Saturday, 23 June 2018 12:25

“ሹመቱ ከሁለትና ከሦስት ዓመት በፊት ቢሰጠኝ አልቀበልም ነበር”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የሙዚቃ መምህርና ሃያሲ ሰርፀ ፍሬ ስብሃት፣ ከሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ም/ዋና ዳይሬክተር ሆኖ እንዲያገለግል፣ በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተመርጦ ተሹሟል፡፡ አሁን ለተሾመበት ቦታ ሲመረጥ ምን ተሰማው? በቱሪዝም ድርጅት ምን ሊሰራ አቅዶ ይሆን? በሚሉትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ፣ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

   እስቲ ስለ አዲሱ ሹመት የተሰማህን ንገረኝ …
እኔ እንግዲህ እስካሁን በኪነ ጥበቡ ውስጥ የመጣሁበትና የታወቅኩበት መንገድ አለ፡፡ አሁን ደግሞ ድንገተኛም ቢሆን፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ የለውጥ መንፈስ ጋር አብሮ በሚታይ መልኩ፣ የሙያና የእውቀት ሰዎችን ወደ አመራር ማምጣት የታመነበት ይመስለኛል። እኔም በዚህ ውስጥ በመታሰቤና በመመረጤ እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ አሁን የተሾምኩበት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት፣ከአምስት ዓመታት በፊት፣ በቱሪዝም ዘርፍ ይታይ የነበሩ ችግሮች በትልቅ አቅም የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ትልቅ ስራ እንዲሰራ በትልቅ ፍላጎትም ጭምር ነው የተቋቋመው። ቱሪዝም ደግሞ ጥበቡን፣ ባህሉን፣ የተፈጥሮ ሃብቱን----እነዚህን ሁሉ ለዓለም አቀፍ እውቂያ የሚያበቃ ትልቅ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ሁሉን በአንድ የሚያስተሳስር ነው፡፡ ጥበቡን ብንሰራ ስልጣኔውን ብንሰራ፣ ሌላውንም ብናቀናጅ፣ ሁሉም እይታ ይፈልጋል፡፡ መታየት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚው ውስጥም ቀጥታ ጣልቃ ገብቶ ሚና መጫወት አለበት፡፡
ስለዚህ የተሾምክበት ቦታ ከፍተኛ ኃላፊነትና ትጋት የሚጠበቅበት ይመስለኛል…
እጅግ በጣም ከፍተኛ ኃላፊነት ነው፤በአገር ቁምነገር ደረጃ ትልቅ ኃላፊነት ላይ እንድሰራ ነው የተመረጥኩት።
ሹመቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት የመጣ ይመስለኛል?
ትክክል ነው፡፡ ደብዳቤው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 294/2005 አንቀፅ 11 ንዑስ አንቀፅ ሁለት መሰረት፤ ከሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙ መሆኑን አስታውቃለሁ የሚልና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥምና ፊርማ የወጣ የሹመት ደብዳቤ ነው የደረሰኝ፡፡
ሹመቱ አንተም እንዳልከው ድንገተኛ ቢሆንም በባህል ዘርፎች አንዱና ዋነኛው በሆነው በሙዚቃ ውስጥ ስትሰራ ቆይተሃል፤ አሁንስ ምን ለመስራት አቀድክ?
እንግዲህ በቀጥታም ባይሆን የሙዚቀኞች ማህበርን ስመራ በነበረበት ጊዜ፣ ቀጥታ እንገናኝ የነበረው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ነበር፡፡ ቀጥታ ተጠሪነቱም ለእኛ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነበር፡፡ በዛን ጊዜ ያሉትን ነገሮች በማወቅ፣ እንደው እነዚህ ነገሮች እንዲህ ቢሆኑ እንዲህ ቢደረጉ እያልኩ ሳውጠነጥናቸው የነበሩ ነገሮች ነበሩ፡፡
እስኪ ምን አይነት ሃሳቦች ነበሩ?
ለምሳሌ በስትራክቸር ደረጃ፤ ባህሉን፣ስነ ጥበቡንና ቱሪዝሙን የነጠለ፣ትልቅ መዋቅር ያስፈልጋል። እያንዳንዳቸው በተናጠል ሰዎች እንዲረዷቸው እንዲደረጉና ተቋማዊ ጥንካሬ ኖሯቸው፣ ነገር ግን በጎንዮሽ ግንኙነት ኖሯቸው፣ ተናብበው እንዲሰሩ ቢደረግ፣ የሚል ትልቅ ምኞትና ፍላጎት ነበረኝ፡፡ በዚህ ምክንያት መነጣጠላቸው፣ከዚህ ቀደም ለአንዱ ትኩረት ሲሰጥ፣ ለአንዱ ትኩረት ሲዳከም ሌላውም እንደዚህ አትኩሮት ሲነፍገው ሁሌ የምናስተውለው ችግር ነበር፡፡ አሁን ግን እነዚያ አዕምሮዬ ላይ የነበሩትን ሀሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ፣ በቢሮ ውስጥ በሌሎች ኤክስፐርቶች የነበሩ፣ በደንብ ተጠንተው፣ አዲስ የሆነና ጥበቡን ያካተተ ትልቅ እይታና አሰራር መፍጠር ይቻላል፡፡
ልማታዊውንም ሆነ ፕሮሞሽናል ጎኑን፣ ሁለቱንም በጥሩ ሁኔታ ማስኬድ የሚቻልበት መንገድ አለ የሚለው እምነት፣ በውስጤ ስላደረ፣ እሱን እያጠናሁና እየተዘጋጀሁ ነው ያለሁት፡፡ ከቆዩ ልምዶችም ብዙ የምማራቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ታዋቂ የሆኑና እድሜ ልካቸውን ቱሪዝም ላይ የሰሩ ባለሙያዎች ያሉበት ቤት እንደመሆኑ፣ እነሱ  ያጋጠሟቸው ችግሮች፣ እሱን ለመፍታት ያጠኗቸው ጥናቶች እውን የሚሆኑበትን ትልቅ መስመር መፍጠርና ያንን ምቹ ሁኔታ ለእነሱ ማመቻቸትና ይሄም ያለ ምንም ገደብ እስከ ላይ መዋቅር ድረስ አሰራሩ ምቹ የሚሆንበትን መንገድ ለማመቻቸት ዝግጁ ነኝ፡፡ እንግዲህ እስኪ እንሄድበታለን፡፡
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለብሔራዊ ቴአትር፣ ረ/ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬን፣ ለብሔራዊ ባህል ማዕከል አቶ ተስፋዬ ሽመልስን መሾማቸው ይታወሳል። ከነዚህ ተቋማት ጋርም ሆነ ከተሾሙት ዳይሬክተሮች ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ቦታ ላይ እንደ መሾምህ ወደፊት በትብብር ምን ለመስራት እያሰብክ ነው?
እንግዲህ ለእነዚህ ተቋማት ትክክለኛ ባለሞያዎች የመሾማቸውን ጥቅም ልንገርሽ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በቱሪዝም ዘርፍ ሲታዩ የነበሩት የተፈጥሮ ሀብቶች፣ የቀደምት ስልጣኔ ውጤት የሆኑ ቅርሶችና ቁሳቁሶች ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ግን የክዋኔ ጥበቦች (ፐርፎርሚንግ አርትስ) የምንላቸው የቱሪዝሙ አካል ናቸው፡፡ የፈጠራ ስራዎችና ከተማ ውስጥ የሚካሄዱ ትልልቅ ሁነቶችን ሁሉ ሳያዩ፣ ቱሪስቶች ቀጥታ ወደ አክሱም ላሊበላ ነው የሚሄዱት፡፡ እነዚህን ሁነቶችና የክዋኔ ጥበቦች፣ ከቱሪስቱ ጋር የኢኮኖሚ ቀጥታ ግንኙነት ከፈጠርንላቸው፣ ጥበቦች የኢኮኖሚ ምንጭ ይሆናሉ። ከዚያም በላይ በጣም አድገው የመስራትና በጣም ውድና የተከበሩ የመሆን እድላቸው ይሰፋል። ጥበበኛውም ያድጋል፡፡ ጥበቡንና ከተማዋን ሁሉ ለእይታና ለጉብኝት የተመቻቸ ቦታ የማድረግ አጋጣሚው ይፈጠራል፡፡
እነዚህ እውን ሲሆኑ የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜም የሚያራዝሙት ይመስለኛል …
ትክክል ነሽ! ቱሪስቶች ለምሳሌ ሂልተን ያርፉና በጠዋት ተነስተው፣ በአውሮፕላን ወደ አክሱምና ወደ ላሊበላ ነው የሚሄዱት፡፡ እዚህ እንዲቆዩ የሚያደርግ ነገር ስላልፈጠርንላቸው አይቆዩም፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ እነዚህን ጥበቦች በደንብ ከሰራንባቸው ይቆያሉ፡፡ አርቶቹ የሚሰሩባቸው ቦታዎች፣ አርቲስቶቹም በየጊዜው ስራ ይኖራቸዋል። ጥበበኞችም አገርም የኢኮኖሚ  ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህንን ሁሌም ከብሔራዊ ቴአትርና ከብሔራዊ የባህል ማዕከል ጋር በማገናኘት ጥሩ ስራ ይሰራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትን መፍጠር አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ሶስቱ ተቋማት በቅንጅት ትልቅ ሥራ መስራት ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ጋር ከዚህ ቀደም ተገናኝታችሁ ታውቃላችሁ?
ዶ/ር አብይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በቅጅ መብት ምክንያት ቀጥታ ጉዳያችን ከሚኒስቴሩ ጋር ይገናኝ ስለነበር፣ እዛ ተገናኝተን እናውቃለን፤ ነገር ግን ያ የተገናኘንበት አጋጣሚ የእኔን ብቸኛ ሚና የሚያሳይ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ከተለያዩ የኪነ ጥበብ የሙያ ማህበራት አባላት ጋር ነበር የሄድነው፡፡ እነ ድምፃዊ ፀጋዬ እሸቱ ነበሩ፡፡ የኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማህበር ሰዎችም ነበሩ፡፡ ሌሎችም አብረውን ነበሩ፡፡ ከዛ ውጭ በተለየ አጋጣሚ የተገናኘንበት ጊዜ የለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየዘርፉ ለቦታው ይመጥናሉ ያሉ የዕውቀት ሰዎችን እየሾሙ ነው፡፡ ይሄን እንዴት ታየዋለህ?
ትክክል ነው! እኔን ለምሳሌ ከሁለትና ከሶስት ዓመት በፊት ሹመት ቢሰጥህ ትቀበል ነበር ወይ ብትይኝ፣ በፍፁም አልቀበልም፡፡ አሁን የተቀበልኩት የአጠቃላይ የአገሪቱን የለውጥ መንፈስ በማየት ነው፡፡ ከዛ በፊት ያለውን ወንበሩን ምን አይነት እንደሆነ አውቀዋለሁ፤ አሰራርና አካሄዱንም በደንብ ስለማውቀው አልቀበልም ነበር፡፡ አሁን የተሰጠኝን ኃላፊነት ለመወጣት እጥራለሁ። የለውጡ አካል በመሆኔ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡

Read 4750 times