Saturday, 07 July 2018 10:50

“ፕሮፌሽናል ተጫዋች ሆኜ፣ ሀገሬን ወደታላቅ ደረጃ ለማድረስ ህልም አለኝ”

Written by  ግሩም ሠይፉ (ከሞስኮ)
Rate this item
(5 votes)

 ታላቅ ህልም ይህ ህልም አይደለም? እውነት ነው! ከትልቅ ወይም ከትንሽ መወለድ ትልቅ አያደርግም፡፡ ትልቅ ህልም ይዞ መወለድ ግን ታላቅ ያደርጋል የሚል መግቢያ ስለ ዳግማዊ ቴዎድሮስ  የተፃፈውና በየቦታው የሚሰራጨው  የህይወት ታሪክ ተቀምጧል፡፡ ለፊፋ የተላከው ሙሉ ደብዳቤ የተፃፈው ከዚህ በታች እንደቀረበው ነው፡፡….
በኔ ህይወት የመጀመሪያውን ፎቶ የተነሳሁት በተወለድኩ በ20 ቀኔ ነበር፡፡ በመቀጠል ለክርስትና በ40 ቀኔ ለጥምቀት የተነሳሁት ፎቶ ነው፡፡ ሶስተኛ የተነሳሁት ፎቶ ግን የተለየ እና አንፀባራቂ ነበር። በዓለም ህዝብ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው ይህን ክብር ለማግኘት በርካቶች ተቆጭተዋል፣ አልቅሰዋል፣ እራሳቸውን ሰውተዋል፡፡ ይህ የሆነው ለዓለም ዋንጫ አሸናፊነት ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም የ3 ወር ጨቅላ ሳለሁ በአፍሪካ ምድር በደቡብ አፍሪካ የሚዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ ምክኒያት በማድረግ በሰው ዘር መገኛ በአፍሪካ መዲና በሆነችው በአዲስ አበባ በኮካ ኮላ አማካኝነት የዓለም ዋንጫ ታሪካዊ ጉዞ ለማድረግ እዚህ ተገኘ። የአፍሪካ ዋንጫ ለማግኘት እና ለመሳተፍ ሩቅ ለሆነበት ታላቅ ህዝብ የዓለም ዋንጫ ህልም ነበር። ነገር ግን ማግኘት ባንችል እንኳን አጠገቡ ቆሞ ፎቶ ለመነሳት ግን የታደልን ነበርን፡፡ በሚኒሊየም አዳራሽ ከ5ሺ ሰው በላይ ፎቶ የተነሳ ሲሆን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊ በቤተ-መንግስት በመገኘት ልዩ አቀባበል አድርገውለታል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ብቸኛው የሶስት ወር ጨቅላ ህፃን በአባቴ እቅፍ ውስጥ ሆኜ ከታሪካዊው የዓለም ዋንጫ ጋር ፎቶ በመነሳት እድገቴን ጀመርኩኝ፡፡ በሶስት ዓመቴ ለእግር ኳስ ባለኝ የመጫወት ፍቅር በቀድሞ ታላቅ እግር ኳስ ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬ በተመሰረተው አሴጋ ስፖርት አካዳሚ ስልጠና መውሰድ ጀመርኩኝ፡፡ አሁን የ8 ዓመቴ ላይ የምገኝ ስሆን እለት ተእለት ችሎታዬን እያሳደኩኝ እገኛለው፡፡ ትምህርቴን በሚገባ እየተከታተልኩኝ ሲሆን በጊብሰን ስኩል ሲስተም የ3 ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ። ከአገር ውስጥ የማደንቃቸው ተጫዋቾች ውስጥ ሰለሃዲን ሰይድ፤ አዳነ ግርማ ና ጋቶች ፓኖ ሲሆኑ ከውጪ ደግሞ ሚሲ፤ ሮናልዶ፤ ኔይማር፤ ጆርጅ ዊሃ፤ መሃመድ ሳላህ፤ እና ዋይኒሮኒ ቀልቤን ይገዙታል እኔም ከ8 ዓመት በኋላ በ2010 የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ምክኒያት በድጋሚ ታሪካዊውን የዓለም ዋንጫ በኮካ ኮላ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሲሆን ለእኔ ደግሞ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልኛል፡፡ ምክኒያቱም ትልቅ ተጫዋች እንድሆን የዓለም ዋንጫ መነሳሳትን ይፈጥርልኛል። አንድ ቀን በርትቼ በመስራት ህልሜን አሳካለው፡፡ ኮካ ኮላ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ታዳጊዎች ከፍተኛ መነቃቃትን በመፍጠሩ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ህልም አለኝ !ፕሮሽናል ተጫዋች ሆኜ ሀገሬን ወደታላቅ ደረጃ ለማድረስ ! አንድ ቀን!!
ታዳጊ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ባጫ
የካቲት 2010 ዓ.ም
ዳግማዊና አባቱ ከላይ የተጠቀሰውን ህልም በደብዳቤ ለፊፋ አደረሱ፡፡ የፊፋ ሃላፊዎችም በሰጡት ምላሽ ታሪኩን ማየታቸውንና መረዳታቸውን ከገለፁለት በኋላ ያንተን ጀግኖች ሞስኮ መጥተህ እንድትመለከት እናደርጋለን ብለው ቃል ገቡለት፡፡ ከዚያም ወደ 21ኛው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ አገር ራሽያ ገባ፡፡  ከ8 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ታዳጊ የእግር ኳስ ተጨዋች ዳግማዊ ቴዎድሮስ ጋር የተገናኘነው በሞስኮው የፍራንድሺፕ ዩኒቨርስቲ ደጃፍ ላይ በሚገኘው የፊፋ ደጋፊዎች አደባባይ Fan fest ላይ ነው፡፡ ብራዚል ከሜክሲኮ የተገናኙበትን የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በትልልቅ የሲኒማ ስክሪኖች ለመታደም ነበር፡፡ በፊፋ የደጋፊዎች አደባባይ የብራዚልና ሜክሲኮ ጨዋታ ሲካሄድ ዳግማዊ ከራሽያ እና ከሌሎች አገራት ታዳጊዎች እና ወጣቶች ጋር ተቧድነው ኳስ እየተጫወቱ ነበር፡፡ ላቡ ጠፍ እስኪል ለተሰለፈበት ቡድን ይጫወት የነበረው ዳግማዊ እኔ ወደተቀመጥኩበት አካባቢ የመጣው ብራዚል 2ለ0 ሜክሲኮን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ መሸጋገሯን ካረጋገጠች በኋላ ነው፡፡  በላብ እንደተጠመቀ አጠገቤ ተቀመጠና ሶስት ጎሎች ማግባቱን ነገረኝ፡፡ እኔም ታዳጊው ለእግር ኳስ ያለውን ፍቅር እያደነቅኩ ቀጥታ ወደ ቃለምልልሱ ገባሁ፡፡
በመጀመርያ ያነሳሁለት ጥያቄ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ያገኛቸውን ልምዶች በተመለከተ ነበር… ዳግማዊ ሲመልስ ‹‹በዓለም ዋንጫ ያገኘኋቸው ልምዶች ያለኝን ህልም የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት በተለያዩ የቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭቶች፤ ቪድዮች ያየኋቸው ቡድኖች እና ተጨዋቾች በየስታድዬሞቹ ተገኝቼ ስመለከታቸው ቴክኒካቸውን ሲጠቀሙ ነው፡፡ ወደራሽያ ከመጣሁ በኋላ ስታድዬም ገብቼ በጣም ደስ ብሎኝ እየጨፈርኩ ያያኋቸው 3 ጨዋታዎች ናቸው፡፡ አርጀንቲና ከናይጄርያ እንዲሁም ብራዚል ከኮስታሪካ በሴንትፒተርስበርግ ሲጫወቱ ማየቴ በጣም ነው ያስደሰተኝ፡፡ በተለይ አርጀንቲና እና ናይጄርያ ካደረጉት ጨዋታ በኋላ የማደንቃቸውን ሜሲና እና አጉዌሮን ሰላም ብያቸዋለሁ፡፡ እነሱን ሲጫወቱ በማየቴ እና በአካል ተገኝቼ በመጨበጤ ደስተኛ ነኝ፡፡ ሜሲ እነደውም ማልያውን ሲወረውር ይዥው ነበር። ግን ማሊያውን ይዤው ብዙም ሳልቆይ ትልልቅ ሰዎች ጎኔ አካባቢ ጉዳት እስኪሰማኝ ድረስ ላዬ ላይ ተከምረው ነጠቁኝ፡፡ አለቀስኩኝ ግን ያዘነልኝ አልነበረም ሁሉም እንደእኔ ሜሲን ማግኘት እና ማልያውን መውሰድ ብርቅ ሆኖባቸው መሰለኝ፡፡
እንግሊዝ ከኮሎምቢያ በስፓርታክ ስታድዬም ሞስኮ ላይ ያደረጉትን ጨዋታም በፊፋ ጋባዥነት ለመከታተተል ችያለሁ፡፡ ጨዋታው ካለቀ በኋላ ከአሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝ ጌት፤ ከተጨዋቾቹ ሃሪ ኬን እና አሽሊ ያንግ ጋር ፎቶ ሰልፊዎችን መነሳት ችያለሁ። ከአሽሊ ያንግ ጋር ለአራት ደቂቃዎች አወራን፡፡ ማሊያውን አውልቆ ከሰጠኝ በኋላ ትልቅ ኳስ ተጨዋች መሆን እንደምፈልግ ነገርኩት፡፡ የእግር ኳስ የስልጠና እድል በእንግሊዝ እንዲያፈላልግለኝም ጠይቄዋለሁ፡፡ አሽሊ ያንግም በጣም ተገርሞ ነበር። ችግር የለም የኢሜል አድራሻዬን እልክላሃለሁ ብሎኛል። ከአሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት ጋር የተነሳሁት ሰልፊ ፎቶም አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ አባቴ  እና እኔ ሃሪ ኬንን ስናናግር በመላው ብሪታኒያ በቀጥታ የቴሌቭዥ ስርጭት እየተላለፍንም ነበር። ለሃሪ ኬን፤ አሽሊ ያንግ፤ ለራሽፎርድ እና በአጠቃላይ ለ6 ተጨዋቾች የእግር ኳስ ህልሜንና የህይወት ታሪኬን የሚያሳይ ሲዲ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ለነገሩ ከስታድዬም ውጭም ብዙ የድሮ ተጨዋቾች ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ ከናይጄርያው ኑዋንኩ ካኑ፤ ከአርጀንቲናው ሃቪዬር ዛኔቲ….
በአጠቃላይ ራሽያ ከመጣህ በኋላ የዓለም ዋንጫ ህልምህ የባሰ ተቀጣጠለ ነው የምትለው፡፡
ዳግማዊ ምላሹን ሲቀጥል ‹‹የዓለም ዋንጫዋን የስምንት ወር ህፃን ሳለሁ፤ ከዚያም 8 ዓመት ሲሞላኝ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት መጥታ በነበረ ጊዜ አይቻታለሁ፡፡ ዋንጫዋ በመስታውት ውስጥ ነበረች፡፡ አሁን ደግሞ ራሽያ  መጥቼ ግጥሚያዎችን  ከተመለከትኩ በኋላ በግልፅ የማየት ፍላጎት አድሮብኛል፡፡ ከፊፋ ጋር ይህን እድል ለማሳካት ከአባቴ ጋር ሆነን ጥረት ማድረጋችንን ቀጥለናል፡፡ ምናልባትም በፍፃሜ ጨዋታው ላይ ዋንጫዋን የማይበት እድል እንደማገኝ የፊፋ ሰዎች ቀጠሮ ሰጥተውኛል›› ብሏል፡፡
የኢትዮጵያን የዓለም ዋንጫ የተሳትፎ እድል እንዴት እንደሚያስበው እና በእግር ኳስ መድረስ ስለሚፈልግበት ደረጃ… ዳግማዊ ቴዎድሮስን ጠይቄው ሲመልስ ‹‹እኔ እንደማውቀው ከሆነ ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ማለፏ አይቀርም፡፡ አሁን እግር ኳሳችን ያለበት ደረጃ ትንሽ ነው፡፡ ከ10 ዓመታት በኋላ ጠብቁኝ ፤ አድጌ ኢትዮጵያ ዓለም ዋንጫን ትሳተፋለች ወይንም ታዘጋጃለች ወይንም ታሸንፋለች። ኢትዮያ የዓለም ዋንጫን ለመሳተፍ ስትበቃ ሁላችንም በጣም የምንደሰት ይመስለኛል፡፡ ህዝብ ሁሉ የአገሩ አፈር ላይ ይንከባለላል፡፡ ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ ኢትዮጵያ አፍሪካ ዋንጫን ስትሳተፍ የነበረውን ስሜት ትዝ ይለሃል፡፡  እኔ ጨዋታውን ተመልክቼ ውጤቱን ካረጋገጥኩ በኋላ በምንኖርበት ግቢያችን ከጎረቤታችን ልጅ ጓደኛዬ ኢሊሃም ጋራ ሆነነን ግቢውን ከ10 ጊዜ በላይ እየዞርን በጩሀት ነው ያቀልጥነው፡፡ ዋልያ ዋልያ ዋልያ እያልን ስንጮህ ቆይተን ደክሞን ወደቤት ገባን፡፡ ይህ ስሜት በእኔ ስኬት ቢደገመ ደስታዬን አልችለውም።›› ሲል ተናግሯል፡፡
በመጨረሻም ‹‹ለእኔ አቅም የሚሆን እግር ኳስ በባህር ማዶ እንደማገኝ ተስፋ አለኝ፡፡ ይህ ህልሜ ተሳክቶም ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ እንድትበቃ እፈልጋለሁ፡፡ ሁላችንም የኢትዮጵያ ህዝብ በየሙያችን ህልም ቢኖረን ጥሩ ነው፡፡ በህልምና በራዕይ ከሰራን ምንም አያቅተንም።” በማለት በስፖርት አድማስ ዳግማዊ ቴዎድሮስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
የዳግማዊ አባት ቴዎድሮስ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው ራሽያ ከገቡ በኋላ ከፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር እንዳሰቡት ቶሎ መገናኘት ባይችሉም በፊፋ ሃላፊዎች ድጋፍ 3 ጨዋታዎችን ለማየት በመቻላቸው የበለጠ አቅም የገነባላቸው ሆኗል። ዳግማዊ በጣም የሚያደንቃቸውና የሚወዳቸውን ተጨዋቾች በአይኑ ለማየት መቻሉና በአካል አግኝቶ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ሊያገኝ መብቃቱ እንዳስደሰተው የሚገልፀው ቴዲ ለእግር ኳስ ህይወቱ እና እድገቱ መሰረት የሚሆኑ ልምዶችን ስለተሳካለት በጣም ተደስቻለሁ ብሏል፡፡ በተለይ ከ20 በላይ የዓለም መዲያዎች ጋር መገናዐቱ እና በህልሙ ዙርያ ቃለምልልስ ማድረጉ ብዙ እድሎችን የፈጠረለት እና ተስፋውን ያጠናከረለት መሆኑን ለስፖርት አድማስ ያስረዳው ቴዲ ባጫ አንዳንድ ጋዜጠኞች የተነሳበትን ህልም  እና ያነገበውን ዓላማ የሚገልፅበትን የጭንቅላት ፍጥነት እና ቅልጥፍና ማድነቃቸው የሚያበረታታ ነው ብሏል፡፡ በተለይ የፊፋ ሰዎች በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ የእግር ኳስ አካዳሚዎች የስልጠና እድል እንዲፈጠርለት የሰጡትን ድጋፍ እና ምክር አክሎ የገለፀው ቴዲ ዳግማዊ ለእግር ኳስ ያለውን ስሜት እና ፍቅር በማንፀባረቅ ነገ አሳካዋለሁ በሚለው አቅጣጫ የሚገፋው ውጤት መሆኑን በኩራት ተናግሯል፡፡
‹‹ዳግማዊ እንዳሰበው በአውሮፓ እግር ኳስ አካዳሚዎች ገብቶ መሰልጠን ከጀመረ ገና በ16 ዓመቱ የተሳካለት ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ይሆናል። አቅሙን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ልምዶች እያዳበረ ነው። ቋንቋው ጥሩ ነው፡፡ አገሩን  ይወዳል፡፡  ስለዚህም በእግዚአብሄር ፈቃድ ያለመውን ህልም በማሳካት ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ ተስፋ አደርጋለሁ›› በማለት ቴድሮስ ባጫ ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡
የዓለም ዋንጫው አለም አቀፍ ትኩረት እንዳሳበለት ማረጋገጥ የሚቻለው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተደረገው ቃለምምልሶብ በቴሌቭዥኖች መተላለፉ ነው፡፡ በአርጀንቲና፤ በብራዚል፤ በእንግሊዝ እና በራሽያ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የኦንላይን ስርጭቶች ስለ ዳጋማዊ አጫጭር ዘገባዎች ተሰርተዋል፡፡ በሌላ በኩል ሞስኮ ከመጣ በኋላ ከሚወዳቸው እና ከሚያደንቃቸው ጀግኖች ሜሲን፤ አጉዌሮን፤ እነ ራሽፎርድን በአካል ማየትም ችሏል፡፡
ቴዎድሮስ ሲናገር እሱ ለልጁ የማናጀርነት ሚና ሳይሆን እየተጫወተ የሚገኘው የአባትነት ሃላፊነቱን ነው፡፡
‹‹እኔ ዋጋ እየከፈልኩ ያለሁ አባት ነኝ፡፡ ዋጋ የምከፍለው ለምንድነው… ለምወደው ልጄ ነው፡፡  ለሰዎች መናገር የምፈልገው ህፃናቶች እንደችሎታቸው መጠን እየተጫወቱ ማደግ አለባቸው፡፡ ኢንጅነር መሆን የሚፈልግ ልጅ አባቱ ከልጅነቱ ይህን ሙያ ሊያፈቅር የሚችል ነገር ቢያደርግለት ጥሩ ነው፡፡ ዶክተርም… ሌላም  ሙያ ቢሆን ከልጅነት በፍቅር ተኮትኩቶ ሊያድግ የሚችል ነው፡፡ በእኔ በኩል ዳግማዊ ከልጅነቱ የጀመረውን የእግር ኳስ ፍቅር እየተከታተልኩ እየደገፍኩት ነው፡፡ ወደ ስታድዬም ወስደዋለሁ፡፡ እግር ኳስን እንዲጫወት አበረታተዋለሁ። ሜዳ አብሬው እሄዳለሁ፡፡ ከተጫወተ በኋላ ቪድዮ እየቀረፅኩ አጨዋወቱን እየመከርኩት፡፡ እንደ አባት ለልጄ መክፈል ያለብኝን ዋጋ እየሰራሁ እንደሆነ ነው የማምነው፡፡ በ16 ዓመቱ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲመረጥ እና ታሪክ እንዲሰራ ነው ተስፋ የማደርገው፡፡ በአጠቃላይ ዳግማዊ የእኔ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልጅ ይሆናል፡፡›› ነው ያለው
ለዓለም ዋንጫ ማለፍ
መላው የዓለምን ህዝብ መነጋገሪያው በማድረግ ዓለም ዋንጫን የሚያህል የለም፡፡ ማንኛውም አገር በእኩልነት የሚሳተፍበት ታላቅ የስፖርት መድረክም ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ መሳተፍ ለማንኛውም አገር ትልቅ የታሪክ ምእራፍ ከመሆኑም በላይ፤ የእድገት መገለጫ የሚሆንም ስኬት ነው። እያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ በአማካይ በስታድዬም እስከ40ሺ እንዲሁም እስከ 15 ሚሊዮን የቲቪ ተመልካች ይኖረዋል፡፡ ዓለም ዋንጫ በከፍተኛ ወጭ የሚዘጋጅ የውድድር መድረክምነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ 19ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ ወጭ ያደረገችው 2.7 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የብራዚል ወጪ ደግሞ እስከ 14 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል እየተባለ ነው። በ2018 እኤአ ራሽያ 21ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ወጭ  በ2022 ኤአ ደግሞ ኳታር ለ22ኛው የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ወጭዋ እስከ 200 ቢሊዮን ይደርሳል፡፡
ማንኛውም ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ከሚሳተፉ 32 አገራት አንዱ በመሆኑ ብቻ ከፊፋ እስከ 14 ሚሊዮን ዶላር ይታሰብለታል፡፡ በብሄራዊ ቡድን የሚሰለፉ የዓለም ዋንጫ ተጨዋቾች እስከ 30 ፕርሰንት ድርሻ ለእያንዳንዳቸው ያገኙበታል፡፡ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ መልማዮች በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የሚያገኙበትም መድረክ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ግን ቡድኑ በስፖንሰርሺፕ፤ በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ገቢ ሊያገኝበት ይቻለዋል፡፡ ለስፔን እና እንግሊዝ ከ50 እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ሊያስገኝ የሚችለው የዓለም ዋንጫ መሳተፍ እንደ ኢትዮጵያ ላሉት አገራት ቢያንስ እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ሊያስገኝ ይችላል፡፡

Read 5438 times