Saturday, 07 July 2018 10:49

አዲስ ጠላ በአሮጌ ጋን ወይስ አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን ወይስ ሁለቱም አዲስ?!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

 እንደ ሥነ-ተረት በሀገራችን የሚነገር አንድ ታሪክ አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን የጎረቤቱን አገር በመውረር የታወቀ አንድ ንጉሥ ነበረ፡፡ ይህ ንጉሥ እንደለመደው አንድ ዓይነት ጎሣ የሚኖርበትን ጎረቤት አገር ወረረና አገሬውን አስገብሮ ገዥ ሆኖ ያስተዳደር ጀመር፡፡ ያም ሆኖ የአገሬው ህዝብ የተገዛለት እየመሰለ አንድ ቀን እንደሚያጠፋው እየዶለተ መሆኑን መረጃ ደረሰው፡፡ ስለሆነም ንጉሡ ያንን ህዝብ ለማጥፋት ዘዴ ያውጠነጥን ገባ፡፡ በመጨረሻም ህዝቡ ሁሉ ግብር የሚበላበት አንድ ታላቅ ድግሥ ደገሠና፤
“ህፃን፣ ሽማግሌ፣ ወጣት፣ ጎልማሳ፣ ወንድ፣ ሴት ሳይባል ሁሉም ሰው ከንጉሥ ግብር እንዳይቀር” ሲል አወጀ፤ አዘዘ፡፡
አገሬው አንድም ሳይቀር ወደ ድግሱ መጉፍ ጀመረ፡፡
በዚያ አገር ላይ አንድ እጅግ ብልህና አብራሄ ህሊና ያለው ዐይነ ሥውር ሰው ነበረ፡፡ በዚያው አገር ከሴት ልጁ ጋር ይኖራል፡፡ የዚህን ዐይነ-ስውር አስተዋይነትና ጠቢብነት ያ ክፉ ንጉሥ ያውቃል፡፡ ስለዚህም የቅርብ ሰዎቹን ጠርቶ፤
“ያ ዐይነ-ስውር ሰው ወደ ድግሴ መጥቷል ወይ?” ሲል ጠየቀ፡፡
ሰዎቹም፤
“ንጉሥ ሆይ! እስካሁን አልታየም” አሉት፡፡
ንጉሡም፤
“በሉ፤ እስከመጨረሻው መምጣት አለመምጣቱን አጣርታችሁ እንድታሳውቁኝ” ሲል አዘዘ፡፡
ዐይነ ስውሩ ብልህ ሰው ከልጁ ጋር እቤቱ ነበረ፡፡ ሴት ልጁም፤
“አባዬ፤ ንጉሡ ወደ ግብሩ ማንም እንዳይቀር” ብሎ አዟልና እንውጣ? አለችው፡፡
ብልሁ ዐይነስውርም፤
“እስቲ ብቅ በይና ወድ ድንኳኑ የሚሄደውን ሰው ሁኔታ አጣሪና ትነግሪኛለሽ?” አላት፡፡
ልጅቱ አባቷ እንደነገራት ወደጎዳናው ወጥታ የህዝቡን አካሄድ ተመለከተችና ተመለሰች፡፡
“እህስ? ምን አየሽ?” አላት አባቷ፡፡
“ህዝቡ ወደማብሩ እንደጉድ ይጎርፋል” ስትል መለሰችለት፡፡
ዐይነ-ስወሩ አባትም፤
“ለመሆኑ የሚሄድ እንጂ የሚመለስ ሰው አይተሻል?”
ሲል ጠየቃት፡፡
ልጅቱም ትንሽ አስባ፤
“ኧረ አባዬ፤ ማንም ሲመለስ አላየሁም” ስትል መለሰችለት፡፡
ዐይነ-ስውሩ አባትም፤
“በይ ተነሽ ወደ አንድ ስውር ሥፍራ ውሰጂኝ”
“ለምን?”
“ለመደበቅ”
“ከማን ነው የምንደበቀው?”
“ከንጉሡ ጋሻ-ጃግሬዎች”
“ለምን?”
“አየሽ የኔ ልጅ፤ ህዝቡ ሁሉ ወደ ድግሱ እየሄደ ማንም ሰው ሳይመለስ ከቀረ፤ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ንጉሡ እኔና አንቺ መቅረታችንን ሲያውቅ ጋሻ- ጃግሬዎቹን ወደ ቤታችን መላኩ አይቀርም፡፡ አስገድደው ሊወስዱን ይችላሉና መጠንቀቁ አይከፋም፡፡”
“ግንኮ ድግስ ነው አባዬ፡፡ ከመብላት ከመጠጣት በስተቀር ምን ይኖራል ብለህ ነው?”
“አየሽ ልጄ፤ ህዝብ እንዲህ ጥርግርግ ብሎ ወደ አንድ አቅጣጫ ሲነጉድ መጠራጠር ጥሩ ነው፡፡ አገሬው አንድ ችግር ቢገጥመው እንኳን እኛ አንተርፋለን፡፡
አባትና ልጅ አንድ ጉድጓድ ውስጥ ተደበቁ፡፡
*    *    *
ዕውነትም ንጉሡ የዐይነ-ስውሩን ሰው አለመምጣት ሲገነዘብ፤
“ሂዱና ቤቱ ፈልጉት፡፡ ቤቱ ካጣችሁ ሰፈሩን አስሱ” አለና ጋሽ አጃግሬዎቹን ላከ፡፡ ፈረሰኞች ወደ ዐይነ-ስውሩ መንደር መጡ፡፡
ዐይነ-ስውሩ ብልህ ሰው፤
“ልጄ የምሰማው ድምፅ ምንድነው?” ሲል ጠየቃት፡፡
ልጅቱም፣
“አባዬ፤ ፈረሰኞች እየመጡ ነው!”
“በይ ብዙ ጠጠሮች ልቀሚና ያዥ”
“ከዚያስ?”
“አንድ ፈረሰኛ ሲያልፍ አንድ ጠጠር ትጥያለሽ፡፡ ለሁሉም እንደዚህ ካደረግሽ በኋላ፤ ሲመለሱም እነዚያን የጣልሻቸውን ጠጠሮች እያነሳሽ ትቆጥሪያቸዋለሽ፡፡ ያለፉት ፈረሰኞች መመላለሳቸውን በዚያ ታረጋግጫለሽ!”
ልጅቷ አባቷ ያላትን አደረገች፡፡ ያለፉት ፈረሰኞች መመለሳቸውንም በትክክል አረጋግጣ ለአባቷ ነገረችው፡፡
አባቷም፤
“አየሽ ፈልገው አጥተውን ተመለሱ ማለት ነው!”
* * *
ንጉሡ ባዘጋጀው ግብር እጅግ የሚያሰክር፣ የዝሆን ሐሞት የተቀላቀለበት ጠጅ ተዘጋጅቷል፡፡ ድንኳን የተሠራው እገደል አፋፍ ላይ ነው፡፡ ሰው በልቶ ጠጥቶ እንዲወጣ የተደረገው ወደ ገደሉ ነው! ሰክሮ የሚወጣው ህዝብ እየተንገዳገደ ገደል ገባ! በፈቃዱ ገደል እንደገባ ተቆጠረ፡፡ ማንም አልተረፈም፡፡
ዐይነ-ስውሩና ልጅ ወደ አቅራቢያው አገር ተሰደዱ፡፡ ከዚያም፤
“እንግዲህ ልጄ የእኛ አገር ሰው አለቀ፡፡ የቀረነው እኔና አንቺ ብቻ ነን፡፡ ስለዚህ ተጋብተን፣ ተዋልደን ትውልዳችንን ማቆየት አለብን” አላት፡፡
ልጅቱም፤ “አባዬ አገር ጉድ ይለናል! እኔ አላረገውም!” አለች፡፡
“እንግዲያው የጅብ ቆዳ ፈልጊና አምጪ” አላት፡፡
ፈልጋ፣ ገዝታ አመጣች፡፡
“በይ አሁን እኔ ያልኩሽን ታደርጊያለሽ? ቃል ግቢልኝ”
“እሺ” ብላ ቃል ገባች፡፡
“የጅብ ቆዳውን ለብሰሽ ወደ ገበያ ሂጂ” ብሎ አዘዛት፡፡ ቃል ገብታለችና ለብሳ ሄደች፡፡ ገበያተኛው “ጉድ! ጉድ!” እያለ ተበተነ። በሣምንቱ አባት ልጁ አሁንም የጅቡን ቆዳ ለብሳ እንድትሄድ አዘዛትና ሄደች፡፡ አሁን ደግሞ ሶስት አራተኛው ገበያተኛ ተበተነ፡፡ ልጅቱ ለአባቷ የሆነውን ነገረችው። አባትዬው በሶስተኛው ሳምንትም የጅቡን ቆዳ ለብሳ እንድትሄድ አደረጋት፡፡ አሁን ደግሞ ግማሹ ገበያተኛ ብቻ ተበተነ፡፡ ቀስ በቀስ፣ በአምስተኛው ሳምንት፤ ማንም ገበያተኛ የጅብ ቆዳ የለበሰችው ልጅ ከጉዳይ ሳይጥፋት ገበያውን ቀጠለ፡፡ ይሄንኑ የሆነውን ተመልሳ ነገረችው፡-
“አባዬ ዛሬ ማንም አልሸሸኝም፡፡ ሰው ሁሉ ዝም ብሎ መገበያየቱን ቀጠለ!
አባትዬውም፤
“ይሄውልሽ ልጄ፤ “ጉድ አንድ ሰሞን ነው!” እኛ ብንጋባ ዘራችንን እናተርፋለን፡፡ ከዚያም ልጆቻችን ከሌሎች ሰዎች ጋር ይጋባሉ”
ልጅቷም፤
“ታዲያ በመጨረሻ ያው ከሌሎች ከተጋባን ተደባለቅን አይደለም እንዴ?”
አባትዬውም፤
“ልክ ነሽ ልጄ! ሰው ሆኖ ከሌላ ዘር ያልተደባለቀ የለም፡፡ የኔ ዘር ነው ንፁህ የሚባል ነገር ፈፅሞ የለም!” አላት፡፡
* * * * *
 “አሰላም አሌኩም አሁንም አሁንም ያለንበት ዘመን አያስተማምንም” ይላል የመንዙማው ግጥም! ያለንበት ዘመን ከምንም ነገር በላይ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው፡፡ ፍቅር ወደ አምልኮተ- ሰብ (Cult) እንዳያመራ ጥንቃቄን የሙጥኝ ማለት ያለብን ዘመን ነው፡፡ የምንወድደው መሪ አስተሳሰብ ላይ ድክመት ብናይ፤ ያቀዋል፣ አውቆ ነው፣ ሳያስብበት አይቀርም ማለትን መፆም ይኖርብን ይሆናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ስህተት የሚከሰተው የአላስፈላጊ መላላት ሰለባ በምንሆንበት ጊዜ ነው! ሰዎችን ከእሥር ቤት አስፈታን ማለት ከእንግዲህ እሥር ደህና ሰንብች ማለት አይደለም፡፡ ህዝብ እንዳሻው ሊተረጉም ይችላልና ፍፁም ህገ-ወጥ ድርጊት ሲፈፅሙ የተገኙ ግለሰቦች፤ አግባብ ያለው ህጋዊ እርምጃ ቢወሰድባቸው፤ “ይሄዋ መሪያችን ራሱ ሲቃወም የነበረውን ነገር፣ ገና በሩብ ዓመት ውስጥ ገብቶ ተዘፈቀበት”፤ “ያመኑት ፈረስ፣ ጣለ በደንደስ!”
ከተማረ ፉከራ
ያልተማረ እንዴት አደርክ?” ይሻላል ወዘተ ይባላል። ያለንበት ዘመን የገዛ ደጋፊያችን እገዛ፤ “አያድን ጋሻ ቂጥ ያስወጋል” እንዳይሆን በተቻለ የምንጠነቀቅበት ነው!
“አይዞህ” ለመባባል እንኳ ሰዓት የምናጣበት ጊዜ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ነፃነትን የመራብ፣ ዲሞክራሲን የመጠማት፣ ፍትህን የማጣት በደል የነበረበትን ህዝብ፤ ሁሉን በአንዴ ተጎናፅፈሃል ሲባል ከባድ የመሳከር ስሜት ውስጥ የመስጠም አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ሚዛን ይጠፋል፡፡ ሳይግባቡ በስሜት መነዳት ይከተላል፡፡ ጓዳና ገመናን ግልጥልጥ አድርጎ መዋረድን ያመጣል፡፡ ትፍሥሕተ- ገነትን የተጎናፀፍን ይመስል በሀሴት ማዕበል እንጥለቀለቃለን!! ይሄ አደጋ ነው! ያለንበት ዘመን አንዱ ልል ገፅታ ይሄ ነው!
የቋንቋ መወራረስ ሌላው አስገራሚ ባህሪ ነው! የደርግ ዘመን ካድሬያዊ ልሣን ነበረው፡፡ ከላይ እስከ ታች የሚፈስ፣ ከተመሳሳይ ጣር የሚፈልቅ የሚመስል የቃላት ጋጋታ- እንደ በቀቀን መትከንከን፤ ይውደም ብሎ ይለምልም እስኪባል ድረስ የሚደጋገም ፈሊጥ፡፡ ከዝቅተኛው መደብ ሰው እስከ አብዮታዊ ጓድ  ድረስ በክሊሼ የቁም ቃላት ውርስ መጥለቅለቅ! መሸቀጫ አሰልቺ ሐረጎችን ማነብነብ! አርቲፊሻል የቃላት የደም ቧንቧ የተገጠመልን እስኪመልስ ድረስ መንደቅደቅ!
አድሃሪ፣ አብዮተኛ፣ ንቃት፣ ትግላችን መራራ፣ ሂስና ግለሂስ፣ ዘመቻ  ወ.ዘተ… ከዚያ የኢሕአዴግ ዘመን መጣ! ሁሉም የፖለቲካ ቃላት ከአንድ ፋብሪካ የተፈለፈሉ ይመስል በግምገማ ቢጋር ውስጥ ያሉ- “ይሄን አልወስደውም”፣ “ጉዳዩን አጥርተን እንየው”… “ሥራውን አላደማኸውም”… “በሂደት ይረጋገጣል”… “ዝግጁነት ይጎድለናል”… “መንቀልያዋን (ሥራ መሠረቷን) አምጣት፡፡” “ድክመትን የመሸፋፈን አካሄድ ተንፀባርቆበታል”… “ጓዱ የባህሪ ለውጥ አሳይቷል” ወዘተ ሆነ የቋንቋው ወጀብ! እያንዳንዱ ዘመን የየራሱን የቋንቋ ወረት መቀፍቀፉን ዛሬም እናያለን፡፡ “ስቴሪዮታይፕ” /Stereotype/ cliché/ በቀቀናዊነት፤ አሻራው ፍጥጥ ብሎ እንደጎረምሳ ብጉር ይታያል!
ፍቅር…ሰላም…አንድነት…መቻቻል…መግባባት…በጠረጴዛ ውይይት መፍታት…እርቅ…ምህረት…ይቅርታ ወዘተ የዘመኑ ፈርጣ ፈርጦች ሆነዋል! የሚገርመው እነዚህ ቃላት “በራሳቸው ጊዜ” የመጡ እንጂ፣ ማንም ማንንም ይህን ተናገር ብሎ አሊያም በዚህ ልሣን ካልተናገርክ ትቀጣለህ ብሎ መንግስት አዞ/አስፈራርቶ አይደለም! የየዘመኑ ቋንቋ ያለማንም መመሪያዊ ተፅዕኖ በየራሱ አሸንዳ ውስጥ ይፈስሳል! በየድጋፍ ሠልፉ የምንታዘበው ድግግሞሽ ይህ መሆኑ ያስገርማል!
ሌላው የዘመኑ ተመሳሳይ ባህሪ የቢሮክራሲው መሣሪያ (bureaucratic apparatus) ተመሳሳይ ጎራዊ ዘዴ ነው። የሥራ ማቀዛቀዝ፣ በዱሮው ቋንቋ sit-down-strike እና አቅጣጫ የማጣት ግራ-ገብ አካሄድ አሊያም መላ-ማጣት (obscurantism) ደርጋማነት ነው! በወገናዊነት ድርና-ማግ የተተበተበ ቢሮክራሲ፣ በአዲስ ደም ሥርዐት (new-blood-injection) እና መተካካት ቡድናዊ ዝምድና (partisan nepotism) ውስጥ በመቆላለፉ አሁን ለታሰበው ሽግግር እንቅፋት አይፈጥርም ብሎ ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው! በአሮጌ ጋን አዲስ ጠላ መጥመቅ (old wine in a new bottle) አባዜው ብዙ ነው!! ነባሩ ሥርዓት የፈጠራቸው ሙሉ በሙሉም ባይሆን በመንገድ ላይ ያሉ ኢ-ዲሞክራሲያዊ /ሀሳዊ-ዲሞክራሲያዊ ተቋማት (Pseudo-democratic institutions) ዕጣ- ፈንታ አለመታወቁ፣ የሂደቱ ድንግዝግዝ ውዥንብር ነፀብራቅ ነው፡፡ ሰፋ ያለ አዲስ ዕይታን (a new vista) ይጠይቃል፡፡ አልፎ አልፎ እንደተወርዋሪ ኮከብ ፍንጥቅ ፍንጥቅ ያሉትን ግለሰቦች ተመልከተን፣ የአሮጌውን ቢሮክራሲ አዋሽ በርሜል (ጋን) ስፋትና ከዚህ አብራክም ሊወለድ የሚችለውን አዲስ አራስ ሙሉ በሙሉ መቀበል (ማመን) ፈታኝ ነው! አዲስ ምንጊዜም አሸናፊ ነው /the new is invicible/ የሚለውን ዲሌክቲካዊ ዕውነታ ብናበረታታም፣ የጎታቹን ቢሮክራሲ አቅም የምንንቀው አይሆንም፡፡ በተለይም ከአቀባባይ ነጋዴ ጋር ፋይናንሳዊ ትሥሥር እንዳለው ስናሰምርበት፣ ቢሮክራሲያዊ ከበርቴው ምን ያህል አንገቱን ቀና አድርጎ እንደሚጓዝ እንመሰክራለን! በዚህ አንፃር በአሮጌ ጋን አዲስ ጠላ መጥመቅ፣ ወይስ በአዲስ ጋን አሮጌ ጠላ መጥመቅ ወይስ ጋኑም ጠላውም አዲስ ነው የሚል ጥያቄ መጠየቅ ይታሰበን! ይታሰብበት!

Read 7689 times