Saturday, 21 July 2018 13:04

“ምን ዋጋ አለው?”

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)


    “ምን ዋጋ አለው?” የሚለው መጠይቃዊ ሀረግ ራሱ ትክክለኛ ዋጋውን በአጠቃቀም ስህተት ምክኒያት ካጣ ቆይቷል፡፡ … “ምን ዋጋ አለው?” የሚለው ጥያቄ፣ የተስፋ መቁረጫ እስትንፋስ ሆኗል፡፡ የቃላት ሀብታም መሆን ቃላት ዋጋ ከሌላቸው “ምን ዋጋ አለው!”
“የፍትህ እና እኩልነት መስፈን አለባቸው” ከሚለው አረፍተ ነገር በላይ የማህበረሰብ የአብሮ መኖርን እሴት ገላጭ የቃላት ስብስብ የለም፡፡ … ግን ቃላቶቹን ነጣጥለን እሴታቸውን ስንለካ፣ እንደ ወርቅ ንጹህ “ዋጋ” መስለው ከሚቀርቡት በላይ የረከሱ እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ መርከስ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ ዋጋ የሌላቸውም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
“ፍትህ” ወይም “እኩልነት” በጭራሽ እውን ሆኖ የማያውቅበት ሀገር ላይ፣ ቃላቱን የሚጠቀም ሰው ራሱ እንደ ሰባኪ ዋጋው አጠራጣሪ ነው፡፡ ቅን ልቦና ያለው የህዝብ መሪ፤ ፍትህና እኩልነት በተጨባጭ የማያውቅ ህዝብ ላይ እንዴት ነው የሚናገረውን በተግባር፣ ከስብከት ባሻገር ተጨባጭ የሚያደርገው?
የኔጌሽን ኔጌሽን አይሆንም? የሌለ እሴትን በፅኑ እምነት ለመፍጠር መሞከር የኔጌሽን ኔጌሽን ነው። በሀሳብ ደረጃ ወይንም በ“concept” ደረጃ ያለ እምነትን ወደ ተጨባጭ መቀየር የሚቻለው … መቀየር የሚቻልን፤ ከዚህ ቀደም ተቀይሮ የተሞከረ ነገርን ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ያለ ምክኒያት የታሰረ ሰውን በምክኒያት ማስፈታት፣ የፍትህ ማስፈን ሙከራ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ያለ ምክኒያት መታሰር እንዳይኖር ማድረግ እስከ ዘላቂው ካልተቻለ ግን በምክንያት ማስፈታቱ ካለ ምክንያት እንደ ማሰር  ዋጋው ይዋዥቃል፡፡ “ምን ዋጋ አለው?” የሚል ጥያቄ ይቀሰቅሳል፡፡
ህግን ማርቀቅ ወይም ህገ መንግስትን መፃፍ ብቻ ፍትህን እውን አያደርገውም፡፡ ትክክለኛ ህግን በተሳሳተ መንገድ የሚያነበው አንባቢ የእውነትም ዋጋ አርክሷል። የተሳሳተ መፅሐፍን በትክክለኛ ቅንነት ማንበብም ተመሳሳይ ነው፡፡ የአንባቢውን ዋጋ አጥፍቶ “ምን ዋጋ አለው! ባያነበው ይሻል ነበር” ወደሚል ርካሽነት ቅኑን አንባቢ ይጥለዋል፡፡
ቃላት እንደ ገንዘብ ናቸው፡፡ ቃላቱ የሚወክሉት እሴት በተጨባጭ ሲኖር ብቻ ነው ዋጋ የሚኖራቸው። “ነፃነት” እና “እውነት” በተጨባጭ ታይተው በማይታወቁበት፣ እነዚህን “abstracts” አጽንኦት ሰጥቶ እየደጋገመ ንግግር የሚያደርግ ሰው፣ በእውነተኛ ቅንነት ቢሆንም፣ ንግግሩ ዋጋ  አይኖረውም፡፡ ምክኒያቱም፤ የሚጠቀማቸው ልኮች ተመናቸው ምን እንደሆነ በአፋዊ ዲስኩር እንጂ መሬት በያዘ መልኩ አይታወቅምና ነው፡፡
ወዛደር ኖሮ በማያውቅበት ሀገር ላይ “የወዛደር እኩልነትን ከበዝባዥ ቡርዧ ለመንጠቅ” የሚደረግ አብዮት ውጤቱ ዋጋ አይኖረውም፡፡ “The negation of the negation is based on correct reading of the wrong books” እንዲል ዶናልድ ባርተልሄም፡፡
እምነትን እውን ለማድረግ ስሜት ግድ ይሆናል ያኔ፡፡ በስሜታዊነት ህግ ይረቀቃል፡፡ መፈክር ይፃፋል። ስሜታዊነት ጥርጣሬን ይፈጥራል፡፡ ተናጋሪ እና በጥርጣሬ አድማጭን ያፈራል፡፡ ስሜት፤ ፉከራ አቀባይንና ተቀባይን ያስተሳስራል፡፡ መጨረሻ ላይ ዋጋ ያለው ነገር፣ ፍርሃትን መፍጠርና ማከፋፈል ብቻ ይሆናል፡፡ የበለጠው ስሜታዊ የበለጠ ፍርሀት አምራች ይናል፡፡ “Fear is the great mover in the end” … ፍርሃት አብዮትንም ሆነ ትውልድን ይሰራል፡፡ ወይም ይመራል፡፡ ግን መጨረሻ ተመራርተው የደረሱበት መፈክር መልክ ወደተነደፈው የስሜት ሀገር አይደለም። አይሆንም፡፡ … የማይዋዥቅ እሴት ላይ ያልተመሰረተ ስሜት ወይም ስብከት ተባዝቶ እንደሚታተም ብር ዋጋ አይኖረውም፡፡ ተጨባጭ እውነታ ላይ ያልተመሰረቱ ስብከቶችም፤ የስሜታዊያኑን አፍ በመፈክር፣ ብዕራቸውን ልብ አማላይ በሆኑ ቃላት እንዲሞሉ ቢያደርጋቸውም … ያልነበረ ነገር አብዝቶ ማተም እሴት ሆኖ እንዲዘልቅ አያደርገውም፡፡ በስሜት ላይ ሀገር ሊገነባ የማይችለው፣ ስሜት እውነታም እውነትም ሳይሆን የመቅረቱ እድል ከፍ ያለ በመሆኑ ምክኒያት ነው፡፡ ስሜት ጥሩ “Medium of exchange” አይደለም፡፡ ትክክለኛውን መፅሐፍ (እውነት፣ እውነታ) በትክክለኛ ቅንነት ግን ስሜታዊም፣ ሰባኪም ሳይሆኑ ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ ዋጋው ያለው በቀላሉ የማይለወጥ እውነት ላይ ነው፡፡ የሁሉም የማይለወጥ እሴት ምን ላይ እንዳለ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ “ፍትህ እና እኩልነት” የሁሉም እሴት ቢሆን ኖሮ፣ የጨቋኝና የተጨቋኝ ድራማ በተለያየ መሪ ቅርፅ ሲፈራረቅብን ባልኖርን ነበር፡፡
በቃላት የተመሰረተ ሀገር አስተማማኝ የሚሆነው፣ ቃላቶቹ የወከሏቸው እሴቶች እውነተኛ ዋጋ እስካላቸው ድረስ ነው፡፡ ስሜት ላይ የተመሰረቱ ቃላትን መነገድ፣ ካፒታል ሳይኖር ካፒታሊስት ለመሆን እንደ መፍጨርጨር ነው፡፡ የሌለ እሴትን ለመነገድ ማጭበርበር ይጀመራል፡፡ ማጭበርበር፡- እሴት እንደሌለ እያወቀ ስሜት ለመነገድ ዓይኑን የጨፈነ  የሚያደርገው ተግባር ነው፡፡ በእውነተኛ ቅንነት ግን በተሳሳተ እሴት ትክክለኛ ትርፍ ሁሉም እንዲያገኝ የሚለፋው ነው፡፡ ማጭበርበር ሳይፈልግ ይጭበረበራል፡፡ “The negation of negation”
መጭበርበሩ ወይም ማጭበርበሩ እውነተኛዎቹን እሴቶች ማለትም፡- በህልውና መኖርን፣ ፍትህን፣ ሰው የመሆን ፀጋዎችን በአጠቃላይ … እያጠፉ ሲመጡ ተጭበርባሪው አጭበርባሪ በመሰለው ላይ ይነሳል። ይኼም ስሜታዊነት ነው፡፡ ስሜታዊነት የውሸት እሴትን በፍርሃት መልክ አንብሮ እንዳነገሰው .. በጥላቻ መልሶ ያወርደዋል፡፡ በወረደው ፈንታ አዲስ ዲስኩር ይዞ የሚመጣን ያነግሳል፡፡ የመጭበርበርና የማጭበርበር ወይም የመጨቆንና የመጨቆን ታሪኩ እየተደጋገመ ለብዙ ዘመን ከቆየ እየደነደነ ባህል ይሆናል። ጭቁኑ በህልውና መኖር ሲሳነው የሚያወርደውን ጨቋኝ ለዘብ ባለ መልክ መልሶ አጫርቶ ይሾማል፡፡ እሱ ራሱ በባህል ደረጃ፣ በጭቆና እና ስሜታዊ ምሪት ምክኒያት መላ ማንነቱ “Negation” ሆኗል፡፡ ጥምዝ … እና ሸውራራ በመሆኑ … ደህና መሪ ቢመጣ እንኳን ያበላሸዋል። ስሜታዊ ህዝብን የሚመራ መሪ ምክኒያታዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ልሁን ቢልም ይጠላል፡፡ የለመዱትን ቁንጥጫና ኩርኩም ካልመገባቸው የስሜታዊነት ምሳቸውን አያገኙም፡፡

Read 1682 times