Sunday, 01 July 2018 00:00

መንግሥት፤ ኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስን ከኤርትራ እንዲያስመልስ ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

“ልጆቹ ይመጣል እያሉ በየቀኑ በጉጉት ይጠብቁታል” - (ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ)

   በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በኤርትራ ጦር ከተማረኩ በኋላ አድራሻቸው የጠፋው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ባልደረባ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስን የማፈላለግ ስራ መንግስት እንዲያከናውን ቤተሠቦችና ኢትዮጵያውያን እየጠየቁ ነው፡፡
ከሠሞኑ በተለያዩ ከተሞች በተካሄዱ የድጋፍ ሠልፎች ላይ ከተንፀባረቁ መልዕክቶች አንዱ፤ “ባለ ከፍተኛ ጀብዱው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስን የኤርትራ መንግስት የት እንዳደረሠው መጠየቅ አለበት፤” የሚል ነው፡፡
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የ17 ዓመታት ፍጥጫ አብቅቶ ሰሞኑን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመሩን ተከትሎ፣ በኮሎኔሉ የትውልድ አካባቢ ሆሳዕና ላይ ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተደረገ የድጋፍ ሰልፍ ላይ፤ “የጀግናው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ይመለስልን ጥያቄ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ምላሽ ያገኛል!” የሚሉ መፈክሮች በሰልፈኞች ተስተጋብተዋል፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ታላቅ ወንድም፣ አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በሰጡት አስተያት፤ “የህዝቡ ጥያቄ የቤተሠቦቹም ጥያቄ ነው፤ መንግስት የወንድማችንን ጉዳይ በትኩረት እንዲይዘው እንፈልጋለን፤” ብለዋል፡፡
እስካሁን ኮሎኔሉን ለማስመለስ የኢትዮጵያ መንግስት ያደረገው ጥረት እንደሌለ አረጋግጠናል፣ ያሉት ፕ/ር በየነ፤ በግላቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ለማፈላለግ ሙከራ አድርገው እንደነበረ ጠቁመው፤ “በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት እንጂ እናንተን አይመለከታችሁም፤” ተብለው ጉዳዩን በእንጥልጥል እንደተዉት ተናግረዋል፡፡
“ከኢትዮጵያ መንግስት ስለ ኮሎኔሉ ጥያቄ አልቀረበልንም፤ ፍቱልንም ሆነ መረጃ ስጡን ያለን የለም፤” ተብዬ ነበር ያሉት ፕ/ር በየነ፤ ቤተሠቦቹ በህይወት መኖሩንና አለመኖሩን እንኳ ማረጋገጫ ማግኘት ተስኗቸው፣ ለስነ ልቦና ቀውስ መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
“ልጆቹ በየቀኑ ይመጣል እያሉ በጉጉት ይጠብቁታል፤” ያሉት ፕ/ር በየነ፤ መላ ቤተሰቡም ቁርጥ ያለ መረጃ ባለማግኘቱ፣ በጉጉት ከመጠበቅ ወደ ኋላ አላለም፤ ብለዋል፡፡ በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት፤ የምርኮኛ ልውውጥ ይደረጋል ያሉት ፕ/ር በየነ፤ በጦርነቱ ተማርከው የነበሩ ኤርትራውያን ሲለቀቁ፣ የኛ ወገኖች አልተለቀቁም፣ ኮሎኔሉም በዚህ ምክንያት አድራሻው ሳይታወቅ ቀርቷል፤ ብለዋል፡፡
“ህዝቡ የሚያቀርበው ጥያቄ የቤተሰቦቹም ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጉዳዩን እንደ አንድ አጀንዳ እንዲይዙት እንፈልጋለን፤ ኮ/ል በዛብህ የቤተሰቦቹ ብቻ ሳይሆን የሃገር ጀግና ነው፤” ብለዋል ፕ/ር በየነ፡፡
የኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስ ጉዳይ በቅርቡ ምላሽ ያገኛል፤ የሚል እምነት እንዳላቸውም ፕሮፌሰሩ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ፤ ከደርግ መንግስት ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር ሃይል የተዋጊ ጀት አብራሪ የነበሩ ሲሆን፣ በሶማልያ ወረራና በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በፈፀሟቸው ጀብዱዎች ዝናቸው የናኘ መሆኑ ይታወቃል፡፡

Read 11323 times