Sunday, 01 July 2018 00:00

“ጥይት የሚገድለው የለውጥ አራማጁን እንጂ ለውጡን አይደለም” - ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በቅዳሜው የመስቀል አደባባይ ሠላማዊ ሠልፍ ላይ ስለ ተፈፀመው የቦንብ ጥቃት ባደረጉት ገለፃ፤ “ኢትዮጵያ አሁን የለውጥ ፕሮጀክት ውስጥ ነች፤ ጥይት የሚገድለው የለውጥ አራማጁን እንጂ ለውጡን አይደለም” ብለዋል፡፡
በዚህ ስልጠና ተኮር ውይይት ላይ ሃገሪቱ በሁለንተናዊ ለውጥ ውስጥ እንደምትገኝ የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከአሁኑ በኋላ ኢትዮጵያን ከፍቅር፣ ከእኩልነት፣ ከፍትህና፣ ከዲሞክራሲ ውጭ ማስቀጠል እንደማይቻል አስገንዝበዋል፡፡
ራዕያቸውም ከኢትዮጵያ አንድነት አልፎ የምስራቅ አፍሪካ ህዝብን አንድ የማድረግ እንደሆነም ጠ/ሚኒስትሩ መናገራቸውን፣ በውይይቱ ተሣታፊ የነበሩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ኪነ- ጥበቡ ይህን ራዕያቸውን እንዲያግዛቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን አርቲስቶች አዲሱን ትውልድ በዚህ ራዕይ የማነፅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአርቲስቶቻችን ትልቁ ችግር፣ ጊዜ ሰጥተው እውቀታቸውን አለማሣደጋቸው መሆኑን ያወሡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ምክንያት ስራቸው እንደ ቀድሞዎቹ ዘመን ተሻጋሪ መሆን ተስኗቸዋል ብለዋል፡፡
አርቲስቶች ከገንዘብ ይልቅ ሙያቸውን እንዲያስቀድሙ የመከሩት ዶ/ር ዐቢይ፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ችግርና ሰቆቃ ፈልፍለው ማውጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ ተሳታፊ የነበረው የፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ተሾመ በሰጠው አስተያየት፤ ጠ/ሚኒስትሩ ኪነ ጥበብ ለሃገር ግንባታ በሚኖረው አስተዋፅኦ ላይ ሠፊ ገለፃ ማድረጋቸውን ጠቁሞ፤ ውይይቱ ለኪነጥበብ ባለሙያዎቹ የተሻለ መነቃቃትና ግንዛቤ ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል፤ በመድረኩ ተሳታፊዎች አጠራር ላይ ሰፊ ቅሬታ የቀረበ ሲሆን ይህን ቅሬታ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሠጡ የውይይቱ ተሳታፊዎችም ይጋሩታል፡፡
አጠራሩ ሁሉንም ያካተተ አለመሆኑ ቅር ያሰኛል ያለው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፤ ድሮ የምናያቸው ችግሮች በዚህኛው የለውጥ ሂደት ውስጥ መደገም የለባቸውም ብሏል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ በበኩሉ፤ በተሳታፊዎች አጠራር ላይ ሠፊ ቅሬታ መቅረቡን ጠቁሞ፤ “በርካቶች እኔ ከጠሪዎቹ አንዱ መስያቸው ነበር፤ ይህ ግን ስህተት ነው፤ እኔም እንደ ማንኛውም አርቲስት ተጠርቼ ነው የተሣተፍኩት” ብሏል - ጥሪውን ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እና ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መሆናቸውን በመጠቆም፡፡
ለውይይቱ ከተጠራሁ በኋላ እንዳልሳተፍ ተከልክያለሁ ያለችው አርቲስት አስቴር በዳኔ፤  አዳራሽ ውስጥ ከገባች በኋላ ለቀረፃ ትፈለጊያለሽ ተብላ ከአዳራሽ እንድትወጣ መደረጉንና በስብሰባው መሳተፍ አትችይም ተብላ ወደ መጣችበት መመለሷን ተናግራለች፡፡ “አሁን ባልተጨበጠ ሁኔታ ብዙ መናገር አልፈልግም፤ ነገር ግን ሆን ተብሎ በስብሰባው እንዳልሳተፍ ተደርጌያለሁ” ብላለች - አርቲስቷ ለአዲስ አድማስ በሰጠችው አስተያየት፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ የዳሰሷቸው ዋና ዋና ኪነጥበባዊ ቁምነገሮች በገፅ 14 ቀርቧል፡፡

Read 3588 times