Saturday, 07 July 2018 11:06

የሰኔ 16 ሰልፈኞች ፈተና

Written by  ደ.በ
Rate this item
(3 votes)

“ለምትወደው፤ የማትወደውን ነገር ታደርጋለህ”
            
    ወፍ ሲንጫጫ ስነሳ የልጅነት ጊዜዬ፣ ከሀሳቤ ማዶ ትዝታዬን አመጣው፡፡ የጳጉሜ ጸበል ወይም የክርስትና በዐል ወይም ጥምቀት፡፡ ብቻ በሚያባባ ዜማ ለተረበሸው ሆዴ፣ ከረጢት ሌላ ሸክም አሸከመኝ፡፡ ወደ ኋላ ሩቅ፣ በጣም ሩቅ፣ የልቤ አንገት ላይ የእንባ ዶቃዎች የተንጠለጠሉ መሰለኝ፡፡ የዘመን ትዝታ መረዋ፣ ነፍሴ ላይ ተንጠልጥሎ ቃተተ፡፡
ጓደኛዬ ገጣሚ ታገል ሰይፉ፤ ከደወለልኝ ስልክ ድምጽ ወዲያ፣ ከትዝታዬና ከጫማ ኮቴ በስተቀር ብዙ ነገር በተፈጥሮ፣ ወይም በጊዜ ጉልበት፣ በሰዐት ሕግ ታስሮ ረጭ ብሏል፡፡ ከቤቱ ወረድ ስል ትንሽ ትንሽ ጢስ የሚተፉ መኪናዎች በቆፈኑ ውስጥ ይንተፋተፋሉ። እንደኔ ሰልፍ ሊሄዱ ወይም ሕይወት ከሚባለው የእንጀራ ክብ ጋር መሀረቦሽ ሊጫወቱ ሊወጡ ነው፡፡ ሁሌ “መሐረቤን ያያችሁ” ነው ህይወት፡፡ ተራሮችም የራሳቸው መልስ አላቸው፡፡ “አላየንም” የሰው ልጅ፤ “መሐረቤን ያያችሁ” ሲል አለም፤ “አላየንም” በሚል ጨዋታ እስከ ጥግ ይሄዳሉ፡፡ ቁምነገሩ የተሻለውን ጨዋታ መጫወት ነው፡፡ ‹‹ምንም ሁን የትም ቦታ፣ ስራ ባለህበት ግን የተሻለ ሰራተኛ ወይም ባለ ውጤት ሁን›› ያሉትን የጆን ኤፍ ኬኔዲ አባትን ሀሳብ፣ እኔም እጋራለሁ፡፡
ትንሽ ወጣ ብዬ ወደ ዋናው ጎዳና ስገባ፣ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ምስል ያለባቸውን ካናቴራዎች የለበሱ ብዙ ሰዎች ገጠሙኝ፡፡ በወጣቶች፣ ጎልማሶችና አረጋውያን ላይ የተጋጋለ ስሜት፣ የተራበ መንፈስ ይነበባል፡፡ ቁጭት፣ ጉጉት፣ ተስፋ፣ ሕልም የያንዳንዱን ስዕል አሻራ፤ ግን ምንም አያሳይም፡፡ ናፍጣው ያለቀ ኩራዝ፣ ከጎን ባለችው ጆሮው ናፍጣ ሲያንጠባጥቡበት የሚያመጣው ብርሃን ልክና ኃይል ግን በሁሉም ላይ ይታያል፤ የሙቀቱ ወላፈን፣ ስሜት ይሰጣል፡፡
የሀገሬ ሰው፤ በአዲስ ተስፋ አገግሞ፣ አሁንም ህልም አርግዞ፣ በገዛ ፍቃዱ መሪውን ሊያመሰግን መውጣቱ መንፈሴን ኮረኮሩት፡፡ “ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል” በማለት ሰላምን ቀድሞ ተናግሮታል። የሚለው የማህሙድ አህመድ ዜማ፣ በልቤ ጆሮ ላይ ዘነበ፡፡
ታክሲ ይዤ ወደ ዋቢ ሸበሌ አቀጠንኩ፡፡ ስለ ቀጣዩ ጊዜ፣ ስለ መጪው ዘመን ሳስብ፣ የሰልፉ ቀን ውስጥ የሚፈጠረው ተንኮል፤ ስጋት ቢጤ ጫረብኝ። በሃያ ምናምን ዓመታት ስለ መንግስት ያነበብነው፣ የለመድነው መሰሪ ነገርም አለ፡፡ በተለይ በቅርብ አመታት፣ ከሀገር የወጡ ፖለቲከኞች የጻፏቸው መጻሕፍት፣ ልባችንን ጠርጣሪ አድርገውታል፡፡
ስለ ደህንነቱ ጉዳይ፣ ስለ ቀድሞው አስተዳደርና የለውጡ ወገን ሰዎች አብሮነት፣ ሀሳብ እየፈለፈልኩ ተጓዝኩ፡፡ የቀጠርኩት ሰው መኪናና የይለፍ ወረቀት ስለያዘ፣ አብሬው ለመሄድ ተነሳሁ፡፡ በዘመኔ የማንም ፎቶግራፍ የታተመበት ካናቴራ ለብሼ ባላውቅም፣ ይህኛውን ስለብስ ግን የሀገሬን ክብርና ህዳሴ የለበስኩ ያህል ተሰማኝ፤ አልከበደኝም፡፡ ፍቅር የማይወዱትን ነገር ያስደርጋል፤ ‹‹ለምትወደው የማትወደውን ነገር ታደርጋለህ››ብዬ ለራሴ አወራሁ፡፡
በዚህ መሀል ቴክሳስ አሜሪካ የሚገኝ ሀገር ወዳድ ወዳጄ፣ ዶክተር መለሰ ባልቻ በፌስቡክ ‹‹ደስታም ስጋት ተቀላቅሎብኛል›› አለኝ፡፡
“ምንም ስጋት አይኖርም፤አደባባዩ እየሞላ ነው”
‹‹ሄደሃል?›› አለኝ፡፡
11፡36 ገደማ ከቤት ወጥቻለሁ፡፡
“መሞት እንኳ ቢኖርብኝ፣ ከዶክተር ዐቢይ ጋር እሞታለሁ” ብዬው ከፌስቡኩ ወጣሁ፡፡ እያስመሰልኩም አልነበረም፡፡ ከዚህ በኋላ ዐቢይ በሌለበት ሀገር ከምኖር፣ መሞትን እንደ ጣፋጭ ጽዋ እጎነጨዋለሁ ብዬ ነበር፡፡
ታገል ሰይፉ በጧት የቀሰቀሰኝ፣ በምስል የተቀነባበረ ግጥሙን ሊሰራ ነው፡፡ እኔ ግን ሰልፉንና የሰልፉን ልቦች ለማንበብ፣ በዚያውም እግዜርን ላመሰግን እየወጣሁ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ያለሁ ይመስል፣ ልቤ በምስጋና እንድትተም ፈቀድኩላት፡፡
ይሁንና የፖሊሶቹ ፍተሻ ግን ብዙም ደስ አያሰኝም።
አስራ ሁለት ሰዓት ከምናምን ነው፡፡ ....ዘው ብዬ ቁርስ ቀመስኩ፡፡ እንደ ውስኪ የምቆጥራትን የማኪያቶዬን ስኒ ከንፈር ስሜ፣ ወደ አደባባዩ አቀጠንኩት፡፡ ምንም የተለየና ወደ መድረክ የሚያስገባኝ ካርድ አልከጀልኩም፡፡ ወዲያ ወዲህ ብል አገኛለሁ፡፡ ያንን ግን አልፈለኩትም፡፡ ይልቅስ ልቡ በሀዘን እርር ኩርምት ካለው ወገኔ ልብ የሚወጣውን ጢስና መአዛ ማሽተት እፈልጋለሁ፡፡ እንባ በገረፈው ፊቱ ላይ ደስታ ሲንጠለጠል ማየት ናፍቄያለሁ፡፡ የነገ ተስፋው ከስሞ፣ ቁልቋልና እሾህ ካበቀለች  ነፍሱ ውስጥ የሚወጣውን መዝሙር፤ በጥሞና ማድመጥ ፈልጌያለሁ፡፡
ስለዚህ ከመድረኩ ፊት ለፊት፣ ማዶውን በተሰሩት እርከኖች፣ ከፍ ብዬ፣ ለመብራት የቆመ የብረት ግንድ ተደግፌ ቆምኩ፡፡ ሌላ መካከለኛ ሰው፣ ሌላኛው ጎን ቆመ፡፡ እጁ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ፣ ቀለም ያለው የጨርቅ አምባር አድርጓል፡፡ ፊቱ መጠጥ ያለ ጥቁር ነው፡፡
“ይገርማል! ይገርማል! ህዝቡ ገና ነው!›› አለኝ፤ የህዝብ ጎርፍ ወደ አደባባዩ ሲገባ አይቶ፡፡
እርግጥ ነው ወደ ባህር እንደሚፈስሱ መጋቢ ወንዞች፣ ከያቅጣጫው የሚፈስሰው የህዝብ ጅረት አያቋርጥም፡፡ እየመጣ ያጥለቀልቃል እንጂ!! የባቡር ሀዲዱ ድልድይ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስልና በሰንደቅ ዓላማ ተንቆጥቁጧል፡፡ የተለያዩ ጽሑፎችና ፎቶግራፎች ተሰቅለዋል፡፡
ሕዝቡ ይዘምራል፤ ከመድረክ ሙዚቃ ይለቀቃል። ‹‹ኢ...ት...ዮ...ጵ...ያ ሀገሬ›› ይላል ቴዲ አፍሮ፡፡ ለብዙ አመታት ኢትዮጵያን የተሸከመ አንደበቱ፣ ዛሬም እንደ አዲስ ይዘምራል፡፡ ብዙ ሰዎች በስሜት ሰክረዋል። መድረክ መሪው ወጥቶ ‹‹እንወዳችኋለን!›› ይላል፡፡ ሕዝቡም በል የተባለውን ይላል፤ አድርግ የተባለውን ያደርጋል፤ ተናገር የተባለውን ይናገራል፡፡ በዚህ መሀል የማየው ስሜት በእጅጉ እንደ ፍል ውኃ የሚንተከተክ ነበር፡፡ ሳላስበው የኢሕአፓው ዘመን ታሪክ ጠልፎ ወሰደኝ፤ የእነ ሕይወት ተፈራ ትረካ ነፍሴን ደመና ላይ ሰቀላት፡፡ የዚያ ዘመን ትኩሳትና ቁጣ ልባቸው ላይ ተጥዶ ታየኝ፡፡ ከፊቴ ፀጉሯን ለሁለት ከፍላ፣ ሁለት ገመዶችዋ ትከሻዋን የነኩ ሴት፤ የምትጮህበትና የምትናገርበት መንፈስ ከክንዶችዋ መወርወር ጋር የእነ ሕይወት ተፈራን የሰልፍ ትዝታ ከፊቴ ደቀነው። እነ ጌታቸው ማሩንና የነጻነት ናፍቆታቸውን አስታወሰኝ። የሰላማዊ ትግል ናፍቆት፣ ሆዴን ባር ባር አለው። “ኢትዮጵያ ደም ጠጥታ የማትረካ፣ ተበጥብጣ የማትሰክን --- ሀገር ለምን ሆነች?” ብዬ አይኔን በፈጣሪ ላይ ሳፈጥ፣ “ጥፋቱ የእርሱ አይደለም” የሚል መልስ አገኘሁ፡፡ ወደ ራሴ ተመለስኩ፡፡
ዶክተር ዐቢይና አቶ ለማ መገርሳ፤ የዘመናት ጩኸት መልስ ናቸው፡፡ ከሀዘን ከረጢት ውስጥ መውጫ መሰላል ሆነው ተልከዋል፣ ብዬ ከሀሳቤ ወደ ሰልፉ ተመለስኩ፡፡
ወፍራም፣ ጥቁር፣ ጉንጫምና መላጣ ሆኖ፣ ዳርና ዳሩን ያሉት ጸጉሮች ወደ ነጭ የተቀየሩና መነጽር ያደረገ ሰው ላቡ ጠብ እስኪል ይጮሃል፡፡ በጣም ተገረምኩ። የሀገሬ ሕዝብ ነጻነትና ፍቅር ተርቧል ማለት ነው ብዬ ቋጨሁ፡፡ ዶክተር ዐቢይ፤ ገና የሕዝቡን ኑሮ አልቀየረም፤ ዳቦና ብር አላደለም፤ ሰው ግን በፍቅር አብዷል፡፡ የሰጠው ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ያ የሕዝብ ውቅያኖስ፣ በማለዳ ከቤቱ ገፍቶ ያወጣው፣ያን ሁሉ ፎቶግራፍና ጽሑፍ ተሸክሞ፣ ከሰፈሩ እየጨፈረ ያስመጣው፣ የተሰጠው ተስፋ ብቻ ነው፡፡ ቃልና ጥቂት ገቢር ብቻ፡፡ የነጻነት ምልክት፣ የሀገር አንድነት ናፍቆት ነው - ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው ስም ውስጥ ያለው የሚነዝር ትዕምርት!
“ከለገጣፎ ነው የመጣሁት›› አለኝ፤ አጠገቤ የቆመው ሰው፡፡
“ከሩቅ ቦታ ነው የመጣኸው!››
“አረ ሰዎች ከአምቦ በፈረስ እየመጡ ነው››
“ውኡኡ!!!›› አልኩ፤ ድካማቸው እየታሰበኝ፡፡
“መንገድ ያድራሉ›› ብሎ፤ የሆነች ትንሽ ከተማ ስም ጠቀሰለኝ፡፡
‹‹ቢሆንም ከባድ ነው›› አልኩት፤ እርሱ ግን “ለዶክተር ዐቢይ የትኛውም ነገር ቢደረግ አይበቃም›› አለኝ፡፡ እኔም ተስማማሁ፡፡ በአጭር ጊዜ ብዙ ጭጋጎችን እንዲሁም የሰቆቃና የሀዘን ድምጾችን አስቁሞ፣ በተስፋ ጸበል የረጨ ጎበዝ፤ ከዚህም በላይ ይገባዋል፡፡
በሰልፉ ላይ ‹‹ዘር ለገበሬ፣ ክልል ለእረኛ ነው›› የሚሉ መፈክሮች ተይዘው ነበር፡፡ የአቶ ለማ መገርሳ ፎቶግራፎችና ለፕሬዝዳንቱ የተሰጡ የክብር መግለጫዎች፣ በበርካታ ሰዎች ተይዘው ነበር፡፡ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም፣ በሰልፈኞቹ ከሚደነቁት አንዱ ነበሩ፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንንም የሚያወድሱ ተገኝተዋል። ብዙ ነገሮች በሰልፈኞች እጅ ታይተዋል፡፡
መድረኩ በመድረክ መሪዎች እየተመራ፣ ሀገራዊ ስሜት የሚያምሩ ሀሳቦች፣ በጋለው የሕዝቡ ልብ ላይ እያቀጣጠለ ሄደ፡፡ በድንገት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ሱፍ ልብሳቸውን ግጥም አድርገው ብቅ ይላሉ ሲባል፣ የነጻነት ታጋዩ፣ የማንዴላ ምስል ያረፈበት ካናቴራ ለብሰው፣ የአዘቦት ኮፍያ ራሳቸው ላይ ጣል አድርገው፣ ወደ መድረክ ብቅ አሉ፡፡ ሰልፈኛው እንደ እሳተ ገሞራ እሳት ሆኖ ገነፈለ፡፡ ጠቅላዩም ባልተለመደ ሁኔታ ከአንገታቸው ሳይሆን ከወገባቸው እጥፍ ብለው አክብሮታቸውን ገለጡ፡፡ ከዚያም ወደ መናገሪያው ምስባክ ሄደው፣ ንግግራቸውን ሲጀምሩ፣ ሰልፈኛው ልቡን ነሳው፤ አበደ፤ ጮኸ፡፡
ዐ...ቢ...ይ!.... ዐ...ቢ..ይ! ዐ...ቢ...ይ!  አለ፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ሕዝቡ በታላቅ ድምጽ፣ በላቀ መንፈስ ከፍ እያለ ሄደ፡፡ ሩብ ዐመት በማይሞላ አጭር ጊዜ ውስጥ፣ የሕዝብን ቀልብ ነጥቆ አየር ላይ ማንሳፈፍ ያልተለመደ ነው፡፡ የዚህ አይነት ሰልፍ ያለ ቀበሌ ቅስቀሳ፣ ያለ አበልና ጥቅማጥቅም፣ በራስ ትራንስፖርት፣ በራስ ብር የተገዛ ካናቴራ ለብሶ መገኘት ---- በእጅጉ የጠቅላዩን ደማቅ ቀለማማ ስራ ያሳያል፡፡ ፍቅርና የአቀራረብ ኃይል፣ የአገልጋይ መሪን ውጤታማነት፣ ሰንደቅ ከፍ ያደርጋል፡፡
በጉባዔው ላይ ጠቅላዩ ለጥቅስ የሚሆኑ ንግግሮችን ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡም ተደንቋል፤ ጨፍሯል፡፡
ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ፍንዳታ ሲሰማና ጢሱ ሽቅብ ሲትጎለጎል እያየሁ፣ አጠገቤ ያለው ሕዝብ፤  ‹‹አንፈራም.!.. አንፈራም.!.. አንፈራም!›› ማለት ጀመረ፡፡
በጣም አስገራሚ የሆነው፣ ሞት ያዘለው እሳትና ጢስ ሲወረወር፣ ሕዝቡ መሸሹን ትቶ ‹‹ዐቢይን ብቻ አድኑት፤ ዐቢይን ብቻ አድኑት!›› እያለ ወደ መድረክ መሮጡ ነው፡፡ ሕዝቡ ፍቅር የሚሰጠው መሪ ካገኘ፣ ነፍሱን እንደማይሰስት የተፈተነበት ነው፡፡ ብዙ ቦታ በጆሮዋችን የሰማነው፤ ‹‹ከእርሱ በፊት እኔ ልሙት!›› የሚለው የፍቅር ቃል፣ በተግባር የታየበት፣ የፈተናም  እለት ነበር፡፡
መዝሙሩ አልቆመም፤ ወኔው አልጠወለገም፤ ተስፋ እንደ ጤዛ አልረገፈም፡፡ እሳቱ ህዝቡን ፈትኖ ወርቁን አውጥቶታል፡፡ ፍቅሩ መገለጫ ብቻ አልነበረም። በእሳት ጋይተው፣ በቦንብ ነድደው፣ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ የመሪያቸው ጉዳይ ከሕይወታቸው ብሶ መገኘቱ ነው፡፡ በተለይ በአደጋው እግሩ የተቆረጠው ወጣት፤ ”ለዶክትር አቢይ ይህ ብዙ አይደለም፤ ህይወቴን ብሰጠው እንኳ ...” ሲል መደመጡ፣ የፍቅሩን ጥልቀት አሳይቶናል፡፡ አደጋ ከደረሰባቸው እህቶቻችንም መካከል አንድዋ፤ ‹‹ዶክተር ዐቢይ ብቻ ደህና ይሁን!›› ብላ የራስዋን ሕመም ስትረሳ፣ በኢትዮጵያ የመሪዎች ታሪክ አዲስ የፍቅር ከፍታ ማማ ላይ እየወጣ፣ በማይጠፋ የታሪክ ድርሳን ውስጥ ደማቅ ታሪክ እየጻፈ መሆኑን አድማሳት እየተቀባበሉ ዘመሩ ...ሸለቆና ሜዳው እየተጠቃቀሱ አወሩ...አወሩ.. ተናገሩ...፡፡ ሁሌም ፍቅር ያሸፍናል!!!


Read 1024 times