Saturday, 07 July 2018 11:09

የዜማ ውበት፣ የድምፅ ጥበብ ከቤቲ አልበም - ወገግታ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(16 votes)


  • በወገግታ ተጀምሮ፣ አገርን በብርሃናማ ትርችቶች የሚደምቅ ብስራት የሚያሰማ - በአወንታ መንፈስ የተትረፈረፈ።
  • የዜማዎች ጣዕም ሽርሽር ነው - የቤቲ አዲስ አልበም። ብርቅ ድንቅ ዘፈኖችን የሚያጣጥሙበት የጥበብ አዝመራ።
  • የባለዜማዎቹ ዓለም ውስጥ ገብቶ እንደመታደም ነው - የሊዮነ ሪች እና የዘሪቱ፣ የአደል እና የነማይክል የጥበብ ዓለም።
       
    በዙሪያዋ ሁሉ እፅዋት በርክተው፣ ልምላሜ ለብሰው፣ አበቦች በህብር አምረው፣ በደማቅ ቀለማት ተንቆጠቁጠው ቢማርኳት፣ በመዓዛቸው የታወደውን ንፁህ አየር እንደልቧመቅዘፍ መክነፍ ቢያሰኛት፣... ደግ አደረገች። ለመብረር የተፈጠረች ቢራቢሮ አይደለች?
ቢራቢሮ
ያጌጡ ክንፎቿን ከመቅፅበት ለመዘርጋት፣ ወደ አበቦቹ እየዘመረች ለመብረር ልቧ ስቅል ብሎ፣ እመር ብላ ለመነሳት የጓጓች ቢራቢሮ! ጤናማ የሕያዋን ፍላጎትና የተቀደሰ ምኞት ነው!... ምኞት ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ አቅምም አላት። ግን፣ ወዳሰበችው የመሄድ ወደ ከፍታ የመድረስ ብቃትስ? መመኘት ማለት፣ በአፍታ ዘልሎ ለፍሬ መድረስ ማለት እንዳልሆነ አላወቀችም። የተፈጥሮ አቅምም በቅፅበት የመቻል ብቃት ይሆንላታል ማለት አይደለም። ወዲያው ተወልዶ ወዲያው ባለክንፍ አይኮንም። የታለ የሚዘረጋ ክንፍ? መብረር ቀርቶ፣ የታለ ቀና የማለት ብቃት? የታለ የቢራቢሮነት መልክና ቅርፅ? ከአፈር ላይ የሚንፏቀቅ፣ ከጭቃ ላይ መላቀቅ የቃተው አባጨጓሬም ሳይሻል አይቀርም ያስብላል - ሁኔታዋ።
ገና ጀማሪ ቢራቢሮ፣... ገና ባዶ እጇ፣... የነጣች የገረጣች፣... በዚህ ሁኔታዋ፣  ያጌጡ ክንፎችን ማብቀልና ወደ አበቦች መብረር፣... ከሰማይ የራቀ፣ ያለተስፋ የቀረ ከንቱ ምኞት መስሎ ይታያት ይሆን? ከመቅፅበት ለመብረር የጓጓች ባለወኔ ንፁህ ነፍስ ናት። ይሄ አልሆን ሲል ደግሞ፣  አሁኑኑ ካልበረርኩ፣ ወደፊትም ተስፋ አይኖረኝም በሚል አንገት መድፋት? የጀማሪ ነገር፣... ከአንድ ስህተት ሌላ ስህተት? የምታበረታ የመካሪ አስተማሪ ብትኖራትስ?
የስኬት ሕልሟን በማክበር፣ የስኬት ጥረትን በማድነቅ የምታበታታ መካሪ አለች - በቀና መንፈስ የተሞላች መካሪ። ይህች ቀና መንፈስ፣... ከምር ነፍስ ዘርታ መጥታለች። “የስኬት አላማና ጥረት፣... ምንኛ ከውድ እንቁም በላይ የከበሩ፣... በአድናቆትና በፍቅር፣ ልንቆረቆርላቸው፣ ልንጠነቀቅላቸው፣ ልናስብላቸው እንደሚገቡም ከምር ያወቀች” ናት። ይህች ብሩህና ቀና መንፈስ፣ በእውን ምን እንደምትመስል በአካል የመዳሰስ ያህል የሚያሳይ ነው - “ቢራቢሮ” የተሰኘው የቤቲ ድንቅ ዜማ። ባወቀ አእምሮና በተረዳ መንፈስ፣ በድንቅ የድምፅ ብቃትና ጥበብ የተሰራ ግሩም ዘፈን ነው።
ቢራቢሮ... ልትበር ቶሎ፤
ውብ አበባ... አይታ ኖሮ፤
አኮብኩባ... ልትነሳ፤
አላወቀች... ወይ ኩብኩባ።
የመዝሙር በሚመስሉ በእነዚህ ጥቂት ቃላት ነው ዘፈኑ የሚጀምረው - ግን ደግሞ በብልሃት የተሰናሰለች ግጥም ናት። ከዚያማ፣ ቤቲ... እንዴት በዜማ ጥበብ ተዓምረኛ ሕይወት እንደምትሰጠው፣ እየሰሙ መደመም ነው። በገለፃ የሚሆን ነገር አይደለማ። ዘፈኑን በማዳመጥ እንጂ! ዜማውን በማጣጣም እንጂ።
ቢራቢሮ...
ሲታይ መልክሽ... ...ሌላ ሆኖ፤
ተስፋሽ... ምነው ተመናምኖ፤
በችኮላ መብረር ተመኝታ ያልሆነላት ቢራቢሮ፣ መልኳ ገና ቢራቢሮ አለመምሰሉንም እያየች፣ የራሷንም ተፈጥሮ መጠራጠርና ተስፋ መቁረጥ እየሞካከራት ነው። ገና ምኑንም አለማወቋ ነው ችግሯ። ጀማሪዋን ቢራቢሮ ለማስረዳት፣ “ቢራቢሮ መሆንሽማ እውነት ነው” እያለች ትሞክራለች ብሩህዋ መካሪ። “ስሚኝ ዛሬ” እያለች ለማሳወቅ ትጣደፋለች፣ አሁኑኑ ለማስገንዘብ፣ ከመቅፅበት ለማስረዳት፣ በአንድ አፍታ ለማስተማር ትቻኮላለች - ብሩህዋ መካሪ።
ቢራቢሮዋ፣ በቀና መንፈስ ወደ ላቀ ከፍታ ለመብረር የምትቻኮል ገና ጀማሪ ቢራቢሮ!
መካሪዋም በቀና መንፈስ ለመምከር የምትቻኮል ገና ጀማሪ ናት ለካ! በመነሻና በመድረሻ መካከል ያለውን “ሂደት” መርሳት፣ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ እንደየደረጃው ሁሉንም የሚፈትን ጉዳይ ነው ለካ።
አስገራሚው ነገር፣ ይህንንም መንፈስ፣ በዜማ ማሳየት የሚቻል መሆኑ ነው - ማለቴ ቤቲ ችላለች። ችላም ዘፍናዋለች። በእርግጥ፣ የግጥሙ የቃላት አመራረጥ፣ ድርሻ አለው። ለምሳሌ፣ “ሂደት አለውና” የሚለው አገላለፅ፣ የመካሪዋ የጀማሪነት መንፈስን ለማሳየት ይጠቅማል። ጀማሪ ለጀማሪ የሚለውን መንፈስ፣ ስጋ አልብሶ ለማሳየት የቻለችው፣ በዜማውና በአዘፋፈን ጥበቧ ነው። ዘፈኑን ፈጠን ወዳለ ሁለተኛ የዜማ ክፍል ታሻግረዋለች - ኧረ ቢራቢሮዬ... እያለች።
ኧረ ቢራቢሮዬ፣ ስከኝ ቀስ በይና
ባንዴ መች ይበረራል፣ ሂደት አለውና
ኧረ ቢራቢሮዬ፣ ስከኝ ቀስ በይና
ባንዴ መች ለውጥ ይመጣል፣ ሂደት አለው ገና።
ቤቴ እነዚህን ስንኞች፣ ሞቅ ደመቅ ባለ ዜማና አዘፋፈን ነው፣ ነፍስና ስጋ የምትሰጣቸው። ለመሆኑ ጀማሪዋ ቢራቢሮና ጀማሪዋ መካሪ መጨረሻ ምን ይሆን? “ባንዴ ለውጥ ይመጣል፣ ይበረራል” ብለሽ የምታስቢው አዲስ ስለሆነብሽ፣ ስላላወቅሽ እንጂ... “ሂደት አለው”። ሂደት ግን ሄዶ ሄዶ በዚያው አይቀርም። አፈር ላይ እየተንፏቀቁ፣ ጭቃ ላይ እየተላወሱ መቅረት የለም - መብረር አለ። ግን፣... ያው በችኮላና ያለሂደትኮ አይሆንም። እናም፣ የቢራቢሮዋን የስኬት ምኞት እያደነቀች፣ እስሰምር ራዕይሽ፣ ሲታይሽ ክንፍሽ፣ ሲበር በምናብሽ፣ የመለወጥ ህልምሽ እያለች ካወዳደሰች በኋላ... ትቀጥላለች። (የዘፈኑ ሃሳብና የዜማው ስሜት፣ በጥበብ ሲታጠፍ፣ ግጥምጥም ብሎ ሲሰምር (በsurprise twist)፣ ምርጥ መቋጫም ላይ ሲደርስ አድምጡ - በሦስተኛው የዘፈኑ ክፍል።)
ታዲያ “ቢራቢሮ
አይሆን ተቸኩሎ
ያልሆኑትን ሆኖ
ሂደቱ... ተጠልቶ”...
ብዬ የምነግራት
ልቧን ልመልሳት
ከድካም ከጥፋት፣...
እልፍ ብዬ ባያት
እቺ ቢራቢሮ
እኔ ሆኜ ኖሮ
ይሄውና፣ ዘፈኑና ዜማው፣ በጥበበኛ የእጥፋት ስምረት... ምርጥ መቋጫ ላይ ደረሰ። ጀማሪዋ የብሩህ መንፈስ መካሪ እና ጀማሪዋ ቢራቢሮ፣... አንዷ የሌላኛዋ ምስል ናቸው። ከመቅፅበት አላማን ከስኬት ላይ የማድረስ ምኞት፣... ይሄ አልሳካ ሲል ደግሞ ተስፋ መቁረጥ፣... በምኞትና በስኬት መሃል ያለውን “ሂደት”፣... በአላማና በውጤት መካከል ያለውን ቁልፍ ነገር መርሳት (ምሁራኑ ስትራቴጂና የተሰናሰለ ተግባር የሚሏቸውን ነገሮች፣... ወይም ዘዴን እና ጥረትን መዘንጋት)፣ ሁሉም ሰዎች ልብ የሚሉት ቁምነገር ነው -ሁሌም፣ በሁሉም ጉዳይ ላይ። ይህንን እውነት የሚያሳይ በመሆኑም ነው፣ ጥበበኛው የእጥፋት ስምረት ትልቅ ትርጉም የሚኖረው (surprise twist፣ ሌጣው ሲሆን፣ ጥበብነትም ትርጉምም አይኖረውም)።  
ከዚህ ዘፈን ቀጥሎ ያለው ሌላው ድንቅ ዘፈን ላይም፣ ጥበበኛ የእጥፋት ስምረትን ማጣጣም ይቻላል። ዋናው ጥበብና ውበት ግን ሌላ ነው። በተፈጥሮ ተዋድደው የተፈጠሩ በሚመስሉ ሦስት የዜማ ክፍሎች የተዘጋጀ የዘፈን ጥበብ ነው - “ይሄ ነው አገር ማለት!› የሚያሰኝ። “ይሄ ነው የአገር ፍቅር ማለት” በሚል መንፈስ፣ ነፍስ የሚያድስ። ምንም ሳያግደው የሚናኝና ሰርጎ የሚዋሃድ በሚመስል ምርጥ የዜማ ፍሰት፣ በምርጥ የድምፅ ብቃት፣... ባወቀ አእምሮ፣ በተረዳ መንፈስ፣ ከሙዚቃው ጋር በፍቅር በተዋሃደ የጥበብ ማንነት የተሰራ ነዋ።
አገርን በአድናቆትና በፍቅር እጅጉን በማወደስ ትጀምራለች... ያምላክ ጥበብ ባንቺ ታየ እያለች። ከዚያስ?  
አገር      
መስኩ ተራራው
ሸንተረር ጋራው
የአምላክ ጥበብ፣ ነው ባንቺ የታየ
ያየሩ ምቾት ሁሌ ሚናፈቅ
ቅርሳቅርሱማ ልብ የሚሰርቅ...
...ግን ይሄ ነው ወይ አገር ማለት
ለዚህስ ብቻ ነው ወይ የሞቱለት
ቤቲ፣ የመልክዐምድርና የቅርስ አድናቆትን ወደ የላቀ አድናቆት ለማምጠቅ፣ ከልብ በመቆርቆር በምታቀነቅነው ጥያቄዋ፣ ህሊናን እያንኳኳች ታስከፍታለች።
የተፎከረው፣ የተለቀሰው
ያባቶቻችን ደምየፈ-ሰሰው
ለቡናው ነበር ወይ
ወይስ ለንጀራው
ለአራዊቱ ላፈር ለሜዳው
ኧረ ይሄ ነው ወይ አገር ማለት
ለዚህስ ብቻ ነው ወይ የሞቱለት
ኧረ ይሄ ነው ወይ አገር ማለት
ለዚህስ ብቻ ነው ወይ ምንሞትለት?
አገር ማለትማ... ከዚህም በላይ በእጅጉ የላቀ መሆኑን ብንረዳ እንደሚበጀን ነው መልዕክቷን የምትነገረን። ግን፣ በቃል ሳትናገር መልዕክቷን የምታስተላልፍልን - በዜማዋ የማሳመን ሃይል ወደ አድማጮች ህሊና እንደምትደርስ በመተማመን።
የአገር ትርጉም፣... ላይ ላዩንና የቅርብ የቅርቡን ብቻ ሳይሆን፣ ውስጡን በጥልቀት፣ ከዳር ዳርም ስፋቱን እንድንረዳ፤ በአጭር ሳንታጠር የብዙ ምዕተዓመታት የህልውና መሰረቶችን፣ የታላቅነት ጀግኖችን፣ የእውቀትና የፈጠራ ሰዎችን፣... የወደፊቱንም ራዕይ ጭምር... እና ሌላም ሌላም ብዙ የአገርን ትርጉም አጥርተን፣ በአንድነት አዋድደን እንድንጨብጥ፣... ከመንፈሳችንም ጋር እንድናዋህድ... ነው?
ሊሆን ይችላል። በደንብ አውቀን ከራሳችን ጋር ያዋሃድን ጊዜ፣ የት እንደምንደርስና ምን እንደምናገኝ በእርግጠኛነት ታዜማለቻ። የአገርን ምንነት፣... እጅግ ብዙ ውድና ድንቅ የአገር ትርጉም፣ በአንድነት ማዋደድ!... ይህንን ለመረዳት “ብዙ ነው ቋንቋው/ ግን አንድ ቤተሰብ” ብላ ያቀነቀችበትን ድምፅና ዜማ ያግዘናል። የአገርን ትርጉም እየተረዳን ስንሄድ... ያኔ በኑሮም በመንፈስም ከፍ ከፍ እንደምንል እንዳትጠራጠሩ አድርጋ ታዜማለች - ቤቲ። ሃገሬ ሃገሬ... በሚል አጀብ።
ሁሉ ከእንቅልፉ ሲነቃ...
ሁሉ ባንድላይ ሆኖ ሲነሳ
ሁሉም ይለወጣል
መልካምም ይሆናል
ሁሉም ተርፎት ያድራል
ደስታችንም ይበዛል
ይጠፋል መጠላላት
አንዱ አንዱን ባሽሙር መውጋት
ሰው ለሰው መድሃኒቱ
የዛኔ እንደሆነ ሲገባን
ሃገር ነው ወገን፣ ወገንም ሃገር
ብዙ ነው ቋንቋው
ግን አንድ ቤተሰብ
አይ ዘንድሮ (ከርዕሱ በላይ በላይ ልቆ የሄደ ትልቅ ዘፈን!)
ያማረ ውድ የምናብ ዓለም ነው መነሻው - የፍቅር ዓለም ጅምር፣ የፍቅር ኑሮ ውጥን። ለዘላለም የሚመስል፣ የምናብ ዓለም። ለዘላለምም መሆን ይችላል። በንፁህ ህሊና አስበው በቀና የተነጋገሩት የትናንቱ ቃልኪዳንም፣ ለይስሙላ አልነበረም። የምር እንጂ። ለዛሬም፣... ለነገም፣ የፍቅር ዓለም እየለመለመና እየደመቀ፣ የፍቅር ኑሮ እንዲሆንላቸው ነበር ሃሳባቸው።
ግን፣ ቀናት አልፈው ወራት ሲተኩ፣... ያ በምናብ የወጠኑት የፍቅር ኑሮ በእውን ሊይጨብጡት ሊይዙት ሲሞክሩ፣ በዚህና በዚያ እያመለጠ፣ አልሆን የሚላቸው ለምን ይሆን?
“የታል፣...
በበጎ በክፉም ጊዜ
ፍፁም ላንለያይ፣ ቃል የገባነው ያኔ”
ይሄ የዘፈኑ አጀማመር፣... ወደ እሮሮ የሚያመራ ከመሰላችሁ፣ ተረጋጉ። እሮሮና ማማረር የለም። ... “ብርታት ጠፍቶ፣ መለያየት ደርሶ፣ ልባችን ተሰበረ” በሚል ሃሳብ፣... “ስለፍቅር አለማወቃችን ጎዳን” የሚል የቁጭት ስሜትን ያዘለ ነው። አወቅን የምንለው ከጥቂት ቀናት በላይ በማይሰራ እውቀት ነው እንዴ?... ብርታትን የሚፈትን አጋጣሚ ሲፈጠር የሚደበዝዝ የአፍታ እውቀት? ይህን ብሎ አዋቂነት!... በዚህ መንፈስም ነው፣ በቁጭት፣ “ፍቅር በመለያየት አያምንም” በማለት ስለፍቅር የምታዜመው፣... ስለ ፍቅር ስለ ራሱ!. “ፍቅር ፀንቶ ይቆማል”... እያለች!
“ፍቅር ይታገሣል
ቸርነትን ያደርጋል፣ እንዲሁ አይወድቅም ከቶ”፤
ስናበላሽ እንዲህ እያልክ...
ትመልሰኝ አልነበር፣ ለምን ልብህ ዛለ ቶሎ።
ፍቅር ፍቅር
አይ ዘንድሮ...
ጥሬ ዞሮ፣ አልበሰልንም፣ አዋቂ እኛን ብሎ።
ፍቅር አይታበይም
በደልንም አይቆጥርም
በመለያየት አያምንም
ፍቅር ይታገሣል
ቸርነት ያደርጋል
አይወድቅም ከቶ
ፍቅር ተስፋ ያደርጋል
ፀንቶም ይቆ...ማል
በጣም ምርጥ ዘፈን ነው። እውነት ለመናገር፣ ጥቅል ሃሳቦች የበረከቱበት እንዲህ አይነት ግጥም፣ ለዘፈን በጣም አስቸጋሪ ነው። ግን፣ በጥበቧ፣ በድንቅ ዜማዋና በድምፅ ብቃቷ፣... ምርጥ ዘፈን ሰራችበት - “ወይ ዘንድሮ” የሚለው ርዕስ። እንዲያውም... የይሄው ዘፈን፣ የአልበሟ የምርጦች ምርጥ ዘፈን ነው ቢባል ያን ያህልም አይበዛበትም።
ግን ደግሞ፣ “አገር” የሚለው ዘፈን አለ። ይሄም አስገራሚ ዘፈን ነው።
“ጥልቅ ስሜት” የሚለውስ ዘፈን? የምርጦች አንደኛ ከመሆን ምን ያግደዋል?
“ዋጋ” የተሰኘው ዘፈንም ጉደኛ ነው። “ሩጫም ለፈጣን፣ ውጊያም ለሃያላን፤ ሞገስ ለአዋቂ፣ ሃብትም ለጠቢባን...” መሆን አለበት፤ ብዙ ጊዜ እውን የሚሆን ባይመስልም፣ አይቀርም ይሳካል... እያለት የምታቀነቅንበት ዘፈን ነው። አዎ፣ ፈተናዎች ለማለፍ ብዙ ጥረት ያስፈልጋል። ግን፣ ይሄም ዋጋ አለው። ከንቱ ልፋት አይደለም። ውጤት አለው... የሚል ነው ዘፈኑ።

ዋጋ አለው ህይወት ስታልፍ መከራ
እንደወርቅ እሳት ውስጥ ተፈትና ስትሰራ።
ዋጋ አለው መታገስ አይደለም ለከንቱ
እንቁ  ሲታሽ ነውኮ የሚደምቀው ውበቱ።

የምርጦች ምርጥ ዘፈን የትኛው እንደሆነ መናገር ያስቸግራል። “ቢራቢሮ” የሚለው ዘፈንምኮ ምርጥ ነው። ምን ይሄ ብቻ!
“አስተውሎ መርምሮ፣ ጥሮ ሰርቶ፣ በፈተና በችግር ሳይረታ፣ የስኬት የሚደርስ፣ ለአርአያነት የሚበቃ ጀግና የታለ? ኧረ ማነው? እያለች በሌላ ዘፈን ትጣራለች፣ ታፈላልጋለች ቤቲ። የእውቀትና የጥበብ፣ የትጋትና የስኬት ጀግኖችን በአርአያ የማየት ጉጉትና ረሃብ ነው -  “ኧረ ማነው?” የሚለው በምርጥ ዜማና ድምፅ የተሰናዳ ዘፈን። ይሄስ፣ የምርጥ ዘፈኖች አንደኛ ለመባል ምን ያንሰዋል?
ለነገሩማ፣ “እንጃ” የሚለው ዘፈንምኮ፣... አሪፍ ነው። “እንጃ”... ፍቅርን የሚበላ አስቀያሚ ዝገት መስሎ ይታያችኋል - ዘፈኑን ስትሰሙ። ያው፣... ይሄም፣ በድንቅ ብቃት የተሰራ ዘፈን ነው። “እንጃ”፣ ምርጥ ነው (ዘፈኑን ማለቴ ነው። ዝገቱን ማለቴ አይደለም)።
“ብሩህ ጠዋት” የሚለው ዘፈን ደግሞ አለላችሁ! በብርሃናማ ርችቶች የአገር ብስራት የሚያሰማን ዘፈን ነው - ለአልበሙ ልዩ ክብር የሚያጎናፅፍ የመጨረሻ ዘፈን!
ብርሃን ብርሃን፣ ለጨለማ
ብርሃን ብርሃን ይሁን ዛሬ
ብርሃን ብርሃን ይብራ ፋና
ብርሃን ብርሃን ይሁን ለኔ
እልልታ በመሰለ እጅግ ፈጣንና ደማቅ ዜማ፣ አገሬውን ፏ አድርጋ ታበራዋለች።
ብቻ ማናለፋችሁ? የቤቲ አልበም፣ የዜማ ጣዕም የተንበሸበሸ የጥበብ አዝመራ ነው። ከምኞትም በላይ በርከትከት ብሎ የተሟላ። በላቀ ብቃት፣ ለጥበብ በቆረጠ ልብ፣ ከስራ በሚገኝ የሃሴት ብርታት፣ ጥንቅቅ አድርጋ የሰራችው አልበም ነው። የምትዘፍንበት ድምፅ እና ስሜት አስገራሚ ነው።  የድምፅ ብቃት፣ የሙዚቃ ሙያ ፍቅርና ፍንክች የማይል ትኩረት፣... ከዚህም ጋር፣ የእያንዳንዱን ግጥምና ዜማ ይዘት፣ የሃሳብና የስሜት መልዕክት፣ ከመነሻ እስከ መድረሻ፣ ዜማውና ፍስሰቱን፣ ጠልቆ መገንዘብ፣ መረዳት፣ ከራስ ጋር ማዋሃድንም ሁሉ ማሟላት! ቤቲ ምን ያህል ዘፈኖቿን ከራሷ ጋር አዋህዳ እንደዘፈነቻቸው ሲታይ፣ የዘፈኖቿ ግጥሞችና ዜማዎች አብረዋት የተወለዱና ከራሷ ፈልቀው የተቀረፁ ነው የሚመስሉት።     

Read 2550 times