ይቅርታን አድርጎ፣ ሌላውን ተረድቶ የሚኖሩበት ዕድል ይሰጣቸዋል የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ በልጅነታችን ያሳለፍናቸው ነገሮች፣ በአዋቂነታችን የሚገለጡ ናቸው፡፡
እኔ ለሰዎች የምክር አገልግሎትና ስልጠና በምሰጥበት ጊዜ እንደገጠመኝ፣ አብዛኞቹ በ60 እና 70 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ አዛውንቶች፣ የችግሮቻቸው መነሻ ሆኖ የሚገኘው፣ የልጅነት አስተዳደጋቸው መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡
ለምሳሌ አንድ የ70 ዓመት አዛውንት፣ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት ቅኝት፣ ልጆቹን የባህርይ ችግር ውስጥ እየከተታቸው ስለተቸገሩ፣ እኔ ዘንድ መጥተው ችግሩን መፈተሽ ጀመርን፡፡ የማታ ማታም የአዛውንቱ ዋነኛ ችግር፣ ከአስተዳደጋቸው ጋር የተያያዘ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ 70 ዓመት ሆኗቸዋል፤ ይህንን ሁሉ ዘመን ዘልቆ የሚመጣው የልጅነት ትዝታ፣ የቤተሰብ ሃሳብ ሥዕል ነው፡፡ ስለዚህ በልጅነት ዘመን ጥሩ ቤተሰብና የተሻለ ተፈጥሯዊ አካባቢ፣ ተግባቢ ማህበረሰብ፣ የተለያዩ ብሔረሰቦችና የሃይማኖት ተከታዮች ባሉበት ማሳለፍ ጠቀሜታው የትየለሌ ነው። ዛሬ የምናየው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ቅርብ መሆንና በይቅርታ መንፈስ መሞላት፣ የዚህና የዚህ ዓይነቱ አሻራ ውጤት ነው ማለት ያስደፍራል፡፡
ከላይ ያነሳናቸውን አካባቢያዊ፣ ቤተሰባዊና ማህበረሰባዊ ገፅታዎችን አይተናል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ብቻቸውን የሰውን ልጅ ምሉዕ አያደርጉትም። ያደግንበት አካባቢ ሰዎች ለህይወት የሚሰጡት ትርጉም ምን ዓይነት ነው? የሚከተሉት ፍልስፍናና ስለ ህይወት ያላቸው አተያይ ምን ይመስላል? የሚለውም ወሳኝ የሚሆንበት ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡ አንዳንዴ የምንኖርበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ለህይወት ያላቸው ትርጉም ይዛባና በልተው ጠጥተው፣ ማለፍን ብቻ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ወሰናቸውም በጣም ቅርብና ቀላል ይሆናል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከሞት ባሻገር ስላለ ታሪክ፣ ለትውልድ ስለሚኖር ተስፋ፣ ለሌሎች ስለ መኖርና ለሌሎች ህልም ስለማቀፍ ሊሆን ይችላል የሚጨነቁት፡፡ ሌሎች ደግሞ ለራሳቸው ገንዘብ ስለ ማግኘት፣ የምቾት ህይወት ስለ ማሳለፍ፣ የዝና ማማ ላይ ስ መውጣት ይሆናል የሚያስቡት፡፡  
ይሁንና ለሌሎች ሕይወታቸውን የሚያጋሩ፣ የሌሎችን ፈንታ የሚኖሩ፣ ለሌሎቸ ህይወት መለወጥ የሚታትር ልብ ያላቸው ሰዎች፤ ስልጣን ላይ በሚወጡ ጊዜ ከዚህ መንፈሳዊ ህይወትና አተያይ በመነሳት፣ ለሚያስተዳድሩት ህዝብ ይህንኑ መልካምነት ማንፀባረቅ ይጀምራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በዚህ ምድር ላይ ሳለሁ “ማድረግ ያለብኝ ነገር ምንድነው? የህይወቴስ ግብ?” የሚል ጥያቄ ይኖራቸዋል፡፡ በመሆኑም የሚኖሩበትን ምክንያት ስለሚያውቁ፣ ውጤታማ የሆነ አመራር መስጠት ይችላሉ፡፡ ከፈጣሪ ጋር ያለ ግንኙነትም እንደዚሁ ለመሪዎች ማንነት ወሳኝ ነው። ለምሳሌ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችና መሪዎች “God Bless America” ይላሉ፡፡  “ፈጣሪ አሜሪካንን ይባርክ!” የሚለው ንግግር ለእኛ የሚያስቀና ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ታች ያለውን ተርታውን ሕዝብ ህይወት የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ ሃይማኖት አለ፡፡
በአውሮፓና አሜሪካ፤ ቤተሰብና ሃይማኖት በመሪዎች ዘንድ ትልቅ ግምት ይሰጠዋል፡፡ ስለ ቤተሰቡ የማይናገር የአሜሪካ መሪ አልገጠመኝም። ብዙዎቹ ከቤተሰብ ጋር ራሳቸውን ያቆራኙ ናቸው። ይህ ሰብዕናቸው እሴቶቻቸውን የሚያሳይ ነው። የኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም ባልተለመደ ሁኔታ፣ በፓርላማ ንግግራቸው ያሳዩት ይህንኑ ነው፡፡ በውስጣቸው ህልም ስላኖሩት እናታቸው፣ በህይወት መስመር አጋር ስለሆኗቸው ባለቤታቸው ተናግረው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የብዙዎችን ልብ የነካና ያስደመመ ነበር፡፡ ከዚያም ባለፈ ለሰዎች ቅርብ ያደርጋቸዋል፡፡
ስልጣን በያዙ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ማየታችን፣ የቀደሙት መሪዎች ባሳለፍናቸው ሃያ ሰባት ዓመታት፣ ለምን በአንድ ቀለበት ሲዞሩ ኖሩ? የሚል ጥያቄ ይፈጥራል፡፡
ለካስ እስረኞችን መፍታት ሀገርን አያተራምስም
ለካስ ሰዎችን ማስፈታት ሀገርን አያፈርስም
ለካስ በጎ መናገር አሉታዊ ውጤት የለውም
በማለት ሕዝብ እንዲደነቅ አድርጎል፡፡ ምክንያቱም የኛ ሀገር መሪዎች፣ ከዚህ ቀደም ወደተለያዩ ሀገራት ሄደዋል፡፡ ኬንያ ሄደዋል፣ ሱዳን ሄደዋል፣ ሌሎች ሀገራትም ሄደዋል፡፡ ነገር ግን ዜጎችን ለማስፈታት ጥረት ሲያደርጉ አልታየም፡፡ አስበውት የሚያውቁም አይመስሉም፡፡ ይህ ከአስተሳሰብ ጋር የተገናኘ፣ ቅድም ካልነው መንፈሳዊ የህይወት ፍልስፍና ጋር የተዛመደ፣ የህይወት ትርጉምና የዜግነት ክብርን መሰረት ያደረገ፣ ጥልቅ እሴት በአዲሱ ጠ/ሚኒስትራችን ውስጥ  መኖሩን ያሳያል፡፡
ይቅርታ፣ ፍቅር መደመር!
ኢትዮጵያዊነት ጠውልጎ ነበር፣ እንደገና እየለመለመ ነው፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ መልኳን እየቀየረች ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ጅማሬ ላይ ብንሆንም፣ የሚታዩት ምልክቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ የእስረኞች መፈታት፣ ሹመታቸውን ተከትሎ የመጣው ብሩህ ተስፋ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች የፈጠሯቸው ህልሞች፣ ባለስልጣናት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የተሰጣቸው አመራር ወዘተ--- በከፍተኛ ሁኔታ የህዝቡን የመኖር ጉጉት የሚያንርና ለትጋት የሚያነቃቃ ነው፡፡
የጎሳ ግጭቶች የሚፈጥሯቸው ችግሮች፣ ጉበኝነት፣ ሌብነትና የመሳሰሉት በመንሰራፋታቸው የተነሳ በተለይ ወጣቱ፣ ህይወቱ ተመሳቅሎ፣ ተስፋ በመቁረጥ፣ ለዓመታት ሀገሩን ጥሎ ሲሰደድ ኖሯል፡፡ የአሁኑ እንቅስቃሴ ግን ሰዎች ይህን ከመሰለ ተስፋ መቁረጥና ፍርሃት እንዲወጡ፣ በዜግነታቸው እንዲኮሩ፣ ከዚያም ባለፈ ህዝቦች በአንድነት እንዲያምኑ እየሰሩ ነው፡፡ አንድነት ጠቃሚ እንጂ ጎጂ እንዳልሆነ እያስተማሩና በተግባር እያሳዩ ነው፡፡ አንዱ የሌላውን መብት ማክበር የሚችልበትን አንድነት የመፍጠር ሂደት እየታየ ነው፡፡ ይህ ሀሳብና የዚህ ሀሳብ ማሄጃ ቃላት፣ እስከ ቤተሰብ ገብቶ ስራ ላይ እየዋለ ነው፡- “አብሮ መኖር፣ መደመር፣ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ምህረት” የሚለው፡፡  
እንደሚታወቀው፤ መሪዎች አንድን ትውልድ የመገንባትና የማፍረስ አቅም አላቸው፡፡ የመሪዎች ንግግርና ቋንቋ በህዝቡ ላይ የሚፈጥረው የአስተሳሰብና የኑሮ መልክ አለ፡፡ ለምሳሌ “ተፎካካሪ ፓርቲ” የሚለው ቃል፤ አሁን ህዝቡ እንዲጠቀምበት ሆኗል። ትርጉሙንና ሥዕሉንም ይቀይረዋል፡፡ ከባላንጣነት ስሜት ይልቅ ለጋራ ጉዳይ መወዳደርን ያሳያል። “መደመር!” የሚለው ቃል በጣም አዎንታዊ ነው። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት፣ አብሮ መኖር፣ ተጋግዞ፣ ተያይዞ ይቅር በመባባል ሀገር ማልማት ነው፡፡ በተለይ ለብዙ ዓመታት የተጎዳች አገር ከመሆኗ አንጻር  ይህ እንደ ህክምና ነው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነው፡፡
ለምሳሌ ፍቅር ሲኖር ሰዎች ይታገሳሉ፤ ፍቅር ሲኖር ሰዎች መልካም ነገር ያደርጋሉ፡፡፡ ስለ መስጠታቸው እንጂ ስለ መቀበላቸው አያስቡም፡፡ ፍቅር ሲኖር ለሀገር ማሰብ ይጀመራል፣ ከራስ ወዳድነት መውጣት ይቻላል። ፍቅር ሲኖር ስለ ጎረቤት፣ ስለ ሥራ ባልደረባ፣ ስለ ዜጎች ማሰብና መመኘት ይጀመራል፡፡ ወደ ምህረት ስንመጣ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካው ዓለም የተለመደው፣ አንዱ ወደ ስልጣን ሲመጣ፣ የቀደመውን የመበቀል ዝንባሌ ነበረው፡፡ ይህ ብዙ አያስኬድም። አንዳንድ አሰራሮችን መቀየር ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይቅርታ ማድረግ አብሮ ለመኖር፣ የሚባጅ ነገር ነው። የበደሉንን ሰዎች ይቅር ስንል፣ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት፣ ቀንና ሌሊት ሲያሰላ ጊዜውን አይፈጅም፡፡ ይልቅስ ሕዝቡ በጤናማ አእምሮ፣ ለሀገሪቱ ዕድገት የተሻለ ሥራ ይሰራል ብዬ አምናለሁ፡፡
በመበቀል የምናገኘው ነገር የለም፤ በይቅርታ ግን እንደ ሀገር ብዙ እንጠቀማለን፡፡ በተቻለ መጠን ስለ ምህረት ማሰቡ መልካም ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ያጠፉ ሰዎች አይቀጡም ማለት ነው ብዬ አላስብም፡፡ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት የሚዳኙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ከዚያ ውጭ አንዱ ሌላውን በጠላትነት የሚፈርጅበት ነገር መወገድ አለበት፣ በሚለው ሀሳብ በጣም እስማማለሁ።
በነዚህ ተስፋ ባዘሉ ሀሳቦችና መመሪያዎች፣ ሀገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግና የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር፣ እያንዳንዳችን የየራሳችንን ችቦ መለኮስ እንዳለብን መገመት አያቅትም፡፡ ለውጡን ወደፊት ለማስኬድና ከግብ ለማድረስ፣ የሁሉም ዜጋ ሚና ወሳኝ ስለሆነ፣ ቀጣዩ ጊዜ የሁላችንንም ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ ለመልካም እርምጃዎች፣ ለበጎ ህልም አብሮ መቆም ግድ ይላል፡፡ መልካም የሆኑ እንቅስቃሴዎችን የምናጥላላና ዝቅ የምናደርግ ከሆነ፣ ለመልካም መሪዎች እንቅፋት ይሆናል፡፡

Read 2546 times