Saturday, 14 July 2018 12:02

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር

Written by  ባህሩ ሰጠኝ
Rate this item
(1 Vote)

 ሰላም ጠቅላይ ሚኒስትር፤ እንደምን ሰነበቱልኝ። ሰላምታዬ በተለመደው የ[አዲስ አድማስ] ጋዜጣ ቢሮዎት ድረስ ከች እንደሚልልዎት አልጠራጠርም። እስካሁን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የጻፍኩልዎትን ደብዳቤ አንድ በአንድ እየተገበሩልኝ በመሆንዎት በጣም አመሰግንዎታለሁ፡፡ እንኳን ለ100ኛ ቀን ሲመትዎ አደረስዎት፡፡ [መደመር] የሚል ፍልስፍና አንግበው በ100 ቀናት፣ የ100 ዓመት ስራ ሰርተዋል ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ [የሚወጣ ጥጃ ከማሰሪያው ይለያል፤ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል]፤ እስካሁን የሄዱበት ውጤት እጅግ ፈጣን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከሹመትዎት ማግስት ጀምሮ እያንዳንዷን ቀን በተግባር መንዝረው አሳይተውናል፡፡ ኢህአዴግ ለ27 ዓመታት ያልፈታውን ውስብስብ ችግር፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ እልባት ሲሰጡ አይተናል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሶቭየት ህብረት ልትበታተን ስትል እርስዎ በነፍሷ ደርሰውላታል፡፡ ምን ይህ ብቻ የኢህአዴግንም ዕድሜ አራዘሙለት እንጂ፡፡ ቦንቧን የዘነጋኋት በዋዛ እንዳይመስልዎት፤ ማንም ኢትዮጵያዊ መቼም ቢሆን አይዘነጋትም፡፡ ከፈነዳው ቦንብ የፈነዳው ፍቅር በለጠ ተብሏል፡፡ የእርስዎ ፈጣን ለውጥ ያላስደሰታቸው ምቀኞች የእርስዎን ዓላማ ለማጨናገፍ መቼም ቢሆን አይተኙም፡፡ ሌትም ቀንም ተጉዘው የሚያደርጉትን ተከታታይ ጉብኝት ሳስብ ድ…ክ…ም ይለኛል፡፡ ከጂቡቲ እስከ ኬንያ፣ ከሱዳን እስከ ዩጋንዳ፣ ከግብጽ እስከ ሶማሊያ፣ከሳውዲ አረቢያ እስከ ኤርትራ…. ጎራ ብለው ብዙ ነገሮችን አምጥተውልናል፡፡ ከሁሉም ሀገሮች ጋር የተደረገው ጉብኝት ታሪካዊ ቢሆንም የኤርትራው ግን ዓለምን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ አስደምሟል፤ ታጥሮባቸው የነበሩ እናትና ልጅ፣ ከእህት፣ ከወንድም…..ጋር ያገናኘ ታሪክ ሰርተውልናል፤ በእውነት ኮርተንብዎታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር፡- በየጊዜው የፍቅር ሚሳኤል እያስወነጨፉ አለምን አስደመሙት እኮ፡፡ ዜመኛ ንግግርዎት በሽተኛ ይፈውሳል። የፍቅር ዶክተር ቢባሉ ያንስብዎታል እንጂ አይበዛብዎትም፡፡ ባለፈው የግብጹ መሪ አልሲሲ በፍቅርዎ ተማርከው፣ “ወላሂ ጥሩ ሰው ነህ” ሲሉዎት ሰማን፡፡ መቼም እርስዎ በየቀኑ [ሰርፕራይዝ] ማድረግ ተክነውበታል፡፡ ባለፈው እሁድ  ደግሞ አስመራ ከተማ ድንገት ከች ብለው፣ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ከወንድምዎ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተደምረው ሰርፕራይዝ አደረጉን እኮ። ግራ ቀኝ ከ100 ሺ በላይ ወገኖቻችን ያለቁበትን ጦርነት በፍቅር አሟሹልን፡፡ ይኸው የጥላቻ ጨለማው ተገፈፈ፤ የሰላም ብርሀን ወገግ አለ። እነሆ በሁለቱ ሀገራት መካከል የአየር መንገድ፣ የወደብ፣የኤምባሲ፣ የስልክና ሌሎች አገልግሎቶች ሊጀመሩ ነው፡፡ በUNESCO ትንl ሮም ተብላ በምትጠራው አስመራ፣ የኢትዮጵያ አውሮፕላን የሰላም አየር ተነፈሰ፡፡ የኤርትራን ህዝብ በፍቅር መድፍ አንበርክከውት መጡ፡፡ የአስመራ ህጻናት እንኳ ዝናዎትን ሰምተው፤ “አብይ አብይ” እያሉ ሲጠሩዎት ዓለም ተደመመች፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንኳ ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር በፍቅር ተደምሮ እየቀዘፈ አስተላለፈ፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ በፍቅር ሲደመሩ የተባበሩት መንግስታትና መላው ዓለማቀፍ ማህበረሰብ አጃኢብ አለ፡፡ ኢሳያስ  እንኳን ሲስቁ ፈገግ ሲሉ አይተናቸው አናውቅም፤ በርስዎ ምትሃታዊ ንግግር ደስታ ፈንቅሎአቸው ሳቅ በሳቅ ሲሆኑ ተመለከትናቸው፡፡ እንግዲህማ [ኤርትራ] ሄደን ከወንድሞቻችን ጋር በአስመራ ከተማ በቀይ ባህር ሽር ሽር ልንሄድ ነው፡፡ መቸም እርስዎ ዕረፍት የለዎትምና በቅርቡ ደግሞ ወደ [አሜሪካ] ጎራ እንደሚሉ ሰማን፤ ቅቡል ነው፤ ለኢትዮጵያ ብዙ ቁም ነገርና ዶላር ተሸክመው እንደሚመጡ እርግጠኞች ነን፡፡  
እርስዎ ፈጣሪ ለኢትዮጵያ የለገሳት ልዩ ስጦታ ነዎት፡፡ በየወህኒ ቤቱ የታጎረ ኢትዮጵያዊ ፍትህ አገኘ፡፡ እስካሁን ባለው የኢህአዴግ ሁኔታ ከእስር ቤት ከመውጣት ይልቅ በመርፌ ቀዳዳ ግመል ማሳለፍ ይቀላል፡፡ የእስረኞችን ቁጥር ማሳደግ በትራንስፎርሜሽኑ ግብ የተቀመጠ ይመስል [በጅምላ ማሰር] እንጂ [በጅምላ መፍታት] አልነበረም፡፡  ስንት የሚታሰር ወንበዴ [ሌባ] በየመንደሩ ሞልቶ ተርፎ፣ ንጹሃን ዜጎች ታጉረው ሲማቅቁ ባጁ፡፡ ያን ሁሉ እስረኛ አጉሮ የኖረ ማረሚያ ቤት ምን ያህል ቢሰፋ ነው፤ ለካ የእኛ እስር ቤቶች [ቤርሙዳ] ናቸው፤ ዋጥ አድርገው ዝም ነዋ፡፡ እነሆ ጊዜ ለኩሉ ሆነና [ቤርሙዳ] የገቡ እስረኞች ወጡ፡፡ ዕድሜ ለእርስዎ! ኢህአዴግ እያመቀ ወህኒ ቤት ሲያስገባው የነበረውን እስረኛ በጅምላ ለቀቁልን፡፡ ይህን ያህል እልፍ እእላፍ ወገናችን በሱዳን፣ በሳኡዲ፣ በኬንያ……በሌሎች ባዕዳን ሀገራት ወህኒ ቤቶች ታጉሮ እየማቀቀ፣ መሪዎቻችንና አምባሳደር (ዲፕሎማት) ተብየዎቻችን ምን እየሰሩ ነበር፤ እንዴት የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብለው ዝም ይላሉ፡፡ አሳዛኝም አሳፋሪም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት መንግስት አልባ ሀገር ነበረች ማለት ነው?
ክብርና ምስጋና ለእርስዎ ይግባዎትና ሌትም ቀንም ተጉዘው ባደረጉት ዲፕሎማሲ፣ ዜጎቻችንን ከባርነት አወጡልን፡፡ በየሄዱበት እስረኞችን እያስፈቱ፤ በሽተኛ እየጠየቁ ከኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ተጎዘጎዙበት። ባለፈው ከግብጽ እስረኞችን አስፈትተው በአንድ አውሮፕላን ተሳፍረው ሲመጡ ስንቱን በፍቅር አስለቀሱት መሰልዎት። ደስ ሊልዎት ይገባል፡፡ ውጭ የታሰረን እስረኛ [የፊጥኝ አስራችሁ ላኩልን] ጉርሻ እንሰጣችኋለን በሚባልበት ሀገር፤ እስረኞችን በጅምላ እንደ መልቀቅ ምን የሚያስደስት ነገር አለ፤ምንም። ይህ መሰል ሰናይ ምግባርዎት በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሞካሽተውና ተጨብጭቦልዎት የኖቤል [ተሸላሚ] እንደሚሆኑ ቅንጣት ታህል አልጠራጠርም፡፡
ኢትዮጵያ የ100 ሚሊዮን ህዝብ መገኛ፣ የጥቂቶች መኖሪያና መንደላቀቂያ ሆና፣ ለሁለት አስርት  ዓመታት ቆየች፡፡ ከሀገር ውስጥ አልፎ በውጭ ሀገር ስለ ወገናቸው ግፍ በሚጮሁት በእነ ታማኝ በየነ፣ በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ…….ላይ የሞት ፍርድ መፈረዱ ትያትር (ፊልም) ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሳስበው ብቻዬን ያስቀኛል፡፡ ይኼው ሁሉም አለፈና እነ ታማኝ፣ እነ ዶ/ር ብርሀኑና ሌሎችም ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲታገሉ ጥሪ ተደረገላቸው፡፡ የተከመረው የግፍ ክምር በእርስዎ የፍቅርና የይቅርታ ደማሚት ተንዶ እነሆ ወደ አዲስ ዓለም ተሸጋገርን፡፡  ከእስር ከተለቀቀው እስረኛ፣ ለጆሮ የሚዘገንን ሰቆቃ እየሰማን ቅዠት ሆኖብናል፡፡ ከቂሊንጦ እስከ ማዕከላዊ፤ ከባህር ዳር ኢሚግሬሽን እስከ ዝዋይ በኢትዮጵያውያን ላይ ያልተሰራ የግፍ ዓይነት የለም። በጠራራ ፀሐይ ላይ ከማሰር እስከ ጨለማ (በረዶ) ቤት ማጎር፤ እግርን በሚስማር ከመብሳት ጥርስን በፒንሳ እስከ ማውለቅ፤ ከኤሌክትሪክ ንዝረት ግርፋት እስከ ጥፍር መንቀል፤ ርቃንን ከመመርመር ብልት ላይ የኮዳ ውሃ በማንጠልጠል እስከ ማኮላሸት፤ ከአሰቃቂ ድብደባ እስከ ግድያ…..ኧረ ስንቱ! በኦሪት ዘፍጥረት 6፣6 “እግዚአብሄርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል፣ የሰው ክፋት በምድር ላይ ምን ያህል እንደበዛ ያሳያል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር፡- ታዲያ የወገኖቻችንን እግር በሚስማር የበሱ፤ ጥርሳቸውና ጥፍራቸውን በፒንሳ የነቀሉ፣ ብልታቸው ላይ የውሃ ኮዳ (ሀይላንድ) በማንጠልጠል የዘር ፍሬያቸውን ከጥቅም ወጭ በማድረግ ዘርን እንዳይተኩ ያደረጉ፤ ልብና ኩላሊታቸውን ያወጡ፤ እንዲሁ ነው የሚታለፉት ወይስ ተመጣጣኝ ቁንጥጫ ይቀምሳሉ? ኢትዮጵያዊያንን በጫካኔ በኤሌክትሪክ ንዝረት የገረፉ፣ ሽንት እንዲጠጡ ያደረጉ፤ ጨለማ ቤት ያጎሩ፤ ወፌ ላላ የገረፉ፤ እግርና እጃቸውን አስረው እንደ ብቅል ዘቅዝቀው ዥዋዥዌ መጫወቻ ያደረጉ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ  እንዲሁ ነው የሚታለፉት ወይስ ተመጣጣኝ ቁንጥጫ ይቀምሳሉ? በልማታዊ መንግስታችን ተደብድበውና ተገርፈው አካል ጉዳተኛ የሆኑ፣ የቆሰሉ፣ የአዕምሮ በሽተኛ የሆኑ፣ ሌላ አሰቃቂ ግፍ የደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያን ካሣ ይከፈላቸዋል ወይስ እንዲሁ ነው የሚታለፉት?
ጠቅላይ ሚኒስትር፡- ይህን ሁሉ ግፍ የፈጸሙ አረመኔዎች እንዲሁ ሊታለፉ ነው? ፖሊስ፣ ዳኛ፣ ደህንነት…ተብየዎችና ግብረ አበሮቻቸው በሐሞራቢ መርህ ዓይን ላጠፉ ዓይናቸው ይጥፋ  ባይባሉም ህጋዊ ቅጣት ሊቀምሱ ይገባል፡፡ ከአማራና ከኦሮሚያ በፌደራል ፖሊስ ታፍሶ የገባ እስረኛ ኦዲት ይደረግ፤ የተገረፉት ተገርፈዋል፤ የሞቱት ሞተዋል፤ ደብዛቸው የጠፋ መኖራቸው ወይም መሞታቸው ይረጋገጥልንማ።
የሚዲያ ነጻነት መኖሩን ያስተዋለው ኢቢሲ፤ እንደ ቢቢሲ ያን ሁሉ ስቃይ በነጻነት ዘገበው፡፡ ዴሞክራሲ በተለበጠ አምባገነንነት ታፍነው የቆዩት ጋዜጠኞች፣ የዘገባ ችሎታቸውን አሳይተው፣ ኢሳት ለምኔ አሰኝተው ዘገቡት፡፡ እንደ ኢቢሲ ህይወቴን ቀይርልኝ ተብሎ የሚጸለይበት ጊዜ ደረስን፡፡ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እንደ አልጀዚራ ስቃይ ያገነፋቸውን ዜጎች ከእነ ቁስላቸው አቅርቦ አሳየን፡፡ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) እንደ CNN ጉዱን አፍረጥርጦ አወጣው፡፡ ሌሎች የአገር ውስጥና የውጭ ሀገር የሚዲያ አውታሮችም ስቃዩን እየተቀባበሉ ዘገቡት፡፡ ገና ብዙ ጉድ ይወጣል፡፡
የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ፣ ባህርዳር ሰልፍ ላይ እንደተናገሩት፤ ከጅቦችና ከቁማርተኞች እንዲጠነቀቅ ለህዝቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አሁንም አዛኝ ቅቤ አንጓች እንዲሉ፣ እነሆ የበግ ለምድ ለብሰው፤ አዛኝ መስለው፤ አልያም እብድ መስለው ወደ ህዝቡ እየተሰገሰጉ ነው አሉ። አሁን ሳይት ቀይረዋል፤ ልዩ ድጋፍ ወደ ሚሹ ክልሎች (ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ሶማሊያ) ነው የትርምስ ዕቅዳቸው፡፡ ግጭት እየፈጸሙም  ይገኛሉ፡፡ [ህይወትና ንብረት] ሲያጠፉ የነበሩ ወንበዴዎች [የእጃቸውን ካላገኙ አይተኙም)። የእርስዎ ትዕግስት እኮ እንደ ፍራቻ ተቆጠረ። አሁን ወደ ህጋዊ  እርምጃ መግባት ያለብዎት ይመስለኛል። [ጥቂት ክፉ አሳቢዎች፤ አንደመርም ካሉ ሊቀነሱ ይገባል]፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር፡- ደብዳቤዬን ከመቋጨቴ በፊት አንዲት ቁምነገር ላንሳ፡፡ ሕገ መንግስቱ ፓርላማ ላይ ከቀረበ እግረ መንገድዎን የአንቀጽ 39ን ጉዳይ እንደሚያዩት እምነቴ ነው፡፡ እስከ መገንጠል የሚለው እስከ መዋሃድ በሚል ቢተካልንስ? እስከ መገንጠልን የሚያበረታታው [ኤርትራን ከጉያችን ያወጣው አንቀጽ 39] አሁንም ሳይገነጣጥለን ተገንጥሎ ቢወጣ ይሻላል። በሌላ ደብዳቤ እስክንገናኝ ክፉ አይንካዎት፡፡ ፈጣሪ አይለይዎት፡፡
ቸር ያሰማን!!

Read 2493 times