Saturday, 07 July 2018 10:54

ኢትዮጵያን ያላችሁ እስኪ እንያችሁ! (አገራዊ ጥሪ)

Written by  ሳምሶን ጌታቸው
Rate this item
(5 votes)

         ከጥቂት ወራት በፊት በሀገራችን ተከስቶ የነበረው እጅግ አሳሳቢ የፖለቲካ ሁኔታ፣ ሀገራችን ላይ ከባድ የእርስ በርስ የመተላለቅና ሀገር የመበተን ሥጋት ደቅኖብን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሆኖም ግን ሁኔታው ማንም ሰው ባልገመተውና ባላቀደው ተዓምር በሚመስልና በአስደናቂ ሁኔታ ሊወገድ ችሏል፡፡ በሁኔታውም ሁሉም የሀገራችን ሰላም ወዳድ ዜጋ፣ ዕጥፍ ድርብ ደስታ እንደተሰማው በየአጋጣሚው እየገለፀ ይገኛል፡፡
የዚህ የፖለቲካ አካኼድና ስኬታችን ዋነኛ ፊታውራሪ ደግሞ የተከበሩ መሪያችን ጠ/ሚ  ዶ/ር አብይ አህመድና ቅን የሥራ ባልደረቦቻቸው መሆናቸው ይታወቃል። ጠ/ሚኒስትራችን፣ የወቅቱን አሳሳቢ የሀገር ነቀርሳ ማከም የጀመሩት፣ ከበዓለ ሲመታቸው ዕለት ጀምረው፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለብዙ አመታት ርቃ የተጓዘችበትን የጥላቻና ያለመተማመን ልማድ፣ ከስሩ መንግሎ ለመጣል ቃል በመግባት ነበር፡፡ በምትኩም የይቅርታ፣ የምህረት፣ የፍቅርና የሠላም መንገዶችን እንደሚከተሉ አረጋገጡ፡፡ ይህንንም ቁርጠኝነታቸውን ባረጋገጡ ማግስት፣ መገመት ከሚቻለው ፍጥነት በላይ በርካታ ለማመን የሚያስቸግሩ እጅግ አስደሳች ተግባራትን በቃላቸው መሠረት አከናውኑ፡፡
በዚህም የተነሳ ዜጎች ከመቼውም የቅርብ ዘመን የሀገራችን ታሪክ በተሻለ፣ በሀገራችን ላይ ላቅ ያለ ብሩህ ተስፋን መሰነቅ ችለናል፡፡ ለአመታት የተገመዱና የተወሳሰቡ፣ ውል አልባና አደገኛ የፖለቲካ ችግሮቻችን፣ መፍትሔ ለመስጠት ቀርቶ፣ በአይነት ዘርዝሮ ለመጨረስም የማይታሰብበት ደረጃ ደርሰን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የጠ/ሚ አብይ አህመድ የአመራር ብቃት ግን ነገሮችን በፍጥነት መልክ እንዲይዙ እያስቻለ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ይህን የተገኘውን የስኬት ተስፋ ዘላቂነቱን ለማስቀጠለል ከተፈለገ፤ ሀገራችን ከፖለቲካዊ ውጥንቅጦሹ በተጨማሪ፣ በብዙ አቅጣጫዎች አሳስረዋት የሚገኙ ፍፁም ጊዜ የማይሰጡ ተደራራቢ ችግሮቿ እንዲፈቱ፣ የሁሉንም ዜጋ ትብብር መጠየቁ ግልፅ ነው፡፡ በአስፈሪ ሁኔታ በመገስገስ ላይ የሚገኘው የሀገራችን ሕዝብ ቁጥርና ተያያዥ ፍላጎቶቹ፣ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ብዙ ነገሮች ከማበለሻሸቱ በፊት፤ ከፖለቲካ መጠላለፍ  በፍጥነት ወጥቶና በፍፁም ሀገራዊ መግባባት ላይ ወደተመሠረተ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ሥርዓት መግባት፣ ለነገ  የማይባል፣ አጣዳፊ ተግባር መሆን አለበት፡፡
በመሆኑም አሁን የተገኘውን ሀገራዊ ተስፋ ለመጨበጥ፣ እኛ ዜጎች በቃልና በሀሳብ ከምናቀርበው ድጋፍና ምሥጋና ባልተናነሰ፣ አጋርነታችንንም ሆነ ታዛዥነታችንን፣ ከአንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ በሚጠበቅ መጠን፣ በፍፁም ቅንነት በተግባር ለመወጣት መረባረብ ይጠበቅብናል፡፡ እንደሚታወቀው ያለ  ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ መሠረቶች፣ ለፖለቲካዊ ችግሮች ብቻ መፍትሔ በመስጠት፣ ሀገርን ለውጤት ማብቃት አይቻልም፡፡ ሆኖም ግን የተለየ ኢኮኖሚያዊ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ በመንግሥት በኩል ሳይጠበቁ፣ በዜጎች ቅንና ፈጣን ትብብር ብቻ፣ መስተካከል የሚችሉ ችግሮች አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አዲሱን የመንግሥት አመራር በጉልህ መደገፍ የሚያስችሉ ዕድሎች በእጃችን ይገኛሉ፡፡ ከእነዚሁ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቀጥተኛ ትብብር ብቻ፣ በጉልህ ጋብ ማለት ከሚችሉ አንገብጋቢ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አንዱ፣ የሀገሪቱን ህልውና እጅግ የከፋ አደጋ ላይ ጥሎት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ጉዳይ ነው፡፡
የሀገራችን ኢኮኖሚ ለአምራቾች በግብአትነት ከሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎች ጀምሮ እስከ አለቀላቸው ምርቶች ድረስ፣ ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ ጥገኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በቀዳሚው አመራር የተሳሳቱ የፖሊሲ ችግሮችና መረን የለቀቁ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውንብድናዎች የተነሳ፣ ከወጪ ንግዱ የሚገኘው ገቢ፣ የገቢ ንግዱ የሚጠይቀውን የምንዛሬ ፍላጎት ሊያሟላ በሚያስችል አቋም ላይ እንዲገኝ አላስቻለውም። በዚህም ትልቅ የንግድ ሚዛን መዛባት ተከስቷል፡፡
ለውጭ ምንዛሪውም ዕጥረት ሆነ ለአጠቃላዩ የኢኮኖሚው መሽመድመድ፣ ሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች ዋነኞቹ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ግን ደግሞ በሌላ ጎኑ ከሀገር ውጭ የምንዛሬ ዕጥረቱን ችግር ካባባሱት ነጥቦች መካከል፣ የነበረውን የመንግሥት አስተዳደር በመቃወም፣ ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የሚላኩ ገንዘቦች ላይ ማዕቀብ የመጣሉ ተግባርና ቅስቀሳ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡  ሌላውና ዋነኛው፣ የውጭ ምንዛሬው በሚገኝባቸው ሀገራት ላይ ተመሥርቶ፤ የሚላከውን ገንዘብ እየጠለፈ የሚያስቀር፣ ረቀቅ ያለ የጥቁር ገበያ መስመር መስፋፋትና መጎልበትም መጠቀስ ያለበት ጉልህ ችግር ነው፡፡ ሀገሪቱ ከምታስመዘግበው የወጪ ንግድ መጠን በተሻለ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚያስችላትን የሐዋላ ገቢ ማዳከም፣ ማስቆምና ምንዛሬውን መጥለፍ በእርግጥም ከባድ አሉታዊ ጫናውንና የሚያደርሰውን ሀገራዊ ክስረት መገመት አይከብድም፡፡
ጥቁር ገበያውን አንዴ መጠቀም የጀመሩ ሰዎች ደግሞ ተላምደውት እንዲቀሩ የሚያደርጉ ጣዕሞች አሉት፡፡ ለምሳሌ፦ ጥቁሩ ገበያ ከባንኮች ሻል ያለ ጥቅም ማስገኘት ማስቻሉ፣ ያለ ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ መላክ መቻሉ፣ በተፈለገው ሰአትና ቀን፣ ቅብብሎሹ በቀላሉ፣ በስልክ ጥሪ ብቻ ማከናወን መቻሉ ይጠቀሳሉ፡፡ በተጠቀሱት ነጥቦች አማላይነት የጥቁሩ ገበያ አስተላላፊዎች፣ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ይገባ የነበረውን ምንዛሬ፣ እዚያው የሚላክበት ሀገር፣ ከላኪ እጅ ጠልፈው ያስቀሩትና ኢትዮጵያ ለሚገኘው ተከፋይ ሰው የምንዛሬ ተመኑን አስልተው፣ ሀገር ውስጥ ባለ፣ ሸሪካቸው በኩል በብር እንዲከፈል ያደርጋሉ፡፡
ይህ ተግባር ደግሞ ሁለት አሉታዊ ውጤቶችን በሀገር ላይ ያስከትላል፡፡ አንደኛ፤ በገቢ ንግድ ላይ የተመረኮዘው የሀገራችን ኢኮኖሚ፤ ከውጭ ዕቃ የመግዣ የውጭ ምንዛሬ ምንጩን ያዳክምበታል። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ ውስጥ በቂ የሸቀጦች አቅርቦት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ በሁለተኛነት ደግሞ የተላከለትን ገንዘብ በብር የተቀበለው ኢትዮጵያ ያለው ሰው ዕቃ ሊገዛ ወደ ገበያው ይወጣል፡፡ ገበያው ደግሞ በተፈጠረው የምንዛሬ ዕጥረት የተነሳ ፣በቂ አቅርቦት ስለሌለው የዕቃዎች ዋጋ ንሮ ይጠብቀዋል፡፡ ስለዚህ ገዢው በተላከለት ብር አቅም ተጠቅሞ ውድ በመክፈል ይገዛል፡፡ ሁኔታው፤ የሚሸጥ ዕቃ እንዳይኖር እየከለከሉ፣ መግዣ ብር እንደ መስጠት አይነት “ጨዋታ” ይመስላል፡፡ ይህም አካኼድ በጥቅሉ በሀገር ደረጃ በቂ አቅርቦት ሳይኖር፣ ከፍ ያለ ፍላጎት እንዲኖር ያደርጋል። በዚህም ሳቢያ የዋጋ ንረት ብሎም አጠቃላይ የኑሮ ውድነት ይከሰታል፡፡ ጫናው ከውጭ ገንዘብ የሚልክ ዘመድ በሌላቸው ዜጎች ላይ ይበልጥ ይበረታል፡፡
በአጠቃላይ አሁን በጠ/ሚ አብይ አህመድ የሚመራው መንግሥት፣ ችሎ መቋቋም ከተቸገረባቸው ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች አንዱና ዋነኛው፣ የዚሁ የምንዛሪ እጦት ችግር ነው፡፡ አዲሱ የመንግሥት አመራር በበርካታ እና ጊዜ በማይሰጡ አንገብጋቢ ሀገራዊ ፈተናዎች መወጠሩ አልበቃ ብሎ፣ በገቢ ንግድ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላትን ሀገር መላወሻ ከሚያሳጣ፣ የምንዛሬ ዕጥረት ጋር መረከብ፣ ምን ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡
ስለሆነም ሀገር ወዳድ ውጭ-ኗሪ ኢትዮጵያውያን ኹሉ፤ በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በታላቅ የተስፋ ብርሃን እየተመራች በመጓዝ ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን የተገኘው ተስፋ፣ የተጨበጠ ስኬት እንዲሆን፣ የሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ቀና ትብብርና ርብርብ ማስፈለጉ አሌ የማይባል ሀቅ ነው፡፡
ይህ ወቅት በፖለቲካው ዘርፍ ስታበረክቱት እንደነበረው አስተዋጽኦ ሁሉ በኢኮኖሚውም፣ ሀገራችሁን የምታግዙበትና የኢትዮጵያዊነት አሻራችሁን በለውጡ ጎዳና ላይ ማሳረፍ የምትችሉበት ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ሀገራችሁን ለማገዝ የሚያስችላችሁ በእጃችሁ የሚገኝ ይህ ዕድል፣ ከኪሳችሁ ምንም አይነት ትርፍ ገንዘብ ማውጣት አይጠይቃችሁም። የሚጠይቃችሁ፤ ወደ ሀገር ቤት የምትልኩትን የውጭ ሀገር ገንዘብ፣ በሕጋዊ የሐዋላ ማስተላለፊያ መንገዶች መጠቀምንና በዚያም ሳቢያ የምታጧት ትንሽዬ የምንዛሬ ልዩነት መተው ብቻ ነው፡፡
አሁን ሀገራችን መታገዝ የሚገባው የለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለችና በጥቁር ገበያ በመላክ የምታገኙትን “ትርፍ” ብትተዉት፣ ለምትወዷት ሀገራችሁና ሕዝቧ የተከፈለ ታላቅ የዜግነት ስጦታ እንደሆነ አድርጋችሁ መቁጥር ትችላላችሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እርስ በርስ፣ ከፍተኛ መቀሳቀስ ብታደርጉ፣ ብዙ ውጤት ይገኝበታል፡፡ ለእናት፣ ለአባት እና ለቤተሰብ ከምትልኳት ከትንሿ ገንዘብ ጀምሮ፣ ለትላልቅ የንግድ ሥራዎች ማከናወኛ ሳይቀር፣ በጥቁር ገበያ መጠቀሙ፣ በደሃ ሀገር ላይ የሚፈፀም በደል ስለሆነ ከዚህ በኋላ እርግፍ አድርጋችሁ ተዉት፡፡ እያንዳንዷ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ስትገባ፣ በምጥ ተይዛ ለምትገኘው ለምንወዳት ኢትዮጵያ፣ ደም የመለገስ ያህል ስሜት ይኖረዋል፡፡ የዚያን ያህል ጥቅሙ የጎላ ነውና፡፡
ጠ/ሚራችን፣ ከሀብታም ሀገራት መሪዎች ጋር በተገናኙ ቁጥር፣ ልጆቿን ያለ አባት ለብቻዋ በመከራ እንደምታሳድግ እናት፣ በየደረሱበት ለምንዛሬ ምፅዋት መለማመጥ የለባቸውም፡፡ ሥራው በግላቸው እጅግ ቢያስመሠግናቸውም፣ እንደ ሀገር ግን ነገሩ የሚያሳፍረን እንጂ የሚያኮራን ተግባር ሊሆን አይችልም፡፡ በየደረስንባቸው ሀገራት፣ የሀገራችንን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ብቻ መነጋገርም ሆነ አቋም መያዝ የምንችለው፣ በገንዘብ ዕጦት ያልተቀፈደደ መሪ እና ሀገር ሲኖረን፣ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ስለሆነም በውጭ ሀገራት ያውም፣ በራሳችን ወገኖች የተጀመረውን አደገኛውን የጥቁር ገበያ መስመር በአጭሩ መልክ እናስይዘው፡፡ ኢትዮጵያን ያላችሁ እስኪ እንያችሁ! ኢትዮጵያ ትቅደም!

Read 2452 times