Sunday, 01 July 2018 00:00

ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጠቃሚ ምክር

Written by  ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ
Rate this item
(3 votes)

ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፡-
ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ባለዎት ፍቅር የተነሳ ስልጣን ከያዙ ሶስት ወር እንኳን ሳይሞላ እርስዎና ባልደረቦችዎ የፈጸማችኋቸውን ታላላቅ ተግባሮች፣ እዚህ አልዘረዝራችውም። እርስዎ፣ እቶ ለማ መገርሳና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ የለኮሳችሁት ኢትዮጵያዊነት፣ እሁን ወደ ፍቅርነት አየተለወጠ፣ እየነደደ ነው።  በፍቅር ላይ ደሞ እርስዎ መደመርን፣ እንዲሁም ይቅርታና ምህረት ማድረግን ጨመሩባቸው። በጣም ደስ ይላል።  ዳሩ ግን የእርስዎ ፍቅር፣ መደመር፣ ይቅርታና ምህረት የማይስማሟቸው፣ የጭለማ ሰራዊቶች መኖራቸውን፣ ባለፈው ቅዳሜ  ለእርስዎ አነጣጥረው፣ በህዝብ መሀል ያለ ርህራሄ ባፈነዱት ቦንብና ባፈሰሱት ንፁህ ደም ይፋ አድርገዋል።
ከቡር ጠቅላይ  ሚኒስትር ሆይ፡ የምንኖረው አብሪት፣ ትእቢት፣ ጭካኔ፣ ሴራና ግድያ በሞሉበት ዐለም ውስጥ ነው። ይህ የጭለማ ዐለም  የፍቅርን፣ የይቅርታንና የምህረትን ብርሃን ጠልቶ ሊያጠፋው እንደሚጥር እሙን ነው። ሆኖም ቦምቡ የተወረወረው ከላይ ለእርስዎ ቢሆንም፣ ከውስጥ መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለማጥቃትና አሁን የተቀዳጁትን ፍቅር፣ አንድነትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ለመንጠቅ የታቀደ እኩይ ሴራ ነው።
እርስዎ ያበሰሯቸው ይቅርታና ምህረት፣ በመሰረቱ፣ መልካም ቢሆኑም፣ ይቅርታና  ምህረት የሚደረጉት ስለ በደሉ ተፀፅተው፣ ይቅርታንና ምህረትን ለሚጠይቁ ሰዎች ብቻ ነው። አጥፍቻለሁ ይቅር በሉኝ፣ ማሩኝ የሚሉ ሳይኖሩ፣ ይቅርታ እድርጌላችኋለሁ፣ ምሬአችኋለሁ ማለት ትርጉም የለውም።  በዳዮቹ ስንትና ስንት ግፍ ፈፅመው፣ ሳይፀፀቱ፣ በቀላሉ ምሬአችኋለሁ ሲባሉ፣ ስላልተቀጡ፣ ታብየው፣ አዲስ ጥፋት ሊያደርሱ ይችላሉ። ለማድረስም ሲጥሩ እየታየ ነው። ይህ እውነት ለመሆኑ ማረጋገጫው ምህረት፣ ፍቅርና መደመር በሚሰበክበት ሰዐት፣ የተወረወረው ቦምብና አሁንም በሃገራችን የተለያዩ ቦታዎች የሚከሰቱት ትርምስና የህዝብ ፍጅት ናቸው።  እውነተኛ ምህረት ማድረግ የሚገባው፣ በዳይ በይፋ ወጥቶ፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንደተደረገው፣ ወንጀለኛም ፊት ለፊት ቆሞ “አጥፍቻለሁ፣ ተፀፅቻለሁና ይቅርታ አድርጉልኝ፣ ስለ ፍቅር በስመአብ ይቅር፣ እባካችሁ ማሩኝ” ሲል ብቻ ነው። ከዛ በፊት ግን ወንጀል የፈፀሙትን ገዳይዎችንና ሌቦችን ጨምሮ፣ ለፍርድ ማቅረብ ግድ ይላል። እነዚህ ግለሰቦች፣ ከያሉበት ተሰብስበው ተይዘው ወንጀላቸው በህግ ታይቶ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ዘብጥያ መውረድ አለባቸው። ከዛ በኋላ ተፀፅተናል፣ አጥፍተናል ሲሉ ጉዳያቸው ተምርምሮ፣ ምህረት ሊደረግላቸው ይገባል። ስለዚህ ከምህረት ፍርድ መቅደም አለበት። መቼም እንደ እግዚአብሄር መሀሪ የለም። ሆኖም አግዚአብሄር እውነተኛ ፈራጅ ነው። በተለያዩ ጊዜያት በግፈኛች ላይ የፈረደ ቢሆንም ትልቁን ፍርድ ለዐለም ፍፃሜ ጊዜ አዘግይቶታል። በዚያን ጊዜ ተደብቀውም ሆነ በጉልበታችውና በገንዘባችው ተማምነው ወንጀል የሠሩትን አጋልጦ ይፈርድባቸዋል። እግዚአብሄር መሀሪ እንደመሆኑ መጠን፣ ፈራጅም ስለሆነ፣ እርስዎም የእሱን ፈለግ ተከትለው ፈራጅም መሆን ይገባዎታል። ምህረትና ፍርድ እይነጣጠሉምና። ስለዚህ በየቦታው እየዞሩ የእርስዎን አስተዳደር ለማሳጣት፣ ፀጥታ የሚያደፈርሱትንና ጎሳን በጎሳ ላይ እያነሳሱ ባለፉት 27 ዓመታት እና አሁንም ደም የሚያፋስሱትን እብሪተኞች መቅጣት ይገባዎታል። እንዲህ ዐይነቶቹ እብሪተኞች፣ ፍቅርና ምህረትን እንደ ፍርሃትና ልምምጥ ስለሚቆጥሩት፣ እነዚህ መልካም ቃላት ያስቋቸዋል እንጂ ልባቸው ውስጥ አይሰርፁም።     
ደህንነትዎን አስመልክቶ፣ ምንም በህዝብ ፍቅር ነደው፣ ያለ እጃቢና ጠባቂ፣ በህዝብ ውስጥ ለመደባለቅ ቢወዱም፣ እርስዎ የጀመሩትን የለውጥ ሂደት የሚቃወሙ ግለሰቦችም ሆኑ የተደራጁ ኃይሎች በህይወትዎ ላይ አደጋ ለማድረስ ምንጊዜም ወደ ኋላ አይሉም። ይህም እባባሌ፣ በቦምቡ ውርወራ ተረጋግጧል። እርስዎም ክእዚህ ክስተት ተምረው፣ ለወደፊቱ ራስዎን ይጠብቁ። በደህንነት ሙያ፣ በብቃት በሰለጠኑ ታማኝ ሰዎች ይታጠሩ። እርስዎ የሚወክሉት ራስዎን ብቻ ሳይሆን፣ 100 ሚሊዮን ህዝብን ነው። እርስዎ አንድ ነገር ቢሆኑ የሚጎዱት እርስዎና ቤተሰቦችዎ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብና እርስዎ ሊተገብሩት ያሰቡት ራዕይም ጭምር ናቸው። ራስዎን ጠብቁ ሲባልም፣ እንደነ ኮሎኔል መንግሥቱ እና አቶ መለስ ዜናዊ፣ መንገዱን ሁሉ አዘግተው፣ ዜጋው ወደ እርስዎ አቅጣጫ እንዳያይ፣ ፊቱን ወደ ግድግዳ ማስዞርና ህዝብን በፍርሃት ማስራድ አይደለም። ተገቢውንና ዜጎችን የማያሸማቅቅ፣ ለህይወትዎ የሚገባውን ጥበቃ ያገኙ ዘንድ ግድ ይላል። ለወደፊቱ ሀገር ከተረጋጋች በኋላ ጥበቃውን ጥቂት ላላ ማድረግ ይችላሉ።  እንደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤና ከሳቸው ቀዳሚ እንደነበሩት ነገሥታት ማለት ነው።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ፣ በጥቂት የክቡር ዘበኛ እንጋቾቻችው ታጅበው፣ ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችንና ህዝብ ያሉባቸውን ስፍራዎች ይጎበኙ ነበር። አፄ ኃይለሥላሤ ክፍለሃገር ሲሄዱ፣ ጠባቂዎቻቸውን በርቀት ወደ ኋላ አስቀርተው ወይም ወፍራሞቹ አንጋቾቻቸው እያለከለኩ፣ ሸንቃጣው እሳቸው ፈጠን ብለው ሲራመዱ ተስተውለዋል። አፄ ምንይልክም ያለ ፍርሀት፣ ከህዝባቸው መሀል ይገኙ ነበር። ዜጎቻቸው በእጅ ሥራ እንዲሰለጥኑ ይፈልጉ ስለነበር፣  በተለይ በአንዳንድ ምሽቶች፣ ህዝቡ ፈጠራውን ይዞ እመንገድ ዳር ተኮልኩሎ ሲጠብቃቸው፣ እሳቸው በቅሎ ላይ ተፈናጠው፣ ፈጠራቸውን እያዩላቸው፣ ለፈጣሪዎቹ የሚገባቸውን ሽልማቶች ይሰጡ ነበር።  አጴ ቴዎድሮስም፣ ምንም እንኳን ራሳቸው ብርቱ ጦረኛ ቢሆኑም፣ ጋሻ ጃግሬዎችና ታማኝ ዘበኞች ነበሯቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ የአንድ ጎበዝ ጠባቂያቸው ታሪክ ይወሳል። ከእለታት አንድ ቀን፣ አንድ ሰው፣ ወንጀል ፈፅሞ ሊገደል ሲወሰድ፣ ንጉሱን ያይና፤ “ንጉሥ ሆይ ያስጥሉኝ፣ እኔ ጎበዝ ሰው ነኝ፣ አንድ ቀን እጠቅምዎታለሁ፣” እያለ ሲጮህ፣ አፄው ልቀቁት ብለው እስጣሉት። ከዛም  “እስቲ እውነት ጎበዝ ከሆንሽ፣ እኔን ታግለሽ ጣይኝ፣” ብለው ታገሉት። ሰውዬው አልወድቅ ብሏቸው፣ ብዙ ከታገሉት በኋላ እሳቸው ጣሉት። ጥንካሬውንም ዐይተው፣ “እውነትም ጎበዝ ነሽ”፣ ብለው  ሞቱን ሽረውለት፣ ጠባቂያቸው አደረጉት። ታዲያ አንድ ቀን እሳችው ከፊት፣ ይህ ጠባቂ ከኋላ ሆነው ሲራመዱ፣ የሰጉ ሰዎች፤ “ጃንሆይ እርስዎ ከኋላ ይሁኑ” ቢሏቸው፣ “ወግድ! እሱ ጎበዝ ነው፣ ጎበዝ ሰውን ከኋላ አያጠቃም፣ ሰውን ሳያየው ከኋላ የሚያጠቃ ፈሪ ብቻ ነው” አሏቸው።
በጥንት ዘመንም ሆነ አሁን እውነተኛ የስልጣን ወንበር ላይ የሚቀመጠው አንድ ሰው ብቻ ነው። በአንድ ወንበር ላይ ብዙ ሰዎች አይቀመጡም። ወንበሩም ቢሆን ለአንድ ሰው ብቻ ስለታነፀ።  በድሮ ዘመን የኢትዮጵያ ነገሥታት ስልጣን ላይ ለመፅናት የሚጠቀሙበት አንድ ዘዴ ነበራቸው። የስልጣን ተቀናቃኛቸው ሊሆኑ የሚችሉትን ልዑላን ዘመዶቻቸውን፣ በተራራ ውስጥ በተመሸገ ዋሻ ውስጥ ያስሯቸው ነበር። ተራ እና እድል የገጠመው ተመርጦ፣ ከዛ ውስጥ ተጠርቶ እስኪነግሥ ድረስ። ይህ ባይደረግ ኖሮ፣ ሁሉም እነግሣለሁ እያለ አየተላለቀ፣ ህዝብን እያጫረሰ  አገር ባመሰ ነበር። በአሁኑ ሰዐት ኢትዮጵያን መምራት የሚገባን ልዑላን እኛ ነን እያሉ፣ ከዚህ ቀደም የመሪነት ዕድል ቢገጥማቸውም፣ ስልጣናቸውን ለጥፋትና ሙስና ያዋሉት ግለሰቦች፣ አሁንም በዙሪያዎ አሉ። ከፍ ብዬ እንደጠቅስኩት፣  እርስዎ በፍቅር ተሞልተው፣ ይቅርታ ይደረግላቸው ብለው ቢለምኑም፣ እነሱ እርስዎን እንደ የዋህ ቆጥረዋል። እነዚህን እገር የሚያሸብሩ ግለሰቦች፤ አገር እስኪረጋጋ ድረስ ከህዝብና ከራስዎ መሀል ገለል አድርገው፣ ፀጥታና ሰላምን ቢያስከብሩ፣ ለኢትዮጵያ ይበጃታል፣ ብዬ ደግሜ አበክሬ እመክርዎታለሁ።         
ስለ መደመርም አንድ ቃል ማለት እፈልጋለሁ። እርስዎ ያመጡት መደመር እጅግ መልካም ነው። እንደ መርሆ ከመቀናነስ መደመር ወይም መደማመር ይሻላል። ቢቻልም ደግሞ ከመደመር ይልቅ መዋሃድ ይመረጣል። ለጊዜው ስለ መደመር እናውሳና፣ አብዛኛው ህዝብ መደመርን ቢወድም  መቀነስን የሚፈልጉና  መደመርን የማይሹም እንዳሉ ማስተዋል ይገባናል። አነዚህ ፍጡራን ከባህሪያቸው የተነሳ በምንም ተዓምር አይደመሩም። እነሱን በግድ ለመደመር መሞከር፣ የጠራ ውሃ ውስጥ ጋዝ ጨምሮ በግድ ለመደባለቅ መሞከር ነው። ስለዚህ የማይደመሩትን ችላ ብሎ ወይም ቀንሶ፣ የሚደመሩትን ብቻ መደመር ነው።  በቀውጢ ቀን ከህዝብ ገፊዎች ጋር ተደምረው፣ ሀብትና ስልጣን ሲያካብቱ የኖሩትን መንገደኞች፣ ለማተባቸው ከቆሙት እኩል፣ በሉ ተደመሩን ብሎ መጋበዝ፣ ፍትህን ማጓደልና ፍርድን መበደል ነው። ስለዚህ፣ ከመደመር ይቅደም መመርመር።      
ፖሊሶችና  ወታደሮችም ከአዲሱ ለውጥ ጋር አብረው እንዲራመዱ መታደስ አለባቸው። ዛሬ ያሉት  በተለይ ፌዴራል የሚባሉት ፖሊሶች፤ ሰውን ከመደብደብና ከመግደል በቀር ምንም ሙያ የላቸውም። እኔ ሳድግ ድሮ የማውቃቸው በፖሊስነት ተግባር የሰለጠኑት እውነተኛ ሰላማዊ  ፖሊሶች ግን ዜጎቻቸውን አክብረው፣ ስርዐትን ተከትለው ነበር ፀጥታን የሚያስከብሩት። መልካም ከመሆናቸው የተነሳ “ፖሊስ፣ ፖሊስ የነፃነት፣ የሰላም ሰንሰለት” ተብሎ ተዘምሮላቸው ነበር።  እነዚያ ምርጥ ፖሊሶች በጣም ልዩ እና አደገኛ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር የጋዝ ጭስ እንጂ ሜዳ የወጣ ማንኛውም  ህዝብ ላይ ጥይት አይተኩሱም  ነበር። ሰው በአንድ ወንጀል ከተጠረጠረም፣ በፖሊስ ጣቢያ ከታገተ ከ24 ሰዐት በኋላ ወይም ከዘገየ በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት ያቀርቡ ነበር። ሰውን ከቤቱ ለመያዝም ሆነ የቤት ፍተሻ ለማድረግ  ህጋዊ የመጥሪያ ደብዳቤ ይዘው ሲመጡም ታይተዋል። የአሁኖቹም እንደዚህ ለህግና ስርዐት ተገዢ እንዲሆኑ በአስቸኳይ መታደስ አለባቸው።
ክቡርነትዎ፤ እንደመር፣ እንፋቀር፣ ይቅር እንባባል  ብለው ሰላምና ፀጥታን ለማፈን ሲጣጣሩ፣ ፍቅርና ይቅርታን የሚጠሉ፣ ሌብነታቸውንና አምባገነንነታቸውን የሚያስቀረውን፣ እርስዎ የጀመሩትን ለውጥ የሚቃወሙ ኃይሎች፣ ቦምቦችን እንደ ቆሎ በየኮሮጆው እየሞሉና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ በየቤታችው ቆልለው፣ አገሪቷን አያደሙና በብዛትም ሊያደሙ እያሴሩ መሆናቸው ከእርስዎ የተሰወረ አይደለም። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች፣ ምስኪኑን ህዝብ ሳይጨርሱና ሳያጫርሱ፣ መሳሪያቸውን ድንገት ሳያስቡት፣ ከየቤታቸው መልቀምና ሀገር እስኪረጋጋ ድረስ እነሱን ጠራርጎ፣ወህኒ ቤት ማቆየት በጣም ያስፈልጋል። ይህን ነገር ችላ ሳይሉ በቶሎ እርምጃ ይወሰዱ። እነሱን በሚያስሩብት ጊዜ ደግሞ እነሱ በግፍ ለዓመታት ያሠሯቸውን፣ አሁንም በየእስር ቤቱ የሚገኙ፣ ያልታወቁና የተረሱ ዜጎች፣ በፍጥነት ተፈተው፣ ክቤተሰቦቻቸው ይደባለቁ ዘንድ ያስታውሷቸው።
ከጥቂት ቀናት በፊት እርስዎ እንደ አበሰሩን፣ ኢትዮጵያ ቤንዚንና የተፈጥሮ ጋዝ አግኝታለች። እሰየው ነው። ባለፉት 50 ዓመታት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ኦጋዴን ውስጥ ቤንዚን እንደተገኘ ሲሰማ ከርሟል። ዳሩ ግን ቤንዚኑ የህልም እንጀራ ሆኖ ቀርቶ ነበር። ይህን መልካም ዜና ለኢትዮጵያ ህዝብ አብሳሪው እርስዎ በመሆንዎ፣ በእውነት እድለኛ ነዎት። ምንም እንኳን ይህ ዜና መልካም ቢሆንም፣ በዚህ ጠንቅ በነዳጅ ጉድጓዶቹ አካባቢ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የሶማሊያ ሱማሌዎች መካከል ጠብና ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ታላቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል። ዳሩ ግን እርስዎ  አርቀው ስላሰቡ፣ ከሶማሊያ መሪዎችም ጋር አብሮ የመሥራት ውይይት አካሂደዋል። ይህም ውይይትዎ፣ ፍሬ እንደሚያፈራ ተስፋ አለኝ።
በመጨረሻም በእግዚአብሄር ስለማመንዎ ደስተኛ እንደሆንኩ ልገልፅልዎት እወዳለሁ። ከአፄ ኃይለሥላሤ በኋላ ባለፉት 45 ዓመታት ሥልጣን የያዙ መሪዎች ሁሉ፣ እግዚአብሄርን ክደው፣ ችግሩን ሁሉ በራሳችን ጉልበት እንፈታዋለን ሲሉ ተደምጠዋል። አርስዎ ግን ከተመረጡበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሄርን ሲጠሩ ተሰምተዋል። ይህ ትልቅ እርምጃ ነው። ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሄር ናትና። በሚሠሯቸው ሥራዎች ውስጥ ሁሉ የሚያምኑበት፣ በአደባባይም ስሙን  የጠሩትና ያከበሩት እግዚአብሄር ይግባበት።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሰላም፣ በፍቅርና በብልፅግና ለዘላለም ትኑር!!       


Read 4841 times