Saturday, 07 July 2018 10:43

የፌደራል ፖሊስ ልብስ ለብሰው 1.ሚ ብር የዘረፉ ተያዙ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰውና በመሣሪያ ታግዘው፣ ከአንድ ግለሠብ ቤት ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ብር እና መጠኑ በትክክል ያልታወቀ ዶላር የዘረፉ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እያካሄደ ሲሆን ግለሰቦቹ የፌደራል ፖሊስ አባላት ይሁኑ አይሁኑ፣ በምርመራ እንደሚያረጋግጥም ተገልጿል፡፡
ሰኔ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ቀትር ላይ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ሃና ማርያም አካባቢ፣ ሁለት የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሡ ሰዎች፣ የግለሰብ መኖርያ ቤት ውስጥ በመግባት ዝርፊያውን እንደፈፀሙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ሁለቱ ግለሠቦች የዘረፉትን ገንዘብ ይዘው ሲንቀሳቀሱ  የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች “የድረሱልኝ ጩኸት” በማሠማት፣ ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ዘረፋውን ከፈፀሙ በኋላ የተመለከቷቸውን ሰዎች በመሳሪያ ሲያስፈራሩ እንደነበር የተናገሩት ምንጮች፤ ወዲያውኑ በፖሊስ በተደረገባቸው ክትትል፣ ከአካባቢው ሳይርቁ መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡
ፖሊስ በበኩሉ፤ ተጠርጣሪዎቹ የፌደራል ፖሊስ አባላት ይሁኑ አይሁኑ ማረጋገጥን ጨምሮ፣ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

Read 10070 times