Saturday, 21 July 2018 12:31

“የደህንነት አባላት የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አይችሉም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   ሰማያዊ ፓርቲ ሂደቱን በፅኑ እደግፋለሁ ብሏል

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተቋምን ከፖለቲካ ውግንና ነፃ ለማድረግ አዲሱ የተቋሙ ኃላፊ ጀነራል አደም መሃመድ የጀመሩት እንቅስቃሴ የሚደገፍ መሆኑን ሰማያዊ ፓርቲ የገለፀ ሲሆን የቀድሞ የአየር ኃይል አዛዥ ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት በበኩላቸው፤ ጉዳዩ ከህግ አንፃር መፈተሽ አለበት ብለዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች ከፓርቲ አባልነት መውጣት አሊያም ተቋሙን መልቀቅ እንዳለባቸው ጀነራል አደም መሃመድ ሰሞኑን ያሳሰቡ ሲሆን ከእንግዲህ ምልመላው በእውቀትና በብቃት ብቻ ይሆናል ብለዋል፡፡
ተቋሙን ከፖለቲካ ውግንና ነፃ ከማድረግ ባሻገር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚሰራበትና  የሚሳተፍበት ይደረጋል - ብለዋል ጀነራሉ፡፡
ተቋሙ እውቀት ባላቸው ብቻ ይመራል፤ ኢትዮጵያዊነትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማሻገር ደግሞ ዋነኛ ተግባሩ ይሆናል ያሉት ጀነራል አደም፤ ተቋሙ በዜጎች የሚፈራ ሳይሆን ሊያገለግሉበት የሚመኙትና የሚወደድ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል፡፡
አመራሮቹና ባለሙያዎቹም ህግና ስርአትን ተከትለው ብቻ እንዲሰሩ ይደረጋል ተብሏል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ትናንት መግለጫ የሰጠው ሰማያዊ ፓርቲ በአንድ ሃገር የመንግስት አወቃቀር ውስጥ የሚደራጁ የደህንነት፣ የፖሊስና የመከላከያ ተቋማት ስልጣኑን ከተቆጣጠረው የፖለቲካ ፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ መሆን አለበት ብሏል፡፡ የደህንነት ተቋሙ የሃገርን ሉአላዊነትና ደህንነት ነው መጠበቅ ያለበት ብሎ እንደሚያምን የገለፀው ሰማያዊ ፓርቲ፤ የተቋሙ አዲሱ ኃላፊ ጀነራል አደም መሃመድ ተቋሙን ከፖለቲካ ውግንና ነፃ ለማድረግ ያቀዱት እንዲሳካ ሁሉም ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ብሏል፡፡
በየደረጃው ያሉ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሙያተኞች ከየትኛውም የፓርቲ ፖለቲካ የፀዱና ህዝብን በታማኝነትና በቅንነት የሚያገለግሉ መሆን አለባቸው ያለው ፓርቲው፤ ሂደቱንም በፅኑ እደግፋለሁ፤ ለተግባራዊነቱም የድርሻዬን እወጣለሁ ብሏል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ከፖለቲካ ውግንና ነፃ መሆን እንዳለበት በህገ መንግስቱ በግልፅ መቀመጡን የጠቆሙት ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት በበኩላቸው፤ የደህንነት ተቋሙ ላይ ግን እንዲህ ያለ ህግ ስለመቀመጡ መፈተሽ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ስራው ሲሰራ ከፖለቲካ ውግንና ነፃ መሆን ያስፈልጋል ያሉት ሜ/ጀነራል አበበ፤  ይህ ምን ያህል በሀገሪቱ ህገ መንግስት የተደገፈ ነው የሚለው መታየት አለበት ብለዋል፡፡
“በሌላው ዓለም ለምሳሌ በአሜሪካ የሲአይኤ ዳይሬክተር ሆኖ የሚሾመው ግለሰብ በፕሬዚዳንቱ ነው” ያሉት ጀነራሉ፤ በተለይ አመራሩ የፖለቲካ ተሿሚ እንደመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ነፃ ይሆናል የሚለው በሚገባ መፈተሽ አለበት ብለዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ የመከላከያ ሚኒስትሩና የደህንነት ተቋሙ ላይ ሪፎርም እንደሚደረግ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡  

Read 7382 times