Sunday, 01 July 2018 00:00

አርጀንቲናና የዓለም ዋንጫ ተስፋዋ

Written by  ግሩም ሠይፉ (ከሞስኮ)
Rate this item
(1 Vote)

 በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከፍተኛ ድምቀት ከፈጠሩ የተሳታፊ አገራት ደጋፊዎች ከመካከለኛውና፤ ደቡብ አሜሪካ የአትላንቲንክ ውቅያኖስን ተሻግረውና የአፍሪካን አህጉር አልፈው ራሽያ የገቡት ናቸው። በ11 ከተሞች በተደረጉት 48 የምድብ ጨዋታዎች ላይ ከአውሮፓውያን፤ ከአፍሪካውያንና ከኤስያውያን ደጋፊዎች ይልቅ የሜክሲኮ እና የላቲን አሜሪካ ህዝቦች ከአዘጋጇ አገር የራሽያ ህዝቦች ጋር በመሆን የዓለም ዋንጫውን ማራኪ ድባብ አላብሰውታል፡፡ እውነተኛ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ሆነው ከመካከለኛው አሜሪካ ሜክሲኳዊያን እንዲሁም ከላቲን አሜሪካ ፔሩዎች አርጀንቲናውያን፤ ኮሎምቢያውያን፤ ብራዚላውያንና ኡራጋውያን የራሽያን መስተንግዶ ያደመቁት ከ100ሺ በላይ   ይሆናሉ፡፡  ብዙዎቹ በየአገራቱ የሚኖሩ ሰርቶ አደሮች እና መደበኛ ህዝቦች መሆናቸው ደግሞ በዚያ የዓለም ክፍል ዓለም ዋንጫ ልዩ የባህል እሴት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
ከሌሎች የዓለም ክፍሎች በብዛት ደጋፊዎችን ካሳዩ አገራት በብቸኝነት ቢጠቀሱ የሰሜን አፍሪካዋ አገር ሞሮኮ ደጋፊዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከደቡብ አሜሪካ በራሽያ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ከተሞች በብዛት በመገኘት መጠቀስ ያለባቸው ከ36 ዓመታት በኋላ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ያረጋገጠችው ፔሩ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን የፔሩ ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በምድብ ማጣርያው ቢወሰንም በራሽያ ከ45ሺ በላይ የሚሆኑ ፔሩዎች 21ኛውን የዓለም ዋንጫ በአካል ለመታደም ችለዋል። እነዚህ የፔሩ ደጋፊዎች በ21ኛው የዓለም ዋንጫው መክፈቻ ዋዜማ ላይ በመካከለኛው ሞስኮበሚገኘው ቀዩ አደባባይ እና በክሬምሊን አካባቢ የፈጠሩት ድባብ በምስሉ ላይ እንደምትመለከቱት የሚዘነጋ አልነበረም።
21ኛውን የዓለም ዋንጫ ለመዘገብ ራሽያ ከገባሁ 3 ሳምንታት ሊሆነኝ ነው፡፡ በተለያዩ ከተሞች በቀጥታ ለማየት ከቻልኳቸው የምድብ ጨዋታዎች መካከል ሶስቱ አርጀንቲና የተጋጠመችባቸው ናቸው፡፡ የመጀመርያው ከአይስላንድ  ጋር በሞስኮው ሉዚሂንኪ ስታድዬም ተካሂዶ 0ለ0 አቻ የተለያዩበት፤ ሁለተኛው ደግሞ ከክሮሽያ ጋር በኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ስታድዬም የተደረገውና 3ለ0 የተሸነፉበት እንዲሁም  3ኛውና የመጨረሻው ደግሞ ከናይጄርያ  ጋር በሴንትፒተስበርግ ተፋጥጠው 2ለ1 በማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ የተሸጋገሩበት ናቸው፡፡
የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድንና ደጋፊዎቹ ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ ድምቀት ዋንኞቹ ተጠቃሾች ናቸው። በሶስት የተለያዩ የራሽያ ከተሞች ስዘዋወር አግኝቼ ያነጋገርኳቸው የተለያዩ አርጀንቲናዊያን ደጋፊዎች የዓለም ዋንጫን እንደባህል ያደረጉ ህዝቦች መሆናቸውን አረጋግጠውልኛል።  ከ17.4 ሺ ኪሎ ሜትሮች በላይ በሚያቋርጡና በትራንዚት  ከ40 ሰዓታት በላይ በሚወስዱ የአውሮፕላን በራራዎችን አድርገው ራሽያ የገቡት አርጀንቲናውያን ከ30 ሺ በላይ ይሆናሉ፡፡  ጆርጌ ቦሲ የተባለ አርጀንቲናዊ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት የአርጀንቲና ደጋፊዎች በዓለም ዋንጫው ብሄራዊ ቡድናቸውን እስከ ፍፃሜ እንደሚጓዝ በሰነቁት ተስፋ  ራሽያ የገቡት ቢያንስ እስከ 20 ቀናት ለመቆየት ሲሆን በነፍስ ወከፍ ከ5ሺ እስከ 8ሺ ዶላር በጀት ማድረጋቸውን ይገልፃል፡፡ በምግብ፤ በመጠጥ እና በተለያዩ የሽቶ ምርቶች የሚያገለግሉ መዓዛዎችና ቅመሞችን በሚያመርት የስዊዘርላንድ ኩባንያ የሚሰራው ጆርጌ ከሙያ ባልደረባው ጋር በራሽያ የተገኙት የዓለም ዋንጫን ድል ለማጣጣም ስለሚፈልጉ ነው፡፡
አርጀንቲናውያን በዓለም ዋንጫው ታሪካቸው ከፍተኛ ቁጭት ያደረባቸው መሆናቸውን ገልፀውልኛል። ከአርጀንቲናዎቹ ከተሞች ቡነስ አይረስ፤ ባንፊልድ፤ ሳን ጁዋንና ሳንፌቴ እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ራሽያ የገቡት አርጀንቲናውያን ዋንጫውን ከቡድናቸው ጋር ወደ አገራቸው ይዘው ለመመለስ ያስባሉ፡፡ ለጊዜው ቡድናቸው ወደ ጥሎ ማለፍ በመግባቱ በጣም ተደስተዋል። በሴንትፒተስበርግ ከናይጄርያ በጋር የምድባቸው የመጨረሻ ጨዋታን አድርገው ካሸነፉ በኋላ በከተማ ውስጥ የሜትሮ ባቡሮች እንዲሁም በፈጣኖቹ አገር አቋራጭ ባቡሮች ከራሽያውያን በቀር አብዛኛዎቹ የአርጀንቲናን ማልያ የለበሱ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደጋፊዎች ልዩ የሚያደርጋቸው ሁሉም ማለት ይቻላል የብሄራዊ ቡድናቸውን ማልያዎች የለበሱ መሆናቸው፤ በአርጀንቲና ባንዲራዎች፤ የተለያዩ የድጋፍ ልብሶች፤ ባነሮች እና ፖስተሮች በስታድዬም እና ከስታድዬም ውጭ በማያቋርጥ  በዝማሬ የሚተሙ ናቸው። በጉዟቸውና በድጋፋቸው ሜሲና አርጀንቲና እስከ ዓለም ዋንጫው ድል እንደሚጠብቋቸው ከመናገርም ተቆጥበው አያውቁም፡፡
በጥሎ ማለፉ ከፈረንሳይ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ወደ ራሽያዋ ከተማ ሳርናሳክ ያቀኑት የአርጀንቲና ደጋፊዎች ብዛት ከ20ሺ በላይ ናቸው፡፡ ሁሉም አንድ የጋራ ህልም አላቸው፡፡ አርጀንቲና በዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪኳ ሶስተኛውን የዓለም ሻምፒዮናነት ክብር እንድትቀዳጅ ይፈልጋሉ፡፡ የአርጀንቲና እግር ኳስ ባለፉት 20 ዓመታት ያለፈበት ትውልድ ይህን ክብር አለማሳካቱ በጣም እንደሚቆጫቸው ነው የሚናገሩት። ባለፉት 3 የዓለም ዋንጫዎች አርጀንቲና ማሸነፍ እንዳለባት እያመኑ ድጋፍ ቢሰጡም አልተሳካላቸውም። ዘንድሮ ግን ሜሲ ቡድናቸውን በአምበልነት እየመራ ዋንጫውን በራሽያ ምድር ላይ እንዲቀዳጅላቸው የመጨረሻ ተስፋ አድርገዋል፡፡
በምድብ ማጣርያው ባደረጓቸው ጨዋታዎች በስታድዬም ውስጥ ከስታድዬም ውጭ በሚያሰሟቸው ዝማሬዎች ይህን ተስፋቸውን በጉልህ አንፀባርቀውታል።
Vamos Argentina  
በሚለው ዝማሬያቸው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ
‹‹እንደምንወዳችሁ ታውቃላችሁ፤ ለዋንጫው ድል ያለን ሁሉ እንሰጣለን… ማራዶናና ሜሲ የእኛ ናቸው። ወደራሽያ መጥተናል፤ የምንመለሰው ዋንጫውን ይዘን ነው…. እያሉ ነው የሚዘምሩት፡፡ በሌሎች ዝማሬያቸው… ሻምፒዮን መሆን እንፈልጋለን፤ እነሜሲ እንደሚያሳኩትም ተስፋ እናደርጋለንም እንደሚሉ በትርጉም ተገልፆልኛል። በዝማሬያቸው የማራዶናን ጀግንነት እና የማይረሳ ጀብዱ ደጋግመው ይጠቅሳሉ፤ የሜሲ ብቃትን በልዩ ዜማ በማወደስ  ለደህንነቱ መልካም ምኞታቸውን በህብረት በመዘመር ድጋፋቸውን ይገልፃሉ፡፡
በምድባቸው ከናይጄርያ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ ሜሲ የመጀመርያውን ግብ ሲያስቆጥር፤ ከዚያም በናይጄርያ የአቻነት ጎል ሲመዘገብባቸው በመጨረሻም ባለቀ ሰዓት ማርከስ ሮጆ የማሸነፊያዋን ጎል ሲያስመዘግብ አርጀንቲናውያን ደጋፊዎች በዘመናዊው የሴንትፒተርስበርግ ስታድዬም በደስታ እና በሃዘን እንባቸው ታጥበዋል። በየጨዋታዎቹ ሙሉውን  ክፍለ ጊዜ በጋራ ሲዘምሩ ያስደንቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደጋፊዎች በቡድናቸው ተስፋ እንደማይቆርጡ ነው የሚናገሩት በአስጊ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነውም ቡድናቸው እንደሚያሸንፍ በልበሙሉነት ሲናገሩም‹‹  አርጀንቲናውያን እግር ኳስን እናፈቅራለን፤ የትኛውንም ጨዋታ እንደምናሸንፍ እናምናለን›› ይላሉ፡፡
ከ21ኛው የዓለም ዋንጫ ጥሎ ማለፍ በፊት የአርጀንቲና ታሪክ
በዓለም ዋንጫ ታሪክ ስኬታማ ከሆኑ አገራት ተርታ የምትጠቀስ ሲሆን ከፈረንሳይ ጋር በጥሎ ማለፍ ከመገናኘቷ በፊት 78 የዓለም ዋንጫ ግጥሚያዎች አድርጋ 42 ስታሸንፍ፤ 14 አቻ ተለያይታ በ21 ጨዋታዎች ተሸንፋለች፡፡
በ17 የዓለም ዋንጫ በመሳተፍ ከብራዚል፤ ጀርመንና፤ ጣሊያን የምትጠቀስ ሲሆን 2 ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን በ1978 እና በ1986 እኤአ ለሶስት ጊዜያት ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በ1930፤ በ1990 እና በ2014 እኤአ ላይ አስመዝግባለች፡፡
በዓለም ዋንጫ ለብሄራዊ ቡድኑ በ1982፤ በ1986፤ በ1990 እና በ1994 እኤአ በ4 የዓለም ዋንጫዎች 21 ጨዋታዎች በመሰለፍ እና በ16 ጨዋታዎች አምበል ሆኖ ሪከርድ ያስመዘገበው ዲያጎ ማራዶና ነው፡፡ ሃቪዬር ማሸራኖ በ20 ጨዋታዎች (በ2006፤ 2010፤ 2014 እና 2018 እኤአ) እንዲሁም ሊዮኔል ሜሲ (በ2006፤ 2010፤ 2014 እና 2018 እኤአ) በመሰለፍ ይከተላሉ። ዘንድሮ እስከ ፍፃሜው ከተጓዙም ሁለቱም ለአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ብዙ ጨዋታ በዓለም ዋንጫ በማድረግ የማራዶናን ክብረወሰን ያሻሽላሉ፡፡
በዓለም ዋንጫ ለብሄራዊ ቡድኑ 10 ጎል በማስመዝገብ የሚመራው ገብሬል ባቲስቱታ ሲሆን፤ ገየሌርሞ ስታብል እና ዲያጎ ማራዶና በ8 ጎሎች ይከተሉታል፡፡ ሊዮኔል ሜሲ 7 ጎሎች አሉት፡፡
በዓለም ዋንጫ በኮከብ ተጨዋችነት የወርቅ ኳስ የተሸለሙት በ1978 ማርዮ ኬምፐስ፤ በ1986 ዲዬጎ ማራዶና እንዲሁም በ2014 እኤአ ሊዮኔል ሜሲ ናቸው፡፡ በኮከብ ግብ አግቢነት የወርቅ ጫማ የተሸለሙት ደግሞ በ1930 እኤአ ጉሌርሞ ስታብል እንዲሁም በ1978 እኤአ ማርዮ ኬምፐስ ናቸው፡፡

Read 1191 times