Print this page
Saturday, 23 June 2018 12:21

“ወዳጅና ወዳጅ፣ የተጣላ እንደሆን መታረቁም አይቀር፣ እንደጥንቱም አይሆን” - ( አገርኛ ግጥም)

Written by 
Rate this item
(9 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ ኢትዮ-ኤርትሪያ ጦርነት ሊጀመር ሰሞን፤ አንድ ክስተት ላይ ተመርኩዞ በዚህ ጋዜጣ፣ ተረት መሰል ትርክት አቅርበን ነበር፡፡ አንዳንድ ዕውነት እጅግ ሲቆይ ተረት ይመስላል፡፡ ዕውነትና ተረት አንዳንዴ በጣም ከመቀራረባቸው የተነሳ አንዱ አንዱን ተክቶ የሁኔታዎች መግለጫ፣ አሊያም የሂደቶች አንዳች መተንተኛ ይሆናል፡፡ እንግዲህ ያኔ የሚከተለውን ፅፈን ነበር፡፡
እነሆ ዛሬ፤
“ጊዜ በጊዜ ቀለበት
ሰተት …” ሆነና ደግመን እናየው ዘንድ ወቅቱን ጠብቆ ፋይዳው ፍንትው አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በትግራይ ክልል ለስራ ጉዳይ ሄደን ሳለን፤ ዋና ዋና ጉዳያችንን ፈፃፅመን ስናበቃ፤ ወደ ማታ ግድም ትንሽ ዘና የማለት ፍላጎት አድሮብን፣ ከአንድ ቡና ቤት ወደ ሌላ እየተዘዋወርን ስንጫወት፤ ስናወጋና ጭፈራ ስናይ እያመሸን ሳለን፤ በአንደኛው መዝናኛ ቦታ የኤርትራ ዘፋኝ የሚጫወተው ዘፈን ይዘፈናል፡፡ ሰው በየነሸጠው ቅፅበት እየተነሳ ይጨፍራል፡፡ ይደነክራል፡፡ የደከመው ይቀመጣል፡፡ ሌላው በራሱ ጊዜ ይነሳል፡፡
በአጋጣሚ ከእኛ ከአዲሳቤዎቹ እንግዶች አጠገብ የተቀመጡ የዚያው ክልል ሰው፣ ጎምቱ አዛውንት ናቸው፤ ነሸጣቸውና ብቻቸውን ተነስተው ያስነኩት ጀመር - ጭፈራውን፡፡ እስኪበቃቸው ተወዛውዘው መጥተው አጠገባችን ተቀመጡ፡፡
የገረመንን አንድ አንድ ጥያቄዎች ከሰላምታ በኋላ እያነሳን መጨዋወት ቀጠልን፡፡
“እንግዳ ትመስላላችሁ?” አሉ፡፡
“አዎን ከአዲሳባ ነን፡፡ ደሴ አድረን ነው ወደዚህ የመጣን”
“ለሥራ ነው፣ አገር ለማየት? የመጣችሁት?”
“ለሥራ ነው፡፡ ሆኖም ሥራችንን ስናገባድድ፣ አገር ማየታችን አይቀርም መቼም ….
እርስዎ መቼም የዚሁ አገር ሰው መሆንዎ አያጠራጥርም”
“አዎ እዚሁ ነኝ፡፡”
“አሁን ተነስተው ሲጨፍሩ ገርሞን ነበር የምናይዎት”
“በስተ እርጅና እንዴት ይጨፍራል ብላችሁ ነው?”
“ኧረ አይደለም”
“ታዲያ ምንድን ነው ያስገረማችሁ?”
“በሀገራችን እንደምንሰማው ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ ልንገባ አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ደርሰናል ነው የሚባለው”
“አዎን”፤ አሉ አቦይ ሳያመነቱ፡፡
“ይሄ አሁን ሙዚቃው የሚጫወተው ዘፈን ደግሞ ኤርትራዊ ዘፋኝ የሚዘፍነው፤ የኤርትራዊ ዜማ ቅኝት ነው፡፡”
“እንዴታ?!”
“እንዴት ሊሆን ይችላል? ባሁኑ ሰዓት እንዴት ሊዘፈን ቻለ? እርሶስ እንደምን ይደንሱበታል!”
አቦይ፤ አልተደናገጡም፡፡ ግር ማለትም አልታየባቸውም፡፡
“አያችሁ ልጆቼ! አዲሳባ ሆናችሁ ስለ ኤርትራና ኢትዮጵያ ድንበር ጦርነት የሰማችሁት ሁሉ ዕውነት ነው፡፡ ጦርነቱ አይቀሬ ነው፡፡ ደም መፋሰስ ይኖራል፡፡ ከሁለቱም ወገን ሰው ያልቃል፡፡ ጥንት የነበረው አብሮ መኖር ሁሉ ይቀራል!
ግን አንድ ፅኑ ዕውነት ልንገራችሁ፡፡ በኤርትራና በትግራይ (በኢትዮጵያ) ድንበር መካከል፣ በሥራቅና ምዕራብ ጀርመን መሀል እንደነበረው ዓይነት ታላቅ ግንብ ቢገነባ እንኳን፤ ለካሴት መቀባበያ የምትሆን አንዲት መስኮት ትኖራለች!!” አሉና “ተነሱ እንጫወት እባካችሁ!” ብለው “ደርብ!” አሉ፡፡ ጭፈራው በጣም ያምርባቸዋል፡፡
*   *   *
ያቺ የአቦይ መስኮት የባህል በር ናት፡፡ የታሪክ በር ናት፡፡ የልብ ለልብ መተሳሰቢያ ምት ናት! የህዝብ መተናፈሻ ናት!! ከሥጋ ዝምድና፣ እስከ ጋብቻ፣ በጉርብትና ቡና ከመጠራራት እስከ ጠቅላይ አብሮ መኖር ድረስ በዚያች መስኮት ታሪካዊ ቅብብሎሹ ይቀጥላል፡፡ ትላንት ነበረ፣ ዛሬም አለ፡፡ ነገም ይኖራል!! እንደ ዛሬ በራሱ ጊዜ መስኮቱ ሰፊ በር፣ ሰፊው በር ደግሞ ዋናው “ከተም በሪ” ይሆናል፡፡ ብሎ ማን ያስባል? ወይም ደግሞ ግንቡ እንደ ጀርመኑ ግንብ እስከናካቴው ይፈራርስ ይሆናል፡፡ ከዚያም የምናስተውለውን ወለል ያለ ሰፊ እይታ እናስብ፡፡ ገላጣውን የአንድነት አውላላ ሜዳ (ፈረንጆቹ WIDER VISTA የሚሉትን ዓይነት) እንደምን በፍቅር አንቀልባ ጠቅልለን እንደምንይዘው ከርቀት እንይ፡፡
ዛሬ! ጊዜው በራሱ ጊዜ ወገግ ያለ ይመስላል፡፡ እኛስ?
“ጊዜ በራሱ ጊዜ ወገግ
ጭፍግ የራሱን ጭጋግ ጥርግ
ዕድሜ በራሱ ሰዓት ፈገግ! …
እንል ይሆን ቀን ሳንሸሽግ?!
የት ድረስ ነው የምኞት ድግ?
የት ድረስ ነው የተስፋስ ጥግ?...”
ዛሬ! የይቅርታ መስኮት አንድ ፀጋ ነው፡፡ የህገ መንግሥት ሥርዓትና መልክ መያዝ ሌላ መስኮት ነው፡፡ የንቃተ - ህሊናችን ማደግ፣ የትጋታችን መቀስቀስ፣ የተስፋችን ማበብ ዋና በር ነው! ከሁሉም በላይ ግን ዜጋን የማፈን፣ የመሸሸግ፣ የውስጥ ውስጡን መመሳጠር፣ የእስር ቤት አሰቃቂ ህይወት፣ የሸፋፍነህ ግዛ ኢ-ፍትሐዊ ግፍ፣ የነጋዴ ቢሮክራቶች ፖለቲካ - ኢኮኖሚያዊ ምዝበራ፣ የመንግሥት መጨቆኛ መሳሪያዎች ቁልፉ ፍሬ ነገር ነው! የቅርቡ የኢትዮጵያ የሥርዓት እርምት፣ ሽግሽግ፣ ሽግግርና እድሳት አዲስ ሂደት፤ ህዝበ - ሱታፌን የሚጠይቅ፣ ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር መሆኗን በአንድ አፍ፣ በአንድ ልብና በአንድ አቅም፣ አንድም ሦስትም ነን በሚሰኝ ብልሃትና ጥበብ-ተስፈኛ፣ አዎንታዊ እና ልበ - ሙሉ አገር ለዋጮች የምንሆንበት ይመስለናል፡፡
ዛሬ!
እስቲ ከቁጣ፣ ከቂም፣ ከበቀል፣ ‹ከእኔ ብቻ ነኝ ልክ› እንውጣና እራሳችንን ከፍቅርና ከሰላም አቅል አቅጣጫ እንመልከት የምንልበት ቀን ነው! ያጣናቸውንና ያመለጡንን፣ ያልተጠቀምንባቸውን ቀና ነገሮች ሁሉ፣ በቁጭት ከመመንዘር ይልቅ፣ “ነገ የሚባል የማናውቀው ቀን እንይ” ብለን አሰልቺውን ህይወት፣ ከሻካራ ገፁ የምንነጥልበት የምናበለፅግበት ቀን መጥቷል፡፡ ትላንት የቆሰልነውና የደማንበት! “አሸነፍን አላሸነፍን” የተባባልንበት፡፡ በታሪክ፣ በባህል፣ በሃይማኖት አስተሳስሮን፣ አንጀታችን ገብቶ፣ አድሮ የማይሞተውን ፍቅራችንን የሚተካ፣ ዞሮ መግቢያና ማረፊያ አገራችንን የሚያኮራ፣ የማቴሪያልም ሆነ የአካላዊ ጥቅም ፍሬ አላገኘንበትም፡፡ ዋጋው የማይለካ (Priceless እንዲሉ) ነገር! ወንድማማችነታችን፣ ተዛምዶአችን፣ መጋባት መዋለዳችን፤ መግባባትና አብረን መሳቃችን፣ አብረን ማደጋችን፤ የማይበጠስ ማተባችን፣ መንፈሳዊ መቀንቻችን የሁልጊዜ ህልውናችን መሆኑን፣ ዛሬ ባንድ ልብና ልቦና አሳድረነዋል! አንድነት የጠራ ሀቃችን (Crystal Truth) መሆኑን፣ የማይሸራረፍ ህልውናችን መሆኑን፣ የማታ ማታም ቢሆን ነብሳችን ላይ መንቀሳችን ቀዳሚና ላዕላይ እሴታችንን ማስረገጣችንን እንድናሰምር አግዞናል! ለዚህና ስለዚህም ምስክርነት የሚሰጥ፣ ከእኛና ከእኛ ሌላ ማን አለ?
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ በአንደኛው ተውኔቱ ውስጥ ስለ እሥር ቤት የነገረንን ዛሬ ብናስታውስ ደግ ነው፡፡ ባጭሩ ጃንሆይ ወህኒ ቤትን መርቀው ሲከፍቱ ያደረጉት ንግግር ነው፡-
“የአባታችን ርስተ - ጉልት የሆነውን ይህንን የሀገር ወህኒ ቤት መርቀን ስንከፍትላችሁ፤ እናንተም፤ በተለመደው ባህላችሁ፣ በመተሳሰብ እንድትተሳሰሩበት ነው!”
አንዳችን አንዳችንን ስናስር ኖረናል፡፡ በየታሪካችን ምዕራፍ እንደተቀመጠው፤ ጦር ሰብቀን፣ ዘገር ነቅንቀን፣ ደም ተፋሰን፣ ሬሳ ተቋጥረን፣ ድንበር ተቋርሰን፣ … የሁለንተናችን መገለጫ ሰውና የሰው ሰላም መሆኑን አናምንም ብለን፤ እንደ ጉልት ደንጊያ አንነቀነቅ ብለን፤ በጉድ አዋጅ እንደታጠርን ብዙ የደም ዘመን ገፋን! ዛሬስ ይብቃን! ዛሬ በሰፊ አዕምሮ ስናስተውለው፤ “ለዚሁ ነው በሬዬን ያረድኩት?” እንዳለው ሰውዬ መሆናችንን በትዝብት ተገነዘብን! ለልጆቻችን የምናወርሰው ፍቅርና ግብረገብነት የሌለን፣ ባዶ ልብና ባዶ ኪስ ነን! ታሪክ እያለን ታሪክ እንደሌለን የሆንንበትን ምክንያት መመርመር አለብን! ታሪክ ሰሪም፣ ታሪክ - ፀሐፊም ማጣት እርግማን ነው! ኦና ቤት ውስጥ የነግ ዕጣ - ፈንታውን ሳያውቅ እንደተቀመጠ እንስሳ ሆነን መኖራችን ደግሞ የከፋ እርግማን ነው!
“እራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል” (Regional autonomy upto and including cessation) የማለትን መርህ እያስታወስን፤ ወደ ኋላ እየሳቅን፣ ወደፊት ለመራመድ የምናስብበት ወቅት ይመስላል!
ዛሬ!
ጦርነት ኋላ ቀር ነው የሚለውን ሃሳብ እንደ “ማጨስ የፋራ ነው” እንደማለት ማስተዛዘብ ጀምረናል፡፡ ቤርቶልት ብሬሽት “ጀግና የማትወልድ አገር የታደለች ናት!” ያለንን መቀበል ላይ ነን፡፡
የደም ጀግንነት ይብቃን እንደማለት ነው፡፡ “የሰሜንን እህል፣ አልበላም እርሜ ነው ያጨደው መትረየስ፣ ያፈሰሰው ደም ነው!” ያልነውን የምር አረግነው እንደማለት ነው፡፡ ሁሉንም በዲሞክራሲ ገበታ ላይ ብንመካከረውስ? ማለት ስልጣኔ ነው! ወደ ሥልጣኔ ገበታ እኩል እጃችንን መሰንዘር መቻል መታደል ነው! ጥቂቶች የሚሞቁት ደመራ ሳይሆን ሁሉም ችቦ ችቦውን ይዞ “እዮሃ!” የሚልበት በዓል ዘንድ እየደረስን ነው፡፡
የትላንትናን ጥፋት በአንዲት በዛሬ ጀንበር እንሰርዘዋለን ማለት የዋህነት መሆኑን አላጣነውም! ይቅርታን መድፈር ብርቱ ጅማሮ ነው! እርቅ ኃያል ግለ - ሂስ ነው! ያማል ግን ያድናል! ዛሬም ለውጥ አዳጊ ሂደት እንጂ በቁርጥ ክፍያ የሚጨረስ የቀን ሥራ አይደለም! ስንል እንደኖርነው ሁሉ፣ ዛሬም Change is an incremental process- አዳጊ ሂደት ነው! የሁላችንም ድምፅ ወደሚሰማበት አገር ለመሄድ መንገድ መጀመር ነው ዲሞክራሲ፡፡ ዲሞክራሲን ያፈንነው እኛ ነንና፣ የምንፈታውም እኛው ነን! ያማረ ነገር ስናይ “ምነው የእኔ በሆነ” ማለት ሰብዓዊ ምኞት ነው፡፡ “ያ ያማረ ነገር ምነው የእኔ ብቻ በሆነ” ማለት ግን ገና ከጥንስሱ ጤና ያጣ ፍላጎትን ያዘለ ነው፡፡ ሁሉም ነገር፤ የተጣመመው ተቃንቶ፣ የተበላሸው ተስተካክሎ፣ ፀድቶ እንደነበረው እንዲሆን ለማድረግ መጣጣራችን መልካም ነው፡፡ ሆኖም ዛሬ ሌላ ጠዋት ነውና፣ ራሱን ትላንት ጠዋትን ካላገኘሁ ሞቼ እገኛለሁ አንበል፡፡ እንኳን ትላንት ጠዋት፣ ነገ ጠዋትም ሌላ ነው!
“ወዳጅና ወዳጅ፣ የተጣላ እንደሆን
መታረቁም አይቀር፣ እንደጥንቱም አይሆን!”
ተብሎ ሲነገር የኖረው Nothing remains the same; everything changes except the law of change (ምንም ነገር እንዳለ አይቆይም፡፡ ሁሉ ተለዋጭ ነው፣ ከለውጥ ህግ በስተቀር! እንደማለት ነው፡፡) ከዚህ ተነስተን በስንኝ ጥያቄ ብንቋጥር፤
ለሁሉም ጊዜ አለው ብሏል ሰለሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
 መገንጠል የሚሞት ምን ጊዜ እንደሆን?
በለውጥ ጎዳና ላይ የማስጠንቀቂያ ደወል አለ፡፡ እንዲሁም የህይወት ሂደት፡፡
“የአገራችን ፖለቲከኞች ዋና ችግር ማክረር ነው - ሁሉን ነገር ማጥበቅ! ስለዚህ ላላ ፈታ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አይመስልህም?” ብሎ ቢጠይቀው፤
“መላላቱንም አታጥብቀው!” አለው፡፡ የጀመርነውን ተስፋ ያዝልቅልን!!  

Read 11126 times
Administrator

Latest from Administrator