Sunday, 01 July 2018 00:00

በአሶሳ ግጭት 12 ሠዎች ህይወታቸው አልፏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

 ግጭቱን አልተቆጣጠሩም የተባሉ የፀጥታ ሃላፊዎች ታስረዋል

   “ኦሮሚያ ክልል ላይ ሰዎች ታግተውብናል” በሚል መነሻ ተቀስቅሷል በተባለው የአሶሳ ከተማ ግጭት የ12 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ግጭቱን መቆጣጠር አልቻሉም የተባሉ የፀጥታ አመራር አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል፡፡
ለበርካታ ቀናት ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ ባገረሸው የረቡዕ እለቱ ግጭት ብቻ አስር ሰዎች በድንጋይና በዱላ ተደብድበው መገደላቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን የግጭቱ መነሻ “ወገኖቻችን ታግተውብናል፤ ይለቀቁልን” የሚል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የከተማ ከንቲባ አቶ ቶውፊቅ አብዱልቃድር፤ የግጭቱ መነሻ በምንጮቻችን የተገለፀው መሆኑን አረጋግጠው ከሃሙስ ጀምሮ ከተማዋን የማረጋጋት ስራ እየተሠራ መሆኑንና የከተማዋን ህዝብም የማወያየት ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ወገኖቻችን ታግተውብናል የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ ማቅረብ ሲገባ ወዳልተገባ አቅጣጫ ሄዶ ግጭት ተፈጥሯል ያሉት ከንቲባው፤ በቀጣይ ግጭቱን ያነሣሡና በግጭቱ የተሣተፉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለውና ማጣራት ተከውኖ ለህግ ይቀርባሉ፣ ምርምራውም ተጀምሯል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ረቡዕ ለሃሙስ አጥቢያ ከሌሊቱ 8 ሠዓት ገደማ በአዲስ አበባ መርካቶ አንዋር መስጊድ ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ህዝብ ሙስሊሙ በተለያዩ አግባቦች ጥያቄውን እያቀረበ ነው፡፡
የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ በታላቁ አንዋር መስጊድና በመስረጹ ዙሪያ የደረሠው የእሳት አደጋ መንስኤ በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ መገለፅ አለበት ብለዋል፡፡
ፖሊስ በበኩሉ፤ አስፈላጊውን ምርመራና ማጣራት እያደረገ መሆኑን አስታወቋል፡፡
ከሌሊቱ 8 ሠዓት ገደማ በመስጊድ የሴቶች መግቢያ አካባቢ በሚገኙ ሱቆችና መደብሮች ላይ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ መሠማቱን ተከትሎ የተነሳው የእሳት አደጋ፤ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በመስጊድ ላይም ውስን ጉዳት ማድረሡ ታውቋል፡፡
እሣቱም በአካባቢው በነበሩ ሰዎችና በእሳትና ድንገተኛ አደጋ መቆጣጠር ባለሙያዎች ወደ ንጋት አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል፡፡

Read 8117 times