Saturday, 07 July 2018 10:42

በኢትዮጵያ ሁለት የጠረፍ ከተሞች ግጭት ተከሰተ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በያዝነው ሣምንት በሰሜን ምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ሁለት የጠረፍ ከተሞች በተለያዩ መነሾዎች የተከሰቱት ጠንከር ያሉ ግጭቶች በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ማስከተላቸውን ምንጮች አመለከቱ፡፡ ግጭቱቶቹ የተከሰቱትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀው የጠረፍ ከተሞችን ችግሮች የመዳሰስና የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን የመቀመር  ዓላማ ይዞ የተካሄደው አውደ ጥናት በተጠናቀቀ ማግስት ነው፡፡   
በዚህ አውደ ጥናት ላይ ኢትዮጵያ ሞያሌ እና መተማን ከመሳሰሉ የጠረፍ ከተሞች የመጡ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን እነዚሁ ተሳታፊዎች ጉባኤውን አጠናቀው ወደየመጡበት በመመለስ ላይ ሳሉ ግጭቶቹ መከሰታቸውን የጠቀሱት ምንጮቻችን፤ የመተማው ግጭት ሰኔ 27 ቀን 2010 ዓ.ም፣ የኢትዮጵያ ሞያሌው ደግሞ በማግስቱ ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በተከታታይ ቀናት መከሰታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ውጥረት ተለይቷት በማታውቀው የኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ የተከሰተው ጎሣን መሠረት ያደረገ ግጭት መሆኑንና የመተማው ደግሞ ከእርሻ መሬት ጋር የተያያዘ እንደሆነ የጠቀሱት ምንጮች፤ ከሁለቱ ከተሞች የመጡት የጉባዔው ተሳታፊዎች፣ በስብሰባው ላይ ከሰጡት አስተያየት መረዳት እንደሚቻለው በተደጋጋሚ ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡
በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ ከሁለት ወር በፊት ሚያዚያ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ተፈጥሮ በነበረ የጎሣ ግጭት በርካታ ሰዎችን ለጉዳት የዳረገና ንብረትም ያወደመ ግጭት መከሰቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ዳግም ባገረሸው ጎሣን መሠረት ያደረገ ግጭት ከሁለቱም ወገን ሰዎች መሞታቸውንና ከመሐል ሐገር ወደ ሞያሌ የሄዱ ዘጠኝ የጭነት መኪኖችም መጋየታቸውን አመልክተዋል፡፡
በሞያሌ በሚገኘው የፌደራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ላይ ጉዳት መድረሱን የጠቀሱት ምንጮቻችን፤ በገሪ እና ቦረና ጎሣዎች መካከል የተከሰተውን ይህን ግጭት ለማብረድ የጸጥታ ኃይሎች ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ ግጭቱ በዘመናዊ መሣሪያ የተደገፈ በመሆኑ ጉዳቱን ከፍ እንደሚያደርገውና የጸጥታ ኃይሎች ግጭቱን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አስውቀዋል፡፡
በኦሮሚያና በኢትዮ-ሶማሌ ክልል ሥር ለሚተዳደሩ ሁለት ወረዳዎች መቀመጫ በመሆን በምታገለግለውና የአንዳንድ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች መቀመጫ በሆነችው የሞያሌ ከተማ፤ ከሁለት ወራት በፊት ከአስፋልት ግራና ቀኝ በመሆን ባካሄዱት የተኩስ ልውውጥ  በርካታ የከተማው ነዋሪዎች ለአካል ጉዳትና ለሞት መዳረጋቸውን እንዲሁም ንብረት መውደሙን ያስታወሱት እነዚሁ ምንጮች፤ ከተማዋ ዘወትር በውጥረት የምትኖርና ባልረባ ምክንያት ግጭት እንደሚቀሰቀስ፤ ሁለቱ ጎሣዎች በመበቃቀል መንፈስ እንደሚጠቃቁ፤ የከብት ዝርፊያ እንደሚካሄድና በከተማው በሰፊው በሚታዩ የሞተር ሳይክሎች የታገዘ የሰዎች ጠለፋ አንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡
በአንድ የአስፋልት መንገድ ግራና ቀኝ ተለያይተው በሚገኙት በሁለቱ መስተዳድሮች የሚታዘዙ የጸጥታ ኃይሎች፣  በግጭቱ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የተናገሩት ምንጮቻችን፤ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልና የኦሮሚያ ክልል አድማ በታኝ አባላት እንዲሁም የቀበሌ መስተዳድር ሚሊሻዎችን በስም ይጠቅሳሉ፡፡ የገሪ ጎሣ አባላት (ሶማሌ) እና የቦረና ጎሣ አባላት በፈጠሩት ግጭት፣ ከሁለቱም ወገን ሁለት-ሁለት ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንም አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ሱዳንን ከኢትዮጵያ በሚያዋስነው የምዕራብ ጎንደር ዞን፣ መተማ አካባቢ የሚገኝ የእርሻ መሬት ይገባኛል ጥያቄ ለግጭቱ ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘላለም ልጃለም፤ ‹‹ሱዳኖች በኢትዮጵያ መሬት ላይ የሚያነሱት የይገባኛል ጥያቄ ትክክል አይደለም›› ብለዋል፡፡
‹‹የእርሻ ስራ በሚያከናውኑ የአካባቢው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ላይ ትንኮሳ በመፈጸማቸው ምክንያት ግጭቱ ተከስቷል›› ያሉት ኃላፊው፤ የአካባቢው አርሶ አደሮችም የመከላከል አጸፋ መውሰዳቸውንና አሁን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቋራ እና መተማ ጥበቃ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የዞኑ አስተዳዳሪና አርሶ አደሮች እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ ግጭቱ የተረጋጋ ቢመስልም፤  በሱዳን ወታደሮች ትንኮሳ ምክንያት በአካባቢው ባሉ ሌሎቹ የኢትዮጵያ መሬቶች ላይ የእርሻ ስራ ማከናወን አልተቻለም ፡፡
ከአማራ ብዙሃን መገናኛ የተገኘው መረጃ፤ በግጭቱ ምክንያት በመተማ ደለሎ በኩል የሚገኝ የሱዳን ጦር የተደመሰሰ ሲሆን፤ አንድ የሱዳን ሻለቃ አመራር ህይወቱ አልፏል፡፡ በቋራ ነፍስ ገበያ በኩል በተፈጠረው ግጭትም 7 የሱዳን ወታደሮች መሞታቸውንና 2 መኪናዎችንና 7 የጦር መሳሪያዎችም መማረካቸውን አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡
ሶስት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና ሁለት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ህይወታቸው ማለፉንም ሰምተናል፤ 6 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል። ከነዚህም መካከል ሁለቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ናቸው። ለጣምራ የጸጥታ ቁጥጥር በሚል በአካባቢው የሰፈረው የሱዳን ጦር፣ በተለያዩ ጊዜያት ትንኮሳ እንደሚፈጽም የአካባቢው ነዋሪዎችና ዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል። በተደጋጋሚ በሰላማዊ መንገድ ቦታውን ለቀው እንዲወጡ ጥረት ቢደረግም ፈቃደኛ አለመሆናቸውም ታውቋል፡፡
(የድንበር ጉዳዮችን የሚፈትሸውንና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን የተካሄደውን ወርክሾፕ የተመለከተ የቅኝት ዘገባ በሚቀጥለው ዕትም ለንባብ ይቀርባል፡፡)

Read 7721 times