Saturday, 14 July 2018 11:51

የኤርትራ ተቃዋሚ ግንባር ስጋት ውስጥ መውደቁን ገለጸ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

 “ኢትዮጵያን መጠጊያ ላደረጉ ስደተኞችና ተቃዋሚዎች አስጊ ሁኔታ ተፈጥሯል”


     በትጥቅ ትግል ታግዞ የሚንቀሳቀሰው የኤርትራ መንግስት ዋነኛው የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅት፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ እርቅ መፈፀማቸውን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ስደተኞችና ተቃዋሚዎች የደህንነት ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን አስታወቀ፡፡
የኤርትራ ብሄራዊ መድህን ግንባር የተሠኘውና ፅ/ቤቱን በአዲስ አበባ ያደረገው የኤርትራ መንግስት ዋነኛ ተቃዋሚ ድርጅት ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ ከሠሞኑ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው እርቅ፣ ለህዝቦች ግንኙነት ጠቃሚ ቢሆንም በኤርትራ ያለውን “አምባገነን” ስርአት ሸሽተው፣ ኢትዮጵያን መጠጊያ ላደረጉ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞችና ተቃዋሚዎች አስጊ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ውሣኔ ተግባራዊ ለማድረግ በመወሰኗ ደስተኛ ነን ያለው  ግንባሩ፤ ይሁን እንጂ በኤርትራ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እውን ሳይሆን በቀጠናው ሠላምና መረጋጋት ሊመጣ አይችልም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት፤ በኤርትራ ያለውን የዲሞክራሲ እጦት አጢኖ፣ ከፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ጋር እየመሠረተ ያለውን ወዳጅነት በጥንቃቄ እንዲመረምር ግንባሩ በመግለጫው ጠይቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የወሰዱትን ተራማጅ እርምጃ እናደንቃለን ያለው ግንባሩ፤ እርምጃው በሁለቱ ህዝቦች መካከል መቀራረብን እንደሚፈጥርና የህዝቡ መቀራረብ ደግሞ ለሚፈለገው ዲሞክራሲያዊ ለውጥ አስፈላጊ መሆኑን አልሸሸገም፡፡
እንዲያም ሆኖ የተፈጠረው ግንኙነት በኢትዮጵያ ላሉ አባሎቼ አስጊ ሆኗል ያለው የኤርትራ ብሄራዊ መድህን ግንባር፤ የኢትዮጵያ መንግስትና የአካባቢው ሃገራት በኤርትራ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲገነባና የዜጎች ነፃነትና ፍትህ እንዲረጋገጥ እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
ግንባሩ ይሄን ስጋቱን በተመለከተም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በደብዳቤ ማሳወቁን ጠቁሟል፡፡  
“እኛ ሠላም አንጠላም፤ በኤርትራ ያለው ሁኔታ እንዲለወጥ እንፈልጋለን፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን ያገናዘበ በሣል እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን” ብሏል - ግንባሩ፡፡

Read 14643 times