Saturday, 07 July 2018 10:46

በሶማሌ ክልል እስረኞች ላይ በባለስልጣናት የታገዘ አስከፊ ስቃይ ተፈፅሟል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  በሶማሌ ክልል “ኦጋዴን” በተሠኘ እስር ቤት የነበሩ እስረኞች ላይ በባለስልጣናት የታገዘ አስከፊ የሠብአዊ መብት ጥሠት መፈፀሙን “ሂዩማን ራይትስ ዎች” ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ባወጣው ሪፖርት ያጋለጠ ሲሆን የክልሉ መንግሥት በበኩሉ፤ ሪፖርቱ ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አስተባብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በአስቸኳይ በእስር ቤቱ ላይ ምርመራ እንዲካሄድ አድርገው፣ በድርጊቱ የተሳተፉ የክልሉ ባለስልጣናትና የፀጥታ ሃይሎች ለህግ መቅረብ አለባቸው ብሏል - “ሂዩማን ራይትስ ዎች”፡፡
“እንደሞቱት ነን” በሚል ርዕስ ተቋሙ ባወጣው በዚህ ሪፖርት፤ በርካታ ሰዎች ያለ ፍትህ በእስር ቤቱ ውስጥ ታስረው፣ የስቃይ ምርመራ፣ አስከፊ ድብደባና የተለያዩ የመብት ጥሠቶች ተፈፅመውባቸዋል ብሏል፡፡ የመብት ጥሠቱን የማረሚያ ቤቱ ጥበቃዎችና የክልሉ ልዩ ኃይል በጋራ እንደሚፈፅሙ የገለፀው ሪፖርቱ፤ በቂ የምግብ አቅርቦትም ሆነ የህክምና አገልግሎት እንደሌለም አመልክቷል፡፡
“ሂውማን ራይትስ ዎች” ያነጋገራቸው ከ70 በላይ የቀድሞ እስረኞች በወህኒ ቤቱ የደረሰባቸውን አስከፊ ስቃይና በደል በዝርዝር አስረድተዋል፤ ረቋሙ በለቀቀው የቪዲዮ ማስረጃ፡፡ እስረኞቹ ከጠቀሷቸው የስቃይ ምርመራዎች መካከል - ልብስን አስወልቆ መሬት ላይ እያንከባለሉ መግረፍ፣ ሠብአዊ ክብርን በሚገፍ መልኩ ሽማግሌዎችን ሳይቀር በገዛ ሴት ልጆቻቸው ፊት እርቃናቸውን እንዲቆሙ ማድረግ፣ የታሣሪዎችን ሚስቶች መድፈርና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡
እስር ቤት ውስጥ ሴት እስረኞችን አስገድዶ መድፈር የሚፈፀምባቸው በመሆኑ በርካታ ህፃናት እዚያው እስር ቤት ውስጥ ተወልደዋል ይላል - የተቋሙ ሪፖርት፡፡ እነዚህ እስረኞች ስቃይና እንግልቱ የሚደርስባቸው “የኦብነግ አባል ናችሁ” በሚል ውንጀላ እንደሆነም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
የክልሉ መንግስት በበኩሉ፤ ሪፖርቱ ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልፆ፤ ተቋሙ በለቀቀው ቪድዮ ላይ የቀረቡት ሠዎች “የሃሠት ምስክሮች ናቸው” ሲል አስተባብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በጀመሩት ለውጥ ውስጥ የኦጋዴን እስር ቤት አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ትኩረት በመስጠት ጉዳዩ ተመርምሮ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡና የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ “ሂውማን ራይትስ ዎች” ጠይቋል - በሪፖርቱ፡፡

Read 8480 times