Print this page
Monday, 09 July 2018 00:00

የጦረኝነት ሥነልቦናን ለመናድ፣ በሴትነት እንደገና መወለድ

Written by  ሕሊና ፍርድያውቃል
Rate this item
(3 votes)

  በአንድ አካባቢ በጋራ የሚኖር ማሕበረሰብ፤ ለረጅም ዘመናት አብሮ ከመኖር የሚያተርፋቸው ገዢ የሆኑ የወል ስሜቶችና አስተሳሰቦች ይኖሩታል፡፡ ይህንን የወል ስሜቶችና አስተሳሰቦች ቋት፣ ኤሚል ዶርካይም፤ “Collective Consciousness” ብሎ ይጠራዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛ ገዢ የወል ስሜቶችና አስተሳሰቦች ምን እንደሚመስሉ ለመረዳት፣ ኢትዮጵያውያን በጋራ የተካፈልናቸውን የወል ልምዶቻችንን ወይም ገጠመኞቻችንን መመርመሩ ጠቃሚ ነው፡፡ እዚህ ላይ የታሪክ ድርሳናትን ስናገላብጥ፣ ጎልቶ የሚወጣው የወል ታሪካችን፣ ጦርነት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። አገራችን በተደጋጋሚ በተካሄዱ አስከፊ ጦርነቶች ስትታመስ ኖራለች፡፡ የጦርነት ታሪካችን፤ በርካታ የእርስ በርስና አገርን ከውጭ ወራሪ ለመከላከል የተደረጉ የነፃነት ትግሎችን አሰናስሎ የያዘ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ጦነት ገዢ ለሆኑ የወል ስሜቶችና አስተሳሰቦች መፈጠር፣ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ግዙፍ ሀይል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
ጦርነት በሥነልቦናችን ላይ ይህን ያህል ተፅዕኖ ያለው ሀይል መሆኑ ካልቀረ፣ እስቲ በጦርነት የተገነባውን የጋራ ቤታችንን፣ የስሜትና የአስተሳሰብ ቋታችንን በድፍረትና በቅንነት እንፈትሸው፡፡
1ኛ መጠራጠር
በማያባራ ጦርነት ሲቆላ የኖረ ህዝብ፤ ንቁና ተጠራጣሪ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ አገላለፅ፤ የጦርነት አደጋ የተጋረጠበት ሕዝብ፣ ከንቃትና ከጥርጣሬ መጓደል የተነሳ፣ የሚከፍለው ዋጋ፣ ውድ ህይወቱን መሆኑን ውስጡ ይነግረዋል፡፡
መጠራጠር የህልውናው መሠረት መሆኑን በጉልህ ልቦናው ውስጥ ያትመዋል፡፡ በአንፃሩ የእምነት ዋጋው ይንራል፡፡ መታመንን ለማትረፍ ብዙ ውጣውረድ ማለፍን ይጠይቃል፡፡ የሀሳብ ልዩነት በቀላሉ በክህደት ይመነዘራል፡፡ “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” እና “ሰው ማመን ቀብሮ ነው” የሚሉት ብሒሎች፣ የማህበረሰቡ ገዥ ሀሳብ ይሆናሉ፡፡ በመጨረሻም የክህደት አደጋን ለመቀነስ ሰዎች ወደ ዘር፣ ጎሳና ሀይማኖት ከረጢቶች ውስጥ መግባትን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ የዘር፣ የጎሳና የሀይማኖት አንድነት፣ የመተማመኛ የይለፍ ወረቀቶች ይሆናሉ፡፡
2ኛ - ማድፈጥ
ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም “ማድፈጥ” የሚል፣ የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ ለመረዳት የሚያግዝ፣ ድንቅ ፅንሰ ሀሳብ ከእነ ትርጓሜው አስተዋውቀውናል፡፡
“ዘጭ!- እንቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ” በሚለው መፅሐፋቸው፤ ማድፈጥ ኢትዮጵያውያን በአምባገነኖች የሚጫንባቸውን የጭቆና ቀንበር ለመስበር የሚጠቀሙበት መሣሪያ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡ “ማድፈጥ” ድምፅን አጥፍቶ የተሻለ ጊዜ እስኪመጣ መጠበቅ፣ በዝምታ የለውጥ እንቅፋት መሆንን፣ ሆን ብሎ መለገምን፣ ወይም ማኩረፍን እንደሚገልፅ ፕሮፌሰሩ ይነግሩናል፡፡
ጠላት ተብሎ የተፈረጀው ጨቋኝ ገዥ ሀይል እስኪዳከም ለየብቻው አድፍጦ የቆየው ሕዝብ፤ ድንገት የተሻለ አማራጭ ጉልበተኛ ወይም ተገዳዳሪ መምጣቱን ሲመለከት “ቀን ሲደርስ አምባ ይፈርስ” እያለ፣ ጠላቱ ላይ መረባረብ ይጀምራል፡፡ ከየጎሬው ወጥቶ የጠላቱን አምባ ያፈርሳል፡፡
“ማድፈጥ” እንደ ጦርነት ነው፡፡ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ትንፋሽን መዋጥ፣ ድምፅ ማጥፋት፣ ከዚያም ጠላት ኢላማ ውስጥ ሲገባ፣ አልሞ መተኮስና ማውደም ነው። “ማድፈጥ” ስሜትን መደበቅ ወይም መቅበርም ነው፡፡ የታፈነ ስሜት ጊዜ ጠብቆ ሲፈነዳ፣ አብዮት ይሆናል፡፡ ውድመት ያስከትላል፡፡
3ኛ- ጉልበት አምላኪነት
“Survival of the fittest” በሚል አገላለፅ፤ “አሸናፊነት የህልውና ዋስትና” መሆኑን በሚያውጀው የዳርዊን መርህ መሠረት በአገራችንም የጦርነት ጉልበት ማደርጀት፣ የህልውናችን ምሰሶ ሆኖ፣ ለረጅም ዘመናት ዘልቋል፡፡ በጉልበት ያሸነፈ ሁሉ የፖለቲካ አመራሩንና ኢኮኖሚውን እንዳሻው ሲዘውረው ኖሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ጉልበተኝነት በእኛ በኢትዮጵያውያን የስነ ልቦና ቀረፃ ላይ ሰፊውን ድርሻ ይዞ ቢገኝ የሚያስገርም አይሆንም፡፡ “ለመዶሻ ሁሉ ነገር ሚስማር ይመስለዋል” እንደሚባለው፤ በጦርነት አውድ የተቀረፀ ማንነት፣ በሰላሙም ጊዜ በምናደርጋቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር ላይ ጥላውን ያጠላል፡፡ የሕይወታችን ዋናው ገዥ ፎኖተ ካርታ ይሆናል፡፡
ለምሳሌ ህፃን ልጅ እንቅፋት ሲመታው፣ ለቅሶውን የምናስቆመው እንቅፋት የሆነውን ቁስ አካል መልሰን በመምታትና እንደተበቀልንለት በማሳየት ነው፡፡
“አንችን ያለውን
በሳንጃ ሆዱን” … የሚል ባህላዊ ዘፈን፣ የብዙ ወንዶችን ልብ የማሸፈን ምትሃት ያገኘው ለጉልበተኛነት ቅርብ የሆነው፣ የሥነ ልቦና መዋቅራችን ምቹነትም ተጨምሮበት እንደሆነ መጠርጠር አይከፋም፡፡
በጥቅሉ፤ ከሩህሩህና ለስላሳ ባህሪ ይልቅ ወደ ጉልበተኛነት ያመዘነ ኮስትራነትና ጀብደኛነት ተመራጭ እንዲሆኑ፣ ተደጋጋሚው የጦርነት ልምዳችን፣ ያበረከተው አስተዋፅኦ ጉልህ ነው፡፡
በሴትነት እንደገና መወለድ
የጦረኝነት ስነልቦናችን ዋልታና ማገር ሆነው ያነፁት፣ የወል አስተሳሰቦቻችንን ለማየት ሞክረናል። እዚህ ላይ ጦረኝነት፣ የወንድነት መለኪያ ተደርጎም እንደሚታይ ልብ ማለት ይገባናል፡፡ ጀግና ሴትን “የሴት ወንድ ናት” ብሎ ማሞካሸት፣ ከዚሁ አስተሳሰብ የመነጨ ነው፡፡
በአንፃሩ ለስላሳ ባህሪ ያለውና ገራገር ወንድ፤ “ሴታ ሴት” በሚል ይንኳሰሳል፡፡ ከዚህ በዘላለም ያልተቀጣ ወይም ዋልጌ መሆንን ለማመላከት፤ “ሴት ያሳደገው” የሚል የስድብ ሀረግ ፈጥረናል፡፡
በአጠቃላይ በእነዚህና መሠል የአነጋገር ብሂሎች፣ የወንድነትን ባህል አጎልብተን፣ የሴትነትን ፀጋ ከውስጣችን ነቅለን ጥለናል፡፡ የሴትነት ድምፅ የሚታፈነው፣ የሴትነት ነፃነት የሚገፈፈው፣ በይፋ በምናሳየው ድርጊታችን ብቻ ሳይሆን ሴትነትን ከውስጣችን አፍነን በመግደልም ጭምር ነው፡፡ በዚህ መንገድ ርህራሄያችንን፣ ይቅር ባይነታችንን፣ የመቻቻል አቅማችንንና ቅንነታችንን ቀስ በቀስ እያቀጨጭናቸው ሄደናል፡፡
እናም የሕይወት መረጋጋትና ሰላም ከሚጠበቅባቸው መንገዶች ዋነኛውን “የሴትነት እና ወንድነት” ሚዛን፣ በመሳታችን ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን፡፡ ይህ መሠረታዊው የህይወት ሚዛን፣ በሩቅ ምስራቁ የጥበብ መንገድ Yin እና Yang ተብሎ ከጥንቱ ጀምሮ ይታወቃል፡፡ የቅርብ ዘመኑ የስነ ልቦና ጠበብት ካርል ዩንግ ደግሞ Anima እና Animus ሲል ገልፆታል፡፡
በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ፣ ከወንዳወንድነት ከተቀዳው ባህላችን የተገኙ ወንዶች፤ አገር የማስተዳደሩን ሚና እየተፈራረቁ የሚዘውሩት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ሴቶች አገር የመምራቱን ሚና ለመረከብ ጊዜው ገና ይመስላል፡፡ ያም ሆኖ ግን ካርል ዩንግ እንደሚለው፤ በሴቶች ውስጥ የወንድ ድምፅ እንዳለው ሁሉ፣ በወንዶች ውስጥም የሴት ድምፅ በጥልቁ ተቀብሮ ይገኛል፡፡ ወንዶች በውስጣቸው የተቀበረውን የሴት ድምፅ ፈልፍለው ማግኘትና ነፃ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአገራችን ባለው የባህል ተፅዕኖ ምክንያት ይህን ማድረግ ከባድ ቢመስልም የሚቻል መሆኑን ግን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር አብይ አህመድ አይተናል፡፡ ዶ/ር አብይ፤ “ሴት ያሳደገው” መሆንን እርግማን ሳይሆን ፀጋ አድርገው አሳይተውናል። በውስጣቸው የሞላው የፍቅር፣ የርህራሄና የይቅር ባይነት ድምፅ፣ ከወንድነታቸው ጋር ያስታረቁት የሴትነት ድምፅ ነው፡፡
ነገር ግን አሁንም የወንዶች ጉርምርምታ ከሩቅ ይሰማል፡፡ ያልሞት ባይ ተጋዳይነት ትግላቸውን ለማስቀጠል ስልት እየነደፉ ይመስላል፡፡ ሌላ ዙር ማድፈጥ፣ ሌላ ዙር ማውደም እንዳይመጣ፣ በፍቅር ፀንተን ቤታችንን እንጠብቅ፡፡
በፍቅርና በይቅርታ ሀይል ላይ አሁንም ተስፋ አንቁረጥ፡፡ ምኑ ይታወቃል? ታሪካችን ይቀየር ይሆናል። ስለ ጦርነት ያወራንበት አፋችን፣ በፍቅር ታሪኮች ይሞላ ይሆናል፡፡ በጦረኝነት የታሪክ አምዶቻችን የታነፀው ፀባችን፤ ፍቅር የሚፈስበት፣ የሰላም እርግቦች የሚፈነጩበት፣ የዘላለም የሕይወት ዛፍ የሚበቅልበት ስፍራ ይሆን ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል?!


Read 4938 times