Sunday, 15 July 2018 00:00

ከብርጭቆው ጋር ያመለጠኝ ሃሳብ - (ምናባዊ ወግ)

Written by  ሌ.ግ.
Rate this item
(2 votes)

ብርጭቆው ቂጡ ስር ትንሽ ጂን አለ፡፡ በጥንቃቄ የምጠጣበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁኝ፡፡ አለም ሁሉ ተደምስሶ ቢፋቅ ጉዳዬ አይደለም፡፡ እቺ ጭላጭ ስታልቅ አለም ተመልሶ ይመጣል፡፡ ግን አሁን አይገደኝም፡፡ ሀሳብ እያሰብኩ የምጠጣው እስከ ብርጭቆው ግማሽ ድረስ ነው፡፡ ብርጭቆው ግማሽ ሙሉ ሲሆን አስብ የነበረው ሀሳብ ጨለምተኛ ይሆናል፡፡ ሙሉ የሚጨልምብኝ ብርጭቆው ባዶ ሲሆን ነው፡፡
አእምሮዬ በተለምዶ ያውቃል፤ ብርጭቆው ወደ ቂጡ አካባቢ ሲደርስ ማሰብ አቆማለሁ፡፡ ሌላ ቦታ አላስተውልም፡፡ ከብርጭቆው በስተቀር፡፡ በስንት መከራ የተገኘች አንድ ብርጭቆ ጂን ናት፤ ማንም ጨምሮ አይቀዳልኝም፡፡ እንዲቀዳልኝም አልፈልግም፡፡
በደንብ ነው የያዝኩት፡፡ በደንብ ስለጨበጥኩት ሳይሆን አይቀርም … እጄ ተንቀጠቀጠ፡፡ ልክ እንደ ሳሙና አሟለጨኝ፡፡ ሲያሟልጨኝ፤ ብርጭቆውን ለመቅለብ ስንደፋደፍ ብርጭቆው ውስጥ ያለውም ጭላጭ አመለጠኝ፡፡ ብርጭቆው አየር ላይ እንዳለ “Pause” ማድረግ እችል ነበር … ግን ሪሞት ኮንትሮሉ ሌላ ቦታ ነው ያለው፡፡ ልክ ስቅቅ ብዬ ትንፋሼን ስሰበስብ … ስሸማቀቅ አንድ አጭር ልብ ወለድ መጣልኝ፡፡
ከምሽቱ 3፡00 አንድ ብርጭቆ ጂን ተቀዳልኝ፡፡ ወደ ለአራት እሩብ ጉዳይ ሲሆን እሩብ ጉዳይ ጂን በብርጭቆው ውስጥ ነበር፡፡፡ እዚህ ገደማ ነበር ስቅቅ ያልኩት፡፡ ስሳቀቅ ብርጭቆው ያምልጠኝ … ወይም በማምለጡ ልሳቀቅ ትዝ አይለኝም፡፡ ግን እዚህ ገደማ ነው አጭር ልብ ወለዱ ብልጭ ያለው፡፡ ብርጭቆውን አየር ላይ ለመቅለብ በምንደፋደፍበት ቅፅበት፡፡
አንድ ቄስ ነበር፡፡ በአንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ፡፡ በመንደሯ ገበሬዎች ይኖራሉ፡፡
የመንደሩ ነዋሪዎች ቄሱን ይወዱታል፡፡ ወይም ያዝኑለታል፡፡ ውለታ አድርጎላቸዋል። ውለታ መመለስ ይፈልጋሉ፡፡
ከመኸር በኋላ እህል ሸጠው ሲያተርፉ ትንሽ እንደ አቅማቸው አዋጥተው ወደ ከተማ ለህክምና ቄሱን ላኩት፡፡ ቄሱ ፊቱ ከውልደቱ ጀምሮ ጠማማ ነው፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች ይወዱታል፡፡ የሚወዱት ስለሚያሳዝናቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ውለታ ውሎላቸዋል፡፡ ውለታው ሚስኪንነቱ ነው፡፡ በዓለም እና ህይወት እንዲያዝኑ ያደርጋቸዋል፡፡
ባዋጡለት ገንዘብ ሀኪም ዘንድ ሄዶ የተጣመመውን መንጋጋውን አስተካክሎ ተመለሰ፡፡ ሲመለስ ከመንጋጋው መስተካከል ጋር ሌላ የተስተካከሉ ነገሮች ነበሩት። የመንደሩ ልጃገረዶች፤ “መነኩሴው ለካ ቆንጆ ሰው ኖሯል?!... በፊት አይኑ እንደዚህ እንደሚያምር አናቅም ነበር … ከንፈሩም ወደ ቦታው ሲመለስ ውብ ሆነ … በፊት አገጩ በቦታው አለመኖሩ ነው አስፈሪ ያደረገው … አሁን አገጩ ወንዳወንድ አስመሰለው። … ኮስታራ መሆኑም ያምርበታል፡፡ ጀግና መሰለ” አሉ፡፡
ቄሱ ሲመለስ ሚስኪን አልነበረም፡፡ አሁንም የመንደሩ ሰዎች ይወዱታል፡፡ ግን የሚወዱት በተለይ ሴቶች ሆኑ፡፡ አባቶች በሴት ልጆቻቸው፣ ባሎች በሚስቶቻቸው ይጠረጥሩት ጀመር፡፡ ምስኪን! እንደ ድሮው አለመምሰሉ ብቻ ለመጠርጠር በቂ ነበር፡፡
ቄሱ ሴቶቹ እንደሚመለከቱት አይቶ፣ የራሱን መልክ ከመፅሐፍ ቅዱስ በበለጠ መመልከት (በድብቅ) አዘወተረ፡፡ ሴቶቹ በሚወዱት አንፃር ራሱን እና እነሱን መልሶ መውደድ ጀመረ፡፡
ሚስት ማግባት እንደሚፈልግም ተረዳ፡፡
ሚስት አጨ፡፡ የመንደሩ ገበሬ በቄሱ ተበሳጨ፡፡
ቄሱ ከቄስነት ባሻገር መሬት ማረስ እንደሚፈልግ አሰበ፡፡ ሚስቱ ልጅ ስትወልድለት በቄስነት ብቻ ኑሮን መምራት እንደማያዋጣ አስታወሰችው፡፡
ቄሱ ሁለተኛ ልጅ ሲደግም ሙሉ ለሙሉ ገበሬ ሆነ፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች የሚያዝኑለት፣ የሚወዱትና ልጃገረዶቻቸውን ቀና ብሎ የማያይባቸው ምስኪን እና የሆነ አካሉ ለዚህ በሚረዳው መልክ የጎደለ አዲስ ወጣት ቄስ በቀድሞው ምትክ አስመጡ፡፡
***
ብርጭቆው መሬት ላይ ወድቆ ሲሰባበር … ለቅፅበት ብልጭ ብሎብኝ የነበረው ልብ ወለድ ጠፋብኝ፡፡ ብርጭቆው እንደ ውሃ በእየአቅጣጫው ነው የተረጨው፤ ስብርባሪው፡፡ በውስጡ የነበረው ጭላጭ ጂን ግን መሬቱ ላይ ሳይበታተን አንድ ቦታ ቁልል ብሎ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ደስ አለኝ። ብርጭቆ በመሰረቱ አስፈላጊ ነገር አይደለም፡፡ መያዣ ነው፡፡ የጂኑን ጭላጭ መያዝ የነበረበት ብርጭቆ አገልግሎቱን በመሰበር ክዷል፡፡ አሁን ደግሞ ወለሉ ኃላፊነቱን ተረክቦ ይዞታል፡፡
መሬት የተቆለለውን ጭላጭ አጠናሁት። አሁን ክፍሉ ብርጭቆ ሆኗል፡፡ እኔም ጭለጩ ጂንም አንድ ብርጭቆ ውስጥ ነን፡፡ ክፍሉ ውስጥ። ይሄ ሀሳብ ደስ አለኝ፡፡ መሬቱ ላይ ተጋድሜ እንደ ውሻ የፈሰሰውን ጭላጭ ልልሰው ፈለኩ፡፡ ግን ተፀየፍኩት፡፡ ስለማይመችም፣ ራሴን ለማክበር ስለፈለግሁም አይደለም፡፡ ሌላ ሰው ክፍሉ ውስጥ የለም፡፡ ሌላ ሰው ካላየኝ ራሴን ማክበር ወይንም መቆለል አያስፈልግም፡፡ ብርጭቆ ውስጥ ነኝ። የብርጭቆው መጠን አለምን ያህል ቢሰፋም ጭላጯ ግን ያው ናት፤ አላደገችም፡፡ በትንሹ ብርጭቆ ውስጥ እያለች ለአያያዝ ትመች ነበር፡፡ አሁን ለመጠጣትም አትመችም፡፡ ግን ባትመችም አልተዋትም፡፡ አለም ሳትመቸኝ እየኖርኳት አይደለ?
ወለሉ ፈሳሽ የሚመጥ አይነት አይደለም፡፡ የሴራሚክ ወለል ነው፡፡ መስታወት ማለት ነው። ብርጭቆ ነው፡፡ የፈሰሰን ማፈስ ባይቻል እንኳን መምጠጥ ይቻላል አልኩኝ፡፡ የእስክሪፕቶ ቀሰም ማለት ነው፡፡ እኔ ያልኩትን ይሆናል፡፡ ቀስ ብዬ መጠጥኩት፡፡ ጂኑን፡፡ ጣዕሙ ግን አፌ ውስጥ ቀድሞ ሰፍኖ ከተዋሃደው የጣዕም status quo ጋር አልተስማማም፡፡ ሀክ እንትፍ ብዬ መታጠቢያ ገብቼ ተፋሁት፡፡ የበለጠ ለመትፋት ስሞክር ቀድሞ የጠጣሁት በጠቅላላ እየተንኮሻኮሸና ጉሮሮዬን በስብርባሪው እየቧጠጠ እያደማ ወጣ።
ሁሉንም ነገር ከሰርኩኝ፡፡ ብርጭቆው ሲያመልጠኝ ትዝ ያለኝ ብልጭታ አጭር ልብ ወለድ ካስመለስኩም በኋላ ትዝታው አልተመለሰልኝም። … አንድ ጥሩ ብልጭታ ተከስቶ እንደነበር ብቻ ትዝ ይለኛል፡፡
ከብልጭታው በስተቀር ትዝታ የለም፡፡ እሳት አልተያያዘም፡፡ በደንብ የተያያዘው እሳት ደረቴ ላይ በማስመለሴ ምክኒያት እየፋቀ የሚያቃጥለኝ ስሜት ብቻ ነው፡፡

Read 1110 times