Saturday, 21 July 2018 13:07

ኔክሰስ ሆቴል ዓለም አቀፍ ብራንድ ለመሆን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 በመጀመሪያውና በማስፋፊያው ግንባታ 560 ሚሊዮን ብር የፈጀው ኔክሰስ ሆቴል አለማቀፍ ብራንድ ለመሆን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የሆቴሉ ማኔጅመንት ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ ሆቴሉ የሚሰጠው አገልግሎት በዘመናዊ መሳሪያዎች የታገዘና ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ በመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ብራንድ ለመሆን ከብራንድ ሆቴሎች ጋር እተነጋገረ መሆኑን ገልጿል፡፡
በ2004 ዓ.ም የመጀመሪያ ግንባታውን በ150 ሚሊዮን ብር አጠናቆ በ66 የመኝታ ክፍሎች ስራ የጀመረው ኔክሰስ ሆቴል በ410 ሚሊዮን ብር ማስፋፊያ 86 ክፍሎች ጨምሮ የአልጋዎችን ብዛት 151 ማድረሱን የሆቴሉ ዋና አማካሪና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዜናዊ መስፍን አስረድተዋል፡፡
አቶ ዜናዊ፣ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ጠቅሰው፣ ከችግሮቹም ዋነኛው ባለፈው 39 ዓመት በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች በደረሰው የፀጥታ መደፍረስ ችግር ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች “ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ እልቂት አለ” በማለት ለአገር ጎብኚ ቱሪስቶች የተጋነነ መረጃ ሲሰጡ፣ በአገር ውስጥ ሚዲያዎች ማስተባበያ ያለመስጠትና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮች በየጊዜው መቀያየር ከችግሮቹ ጥቂቱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ወደ አገራችን የሚመጡት የቱሪስቶች ፍሰት በቂ አይደለም ያሉት ሥራ አስፈፃሚው፣ የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር መረጃ እንደሚያሳየው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ጎብኚዎች ቁጥር ከ600 ሺህ እስከ 800 ሺህ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ትንሽ የሆነችውን ፈረንሳይ በዓመት 31 ሚሊዮን ቱሪስቶች ይጎበኙታል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የቱሪስቶች ፍሰት እያገገመ እንደሆነ አማካሪው ጠቅሰው ዓለም አቀፍ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች እየተሰሩ ቢሆንም በቂ አይደለም ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ኮንፈረንሶች እዚህ ሲካሄዱ፣ ክፍሎች ፍለጋ ከአዲስ አበባ የሚወጣበት ጊዜ እንዳለ ጠቅሰው በግብፅ አንድ ሆቴል 1,700 አልጋዎች አሉት በማለት አስረድተዋል፡፡
ባለ 4 ኮከብ የሆነው ኔክሰስ ሆቴል ማስፋፊውን ካከናወነ በኋላ ግን ወደ 5 ኮከብ እየተንደረደረ እንደሆነ ሥራ አስፈፃሚው ጠቅሰው፣ በአገራችን ስም የተሰየሙት 5 አዳራሾች፣ ኤርታኢሌ፣ ዳሎል፣ ሀዳርና ሉሲ ከ20-450 ሰዎች ማስተናገድ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ሆቴሉ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟሉ ውብና ማራኪ የመኝታ ክፍሎች ሲኖሩት 60 ስታንዳርድ ደብል፣ 20 ስታንዳርድ ቲዊን፣ 4 የግል ጃኩዚ ያላቸው፣ 50 ቢዝነስ ደብል፣ 10 ቢዝነስ ሱቅ፣ 6 ቢዝነስ ቲዊንና 1 የቤተሰብ ክፍል አለው፡፡
ኔክሰስ ሆቴል ለየት የሚያደርገው የቤት ውስጥና የውጭ መዋኛ ገንዳ ሲኖረው፣ 300 እንግዶች መያዝ የሚችል ሬስቶራንት 150 ሰዎች ማስተናገድ የሚችል የኢጣሊያ ባርና ሬስቶራንት 80 ሰዎች መያዝ የሚችል የምንጊዜም ባርና ሬስቶራንት፣ የአውሮፓና የሜዲቴራኒያን ምግቦች የሚያዘጋጅ የተለየ ኪችን አለው፡፡ ሆቴሉ በተለያዩ ዲዛይኖች ያሸበረቀ ልዩ የአምባሳደሮችና የአፍሪካ ምሽቶች እንደሚኖሩት አቶ ዜናዊ መስፍን አብራርተዋል፡፡  Read 1159 times