Sunday, 01 July 2018 00:00

ኢትዮጵያ የተሞሸረችበት ዕለት በጨረፍታ

Written by  አብርሐም ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)


    “ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፣ ከምንጨፈን እንደዕቡይ ከምንጫረስ እንደ እኩይየነገው ትውልድ በፍርድ፣ ሳይመድበን ከዘር ድውይ እባክህ ሳይጨልምብን፣ አዲስ ራዕይ ኣብረን እንይ፡፡…”
             
    የጥላቻ ግንቦች እስከ ወዲያኛው እንዲፈርሱ ከልብ የሚሹ ኢትዮጵያውያን የተገኙበት ነበር፤ ያለፈው ቅዳሜ በመስቀል ኣደባባይ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ። በስፍራው የተገኙ ኢትዮጵያውያንን የፊት ገጽታ ላስተዋለ በብሩህ ተስፋ የተሞላ ነበር፡፡ በመስኮት በኩል ሰርጎ የገባውን አገራዊ ብርሃን፣ በበር በኩል ገብቶ፣ መላው ኢትዮጵያን በፍቅርና በይቅርታ ብርሃን እንዲያጥለቀለቅ፣ ጥልቅ መሻት የነበራቸው ኣያሌ ኢትዮጵያውያን የታደሙበት ታሪካዊ ቀን፡፡
በእለቱ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ጅማሮን ደግፎ፣ መስቀል ኣደባባይ ከወጣው ህዝብ መካከል ብዙ ያስገረሙኝና ያሳዘኑኝ ክስተቶች ነበሩ። ካስገረሙኝ መካከል ዋነኛው፣ አንድ በግምት የ70 ዓመት ዕድሜ የሚሆናቸው አዛውንት እናት ነገር ነበር፡፡ እኝህ እናት፣ ከቤታቸው ብቻቸውን እንደመጡ ገምቻለሁ፤ ከአጠገባቸው ያስከተሉት ማንም አልነበረምና፡፡ ሰልፈኞቹ ከዚያ በፊት የማይተዋወቁ ይሁኑ እንጂ፣ በኣብዛኛው ተቀራራቢ የሆነ አገራዊ ርዕይ የነበራቸው ኢትዮጵያውያን የተሰባሰቡበት መድረክ ነበር፡፡ ታዲያ እኝህ እናት በኣረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የተጌጠ ደርዝ ያለው ነጭ በነጭ ለብሰዋል፡፡ በቀኝ እጃቸው ትንሽዬ ባንዲራ ከፍ ኣድርገው ይዘዋል፡፡ ትኩረቴን የሳበውና ግርምት የጫረብኝ በተደጋጋሚ ጮክ ብለው የሚናገሯቸው፣ በቃል አጋኖ ድምጸት የታጀቡ ዓረፍተ ነገሮች ነበሩ፡፡ “ኢትዮጵያ አንድ ነች! ኢትዮጵያ አንድ ነች! ኢትዮጵያ አትከፋፈልም!...” የሚሉ ጥልቅ ከሆነ እናታዊ ፍቅር የመነጩ ድምጾች። በአካባቢው ከነበረው የደስታ ሆታና ፌሽታ አንጻር፣ ድምጻቸውን የሰማነው፣ እኔና አጠገባቸው የነበሩት ጥቂት ሰልፈኞች ብንሆንም፣ በድምጻቸው ማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት ግን ግልጽ ነበር፡፡
ከእኝህ እናት ጋር የሚመሳሰል ነገር የገጠመኝ፣ ከዚህ ቀደም በፕ/ር ኃይሌ ገሪማ ‹‹Imperfect journey›› በተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ላይ ነው፡፡ በ1990ዎቹ መጀመርያ አካባቢ፣ በአዲስ አበባ “በኢትዮጵያ ሰላም፣ ዕርቅና የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት” በሚል በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከናዝሬት በመምጣት ሰልፉ ላይ የተገኙ አንድ ኣባት፣ ለምን በሰልፉ መገኘት እንደመረጡ ይጠየቃሉ፡፡ ሰውየውም ሲመልሱ፤ “…ወታደራዊው የደርግ ኣገዛዝ ከመጣ ጀምሮ እኛ እርስ በርስ ተበታትነን፣ አሁንም የመጣው እየከፋፈለን፤ አንዱን ገመቹ፣ አንዱን ታደሰና አንዱን ኃይሌ እያለ እየከፋፈለን ሊኖር ይፈልጋል፡፡ እኛ ደግሞ ያንን መከፋፈል አንፈልግም፡፡ ሞታችንን ነው የምንፈልገው። ኢትዮጵያ አንድ ነች፡፡ ጎይቶምም ያስተዳድር፤ ገመቹም ያስተዳድር፤ ፈይሳም ያስተዳድር እኛ ግን የምንፈልገው በሰላም እንዲያስተዳድር ነው። …እንኳን እኛ አህዮቻችን፣ ፈረሶቻችንና ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ኣላማን ያውቁታል፡፡ …እኔ ደንበኛ የወለጋ ኦሮሞ ሰው ነኝ፡፡ ግን በኣንድ ኢትዮጵያ ነው የማምነው”  ነበር ያሉት የዚያኔው ሰልፈኛ፡፡  ከኔ ጎን የቆሙት እናትም፣ ፕ/ር ኃይሌ ገሪማ በሰራው ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ያያኋቸውን አባት ነበር ያስታወሱኝ፡፡
ኢትዮጵያ ፈክታና ደምቃ የዋለችበት ልዩ ዕለት። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም፡፡ የኢትዮጵያ ዳግም ልደት በህዝቧ በተበሰረበት በዚሁ ቀን፣ ፍቅርና መተሳሰብ ተዘምሯል፡፡ መከባበርና ህብረት ተዚሟል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለውጭ ወራሪዎች ያሳዩትን የነጻነት ተጋድሎና ቀናዒነት፣ ወደ አገር ውስጥ መቀየር ተስኗቸዋል ተብለው የሚታሙበትን ጉዳይም ፉርሽ አድርገውታል፡፡ ህዝቡ የቱን ያህል ለነጻነት ጥልቅ መሻት እንዳለው በተግባር አሳይቷል፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን፤ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ብሎ በሰየመው ግጥሙ ደህና ኣድርጎ የሚገልጸው ይመስለኛል፤በእለቱ የተስተዋለው የህዝቡ የነጻነት ጥልቅ ፍላጎት፡-
“…የኢትዮጵያዊነት መስፈርቱ፣ ነጻነት ለኣንድ ዜጋ፣
መንፈሳዊ ነው እሴቱ፣ የማይዳሽቅ ለስጋ፣
የማይገበር ለጠመንጃ፣ የማይተመን በዋጋ፤
መንፈሱን ቆርጦ ለመሸጥ፣ ሳይሆን እንደ ባንዳ መንጋ፡፡
ወይ እንደ ትላንቶቹ፣ ለዙፋን ባርነት ሳይሆን፣
ወይ ለጦር መኮንኖች ምርጥ፣ ለማጎብደድ ለኣንድ ሰሞን፡፡”
ኢትዮጵያውያን በዕለቱ ከስፍራው የተገኙት የነጻነት ጥማታቸው፤ የፍቅር ሃያልነት በአደባባይ ለመመስከር እንጂ፣ ለአጎብዳጅነትም ሆነ ርካሽ የሆነ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ኣልነበረም፡፡ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ስንሆን፣ እንደ ቀስተ ደመና ጎልተን እንደምንፈካ በግልጽ ታይቷል፡፡ የመተባበርና የመከባበር መንፈስ ለሃገራችን ብልጽግና ዋንኛ ፍኖተ ካርታ መሆኑንም ተገንዝበናል፡፡ በትናንሽ ምስሎች ስር በመሸሸጋችን፣ ደብዝዞ የነበረው ሰው የመሆን ልዕልናችን ዳግም የታደሰበት ዕለት ጭምር ነበር፡፡ ከላይ በጠቀስኩት ግጥም ውስጥ፣ ስለ ኢትዮጵያ ተቀኝቶ የማይታክተው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅንም፣ የኢትዮጵያዊነት ስር መሰረቱ ከየት እንደሆነና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ባህርያት ምን ምን እንደሆኑ ድንቅ በሆነ ግጥሙ ውስጥ ካሰፈራቸው ስንኞች አሁንም ጥቂት እንጨልፍ፤
“…ኢትዮጵያዊነት ክብር ነው፣ ለሃይል ክንድ የማይዳር፣
ህዝባዊነት ነው መስፈርቱ፣ የህዝብ ወገን የህዝብ ኣጋር፣
እንጂ፣ ለዘረኞች ቁማር፣ ለኣንድ ጎሳ ቡድን ገባር፣
ሊሆን እንደ ሚጣል ዕጣ፣ ኣይደለም ሎተሪ ቢጋር፡፡
የየጎሳው ክልል ጣኦት፣ እፍ እንዳለበት ጭቃ ጡብ፣
የሚፍጠረጠር ለቀን ሩብ፡፡
ጠዋት ተፈብርኮ፣ ማታ ‹‹ተገምግሞ›› እንደሚሞት፡፡
ኣይደለም ኢትዮጵያዊነት፣ የኣሻንጉሊትነት ሕይወት፡፡
…የኢትዮጵያዊነት ምስጢሩ፣
ወንድምህን መጥላት ሳይሆን፣ ራስክን ማወቅ ነው ከስሩ፡፡” ብሎ የተቀኘውን ቅኔ፣ በመስቀል አደባባይ ትዕይንተ ሰልፍ ውስጥ በሚገባ ኣይቼዋለሁ፡፡ በሚገባም አድምጬዋለሁ፡፡
ዛሬ በሐገራችን ይሆናሉ ተብሎ ያልተገመቱ ብዙ እንግዳ ነገሮች እየሆኑ ነው፡፡ የሃይማኖት ኣባቶች ስለ ፍትህና ርትዕ በአደባባይ መናገር ተስኗቸው፣ በፍርሃት ቆፈን በተሸበቡበት በዚህ ወቅት፣ “ድሃ ለምን ተበደለ? ለምን ፍትህ ተነፈገ?” ብላችሁ ልትጠይቁና ልትቆረቆሩ ይገባል የሚል መሪ ይመጣል ብሎ ማን ጠበቀ? በፓርላማው “ሽብርተኞች” ለምን ይፈታሉ ተብሎ ሲጠየቅ፣ “ማነው ሽብርተኛ? እኛም እኮ ከሽብር ተግባር ንጹህ አይደለንም” በማለት ሃላፊነትና ተጠያቂነት የሚወስድ መሪ፣ በዚህ ፍጥነት ይመጣል ብሎ ማን አሰበ? በተለያዩ ሃገራት የታሰሩ እስረኞች ዋና ጉዳዬ ነው ብሎ በማስፈታት፣ ከእስረኞች ጋር በኣንድ አውሮፕላን እያወጋ የሚመጣ መሪ፣ በዚህ ወቅት ከጉያችን ይወጣል ብሎ ማን ገመተ? ብቻ በሐገራችን ለዓመታት ብዙዎች ሲብሰለሰሉበት የነበረን፣ አገራዊ ጉዳይ የሚያደምጥ መሪ፣ ኢትዮጵያ የሃዘን ማቅ በለበሰችበት ጊዜ መምጣቱ ነው፤እንግዳ ስሜት እንዲሰማንና ይኸው ስሜታችን ፈንቅሎን ኣደባባይ እንድንወጣ ያደረገን፡፡
በዚሁ እንግዳ ስሜት  እንድንዋጥ ያደረገን፣ ልክ እንደ ኔልሰን ማንዴላ፣ የጥላቻ ግድግዳዎች ተንደው፤ በቦታቸው ፍቅር ይታነጽ የሚል መሪ ብቅ በማለቱ ነው፡፡ የመዘላለፍና የቂም በቀለኝነት እንክርዳዶች ተነቅለው፤ የመደጋገፍና የመተሳሰብ ፍሬዎች፣ በኢትዮጵያችን ይብቀሉ በመባሉ ነው፡፡ በህዝቦች መካከል ኣለያይ ስንጥቆች ፈጥሮ ከማራገብ ተቆጥበን፤ በህዝቦች መካከል አገናኝ ድልድዮች እንዘርጋ የሚል የፍቅር ተማጽኖ በመሰማቱ ነው፡፡
ማንም እንደሚገነዘበው፣ ለዓመታት በሐገራችን የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ የታየው፣ መጠላላትና መናናቅ አገራዊ ርዕይ የሌለን ድንክዬዎች አድርጎናል። ፓን አፍሪካኒዝም በተሰበከባት አገራችን፣ ብሄራዊ አንድነታችን ክፉኛ ደብዝዞና ተናግቶ የጠላት መሳለቂያ ሆነናል፡፡ የጋራ መሰባሰቢያችን ጣራው ተሰንጥቆ፤ ማገሩ ተናግቶ ስናይ፣ የኢትዮጵያ ህልውና እንቅልፍ ነስቶናል። ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ የመጣንበትን የጥላቻ መንገድ ምን እንደሚመስል ማለፊያ አድርጎ ‹‹ምርጫና ቃጠሎ›› በተሰኘው ግጥሙ ውስጥ አስፍሯል፡፡ ግጥሙ የመጣንበትን መንገድ ደህና ኣድርጎ የሚያሳይ ነው፤
“አየሩ በጥላቻ መርዝ፣ በዘር ጎጥ በመበከሉ
አንድነት እንደቁምጥና፣ ድውይ ተራ በመዋሉ
ቃል እንደእርኩስ በመቅለሉ
ጉድ አዋጅ እያስተዋሉ፣…” ሆኖብን ነበር፡፡ ዛሬ ግን ተስፋና ስጋት እየተፈራረቁብን ቢሆንም፣ ተስፋ ሰንቀናል፡፡ ነገአችንን የተሻለ ለማድረግ ነው፤መጠነ-ሰፊው አገራዊ መነቃቃት ዋናው አንድምታው፡፡ አሁን የተከፈተው የብርሃን ጭላንጭል ወደ ፊት ለመጓዝ ትልቅ መሸጋገርያ ድልድይ መሆን ይችላልና፡፡
ይሁን እንጂ የብርሃን ጭላንጭሉ፣ በጽልመት እንዲዋጥ የሚሹ ሰዎች በመካከላችን እንዳሉ እሙን ነው፡፡ ያለፈው ሳምንት ሰላም፣ ፍቅርና መተባበር ሊሰብኩ ወደ አደባባይ በወጡት ኢትዮጵያውያን መካከል እልቂት እንዲፈጠር የፈለጉት ሰዎች፤ ከብርሃን ይልቅ ድቅድቅ ጨለማ የመረጡ  ናቸው፡፡ ህዝቡ በራሱ ፈቃድ አደባባይ ወጥቶ የዘመረላቸው እሴቶች፣ ገቢራዊ እንዳይሆኑ የሚፈልጉ ሰዎች፣ ጥላቸው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንደሆነ ሊያውቁት ይገባል፡፡ ለነገሩ በጥላቻ ጥሻ  ስር የተወሸቁት እኒህ ሰዎች፣ ጠባቸው ከማንና ከምን ጋር እንደሆነ ይበልጥ ራሳቸውን ያጋለጡበት ዕለት ነበር፡፡ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና ሌብነትን ተጠይፎ አደባባይ በተሰለፈ ህዝብ ላይ ቦምብ መወርወር ፍጹም አረመኔነት ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ፤“…እርስ በራሳችን እንድንፋጅ የሚሹ “የቀን ጅቦች” በመካከላችን አሉ” ባሉበት ማግስት መሆኑ ነው፤ የዕልቂቱ ሴራ ወደ ትግበራ የተቀየረው፡፡
“ውሻ እርስ በርሱ በኣጥንት ይጣላል፣ ጅብ ሲመጣ ግን በጋራ ተባብሮ ይጮሃል” እንደሚባለው፣ ከአጥንቱ በመሻገር ጅቡ ላይ ማተኮሩ ብልህነት ነው፡፡ የሃገራችን ጅብ ደግሞ ጥላቻ ነው፡፡ ቂም በቀል ነው፡፡ ሌብነትና በስልጣን መባለግ ነው፡፡ ይህንን ለዘመናት የተጣባንን የክፋት አረም ደግሞ የህግ የበላይነት እንዳይሰፍን፣ የመቻቻልና የመከባበር የፖለቲካ ከባቢ እንዳይፈጠር፣ ኣንጻራዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖርና የሰብዓዊ መብቶች እንደዳይከበሩ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ እዚህ ዘልቋል፡፡ ዛሬ በሃገራችን በጠ/ሚ አብይ አህመድ መሪነት እየተካሄደ ያለውን የዘመናት ዕኩይ አረም በመንቀል፣ የመተሳሰብ ዘር እንዝራ የሚለውን የለውጥ ሃሳብ ያበረታል፡፡ ተስፋን ያለመልማል፡፡
ይሁን እንጂ አጥንቱን ለመጋጥ እርስ በርስ የሚደረገው ፋይዳ ቢስ ሽኩቻ፣ አጥንቱን ብቻ ሳይሆን የራስንም ህልውና፣ እንዲሁም የነጻነትና የፍትህ ጥያቄዎች በጅቡ ማስበላት ነው፡፡ አለመተባበርና አለመደማመጥ የዘመናት የዜጎች የነጻነት ተጋድሎ እንዲሰናከል ቀዳዳ የሚከፍት ጭምር፡፡ በቅርቡ ከኣዲስ አበባ የቦምብ ፍንዳታ በተጨማሪ፣ በሌሎችም የሃገራችን አካባቢዎች የተፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊቶች፣ የነጻነትና የፍትህ ጥያቄዎች ለማጨናገፍ የሚደረጉ ዕኩይ ተግባራት ናቸው፡፡ በቂምና በበቀል የመጣንባቸው መንገዶች ብሄራዊ ውርደት እንጂ፣ ክብር ኣላስገኙልንም፡፡ በተደጋጋሚ የጠቀስኩት ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን፣  ‹‹ይድረስ ለኛ›› በተሰኘው ግጥሙ ውስጥ ጥቂት ስንኞች በመምዘዝ መደምደሚያዬ ኣድርጌያቸዋለሁ፤
“ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፣ ከምንጨፈን እንደዕቡይ
ከምንጫረስ እንደ እኩይ
የነገው ትውልድ በፍርድ፣ ሳይመድበን ከዘር ድውይ
እባክህ ሳይጨልምብን፣ አዲስ ራዕይ ኣብረን እንይ።…”

Read 795 times