Saturday, 14 July 2018 12:15

የ21ኛው ዓለም ዋንጫ ፍፃሜ

Written by  ግሩም ሠይፉ (ከሞስኮ)
Rate this item
(1 Vote)

 ‹‹በእግር ኳስ ደረጃው፤ በመስተንግዶ ብቃትና ጥራት…የምንግዜም ምርጥ ነበር›› ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የፊፋ ፕሬዝዳንት
ራሽያ ያስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ ከክሮሽያ በሚያደርጉት የዋንጫ ጨዋታ በሞስኮ ከተማ በሚገኘው ሉዚንሂኪ ስታድዬም ይፈፀማል፡፡ የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ  በሉዚሂንኪ ስታድዬም ከፍፃሜው በፊት በሰጡት መግለፃ ፍፃሜውን በጣም የተለየ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ የክሮሽያ ለፍፃሜ መብቃት የዓለም እግር ኳስ ላይ ተስፋ የሚፈጥር ወደፊትም በሚካሄዱ የዓለም ዋንጫዎች የሚሳተፉ ብሄራዊ ቡድኖችን የሚያነቃቃ ብለውታል፡፡
‹‹ዓለም ዋንጫው ራሽያን ቀይሯታል፡ እግር ኳስ በአገሪቱ እንዲስፋፋ ምክንያት እንደሆነ ትረዳላችሁ፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ ብቃት፤ የስፖርት መሰረተልማቶቹ በአገሪቱ እግር በኳስ እንዲቀጥል ያደርጋሉ ፡፡ ዓለም ለራሽያ የሚሰጠውን መጥፎ ግምት ዓለም ዋንጫው ቀይሮታል፡፡  እንግዳ ተቀባይና ውብ አገር መሆኗን፤ ዓለም አቀፋዊ ባህሏን ታሪኳን እና አስተዋፅኦዋን ያስመሰከረም ነው፡፡›› በማለት ጂያኒ ኢንፋንትኖ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ ዓለም ዋንጫው አስደናቂ፤ የማይታመንና አስገራሚ የዓለም ዋንጫ ነበር። ላለፉት ሁለት ዓመታት የዓለም ዋንጫው የምንግዜም ምርጥ ስል ነበር፡፡ ባለፈው 1 ወር ይህ በተግባር ተረጋግጧል፡፡ 21ኛው የዓለም ዋንጫ የምንግዜም ምርጥ ነው፡፡ ራሽያ በመላው ልትመሰገን ይገባል፡፡ በማለትም ጂያኖ ኢንፋ ንቲኖ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በጎ ፈቃደኞች የዓለም ዋንጫው ፈገግታ እና ብሩህ ገፅታ ነበሩ አመሰግናቸዋለሁ ያሉት ኢንፋንቲኖ መግለጫውን የሰጡትም የበጎፈቃደኞችን ቱታ ለብሰው ነበር፡፡
ከአዲስ አድማስ ለጂያን ኢንፋንቲኖ ጥያቄ የቀረበላቸው ይህን የዓለም ዋንጫ የምንግዜም ምርጥ ያሉበትን ምክንያት እንዲያብራሩ ሲሆን ስታድዬሞች 99 በመቶ መሙላታቸው፤ ጨዋታዎችን ያስተናገዱ ስታድዬሞች የጥራት ደረጃ እና ኦፕሬሽን፤ የቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭቶች በመላው ዓለም ከ3.2  ቢሊዮን ተመልካች ማግኘታቸው፤የዓለም ዋንጫውን ለመከታተል ከ1 ሚሊዮን በላይ እግር ኳስ አፍቃሪዎች ራሽያ መግባታቸው  የመስተንግዶውን ስኬታማነት ያሳያል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከፍፃሜው በፊት የተካሄዱትን 62  ጨዋታዎችን በስታድዬም የተከታተላቸው ተመልካች ብዛት ከ2.9 ሚሊዮን በላይ ሲሆን ከ16ሺ በላይ የዓለም ሚዲያዎች በራሽያ በመገኘት በተለያዩ የሚዲያ አውታሮቻቸው እየዘገቡት ቆይተዋል፡፡ከ1.7  ሚሊዮን በላይ የደጋፊ መታወቂያዎች መታደላቸውን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን የፊፋን ኦፊሴላዊ ድረገፅ እና የተለያዩ አፕሊኬሽኖች ከ180 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ሲያስተናግዱ በፊፋ ፋን ፌስት ወይም የደጋፊዎች አደባባይ ጨዋታዎች እየተከታተሉ የተዝናኑ ከ7 ሚሊዮን በላይ ናቸው፡፡
የፊፋ ቴክኒካል ጥናት ግሩፕ ከፍፃሜው በፊት በሰጠው መግለጫ የዓለም ዋንጫው  በራሽያ ስታድዬሞች እና ሜዳዎቻቸው ዘመናዊነት ያማረ፤ በስታድዬም ተመልካች የደመቀ፤ በቡድኖች ተመጣጣኝ የፉክክር ደረጃ የታየበት፤ በወጣቶች እግር ኳስ ላይ የሰሩ አገራት ውጤታማ የሆኑበት፤ በየብሄራዊ ቡድኑ ምርጥ በረኞች የነበሩበት በአጠቃላይ በብዙ መልኩ ስኬታማ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የቴክኒካል ጥናት ግሩፑ ሰብሳቢ ብራዚላዊው ካርሎስ አልቤርቶ ፔሬራ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደገለፁት ራሽያ ዓለም ዋንጫውን በግዙፍ ምድሯ ላይ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ከፊፋ ጋር በቅንጅት መስራቷን አድንቀው፤ በዓለም ዋንጫው ከታዩ አዲስ ነገሮች የቪድዮ ቴክኖሎጂ ዳኝነት መሆኑን በመጥቀስ ሚዛናዊ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ያገዘ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የፊፋ የቴክኒክ ዴቨሎፕመንት ሃላፊ ሆኖ የሚያገለግለው ማርኮ ቫንባስተን የዓለም ዋንጫው በፉክክር ደረጃው የሚማርክ እንደነበር አውስቶ በአጠቃላይ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ የጥናት ግሩፑ የሰራው ሪፖርት በመስከረም ወር ሲሰራጭ መላው የእግር ኳስ ዓለም ብዙ ተመክሮዎች የሚያገኝበት ነው ብሏል፡፡ የዓለም ዋንጫን ተወዳጅ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች አንዱ እንደ ክሮሽያ አይነት በጣም ትንሽ አገር ለፍፃሜ መድረስ መቻሉ ነው ያለው ቫንባስተን የፈረንሳይ ቡድን በወጣቶች በተገነባ ስብስቡ ለዋንጫው መሰለፉ ማራኪ ፍፃሜ የምናይበትን እድል ፈጥሯል ሲል ተናግሯል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ከአዲስ አድማስ በቀረቡ ሁለት በጥያቄዎች ላይ የጥናት ቡድኑ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ አፍሪካዊ ቡድኖች በዓለም ዋንጫው በግዜ መሰናበታቸውን በመጥቀስ ምናልባትም አፍሪካዊ አሰልጣኞች በየአገራቸው የሚሰሩበት ሁኔታ ቢፈጠር ውጤት ይሻሻል ይሆን ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጠው ናይጄርያዊው ኢማኑዌል አሙኒኬ ነው፡፡ ለማንኛውም የአፍሪካ ቡድን ውጤታማነት አፍሪካዊ ወይንም የውጭ አገር አሰልጣኝ መስራቱ  ምንም ልዩነት የለውም ያለው አሙኒኬ፤ አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ በወጣቶች ላይ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት፤ አሰልጣዖች ያለቸውን እውቀት ተጠቅመው እንዲሰሩ በእግር ኳሱ አስተዳደር ሙሉ ድጋፍ እንዲኖራቸው፤ በአጠቃላይ ህልምን እውን ለማድረግ በከፍተኛ ትጋት እና ትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድቷል፡፡ ከአዲስ አድማስ ለቴክኒካል ጥናት ቡድኑ የቀረበው ሁለተኛው ጥያቄ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ በየብሄራዊ ቡድኑ ምርጥ ብቃት ስላሳዩ በረኞች የነበረ ሲሆን የፊፋ የግብጠባቂዎች ኤክስፐርት ቡድን ሰብሳቢ የሆነው ስዊዘርላንዳዊው የቀድሞ በረኛ ፓስካል ምላሽ ሰጠቶበታል፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ በረኞች እስከ ዋንጫው ጨዋታ ድረስ ወሳኝ ሚና ነበራቸው የሚለው ፓስካል ግብ ጠባቂዎች የቡድኖቻቸውን አጨዋወት በመወሰን፤ የቡድኖቻቸውን ቴክኒክ እና ታክቲክ በሜዳ ላይ በመተግበር ጉልህ ሚና በመጫወት፤ በጥሎ ማለፍ የቡድናቸውን ውጤት በሚያግዙ ብቃቶች በመስራት አስደናቂ ደረጃ መድረሳቸውን አስመስከረዋል ብሏል፡፡ የፊፋ የጥናት ግሩፕ የ21ኛው ዓለም ዋንጫ አጠቃላይ የግምገማ ሪፖርት ከማቅረቡም በላይ በፍፃሜው በተለያዩ ዘርፎች ኮከብ ሆነው የሚሸለሙትን አሸናፊዎችም የሚመርጥ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በእያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ በዋናነት ስድስት ልዩ  ልዩ ሽልማቶችን በተለያዩ ዘርፎች ለሚመረጡ ተጨዋቾች እና ቡድኖች ያበረክታል፡፡  ለምርጥ በረኛ የወርቅ ጓንት፤ ለኮከብ ግብ አግቢ የወርቅ ጫማና ለኮከብ ተጨዋች የወርቅ ኳስ መሸለሙ በፍፃሜው ቀን ከፍተኛ ትኩረት የሚስብ ነው፡፡  በዓለም ዋንጫ አብይ ስፖንሰርነት የሚታወቀው አዲዳስ የወርቅ ኳስ እና የወርቅ ጫማ ሽልማቶችን በኩባንያው ስም ያበረክታል፡፡ በሶስቱም ሽልማቶች በተጨማሪ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ለሚያገኙት ተጨዋቾች የብር እና የነሐስ  ሽልማቶች ይሰጣሉ፡፡ በዓለም ዋንጫ በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ ሌሎች ሶስት የክብር ሽልማቶችም አሉ፡፡ የዓለም ዋንጫ ምርጥ ተጨዋች፤ የዓለም ዋንጫው ምርጥ ስፖርታዊ ጨዋነት እና የዓለም ዋንጫው ምርጥ ቡድን የሚሸለሙባቸው ናቸው። የዓለም ዋንጫ ምርጥ ወጣት ተጨዋች ምርጫ ለመጀመርያ ጊዜ የተካሄደው በ1958 እኤአ ቢሆንም በደንበኛ ትኩረት መሸለም የተጀመረው በ2006 እኤአ ላይ ጀርመን ባዘጋጀችው 18ኛው የዓለም ዋንጫ ሲሆን የጀርመኑ ሉካስ ፖዶልስኪ ቀዳሚው ተሸላሚ ነበር፡፡ የዚህ ሽልማት ስፖንሰር የመኪና አምራቹ ሃዩንዳይ ኩባንያ ነው፡፡  የዓለም ዋንጫው የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊን መሸለም የተጀመረው በ1970 እኤአ ላይ ነው፡፡ ከ4 ዓመት በፊት የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማቱን የወሰደው ሻምፒዮኑ የስፔን ብሄራዊ ቡድን ነበር፡፡ የዓለም ዋንጫው ምርጥ ቡድን ደግሞ ከ1994 እኤአ ወዲህ ሲሸለም ቆይቷል፡፡
በ21ኛው ዓለም ዋንጫ ከፍፃሜው በፊት በተደረጉ 62 ጨዋታዎች 161 ጎሎች ተመዝግበዋል። በየጨዋታው በአማካይ 2.6 ጎል እየገባ ነው፡፡ የኮከብ ግብ አግቢነቱን የሚመራው b6 ጎሎች የእንግሊዙ ሃሪ ኬን ሲሆን የቤልጅዬሙ ሮሜን ሉካኩ፤ የፖርቱጋሉ ክርስትያኖ ሮናልዶ እና የራሽያው ዴኒስ ቼይቼቭ በ4 ጎሎች ይከተሉታል። በዓለም ዋንጫው ኮከብ ግብ አግቢነት ለወርቅ ጫማ ሽልማት የሚበቃው ተጨዋች በጎሎቹ ብዛት የሚመረጥ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ የጎል ብዛት የሚጨርሱ ተጨዋቾች ከአንድ በላይ ከሆኑ ደግሞ አሸናፊው የሚለየው ለጎል የበቁ ኳሶችን በብዛት ማን አቀብሏል ተብሎ ነው። በግብ ብዛትና ለጎል የበቁ ኳሶችን በማቀበል እኩል የሆኑ ተጨዋቾች ከሁለት በላይ ከሆኑ ደግሞ አሸናፊነቱ አነስተኛ ደቂቃዎች ተሰልፎ ብዙ ላገባው ተጨዋች የሚሰጥ ይሆናል። የወርቅ ጫማ አሸናፊ ሽልማት በሁሉም ዓለም ዋንጫዎች ሲሸለም የቆየ ነው፡፡
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ትኩረት ከሚስቡ የኮከብነት ሽልማት ሌላኛው ምርጥ ብቃት ላሳዩት በረኞች ነው፡፡ የፊፋ ቴክኒክ ቡድን የዓለም ዋንጫውን ኮከብ በረኛ በውድድሩ ላይ ባሳየው አጠቃላይ ብቃት መሰረት መርጦ ለሽልማት ያበቃዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ ምርጥ በረኛ ከ1994 እኤአ ወዲህ በታዋቂው ራሽያዊ ግብ ጠባቂ ሌቭ ያሺን መታሰቢያነት የሚሸለም ነበር፡፡ ከ2010 እኤአ በኋላ ግን የወርቅ ጓንት ሽልማት ተብሎ ለአሸናፊው መበርከት ጀምሯል፡፡

Read 4760 times