Sunday, 01 July 2018 00:00

“ወደ ሃገር ቤት መምጣታችን ምንም ጥያቄ የለውም” -ጋዜጠኛ አበበ ገላው ከአሜሪካ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

• የተስፋ ጭላንጭሉ እንዳይጨልም፣ የመደመር ሃሳቡን ማስፋት ያስፈልጋል
• የኢቲቪን አዲስ ለውጥ በአዎንታዊ ሁኔታ ነው የምንቀበለው
• ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ የሚመጥኑ መሪ ናቸው

   በ2004 ዓ.ም በአሜሪካ በተካሄደ የዓለም መሪዎች ስብሰባ ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ላይ በስብሰባው አዳራሽ ባሰማው የተቃውሞ ድምጽ ብዙ ኢትዮጵያውያን ያስታውሱታል - ጋዜጠኛ አበበ ገላው፡፡ ኑሮውን በአሜሪካ ካደረገ ከ18 አመት በላይ ያስቆጠረው አበበ ገላው፤ በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በመጣው የተስፋ ጭላንጭል ደስተኛ መሆኑንና ወደ አገር ቤት እንደሚመጣም ይናገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሣት) ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ ጋዜጠኛ አበበ ገላውን፣ በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካ ለውጥ፣ ስለ ኢሣት ቴሌቪዥንና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ  በስልክ አነጋግሮታል፡፡

   ከኢትዮጵያ ከወጣህ የቆየህ ይመስለኛል?
ከኢትዮጵያ ከወጣሁ ብዙ ጊዜዬ ነው፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አካባቢ ነው የወጣሁት፡፡ በርከት ያሉ ዓመታትን ነው ከሃገር ርቄ ያሣለፍኩት፡፡
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የፖለቲካ ለውጥ ምን ይመስላል?
አሁን በሃገራችን የሚታየው የለውጥ እንቅስቃሴ እጅግ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ጉዳዮችን በፅሞና እየተከታተልኩ ነው። አሁን ዶ/ር አብይ አህመድ እየሠጡ ያለው አመራር፣ ሃገራችን እስካሁን ድረስ ሲያስፈልጋት የነበረ አመራር ነው፡፡ ህዝብን ወደ ሠላም፣ ወደ እኩልነት፣ ወደ ፍትህ የሚመራ መሪ ያስፈልገናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝቡን አንድ የሚያደርግ መሪ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ሃገር ነች፡፡ በዘር እየተናቆረ ሊኖር የሚችል ህዝብ አይደለም፡፡ አንድ የሚያደርገውን መሪ ይፈልግ ነበር፤ ህዝቡ፡፡ የመሪ ትልቁ ብቃትም ህዝብን አንድ የማድረግ ቀናውን አቅጣጫ ማስያዝ ነው፡፡ ጥላቻና መቃቃር መፍጠር ከመሪ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ዶ/ር አብይ ይህን በአግባቡ የተረዳ መሪ ነው፡፡ እርግጥ ነው ዶ/ር አብይ አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ወንጀሎችን የሠራው ኢህአዴግ መሪ ናቸው፡፡  ድርጅቱ፤ ከሃገራችን እንድንሰደድ አድርጎናል፣ በህዝባችን ላይ ብዙ ግፍና መከራ እንዲሁም መጠነ ሰፊ ዝርፊያ እንዲፈጸም አድርጓል፡፡ ይሄ ሁኔታ በአንድ ጊዜ ይቀየራል ብለን አንጠብቅም፡፡ ነገር ግን የተጀመረው የለውጥ ሂደት፣ ሁሉንም ነገር ይቀይራል የሚል እምነት ነው ያለን። የተጀመረው የለውጥ ሂደት እጅግ አበረታች ነው፡፡ ውጪ ሆነን ስንቃወም የነበርን፣ አሁን ለዶ/ር አብይ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ድጋፋችንን እየገለፅን ነው፡፡ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ በጎ ከመመኘት አንፃር፣ እኚህ መሪ የተስፋ ቃላትን አጉልተው እያወጡ ነው፤ ተስፋ እየሰጡ ነው፡፡ ተግባራቸውም ጥሩ ነው፡፡
በሀገራችን እንዲህ ያለ ጥሩ መሪ እስካለ ድረስ የምንቃወምበት ምክንያት የለንም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፤ ከትግራይ ጫፍ ጀምሮ እስከ ደቡብ ጫፍ፣ ህዝባችን በእኩል የሚተዳደርበት፣ በዘር በተቋጠረ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቱ ክብሩ ተጠብቆለት፣ በሃገሩ መኖር የሚችልበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ግን መንግስት ለህዝቡ ጠላት ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ይሄ ደግሞ ሃገሪቷን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ሊመራት የሚችልበት ጊዜን አምጥቶ ነበር፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት የተደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ አበረታች ነው። ህዝቡም ድጋፉን አልነፈገውም፡፡
ከኤርትራ ጋር የተጀመረውን የሰላምና የእርቅ ጉዞ እንዴት ታየዋለህ?
እነዚህ ህዝቦች ሁለት ተመሣሣይ የሆኑ ህዝቦች ናቸው፡፡ የተለያዩት በፖለቲካ ምክንያት ነው እንጂ ህዝቦቹ ስለሚጠላሉ አይደለም፡፡ አሁን በጉርብትና የሚኖሩ ነገር ግን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናይ፣ የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ባህል፣ የጋራ ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። አሁን በጎሪጥ ከመተያየት ተላቀው፣ አንዱ አንዱን በመደገፍ፣ በወንድማማችነት ስሜት መምጣታቸው በጣም አበረታች ነው፡፡ ይሄን እኛም እንደግፈዋለን፡፡ ሂደቱም መጀመሩ አስደስቶናል፡፡
ኢሣትን በሃላፊነት የምትመራው አንተ ነህና፣ ወደ ሃገር ቤት ገብታችሁ የመስራት እቅድ የላችሁም?
ወደ ሃገር ቤት ገብተን ለመስራት እቅዱ አለን። ይሄም እንደሚሣካ ተስፋ አለኝ፡፡ አሁን ሁኔታውን እያጠናን ነው፡፡ ስንመጣ ህጋዊ በሆነ መንገድ ነው የምንመጣው፡፡ ህጉን ተከትለን ፍቃድ አውጥተን፣ በሃገር ቤት ውስጥ ቢሮ አደራጅተን፣ ለመንቀሣቀስ እቅድ አለን፡፡ ይህ ደግሞ የሚሠምረው የመንግስት በጎ ፍቃደኝነት ሲታከልበት ነው፡፡ ኢሣት የኢትዮጵያ ህዝብ ልሣን ነው፡፡ ይሄ ነፃ የህዝብ ልሣን፣ በሃገር ቤት፣ በህዝቡ መሃል እየተንቀሣቀሠ፣ የህዝቡን ብሶትና ምሬት አጉልቶ የሚያሣይ ሚዲያ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የሚዲያ አንዱ ስራ፣ በህዝብ ላይ የሚፈጸምን በደል ማጋለጥ ነው፡፡ መንግስታት ደግሞ ለህዝብ ተጠያቂ ሆነው ተግተው የሚሠሩት፣ ገመናቸው አደባባይ ሲወጣ ነው እንጂ እስካሁን ድረስ በመንግስት የሚዲያ ተቋማት፣ ውዳሴ ከንቱ ሲቀርብላቸው አይደለም። ሚዲያ የህዝቡን ብሶትና ችግር አጉልቶ ማሣየት አለበት። እኛም በዚህ መንፈስ ነው የምንንቀሣቀሠው። ወደ ሃገር ቤት ስንገባም፣ ይሄንኑ አላማ ይዘን ነው። በሃገሪቱ ያለውን የሙስና ችግር ማጋለጥ፣ የሠብአዊ መብት ጥሠቶችን አጉልቶ በማውጣት እንዲታረሙ ማድረግ የኛ ሃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ ሃገር ቤት ስንገባ፣ እነዚህን ስራዎች ያለማዛነፍ እንሠራለን፡፡
አሁን የለውጥ ሃሣቦች በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንጂ በተቋማት ደረጃ አልወረደም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ከዚህ ስጋት በመነጨም አስተማማኝ ሁኔታ አልተፈጠረም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የአንተ አስተያየት  ምንድን ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቂ ናቸው ለማስተማመኑ፡፡ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ከፍተኛ ስልጣን ያለው  ጠ/ሚኒስትሩ ነው፡፡ ወሣኝ የሆኑ ጉዳዮችን የማስፈፀም አቅም አለው፡፡ እነዚህ በሣቸው ደረጃ ያሉ በጎ ፍቃዶች ወደ ተቋማት እንዲወርዱ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ለማድረጉም ብዙ አይከብዳቸውም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ኢሣት በተደጋጋሚ ኢቲቪን ሲተች ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ አስገራሚ መሻሻል እያሣየ ነው፡፡ እንደውም በዚህ ከቀጠለ የኢሣት ዋነኛ ተፎካካሪ ይሆናል እየተባለ ነው?
መቼም ተፎካካሪ ሚዲያ መኖሩ ለሌላኛው አቅም ይጨምርለታል፡፡ አንድ ሚዲያ ተፎካካሪ ሊሆን የሚችለው በስሙ ሳይሆን በስራው ነው፡፡ ስራው ደግሞ የህዝብን የልብ ትርታ የሚያንፀባርቅ መሆን አለበት እንጂ በተዛባ መልኩ በሃገራችን የሌለ ዲሞክራሲ እንዳለ፣ የሌለ ፍትህ እንዳለ አድርጎ ካቀረበ፣ ከህብረተሰቡ የተነጠለ ነው የሚሆነው። ለምሳሌ ኢቲቪ በፍትህ ስርአቱ ያሉ በደሎችን፣ የሠብአዊ መብት ረገጣዎችን አሁን ገና ነው እየተናገረ ያለው።
በፊት ግን እስረኞች የሚደረግላቸው እንክብካቤ ከፍተኛ እንደሆነ፣ የፍትህ ስርአቱ በአፍሪካ ተወዳዳሪ እንደሌለው፣ የተጀመረው ዲሞክራሲያዊ ስርአት ከእነ አሜሪካን እንኳ የሚበልጥ እንደሆነ አድርጎ የሚሠራቸው ፕሮፓጋንዳዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ናቸው ጣቢያውንም ቁልቁል ከተውት የነበረው፡፡ አሁን ያንን አቁሞ የሚዲያ ስራ እውነትን ፈልፍሎ ማውጣት ነው በሚለው መርህ፣ ከተንቀሣቀሠ፣ ብዙ ለውጥ ያመጣል፡፡ የሚዲያ ስራ እውነት ፍልፍሎ ማውጣት እንጂ ውሸትን አጉልቶ ማቅረብ አይደለም። ለኔ የኢቲቪ ጋዜጠኞች ስራቸውን የጀመሩት አሁን ነው። በፊት ዝም ብለው ደሞዝ እየተከፈላቸው፣ የውሸት ፕሮፓጋንዳ እያሠራጩ ነው የኖሩት፡፡ አሁን ጋዜጠኞቹ ነፃነት ተሠጥቷቸው፣ እውነትን ሲዘግቡ፣ የእነሡም መብት ከፍ ይላል፡፡ ይሄን ካደረጉ በእርግጥም ተፎካካሪ ይሆናሉ፡፡ ለውጣቸውን በአዎንታዊ ሁኔታ ነው የምንቀበለው፡፡
አንዳንድ ፖለቲከኞች፣ ጠ/ሚኒስትሩ በተስፋ ሞሉን እንጂ በተጨባጭ ብዙ አላየንም የሚል ከጉጉት የሚመነጭ የመሰለ ቅሬታ ያቀርባሉ? አንተስ ምን ትላለህ?
 የሚጨበጥ የሚታይ ነገር ባይኖር እንኳ በልቦናዬ የሚሰማኝ ነገር አለ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጨበጡ ነገሮች አላገኘም፤ ነገር ግን በተስፋ ቃላት እየታነፀ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ትልቅ ምዕራፍ ነው፡፡ ለጅማሬው ጥሩ ነው፡፡ ቀጥሎ ህዝብ የተሰጠው ተስፋ እውን ሆኖ ማየት ይፈልጋል፡፡ ዶ/ር ዐብይ ቃላቸውን ወደ ተግባር ሊለውጡ እንደሚችሉ እያሣዩን ነው፡፡ እስካሁን ብዙ ተናግረዋል፤ ነገር ግን ፎኖተ ካርታቸውን አልሰጡንም፡፡ ዘርዘር ባለ ሁኔታ ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚቀይሯት፣ እንዴት እንደሚያሻግሯት እስካሁን አልነገሩንም፡፡ ሌላው መደረግ ያለበት፣ እስካሁን ድረስ አግላይ ስርአት ነው የነበረው፡፡ ይሄ አግላይ ስርአት ደግሞ በዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ብቻ የሚቀየር አይደለም፡፡ ምክንያቱም የስርአቱ መዋቅር በጥቂቶች እጅ ያለ ነው፡፡ ከዚህ መውጣት አለበት፡፡ ዜጎች ሁሉ የሚሳተፉበት ስርአት ለመፍጠር ሁሉን አቀፍ የሆነ ንግግር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ንግግር ላይ ተመስርቶ፣ ኢትዮጵያን ወደ ሽግግር መምራት አስፈላጊ ነው፡፡ የሽግግር መንግስት ሂደት ውስጥ ካልተገባ፣ አሁንም ኢህአዴግ ያለውን መዋቅር ሁሉ ተጠቅሞ፣ በዶ/ር አብይ ቅቡልነት ተከልሎ፣ ጨቋኝነት የበላይ የሆነበትን፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ ይዞ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ስለዚህ ሁሉን አቀፍ ከሆነ ንግግር የሚመነጭ፣ እኩልነት ላይ የተመሠረተ፣ የመንግስት ስርአትን እውን ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ መዋቅራዊ ለውጥ ወሳኝ ነው፡፡
በመጨረሻ የምትለው ነገር አለ?
እኔ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ በጠቅላላ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉም የተጨቆነ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት 40 ዓመታት ብዙ መከራ የያ ህዝብ ነው፡፡ አሁን የተስፋ ጭላንጭል ታይቷል፡፡ ይህ የተስፋ ጭላንጭል ተመልሶ እንዳይጨልም፣ የመደመር ሃሣቡን ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ ሠዎች ሃገራዊ ስሜታቸውን ከፍ አድርገው፣ በእኩልነት የሚተያዩበት ሁኔታ መፈጠሩ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይሄን ስሜት እያጎለበቱ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እኩልነት፣ የሰብአዊ መብት መከበር ሁኔታዎች እስኪረጋገጡ ድረስ ህዝቡ አሁንም ትግሉን መቀጠል አለበት፡፡ መንግስት ተስፋ ሰጥቶኛል ብሎ ማንቀላፋት አያስፈልግም፡፡ ተስፋ ዳር እንዲደርስ ህዝቡ መንግስት ላይ በጎ ጫና ማድረጉን ማቆም የለበትም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለኝን ፍቅር እገልፃለሁ፡፡ ወደ ሃገር ቤት እንመጣለን፤ ለመምጣታችን ምንም ጥያቄ የለውም፡፡

Read 4663 times