Saturday, 07 July 2018 10:57

“እንዴት ልደቴን ትረሳለህ?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ሮቦቷን አያችሁልኝ አይደል!…ጉድ ፈላብን ነው የሚባለው፣ ጉድ ፈላልን! እኔ የምለው… ይሄኔ ሶፊያን ከአሁኑ ፊልም ለማሠራት ያሰቡ ሳይኖሩ አይቀሩም፡፡ ‘ሴሌብሪቲ’ ሆናለቻ!…በነገራችን ላይ፣ የሆነ የአካል ክፍሏ መንገድ ላይ ጠፋ ሲባል ምን አሰብን መሰላችሁ…በቃ “እሷንም ኩላሊቷን መነተፏት ማለት ነው!” እሷን ‘በመገጣጠሙ’ (“በመፍጠሩ” ነው እንዴ የሚባለው!”) የአገር ልጆች መሳተፋቸው አሪፍ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ… ሔዋን አዳምን፤ “ትወደኛለህ?” አለችው አሉ፡፡ አዳም ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ምን ሌላ አማራጭ አለኝና ነው፣!” ብሏታል አሉ፡፡ በነገራችን ላይ አዳም እኰ ይህን ያህል ጣጣ አልነበረበትም፡፡ ልክ ነዋ…ሌላ ተቀናቃኝ በሌለበት፡፡ እንትን ሰፈር ያለው ያ ቄንጠኛው፣ የባንክ ሥራ አስኪያጅ በሌለበት፣ ሲዳሞ ተራ ዶላር የሚያስነጥሰው ነጋዴ በሌለበት…ምን ያሳስበዋል! እና ሔዋንን ምንም ማባባል አላስፈለገውማ! “ሔዋንዬ የእኔ በራሪ ኮከብ!” ምናምን አያስፈልገውም ነበር፡፡ ሌላ አዳም የለማ!
ሔዋንም በነጋ ጠባ አዳምን፤ “የእኔ አንበሳ እንዴት ዋልክልኝ፡፡ ራስሀን ሻል አለህ?” ማለት አያስፈልጋትም፡፡ (“አመመኝ” ሳይል እኰ ነው!) “የእኔ ዝሆን ገዳይ፣ ሸበላዬ፤ የእኔ በመሆንህ በጣም እድለኛ ነኝ፣” ማለት አያስፈልጋትም፡፡ የእሷ ባይሆን ሌላ አማራጭ በሌለበት የማን ሊሆን ነበር! ሌላ በሌለበት  የሚያስተካክል የለም ማለት አይጠበቅባትም ነበር፡፡
አማራጭ ቢኖር ኖሮ የተከለከለችውን ፍሬ አዳም… “ሔዋን፤ እሱን ፍሬ እንዲች ብለሽ ትነኪና፣ እኔና አንቺ አበቃልን ማለት ነው፣” ይላታል፡፡
“ለምን? እኔ ለራሴ እርቦኛል፣ ትነኪና ይለኛል እንዴ!”
“እንግዲህ ነገርኩሽ…የአክስቴ ልጅ ሆዷን አሟት ምግብ አልበላ ስላለች ለእሷ እወስድላታለሁ።” አክስት ሳይኖር እንዴት የአክስት ልጅ ሊኖር ይችላል! ይቻላል…ዘንድሮ እዚቹ እኛዋ ከተማ፣ አንድ አክስት ሳትኖር፣ አስራ ምናምን የአክስት ልጆች ይኖራሉ፡፡ ምክንያቱም ‘ሰበብ’ ለመስጠት የአክስት ልጆች ያስፈልጋሉዋ!
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ከጥቂት ጊዜያት በፊት አንድ የምናውቀው ሰው፣ ዘመድ ከሚባል ሰው ጋር መቆራረጡን ሲነግረን ነበር፡፡ በርስት አልተጣሉ፣ በሚስት አልተጣሉ፣ በገንዘብና ንብረት አልተጣሉ፡፡ ሰውየው ከነበረበት የሥራ ቦታ ይሰጠው ከነበረው ከእጥፍ በላይ ደሞዝ የሚከፍል አዲስ መሥሪያ ቤት ገብቶ፣ የደስ ደስ የተወሰኑ ዘመዶቹና ጓደኞቹን ጠርቶ ነበር፤ ሰውዬአችን ይረሳውና ይቀራል፤ እና ለምን እንደቀረ ሲጠይቀው፣ የአክስት ልጅ ምክንያት አልሰጠውም፡፡ እቅጩን ነገረው፡፡ “ረሳሁት፡፡”
በዚህ ጊዜ ሰውየው በጣም ይናደዳል አሉ፡-
“እኔ ጠርቼህ አንዴት ትረሳለህ?”  
“በቃ የሆኑ ሀሳቦች ስለነበሩብኝ ረሳሁት፣” ይለዋል፡፡ ይሄኔ ሰውዬው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ከእኔ የሚበልጥብህ ነገር ኖሮ ነው!”
እንዴት ነው ነገሩ! እሱ ገንዘብ አገኘሁ ብሎ ሲጋብዝ፣ ይሄኛው እኰ ገንዘብ አጥሮት፤ “አሁን፣ ቤተሰቤን ወር የማደርሰው እንዴት ብዬ ነው?” እያለ ተጨንቆ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህኛው መልስ አልሰጠውም፡፡ ምን ብሎ ሊመልስለት ይችላል! ግን ጋባዥ እየደጋገመ፤ “እንዴት ትረሳለህ!” እያለ ይጨቀጭቀዋል፡፡ ይሄኔ ምን ብሎ ይመልስለታል…
“ይሄን ያህል አታገነዋ! ቤተኛ አይደለሁ እንዴ! ባዳ አታድርገኛ!”
እዚህ ላይ ነው ነገርዬው የመጣው፡፡ “እኔ ስንት ለፍቼ ከፍተኛ ደሞዝ የማገኝበት ሥራ ብቀጠር  ልትደሰት ሲገባህ ቅር ብሎሀል እንዴ!”
ይህ ለሰውያችን ቀይ መስመሩን ማለፍ ነበር፡፡ መልስ መስጠት ነበረበት፡፡
“ለእኔ ስትል ሙሉ ባንኩን ለምን እንዳለ አይሰጡህም!” ይላል፡፡ ያኛውም አልበቃውም፡፡ “ድሮም አኮ የእናንተ ቤተሰብ ምቀኞች ናችሁ…” ምናመን ብሎ ከዘመዶቹ ጨምሮ ይወርድበታል። ሰውዬአችን ሌላ መልስ ሳይሰጥ ጥሎት ይሄዳል። ግንኙነታቸውም ተቋርጧል፡፡ ይህ ነገር ተሰምቶ ኖሮ፣ በሁለቱ መካከል ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውም መራራቅ ጀምረዋል፡፡
ይሄ ሁሉ እንግዲህ እዛች ግብዣ ባለመሄዱ ነው፡፡ ሰዋችን ይሄን ያህል ሆድ ብሶታል እንዴ! ይሄን ያህል ልብ ለልብ ተራርቋል እንዴ! ቀደም ሲል ምንም ችግር ያላየንበትንና ቤተኛ የሆነ ዘመዱን በምቀኝነት መስደብ ምን የሚሉት ዝምድና ነው!
ዘንድሮ እኰ ሰዋችን አይደለም ግብዣ ቅብጥርስዮ፣ ራሱንም እኰ እየረሳ ያለ መአት ነው። ህይወት እኮ ለሰዋችን ይሄን ያህል መልካም አልነበረችም፡፡ የቅርብ ሰዎቻችን ስም እንኳን ወዲያውኑ ትዝ አልል እያለን ተቸግረናል፡፡
“እንዴት ነህ?”
“ታዲያስ ደርቤ፣ ምነው ሰሞኑን አላየሁህም?”
እንዲህ ስትሉ…አለ አይደል… “ምን መሰለህ ለሥራ ናይሮቢ ከርሜ…” ምናምን አይነት ነገር እንዲላችሁ ትጠብቃላችሁ፡፡ ግን የሰውየው ፊት አሸቦ መስሏል፡፡ ጭራሽ ግንባሩን ፈርሰው ‘አፋቸውን ከፍተው የቀሩትን’ የየመንደሮቻችንን መንገዶች ይመስላችኋል፡፡ አጅሬው በጠዋቱ ልፎ ነው እንዴ! ስርአት ያለው ስንብት ሳያደርግ በቆማችሁበት ጥሏችሁ ይሄዳል፡፡ “ይሄኔ የሆነች ሚጢጢ ስልጣን ሰጥተውት ይሆናል…” ምናምን እያላችሁ እያለ ‘ጉዳችሁ’ አእምሯችሁ ፊት መጥቶ ድቅን፡፡ ስሙ ‘ደርቤ’ አይደለም፡፡ እንደውም አጠገቡ አይደርስም፡፡ ስሙ ‘ፍርድአወቅ’ ምናምን ነው፡፡ (አሁን የፈለገው ቢምታታ… አለ አይደል… እንዴት ነው ደርቤና ፍርድአወቅ የሚምታታው!) ምን ይደረግ…ራሳችንን  እያስረሳችን ያለችው ህይወት፣ የሰው ስም ብታስረሳ ምን ይገርማል!
“እንዴት ልደቴን ትረሻለሽ?”
ስንት አእምሮ የሚጨብጥ ነገር እያለ፣ የእሷን ልደት የማስታወስ ግዴታ አለብን እንዴ! ፌስቡክ ላይ “ዛሬ ልደቷ ነውና ‘ሃፒ በርዝዴይ’ በላት የሚል መልእክት አልደረሰንማ!
የልደት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…እሷዬዋ ልደቷን ማክበሯን ለወዳጇ ትነግራለች፡፡  
“ግን ለምንድነው ልደቴ ላይ ያልመጣሽው?”
“እኔ ልደትሽ መሆኑን አላወቅሁማ!”
‘ትለቀቅባታለቻ!’ የእሷ ልደት ስለተረሳ እውነተኛው ስምንተኛ ሺህ የመጣ ታስመስለዋለች፡፡ የእሷ ልደት ስለተረሳ የሆነ በሰው ዘር ላይ የተፈጸመ ዓለም አቀፍ ወንጀል ታስመስለዋለች፡፡ እሷ ሪሃና አይደለች፣ ሲ.አር. ሰቨን አይደለች… እንዴት ብለን ነው ልደቷን የምናስታውሰው! (በነገራችን ላይ የገዛ እህቱን የልደት ቀን በትክክል የማያስታውስ… ግን ሮናልዶ ሲወለድ የነበረውን ስርአት በሙሉ፣ በስእላዊ መግለጫ የሚያስረዳችሁ፣ መአት ሰው ያለ አይመስላችሁም!)
“ግን፣ ለልደትሽ ስንት ሻማ አበራሽ?”
“ሀያ አምስት”
“ሀያ አምስት!”
“አዎ፣ ሀያ አምስት፤ ምነው?”
“እኔ የምለው፣ ሻማውን በሁለቱም በኩል ነው እንዴ የለኮስሽው?”
እናማ… “ልደቴ ላይ አልተገኘሽም?” “የዘመድ ጉባኤ ላይ እንዴት ትቀራላችሁ!” “የወንድሜ ፌርዌል ፓርቲ ላይ ያልመጣሽው ዲሲ በመሄዴ ቅር ብሎሻል እንዴ?” ...ምናምን የምንል ሁሉ ህይወት፣ ሰዎች እነኚህን አይነት ነገሮች የሚያሰላስሉበት ብዙ ምቾት እየሰጣቸው እንደሆነ ማወቁ ደግ ሳይሆን አይቀርም፡፡
እናማ… ስንትና ስንት ሀሳብ እየወዘወዘን ባለበት ጊዜ… “እንዴት ልደቴን ትረሳለህ?” አይነት ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5334 times