Saturday, 14 July 2018 11:55

አየር መንገድ ማክሰኞ ወደ አስመራ የመጀመሪያ በረራውን ያደርጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

 የፊታችን ማክሰኞ ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም የመጀመሪያውን በረራ ወደ አስመራ የሚያደርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ከ20 ዓመታት በኋላ 250 ሰዎችን ይዞ ወደ ኤርትራ አስመራ እንደሚጓዝ ተገለፀ፡፡
ማክሰኞ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከቦሌ አየር ማረፊያ የሚነሣው ቦይንግ 787 ዘመናዊ አውሮፕላን አስመራ ለመድረስ የ70 ደቂቃዎች ጊዜ ብቻ ይወስዳል ተብሏል፡፡ የአንድ ተጓዥ የደርሶ መልስ ቲኬት ዋጋም 8 ሺህ 944 ብር ሲሆን ይህም ወደ ሌሎች የጎረቤት ሃገራት ከሚደረገው የጉዞ ዋጋ አንፃር ዝቅተኛው ነው ተብሏል፡፡
ወደ ካርቱም ለመጓዝ 12172 ብር፣ ወደ ናይሮቢ 9779 ብር እንዲሁም ወደ ጅቡቲ 9561 ብር የደርሶ መልስ ቲኬት ዋጋ ሲሆን የአስመራው ጉዞ ከሁሉም ዝቅተኛው ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ ከግንቦት 1990 ጀምሮ የተቋረጠውን የአስመራ በረራ እንደሚጀምር ይፋ መደረጉንተከትሎ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጓዦች ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያውያን አስመራ ሲደርሱ ወዲያው የኤርትራ ቪዛ እንደሚያገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 8132 times