Saturday, 21 July 2018 12:53

“መብቴ ነው፣” ብሎ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)


     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
  ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የፎቅ ላይ ኑሮ ‘እሱ ራሱ’ ይምጣብን እኛ እንሂድበት እግዜር ይወቀው፡፡ ያው እንግዲህ… ኮንዶሚኒየም የፎቅ ላይ ኑሮ አይደል የሚባለው! በዛ ሰሞን አንድ ወዳጃችን ቅልጥ ስላለ ጠብ ሲነግረን ነበር፡፡ በአንዱ ኮንዶሚኒየም መኖሪያ ሦስተኛ ፎቅ ላይ የሚኖር ሰው ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ከላይ ሆኑ ቁልቁል የጫት ገረባ ይወረውራል። “እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ፤ ነውር አይደለም ወይ?” ምናምን ሲባል ምን ቢል ጥሩ ነው… “መብቴ ነው!” መብት!?
“ሰውዬ ምን እያደረግህ ነው? ትልቅ ሰው አይደለህም አንዴ!”
“ምን ሳደርግ አየሽ?”
“እንዴት የጫት ገረባ ከፎቅ ላይ ትወረውራለህ… ታች ያሉት ሰዎች አይደሉም? ሁሉንም የሚጎዳ አይደለም እንዴ!”
“የፈለግሁትን መወርወር መብቴ ነው፡፡”
ኮሚክ ነገር እኮ ነው…በሚሠራበት መሥሪያ ቤቱ በአለቆቹ መአት ችግር እየደረሰበት፣ ባላጠፋው ጥፋት በሥራ ባልደረቦቹ የትችት ናዳ እየወረደበት…“መብቴን አትጋፉ!” ያላለ፣ “ለማንኛውም ሠራተኛ የሚሰጠው መብት ለእኔም ይከበርልኝ!” ያላለ ሰው፤ የጫት ገረባ ኗሪ አናት ላይ እየወረወረ “መብቴ ነው!” ሲል…አለ አይደል…ቀሺም አርበኝነት ነው፡፡  
እግረ መንገድ ይቺን ስሙኝማ…ጠብ ሊያስነሳ ከሚችል ከሆነ ግርግር፣ ጎመን በጤና ብሎ ይሸሽ የነበረውን ሰው፤ የሴት ጓደኛው… “ወንድ አይደለህም እንዴ! እንትን አለህ አይደለም እንዴ፣ እንዴት ትሸሻለህ!” ትለዋለች፡፡ (አርትኦት ተሠርቶበታል) ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው… “እሱ ታዲያ ለመራቢያ ነው እንጂ ለመደባደቢያ ነው እንዴ!” አላት አሉ፡፡
እናማ…ከላይ በተጠቀሰው በኮንዶሚኒየሙ አለመግባባት ወቅት የተፈጠረው ችግር ከሰውየው ድርጊት አልፎ ወደማይሆኑ ችግሮች ገብቶ ነበር አሉ፤ በፊት ለፊት እንኳን ባይሆን  በተዘዋዋሪ ይሄ እንደ ካንሰር እየተጣባን ያለው የዘር ነገር ሁሉ ተነስቶ ነበር አሉ፡፡ ሰውየው… አለ አይደል… የሆነ ‘ከሌሎች የተለየሁ ዘመናዊ ሰው ነኝ’ አይነት ነገር ነበረበት አሉ። በስተኋላ እንደምንም ነገሩ ተረጋጋ፡፡ ግን ሰውየው በማቆያው የተናገረው ነገር ሌላ ዙር ግርግር ሊፈጥር ይችል ነበር አሉ፡፡ “ከዚህ ጎሬ እወጣላችኋለሁ፣” አይነት ነገር ነበር ያለው፡፡
የምር ግን…አንዳንዶቻችን እንዴት ነው የምናስበው! እንዴት ነው…የአምስት ሺህ ብር ስኒከርና የሀያ ሺህ ብር ሳምሰንግ ጋላክሲ የ‘ዘመናዊነት’ ምልክት እንዳልሆነ የማይገባን! እንዴት ነው ዘመናዊነት ማለት በሌላው የህብረተሰብ ክፍል ላይ መታበይ እንዳልሆነ የማይገባን!
ኮሚክ እኮ ነው፡፡ ‘ቦትልድ ወተር’ ይዞ ወዲህ ወዲያ ማለት ቅልጥ ያለ ዘመናዊነት የሚመስለን ብዙ ነን እኮ! ለዚህ ነው የእኔ ቢጤው፤ ሁለት ጃኬትና ሦስት ሱሪ ለማለቅለቅ የሚበቃውን ውሃ ተሸክሞ የሚዞረው፡፡
ማስመሰል…አለ አይደል…የኑሮ መርህ የሆነበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ብዙዎቻችን ከሌሎች ተለይተን መታየት እንፈልጋለን፡፡ “ለእኛ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ዙፋን ሊዘጋጅልን ይገባል፣” አይነት ነገር፡፡ “እንዴት ብሎ ነው እኔ ከሌላው ጋር አብሬ በእድር ወንበር ላይ የምቀመጠው!” አይነት ነገር፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…‘ሆ’ ብለን የአገር መሪ ለመቀበል በቃን አይደል! ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ እንደውም ትንሽ ለማመን የሚያስቸግር ነው፡፡ ልክ ነዋ…በፊት እኮ…አለ አይደል… ሰርገን የገባን ምናምኖች የሆንን ይመስል ግድግዳ ላይ መለጠፋችን ለአሁኑም እንኳን ቢሆን ብለን መቅረቱ እሰየው ነው። በዚሁ ያስቀጥልልንማ! በነገራችን ላይ…አንዳንዶች የወጣውን ህዝብ ብዛት ወደ ሚሊዮኖች ሲያስገቡ ሰምተናል፡፡ እኔ የምለው… ‘ሚሊዮን’ እንዴት ነው እንዲሀ ቅርብ የሆነችው! እንዴት ነው በሽልንግ አስር የሚገዛ፣ የቲማቲም እጣ ገና ያልደረሰው እቃ ምናምን ነገር የሆነችው!
እግረ መንገድ… በሰልፍ፣ በስብሰባና በመሳሰሉት የህዝብ ቁጥር የሚገመትበት ሳይንሳዊ ምናምን የሚባል መንገድ አለ አይደለ እንዴ! በቀደም ሚሌኒየም አዳራሽ የነበረውን ህዝብ ብዛት ግማሹ “አርባ ሺህ ሰው ነበር፣” ይላል፡፡ ግማሹ ደግሞ “ሃያ አምስት ሺህ ሰው ነበር፣” ይላል፣ ወደ አስር ሺህ ያወረዱትም አሉ፡፡ እንዴት ነው ይህን ያህል ልዩነት የሚኖረው!
አንድ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ብሄራዊ ቡድናችን በሚጫወትበት ጊዜ የነበረውን ህዝብ ብዛት አንድ መገናኛ ብዙኃን ላይ “ከአርባ ሺህ በላይ፣” ሲባል ሰምተናል፡፡ መጀመሪያ ነገር ስታዲየሙ እኮ እንደ ሰርዲን ጥቅጥቅ ብለን እንኳን ሠላሳ ሺህ ሰው መያዙ ያጠራጥራል የሚባል ነው፡፡
የሰኔ አስራ ስድስቱ ሰልፍ ላይ በመስቀል አደባባይ የነበረው ህዝብ ብዛት ከዚህ በፊት ታይቶ አይታወቅም ነው የሚባለው፡፡ በእርግጥም እንደዛ ነው የሚመስለው። የህዝቡን ብዛት ብዙዎች “አራት ሚሊዮን ይሆናል…” ሲሉ ነበር፡፡ አራት ሚሊዮን እኮ ብዙ፣ በጣም ብዙ ነው! ሌሎች ደግሞ ከ1.5 እስከ 2 ሚሊዮን ሲያደርሱት ነበር፡፡ ሚሊዮን የሚሉት ቁጥር እኮ ብዙ፣ እጅግ በጣም ብዙ ነው! የውጪ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ አሽቆለቆሉና በአስር ሺህ ሺዎች አደረጉት፡፡ በዚህ ጉዳይ አንድም ሁለትም ቃላቸውን የምናምንባቸው ታማኝ ወገኖች ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ልክ ነዋ…የህዝብ ቁጥር ብዛትን እንደመሰለን ከመከመርና ከመገንደስ ይገላግለናል፡፡
እናማ…በሆነ ምክንያት ከሰው በላይ የሆንን የሚመስለን፣ ሻል ያለች ኮትና ሱሪ ስለለበስን ከሌላው ህዝብ ከፍ ባለ ስፍራ ላይ ያለን የሚመስለን ቁጥራችን ቀላል አይደለም፡፡
 “ህይወት ውስጥ በቀላሉ የሚገኝ ነገር የለም፣” ነው የሚባለው፡፡ “ህይወት ቀላል ነው ብለህ አታስብ፣” ተብሏል፡፡ በድሮ ጊዜ በጀርባቸው ተኝተው፣ በአፍንጫቸው ቅቤ ይንቆረቆርላቸዋል የተባሉትን አይነት ለመወረፍ የሚጠቀሙባት አንድ አባባል ነበረች፡፡
እነአገልግል ፊቱ፣ እነሸማ ጋርዱ፣ እናሽከር ወጊዱ
ጦርነት ሲመጣ ከመርፌ ቀዳዳ ይጠባል መንገዱ፡፡
የምር ግን…በሰላሙ ጊዜ እኮ ሁሉም ጀግና ነው፡፡ ፀሀይ የሆነች ጊዜ እኮ ሁሉም ‘ታላቁ እስክንድር’ ነው፣ ሁሉም ‘ናፖሌኦን’ ሁሉም ‘ጄንጊስ ካን’ ምናምን ነገር ነው፡፡ ባለፉት ወራት የታዩትን ለውጦች ተከትሎ ሚዲያውን ነገሬ ብላችሁልኛል! “ይሄ ሁሉ ‘ተንታኝ፣’ ይሄ ሁሉ ‘ምሁር፣’ ይሄ ሁሉ ‘ሲናገር ወፍ ከሰማይ ጠብ የሚያደርግ’ የት ነበር?” ያስብላል፡፡
ነገርዬው የሚመጣው ጸሀዩዋን ደመናው በሚያጠይማት ጊዜ፣ ዝናቡ መውረድ የጀመረ ጊዜ ነው። ነገርዬው የሚመጣው ዘፈኑ በሚያቆምበት ጊዜ ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እዚሀ አገር ፖለቲካ ውስጥ አንድ ኮሚክ ነገር አለ። አንድ ሰሞን መቆሚያ መቀመጫ እስክናጣ ድረስ እንጨቀጨቃለን፡፡ ሁሉም ከእኔ በላይ ላሳር ባይ ይሆናል፣ ሁሉም ከእኔ ሌላ ይቺን አገር የሚያድን ባይ ይሆናል፣  ሁሉም ከሌኒን በላይ አብዮተኛ፣ ሁሉም ከጳጳሱ በላይ የተባረከ ምናምን አይነት ይሆናል፡፡ ነገሮች ከረር ብለው ደመናው ጠየም ሲል … ወላ ሌኒን የለ፣ ወላ ምን የለ…ሜዳው ‘ባዶ’ ይሆናል፡፡ ነገርዬው…
እኔም አልጣላ ሲጣሉም አላይ
ጎመኔን አውጪልኝ አንጀራዬ ላይ … እንደሚባለው
ጓዳ ገብቶ… “ጎመኔን አውጪልኝ… አይነት ነገር ነው፡፡ እናማ የሺህ ምናምን ብር ጫማ ስላጠለቅን ብቻ ራሳችንን ከሌሎች የተለየን አድርገን እንደምናይ ሰዎች፣ ቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ሆነው ብቻ የተለዩ የሆኑ የሚመስላቸው፣ “መሲሆቹ እኛ ብቻ ነን፣” አይነት የሚሉ አሉ፡፡ በሰውነታችን፣ በሰብአዊ ፍጡርነታችን ማናችንም ከማናችን አንበልጥምም፣ አናንስምም፡፡ ሀቁ ይሄ ነው፡፡ ይቺን ማየት ስላልቻልን ነው ብዙ ነገሮች ላይ እንዳንግባባ እያደረገን ያለው፡፡ ከዚህ አይነት ኋላ ቀር አስተሳሰብ በፍጥነት የሚያወጣንን ተአምሩን ይላክልንማ!
ይቺን ነገር ብናወራትም እንድገማትማ…ትያትር ቤት ነው፡፡ ውጪ ተመልካቾች ትያትር ቤት ሲገቡ ካፖርታቸውን ተቀብለው የሚያስቀመጡ አስተናጋጆች አሉ፡፡ እናም ካፖርቱን ቀበል ሲያደርግ፣ ጉርሻ ቢጤ ጣል ይደረግለታል፡፡ አንድ ጊዜ የወንጀል ነክ ፊልም ለማየት ባልና ሚስት ይገባሉ፡፡ ሚስት ካፖርቷን ለአስተናጋጁ ትሰጥና መንገዷን ትቀጥላለች። ሁሉም እንደሚያደርገው፤ የተለመደውን ጉርሻ (ቲፕ) አልሰጠችውም፡፡ አስተናጋጁም ተበሳጨ፡፡ ወደ ሴትዮዋ ጆሮ ጠጋ አለና… “ሴትዮዋን የሚገድላት የቤቱ አገልጋይ ነው፣” አላትና አረፈው፡፡ ሰውየው ጉርሻ (ቲፕ) ማግኘትን መብቱ አድርጎታላ! በዛ ህብረተሰብ ምናልባት መብቱ ሊሆን ይችላል፡፡
የኮንዶሚኒየሙ ሰውዬ አይነት ለሆንን ሰዎች ግን በመብትና በግዴታ መካከል ያለው ልዩነት  ምን እንደሆነ ‘ራይትስ 101’ ምናምን አይነት ነገር ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡  
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 4280 times