Saturday, 14 July 2018 12:12

የሚኒስትሮቹ ---- 100 ቀናትስ?

Written by  ከዳግላስ ጴጥሮስ
Rate this item
(6 votes)

የአንድን ሉዓላዊ ሀገር ዋልታና ወጋግራ አፅንተው ካቆሙት መልህቆች መካከል ሦስቱ በመሠረታዊነት ይጠቀሳሉ፡፡ በሦስቱ ውስጥ በርካታ ዘለላዎች ስለሚተነተኑ፣ ለጊዜው የሃሳቤን ሰንሰለት አንዘልዝዬ ለማራዘም አልሞክርም፡፡
ሠልስቱ መልህቆች የሚባሉት፤ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚውና ማኅበራዊው ሥርዓቶች ናቸው፡፡ ሉዓላዊ ሀገር ያሰኘንም የእነዚህ የሦስቱ መልህቆች ጥምረት ነው፡፡ የትናንቷ ጀምበር ጠቁራብን በነበረበት የአምና ካቻምና ዕለታት ግን ሦስቱ መልህቆች ከታሠሩባቸው ገመዶች ተላቀው፣ “እናት ዓለም ኢትዮጵያ” እንደምን በዐውሎ ነፋስ ወጀብ ልትደፈቅ ዳር ዳር እንዳለች የምናስታውሰው ነው፡፡
የፖለቲካው ገጽታ አስፈሪ ጭምብል ለብሶ እንዳትደርሱብኝ እያለ ብዙዎችን በማግለልና ጥቂቶችን ብብቱ ውስጥ በመሸጎጥ እሹሩሩ እያለ ሲያሞቃቸው ስለመኖሩ ምስክር አያሻውም፡፡ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ወገኖች፤ ወይ ለእስራት፣ ወይ ለስደት፣ አለያም ለመገፋት ስለሚዳረጉ የሕዝባችን አንደበት በዝምታ ነቅዞ ነበር፡፡ በአንፃሩ የፖለቲካውን የጨረቃ ፋኖስ የጨበጡት “ዘመንኛ ልሂቃን”  - “የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን” እያሉ ለውጥ እንደማይታሰብ፣ “በመቃብራቸው” ያስፈራሩን እንደነበርም አንዘነጋም፡፡
የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አኪርም እንዲሁ ተሰብስቦ ወደ “ኢምንት ልሂቃኑ” ኪስ ውስጥ ተከማችቶ ስለነበር እኛ ብዙኃንና ግፉዓን ዕጣችን፣ የበይ ተመልካች መሆን ብቻ ነበር፡፡ “የሀገራችንን የሁለት አሀዝ  የኢኮኖሚ ዕድገት” እያወደስንም “ተመስገን” በማለት የሁለት አሠርት ተኩል ዓመታትን እያጨበጨብን ማሳለፋችን አይዘነጋም፡፡ ሊዘነጋም አይችልም፡፡ ማስረጃ አምጡ ከተባለም የአንድ ሰሞን ሚሊዮን ነጋዴዎችን፣ የተንጣለሉ ሰፋፊ እርሻ ባለቤት ለመሆን በላብ ሳይሆን በመሳሳብ የገነኑትን፣ ለምድር ለሰማይ የከበዱ የባንክ ተበዳሪዎችን፣ “ለከተማችን ልዩ ውበት ያጎናፀፉ ሰማይ ጠቀስ ምንትሶችን” የገነቡልንን የአንድ ሌሊት ብሩካን መዘርዘሩ አይገድም፡፡
የጠቃቀስኳቸው ምስክሮች ለዋቢነት የማይበቁ መሆናቸው ለጥርጥር የሚዳርግ ከሆነም የፀረ ሙስና ተቋማችን፤ ያልተገለጡ ፋይሎች ይመርመሩልን ብለን አቤት እንላለን፡፡ የጓዳችን ባዶ ሌማት፣ በንዑስ ግራም ክብደት እየተመዘነች የምንገዛት የዕለት ዳቧችን፣ ፍትህ አጥተው ከገበያው ውድድር በካልቾ ተመትተው ቁስለኛ የሆኑ ነጋዴዎችን ታሪክ ብናዳምጥ ያፈጠጠውን እውነታ ለመረዳት አይከብድም፡፡
የማኅበራዊ ዕሴቶቻችን ሰንሰለትም ጭርሱኑ ባይበጣጠስም በቋንቋ፣ በብሔርና በጎጥ ዘውግ ተሸንሽኖ የተሸመንበት ውብ የአብሮ መኖራችን ጥበብ ሊጎድፍና ሊነትብ፣ የተቆራኘንባቸውና በቀላሉ የማይበጠሱ ክሮችም እየተጎለጎሉ ለአደጋ ሊዳርጉን መቃረባቸውን በተለያዩ አብነቶች ደግመንና ከልሰን እየተወያየንባቸው ስለሆነ፣ እኒህና እኒያ ነበሩ እያልኩ ለቀባሪው አላረዳም፡፡
ሀገራችን በእንዲህ ዓይነቱ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ የነውጥ ሱናሚ እየተላጋች በነበረችበት ወቅት ነበር ሕዝባችን ከዳር ዳር በአንድ ዜማ ሆ! እያለ በቁጣ ገንፍሎ የተነሳውና ራሱን ለትግሉ መስዋዕት አድርጎ ያሰለፈው። ከትግሉ ምጥ ውስጥም ጠቅላይ ሚኒስትራችንና መሰል የክፉ ቀን ታዳጊዎች ሊወለዱ የበቁት፡፡ የለውጡ ነፋስ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ፊት አውራሪነት እየተመራ፣ ፍሬውን ከግርዱ መለየት ከጀመረ እነሆ ድፍን አንድ መቶ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ አንድ መቶ ፍሬያማ ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ምን ያህል ሰዓታት በዕንቅልፍ እረፍት እንደወሰዱ ብንጠይቅ አይፈረድብንም፡፡ ፀሐይዋን በመለኮታዊ ተዓምራት እንዳቆመው እንደ ብሉያዊው ኢያሱ፣ ተፈጥሮ ከሃያ አራት ሰዓታት በላይ መርቃላቸው እንዳልሆነ ግን እርግጠኛ መሆን አይከብድም፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ በሀገር ውስጥ ከሕዝባቸው ጋር፤ ከሀገር ውጭ ከወዳጅ መንግሥታት ጋር ያከናወኗቸው ተግባራት ሁሉ ያለምንም እንከን ሰምሮላቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የቀዳሚ መሪዎቻችን እልህ የጋረደውን የብረት ቅጥር፣ በወንድማማች ሕዝቦች ሰማይ ላይ ጠቁሮ የከበደውን የግትርነት ደመና በፍቅር ገፈው፣ የኢትዮጵያዊያንንና የኤርትራዊያንን ልቦች ያስተቃቀፉበት ጥበብ በዓለም ታሪክ መዝገብ ውስጥ ሲዘከር የሚኖር ይመስለኛል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፈነጣጠቋቸው ተስፋዎችም፣ የነገይቱን ኢትዮጵያ ፊት የሚያፈኩ ስለመሆናቸው ጥርጥር አይገባንም፡፡
ታላቅ ሀገርንና ታላቅ ሕዝብን መምራት ቀርቶ ራስንና ቤተሰብን ለማስተዳደር እንኳ የክብደቱ ጫና የሌሎች ድጋፍን ለማግኘት የግድ ማለቱ አይቀርም። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽንቁር የበዛበትን ሀገራዊ ገመና ለመድፈንና የሕዝቡን የዕንባና የብሶት ምንጭ ለማድረቅ ላይ ታች ሲባዝኑ እያስተዋልን ባንደግፋቸው በግላቸው ምን ያህል ኃላፊነቱ እንደሚከብድባቸው፣ ውሎ አድሮም በጤንነታቸውና በስሜታቸው ላይ ሊያሳድርባቸው የሚችለውን የጉዳት መጠን መገመት አይከብድም፡፡ ድጋፍ ተነፍጓቸው አሯሯጮች የሚያጡ ከሆነም እርምጃቸውን ወደማይፈልጉት ሌላ አቅጣጫ ለማዞር መገደዳቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡
እስካሁን በተረዳነው መጠን ልክ ግን እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ፍቅርን መርሁ አድርጎ፣ የሰላም ርግብን በትከሻው ተሸክሞ፣ በይቅርታ መንፈስ ተሞልቶ የመደመርን ፍልስፍና እየሰበከ ሕዝቡን ከኋላ አስከትሎ የመራ መሪ፤ በታሪካችን ገበታ ላይ ብንፈልግ ልንቆርስ የምንችለውን ታሪክ ማግኘት ይከብድ ይመስለኛል፡፡ የተወረወረበት የቦንብ ጭስ ዓይንን መቆጥቆጡ ገና ሳይቀንስ ሕዝብን ከበቀል ተከላክሎ፣ አጥፊውን በፍቅር ያሸነፈ፣ የተሰበከው የይቅርታ ብስራት እንዳይደበዝዝ ተጠንቅቆ፤ የዛሬን ጥቃት ሳይሆን የነገውን በረከት እንመልከት፤ ያለ መሪ በርግጥም ታሪካችን አስተናግዶ ያውቅ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
በሦስት ወራት ውስጥ የአጥናፈ ዓለሙን ሕዝብና የሀገር መሪዎችን ቀልብ በመሳብ እንደ ኮከብ የደመቀና በአጭር የሥልጣን ወራት ዕድሜ ስላከናወናቸው ግዙፍ ተግባራት ተጽዕኖ ፈጣሪ የምድራችንን ሚዲያዎች ሳይቀር ያስጨበጨበ መሪ ዓለማችን አግኝታ ነበር ስለመባሉም አልሰማሁም፡፡ ለማንኛውም ይህን መሰሉ የመሪያችን ውጤታማ እርምጃ እንዳይገታ ዜጎች ሁሉ እጅ ለእጅ በመያያዝ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጎን መቆም እንደሚገባን እያሳሰብኩ ወደ ሌላኛው ሃሳቤ እሸጋገራለሁ፡፡ የሀገራችን ንብርብር የችግር አለት ጥንካሬውም ሆነ ስፋቱ የትዬለሌ ከመሆኑ የተነሳ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሌትና የቀን ትጋት ብቻ የሚፈለገው ውጤት ይገኛል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ ሚኒስቴር መ/ቤቶችንና የተለያዩ ተቋማትን የሚመሩ የካቢኔ አባላትና የሥራ ኃላፊዎች በየወንበሮቹ ላይ በኃላፊነት ተሹመው እንደከበቧቸው እናውቃለን፡፡ ጥያቄው የሹመት ወንበሮቹ በተቀማጭ ሹማምንቶች መሞላቱ ላይ ሳይሆን ባለሥልጣናቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እኩል እየሮጡ፣ እየሰሩ፣ እየለወጡና እየተለወጡ ነው ወይ የሚል ነው፡፡
የአንድ መቶ ቀናትን የስልጣን ዕድሜ መገምገም ከሰለጠኑት ሀገራት መወሳችንን ሳልዘነጋና የግምገማው አካሄድ ከእኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እንደምን አብሮ ሊጎዳኝ ቻለ? የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው ወደ ጎን ትቼና በግምገማው ላይ ተስማምቼ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ እጠይቃለሁ፡፡
ከሙያና ከብቃት ይልቅ ሹመት በብሔር ዘውግና በፖለቲካ ወገንተኝነት መሆኑ ዛሬም ድረስ ተጣብቆን አልላቀቅ ያለን ክፉ ደዌ ይመስለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም በተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ፊት ቀርበው ስለ ሾሟቸው ሚኒስትሮችና ባለሥልጣናት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት “ክልሎች/በፖለቲካ ድርጅታቸው በኩል ለሹመት ዕጩ አድርገው ያቀረቧቸውን ሰዎች በሙሉ መድበናል”  የሚለው የመጀመሪያ ቀን ንግግራቸው ትንሽ ጎርብጦኝ ነበር፡፡ ይህንን ባያደርጉ ሊገጥማቸው የሚችለውን ተግዳሮት ባልዘነጋውም ከውጤቱ አንፃር ግን በዜግነት መብቴ ማዘኔ አልቀረም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቶ ቀናት ምን ሰሩ እየተባለ በየሚዲያዎቹ ከሚተነተነው ሀተታ ባልተናነሰ መልኩ እያንዳንዱ ሚኒስትርና በየእርከኑ ሥልጣን የያዘው የመንግሥት  የሥራ ኃላፊ በመቶ ቀናት ውስጥ ምን ሠራ፣ ምንስ አልሠራም ተብሎ መፈተሽ ነበረበት፡፡
“በዚህ ወንበር ላይ የተሾምኩት በመንግሥት ፈቃድ ስለሆነ እንጂ እኔ ለተሾምኩበት ዘርፍ ምንም ዕውቀትም አቅምም የለኝም” እያለ በድፍረት የሚናገር ሚኒስትር፤ በሹመት ወንበሩ ላይ ተደላድሎ እንዲቀመጥ ተመርቆለታል፡፡ ይህ ሁኔታ በአንድ ወቅት “እከሌን የሾምነው የኢህአዴግን ተልዕኮ እንዲያሳካ እንጂ . . . አይደለም፡፡ የድርጅታችንን ተልእኮ እስካሳካ ድረስ አቅም ይኑረው አይኑረው ሌላ ጉዳይ ነው፡፡” የሚለውን አባባል ያስታውሰኛል፡፡
ተናግሮ የማሳመን፣ ተከራክሮ የመርታት፣ አግባብቶ የማቀራረብ፣ ሀገር ሲወክል የሚያምርበት፣ ትምህርቱ፣ ዝግጅቱም ሆነ ልምዱ ወይንም ካሪዝማው እንዲሉ . . . ከምኑም ውስጥ የሌሉበት ሰዎች የፖለቲካውን ምርኩዝ በመጨበጣቸው ብቻ ወንበር የተሰጣቸው ምን ያህል ሚኒስትሮች፣ ምን ያህል አምባሳደሮችና ሹማምንት እንዳሉን ተቋማት ይፍረዱ፡፡ ይህም አነሰ ተብሎ አንድን “ሚኒስትር ወይንም ሹም” ሀገር ሌሎች ልጆችን ያልወለደች ይመስል የአስርና የሃያ ቦርድ ሰብሳቢዎችና አባላት ማድረግ ያፈጠጠ የሀገራችን አውነታ ነው፡፡ “ምን ይደረግ፤ በዚህ በዚህ እንኳ ተደገፉ ተብለን ነው” ያሉኝን ባለ አሥራ ሦስት ኮሚቴና ቦርድ አባል ሹም ምንግዜም አልረሳም፡፡
እኒህን መሰል የካቢኔ አባላት፣ የመንግሥት ሹመኞችና በየሀገሩ የተላኩት አንዳንድ የሚሲዮን ተወካዮች እንኳን የመቶ ቀናት፣ የመቶ ዓመት ዕድል ቢሰጣቸውም ራሳቸውን ከፈጣኑ ለውጥ ጋር አስተካክለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እኩል ይሮጣሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ገና ለገና የፖለቲካውን ምህዳር ሙሉ ለሙሉ ገዝቼዋለሁ በሚል ፍልስፍና ግንባር የፈጠሩት ድርጅቶች ይሞግቱኛል ተብሎ ያለ በቂ አቅምና ልምድ አንጠራርቶ ከሥልጣን ሰማይ ላይ መስቀል ዕዳው ለሀገር እንደሚተርፍ የሚጠፋን አይመስለኝም፡፡ የዕዳውን ጫና የሚያከብደው የብቃት ማነስ ብቻ ሳይሆን “ሲሾም ያልበላ . . .” ወደ ሚል አዘቅትም ሊከት እንደሚችል ማሰቡ አይከፋም፡፡
“የሀገራችንን ውስብስብ ችግር ያለማወቅ ብዙ ያናግራል” ባዮች እንደማይጠፉ አይጠፋኝም። ይህ ድፍረት የተሞላበት እውነታም አንዳንዶቹን እንደሚያስቃቸውና እንደሚያበሳጫቸው ይገባኛል፡፡ ምላሼ ሀገር የምትሞተው እንደነዚህ ዓይነት ሹማምንት ያለ ቦታቸውና ያለ ብቃታቸው ሲቀመጡ ነው፤ ይህንን እንድጽፍ ድፍረት የሰጠኝም የዜግነት መብቴ ነው በማለት እከራከራለሁ፡፡
በድምፃችን የመረጥናቸውም ይሁኑ በራሳቸው ድምፅ የተመረጡና በየደረጃው ያሉ የሕዝብ ተወካዮችም ቢሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍጥነት ሩጫ ሊያባንናቸው ይገባል፡፡ “እኔ በመጣሁበት አካባቢ ስለተፈጠረው ችግር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ይላሉ?” የሚለው አስቂኝ የወንበረተኞች ጥያቄም ሊደመጥ አይገባውም፡፡ መልሱ ወደተመረጥክብት ክልል ሄደህ፣ ከመረጠህ ሕዝብ ጋር ተደማምጠህ፣ ችግሩን ፍታ ሊሆን ይገባል፡፡
መቼም “የሕዝብ ውክልና አለው” የሚባልን አንድ ሰው የማክበሩ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ወንበረተኞቹ ለስብሰባ በሚቀመጡባቸው ጠረጴዛዎች ላይ “የተከበሩ” በሚል ቅፅል እየተጎላመሰ የሚደረደረው የስም ሰሌዳ ይዘቱም ሆነ ግዝፈቱ ሁሌም ፈገግ ያስደርገኛል፡፡ ያውም ፊታቸውን በሚሸፍን መጠን። መከበራቸውን በሥራ ቢያሳዩን እነርሱ ለራሳቸው ከሚፅፉት በተሻለ እኛ አድምቀን እንጽፍላቸው ነበር፡፡
ሃሳቤን የማጠቃልለው ያነሳኋቸውን ነጥቦች በማስታወስ ነው፡፡ አንደኛ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባላትም ሆኑ ሌሎች ሹመኞች ከመሪያቸው ተምረው ፍጥነት ይጨምሩ፡፡
የአቅም ውሱንነት ያለባቸውም ራሳቸውን ከኃላፊነት አግልለው ዝቅ ለማለት የሞራል ልዕልናን ይላበሱ፡፡ ሁለተኛ፤ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ መቀመጥ ማለት ከሕዝብ በላይ ከፍ ማለት፣ ራስን የተከበሩ እያሉ መሸንገል፣ ለራስም ሆነ ለቤተሰብ ለአገልግሎት የሚጠቀሙበትን መኪና በጥቁር መጋረጃ ሸፍኖ ከጀማው መሃል ወጥቶ ባይተዋር መሆን አይደለም፡፡ ሲከፋም በቢሮ ደጃፍ ላይ በረኛ አቁሞ መገፋተር አይደለም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትህትና፣ ለሕዝባቸው የሚያሳዩት ፍቅር፣ የሥራ ትጋታቸው፣ በሁሉም የዕውቀት ዘርፍ ራሳቸውን የማብቃት ተሰጥኦዋቸው፣ በራስ የመተማመን አቅማቸውና የሚማርከው ንግግራቸውን እንደ አብነት ወስዶ ከሩጫው ፍጥነት ጋር ራስን ማላመዱ ግድ ይላል፡፡

Read 5510 times